ቀልዱስ ቀልድ ነው ።ይልቅ
¶ይኼኛው ዜና ደግሞ የሶማሊ ኦሮሞን ግጭት ፣ የኦሮምያን የተቃውሞ ሰልፍ ፣ የኦሮሞ ወጣቶችን ወደ ጣና ሐይቅ ሔደው እንቦጭ ነቀላ የመፈጸማቸውን ዜና ለማጠየም አገዛዙ አይኑን ጨፍኖ ህገመንግሥታዊ መብትን በመጣስ ሰሞኑን በያለንበት እንነታረክበት ዘንድ የሰጠን አጀንዳ መሆኑነ ነው ።
የጋዜጠኛ ተመስገን እናት አረጋዊዋ ወይዘሮ ፋናዬ እርዳቸው ሰሞኑን ልጄ ይፈታል በማለት በደከመ አቅመቸው እንዲያው መሬቱ አልበቃ ብሏቸው ሽርጉድ ይሉ እንደነበርና የቤታቸውን ቀለም ሲያስቀቡ ፣ የሶፋ ጨርቅ ሲያስቀይሩ ፣ በአጠቃላይ ቤታቸውን ሲያስውቡ መክረማቸውን ልጃቸው ታሪኩ ደሳለኝ
ነገር ግን አረጋዊዋ እናት እንዳሰቡት አልሆነላቸውም ። አልተሳካምም ። ይኸውም ስለምንድነው ያልተሳካው ቢሉ ፤ ዛሬ ወንድሙን ከእስርቤት ተቀብሎ ከናፈቁት እናቱ ጋር ለማገናኘት ታናሽ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ወደ ዝዋይ እስር ቤት አቅንቶ ነበር ። እናም ወንድሙ ታሪኩ ዝዋይ ደርሶ ለመላው ዓለም ህዝብ የላከው ዜና ግን የምስራች ቃል የነበረው ዜና አለነበረም ። ይልቁኑ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቅስም የሚሰብር ዜና ነው ነበር ታሪኩ ከዝዋይ የላከው ። [የዝዋይ ማረሚያ ቤት ሓላፊዎች ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የእስር ጊዜውን ቢፈጽምም እኛ ግን አንፈታውም ] ብለዋል ብሎ ነው መርዶውን ለዓለም ህዝብ ያረዳው ።
በነገራችን ላይ ታሪኩ ደሳለኝ ማለት የጋዜጠኛው ታናሽ ወንድም ሲሆን [ የዘመን ድራማ ] የካሜራ ባለሙያው ነው።ታሪኩ ደሳለኝ።
የሌላውስ ቀላል ነው፤እንዲያው ግን ይሄንን ክፉ ዜና፤ የልጃቸውን መፈታት በጉጉት የሚጠብቁትና ሌቱም አልነጋ፤ ቀኑም አልመሽ እያለ ምጥ እንደያዛት ሴት በስተ እርጅና በዚያውም ላይ ደግሞ በህመም ላይ ፣ እንደገናም በድካም ላይ ሆነው የልጃቸውን ከእስር ተፈትቶ መምጣት በጉጉት እየተንቆራጠጡ ይጠብቁ የነበሩትን አረጋዊዋ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ወይዘሮ ፋናዬ ምን ይሰማቸው ይሆን ? አለማሰቡ ይሻላል ። እንኳን ከእስር ቤት ከደጅ ውሎ የሚገባ ልጇን ከቤቷ እስኪገባ የማያስችላት እናት በእውነት ምን ይሰማት ይሆን ። ይኽንንስ በእውነት ወላድ ይፍረደው ? ከእናት የተወለደ ፣ እናቱን የሚወድ ይፍረደው ።
እነ አሜሪካ እንኳ አሸባሪ የተባሉና የብዙ ዜጎችን ህይወት የቀጠፉ ፣ ንብረት ያወደሙ አሸባሪዎችን ከጓንታናሞ እየለቀቀች ባለችበት በዚህ ዘመን ፤ ብዕርና ወረቀት አዋሕዶ ገዢውን ሥርዓት ሻይ እየጠጣ የሞገተን አንድ ምስኪን ጋዜጠኛ እንዲህ ከኦሳማ ቢላደን በላይ ፈርቶ [ ከወጣ አለቀልኝ ] ብሎ በመንቦቅቦቅ ምን የሚሉት ነው ? ያውም ህግ ጥሶ ፤ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወትር የሚያመልኩትን ህገ መንግሥት በድማሚት ንዶ ስለ ፍትህ ማውራት እንዴት ይቻላል ?
እርግጥ ነው ህወሓት መራሹ የኢትዮጵያ ገዢ ይኼኛውን የሰላማዊ ትግል ጨርሶ አያውቀውም ። እሱ የለመደው ጠብመንጃ አንስቶ ተራራ ማንቀጥቀጥ ነበር ። ምሽግ መማስ ፣ በቆረጣና ፣ በደፈጣ ውጊያ አቧራ ሲቅም ፣ በረሃ ለበረሃ ኮቾሮ እየበላ ሲንከራተት የኖረ አካል እንደተመስገን ደሳለኝ ፣ እንደ እስክንድር ነጋ ፣ እንደ አንዷለም አራጌ ፣ እንደ በቀለ ገርባ ፣ እንደ ፕሮፌሰር መመራ ጉዲና አይነቶቹን መሀል አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ማኪያቶና ቀዝቃዚ ቢራ እየተጎነጩ በአንደበታቸውና በብዕራቸው የሚሞግቱትን ዜጎች እንዴት ይቋቋማቸው ። አቶሚክ ቦንብ እንደታጠቀ ሰራዊት ባይፈራቸው ነበር የሚደንቀው ። ምክንያቱም የሰለማዊ ትግሉን የጨዋታ ህግ ሲፈጥረው ጀምሮ አያውቀውም እናነው ።
ይኽ ጋዜጠኛ እንደ ሌሎቹ ጋዜጠኞች ከሀገር የሚወጣበት ብዙ ሰፊ እድሎች ነበሩት ። ነገር ግን በፍጹም በዚያ በኩል ለመጠቀም አልፈለገም ። በአንድ ወቅት እኔ ወደ ሀረር ቅድስት ስላሴ እሱ ደግሞ ወደ ድሬደዋ ለሥራ ጉዳይ ሲሄድ አብረን በአንድ አውሮፕላን ነበር ለረጅም ሰዓት እየተወያየን የሄድነው ። በወቅቱ ተመስገንን ለምን እንደሌሎቹ ጋዜጠኞች ከሀገር ወጥቶ እንደማይሰደድ ጠይቄው እንደነበር ትዝ ይለኛል ። እሱ ግን በፍጹም በጭራሽ ስደትን አልሞክረውም ። እነ እስክንድር ነጋ የገቡበት እስር ቤት ወይም እነ ፕሮፌሰር አስራት የገቡበት መቃብር ቤት ነው የሚከቱኝ አይደል? እናም እጄን በካቴና አስረው ዘብጥያ እስኪያወርዱኝ ድረስ እጽፋለሁ ። እጽፋለሁ ዘመድኩን ነበር ያለኝ ። ” አንተ ከእነ በጋሻው ጋር የምታደርገውን ትግል ለምን አታቆምም ብልህ የምትመልስልኝን መልስ ሳትነግረኝ መገመት እችላለሁ ። ይኼማ እምነቴ ነው እንደምትለኝ አምናለሁ ። ለእኔም ጋዜጠኝነት እምነቴ ነው ። ልሰዋለት ፣ ልታሰርለት ፣ ልገደልለት ቃል ኪዳን የገባሁለት እምነቴ ነው ነበር ያለኝ ። ይኸው ይኼ ሰው እምነቱን እንደጠበቀ ህክምና ተከልክሎ ፣ ጠያቂ ተከልክሎ ፣ አመክሮ ተከልክሎ፣ በመጨረሻም በፍርድቤት ውሳኔ መሰረት በዛሬው ዕለት የሚፈታ ቢሆንም ይኽንንም ተከልክሎ ከህግ አግባብ ውጪ በወኅኒ ቤት እንዲበሰብስ ተፈርዶበታል ።
እውነት ነው ልጁ እልኸኛ ነው ። ተሜ በጋዜጣ ላይ ሃሳቡን መግለጽ የጀመረው
አሁን አገዛዙ ውጥረት ውስጥ እንደሆነ ይታወቃል ። ሶማሌ የራሱን መንግሥትና ባንዲራ ህወሓት ሰጥታው ኢትዮጵያውያን ከክልሌ ይውጡ ብሎ እየገደለም ፣ እየገረፈም ከክልሉ አስወጥቷል ። እያስወጣም ነው ። ደቡብ ከኦሮሞ ጋር የመነታረኪያ አጀንዳ ተሰጥቶት ሲዳማና ኦሮሞ ደም እየተቃባ ነው ። መላው ኦሮሚያ በሰላማዊ ሰልፍ ደጅ ውሎ ማደር ከጀመረ ሰነባበተ ። ጎንደር ዓማራ ቅማንት ፣ ከትግራይ ጋር በፀገደ ፀና በጠገዴ ጠ ንትርክ ውስጥ ናቸው ። የብር የመግዛት አቅም እንዘጭ ብሏል ። ኑሮ እሳት ሆኖ ዜጎችን እየለበለበ መሆኑን እያየን ነው። መብራት የለም ። ስኳር የለም ። ዘይት የለም ። ውኃም የለም ። በዚህ ላይ ታላቁን የጣናን ሐይቅ እንቦጭ ወርሮት ሀገር እየተረባረበ ህወሓት ሆዬ ከዳር ቆሞ ይስቃል ።
እናም በዚህ እሳት ላይ ተመስገንን መፍታት በእሳቱ ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ ነው በማለት ላለመፍታት የቆረጡ ይመስላል ። እግዚአብሔር ያሳያችሁ ያውም ሲፈታ የማይሰደድ ፣ ከሀገሩ የማይኮበልል ፣ መጻፍ መሟገት የማይሰለቸው እሳት የሚተፋ ብዕር ጨብጦ የሚጠበጥባቸውን ጀኔራል ከወኅኒ አውጥቶ ማን ሲንከለከል ይኖራል ብሎ ህውሓት ሆዬ ህገመንግሥቱ አስር ጊዜ ለምን አይደፈጠጥም ፣ ለምንስ ከፈለገ አፈር ከድሜም አይግጥም በማለት የፈለገው ይምጣ ፣ ለምን ዓለሙ ሁሉ አይንጫጫም ብሎ ተመስገንን እዚያው በዝዋይ ቋንጣ አድርጎ ጠብሶ ሊበላው በወኅኒ ከርችሞበታል ።
እንግዲህ ምን እንላለን የተመስገን እናት ሆይ ! ወገብዎን በደንብ ይታጠቁ ፣ እናቴ አዝዎት ። ጽዋውን የሚጠጡት ዝኩሩን በስሙ የሚዘክሩለት ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ጽናቱን ይስጥዎት ። ሌላ ምን ይባላል ። ምንም ።
ለአሁን አበቃሁ የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነልኝ በቀጣይ ደግሞ በሌላ ርዕስ እመለሳለሁ ።
ይኽንም ጦማር ራሴው እኔ ዘመዴ በእጄ ጻፍኩት ። 004915217428134 የቫይበር ፣ በኢሞ ፣ በኋትስአፕ እና በቴሌግራም የሚደርሱኝን መረጃዎችና መልእክቶችን የምቀበልበት የእጅ ስልኬ ነው ።
ሻሎም.! ሰላም.