>

የትግራይ ህዝባችንን ስናስብ (አፈንዲ ሙተቂ)

አዎን! ቃል ቃል ነው። ትግራይ ማለት የአክሱም ስልጣኔ ማህፀን ናት። ትግራይ የሌለችበትን ኢትዮጵያ ማሰብ ይከብዳል። እኛም ከትግራይ ህዝብ ጋር የተዋወቅነው ጥንት ነው።

ፖለቲካ ይሞቃል፣ ይቀዘቅዛል። ሲፈልግ ወደ ምስራቅ፣ ሲያሻውም ወደ ምዕራብ ይወናጨፋል። መንግሥታትም ይወጣሉ፣ ይወርዳሉ። ህዝብና ሀገር ግን መቼም ይኖራል።
——–
አሁን ያለውን የሀገራችንን የፖለቲካ አወቃቀር በማደራጀት ረገድ በትግራይ ህዝብ ስም ራሱን የሰየመው ህወሓት/ኢህአዴግ የአንበሳ ድርሻ እንዳለው ለማንም ግልፅ ነው። በኢህአዴግ ውስጥ ከርሱ ጋር የተጣመሩት የሌሎች ድርጅቶች ድርሻ በጣም አነስተኛ ነው።

ስርዓቱ በደርግ ውድቀት ማግስት ሲባል እንደነበረውና እኛም እንደተመኘነው ዲሞክራሲ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ብልፅግናን አላመጣም። ባለስልጣናቱ ዘወትር “ጀማሪዎች ነን” እያሉ ሊያጃጅሉን ይሞክራሉ። ቢሆንም 26 ዓመት በጣም ረጅም ጊዜ ነው። በተግባር እንዳየነው የብዙሀኑ ህዝብ ኑሮ አልተሻሻለም። በዚህም ምክንያት ነው የህዝብ መነሳሳትና መማረር የበረከተው። ታዲያ ይህንን ተከትሎ “ቀጣዩ ዘመን ምን ይዞ ይመጣል?” የሚለው የብዙዎች ጭንቀት ሆኗል።

እኛ ግን ቃላችንን በድጋሚ እናሰማለን። መጪው ጊዜ ያሻውን ነገር ይዞ ቢመጣም በትግራይ ህዝብና በሌሎች ኢትዮጵያዊያን መካከል ያለው መስተጋብር በጭራሽ አይቀየርም። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ ከእኛ ጋር በእጅጉ የተዋሀደ በመሆኑ ነው።

አዎን! እኔ ከህወሓት በፊት የማውቀው የአምስተኛ ክፍል የእንግሊዝኛ አስተማሪዬ የነበረውን ቲቸር እቁባይን ነው።

እኔ ከህወሓት በፊት የማውቀው የስምንተኛ ክፍል የባልትና አስተማሪዬ የነበረችውን ቲቸር አልማዝ ባራኺን ነው።

እኔ ከህወሓት በፊት የማውቀው በገለምሶው የካምቦ ተራራ ስር ቤታቸውን የቀለሱትንና እስከ ዛሬ ድረስ ከአሸዋና ድንጋይ አቅራቢነት ስራ መላቀቅ ያልቻሉትን ጋሼ ገብረ አምላክን ነው።
—–

ህወሓትን የሚቃወሙ ተጋሩዎችን ጉዳይ ሳነሳ አንድ ነገር ትዝ አለኝ። አቶ Beyene G. Tesfu የትግራይ ተወላጅ ነው። ታዲያ ይህ ሰው ከህወሓት ጋር ዐይንና ናጫ ነው። ከድርጅቱ ጋር ተታኩሷል፣ ተጋድሏል። በመጨረሻም በህወሓቶች ተማርኮ ለአራት ዓመታት ታስሯል። ምክንያቱ ደግሞ የኢህአፓ አባልሆኖ መገኘቱ ነው።

አቶ በየነ በኢህአፓ/ኢህአሠ ቆይታው ያሳለፈውን ህይወት የሚመለከት ተከታታይ ፅሑፍ በየሳምንቱ ዐርብ በገፁ ላይ እያስነበበን ነው (እኛ ግን “ፀሐይ ከምታስመታው በጥናት አዳብረኸው በመጽሐፍ ልታሳትመው ይገባል” እያልነው ነው)።

ዶ/ር Ghelawdewos Araiaበወጣትነታቸው የኢህአፓ ታጋይ የነበሩ እንደመሆናቸው ተመሳሳይ ታሪክ አላቸው። ብዙዎቻችሁ ያነበባችሁትን “የአሲምባ ፍቅር” የተሰኘውን ውብ መጽሐፍ የጻፈልን Kahsay Abraha የኢህአሠ አባል የነበረ ትግራይ ተወላጅ ነው። እርሱም እንደ በየነ ከህወሓት ጋር ደም ተቃብቷል።

አርአያ ተስፋማሪያምስ ቢሆን? በዚህ ስርአት የደህንነት አባላት ተደብድቦ፣ ተሰቃይቶ፣ ቃሊቲ ወርዶ መከራው ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት የተሰደደ ውድ ጋዜጠኛችን አይደለም እንዴ? በተወዳጁ የኢትኦጵ ጋዜጣ ላይ ሲፅፈው የነበረው “ከህወሓት መንደር ከቃረምኩት” የተሰኘ አምድ እንዴት ይረሳል?

ብዙዎቻችሁ አቶ መለስ ዜናዊ ከንቲባ አርከበ እቁባይን “ስድስት ድስት ጥዳ ስድስቱንም በአንድ ጊዜ የምታማስል ባልቴት ትመስላለህ” ማለታቸውን ሰምታችኋል። ታዲያ በዝግ ስብሰባ የተነገረውን ያንን አባባል ከማንም አስቀድሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ ዐይንና ጆሮ ያደረሰው አርኣያ ነው። ለዚህም በሰውነቱ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል።

ከዚህ እንደምትረዱት የትግራይ ተወላጅ የሆነ ሰው ሁሉ የህወሓት ደጋፊ አይደለም። ስርዓቱን አምርሮ የሚጠላ ትግራዋይ ሞልቷል። የዚህ መነሻ ደግሞ ምክንያታዊ መሆን በብሄር የተገደበ ስላልሆነ ነው። ትግራዋይ የሆነ ሰው ሁሉ የህወሓት ደጋፊ ነው የሚል ሎጂክም አይሰራም።

የህወሓት ደጋፊዎችም ቢሆኑ የተፈጥሮ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል። ከእንግዲህ ወዲህም ማንም ሰው በፖለቲካ አቋሙ ብቻ እንደልዩ ፍጡር የሚታይበት አካሄድ መቆም አለበት። ቢሆንም ህወሓት ሲነቀፍ “የትግራይ ህዝብ ተነካ” እያሉ ከሚጮኹት ጥቂቶችም ጋር አንስማማም። ህወሓት፣ ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ኦነግ፣ ወዘተ ድርጅቶች እንደመሆናቸው ሊነቀፉና ሊወቀሱ ይችላሉ። ህዝብ ግን ህዝብ ነው። በህዝብ ቀልድ የለም።
——
የኢትዮጵያ ህዝብ አስተዋይ ነው። ህዝባችን ከህወሓቱ ስብሓት ነጋ በፊት በተወዳጁ ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር በኩል ከትግራይ ጋር ተሳስሯል።

ከታጋይ ተወልደ ምሕረቱ በፊት በዶ/ር ተወልደ ገብረ እግዚአብሄር በኩል ከትግራይ ጋር ተሳስሯል።

ከአቶ ሐሠን ሽፋ በፊት በሼኽ ሐሰን ሙስጠፋ በኩል ከትግራይ ጋር ተሳስሯል (ይህንን ስጽፍ የትግራይ ተወላጅ የሆነውና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙስሊም ተማሪዎች ጀመዓ አሚር የነበረው አንዋር ሙስጠፋ ትዝ አለኝ)።

ከዶ/ር ዮሐንስ (አርከበ) እቁባይ በፊት በአፄ ዮሐንስ አማካኝነት ከትግራይ ጋር ተሳስሯል።

ከኢንተርኔቱ አሉላ ሰለሞን በፊት በራስ አሉላ አባነጋ አማካኝነት ከትግራይ ጋር ተዛምዷል።

ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያዊያን በዘመን አመጣሹ የህወሓትና የኢህአዴግ ፖለቲካ ተከፍተን የገዛ አካላችን ከሆነው የትግራይ ህዝብ ጋር የምንቆራረጥበት አንድም ምክንያት አይኖርም። በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ያለው ጠንካራ መስተጋብራዊ ህብረት እየጠበቀ የሚሄድ እንጂ በፖለቲካ ወጀብ የሚበጠስ አይደለም።

መንግስታት ያልፋሉ። ህዝቦች ይኖራሉ። እኛ ከህዝቦቻችን ጋር ነን።
—-
አፈንዲ ሙተቂ
ሸገር
ጥቅምት 3/2010

Filed in: Amharic