>

የትግራይ ህዝብና ህወሓት ምንና ምን ናቸው (በየነ ተስፉ)

— ክቡር ወንድሜ Afendi Muteki፣ የትግራይ ህዝባችን ስናስታውሰው በሚል ርእስ በጻፈው ጽሁፍ ላይ https://www.ethioreference.com/archives/8524 ከተለጠፈበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ሃሳባቸውን/አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል፣ ከበጣም የተወስኑ ውጭ አብዛኛው ውይይት በጨዋ ቋንቋ የትካሄደ ነበር ይህ ደግሞ ለወደፊትም መቀጠል አለበት። ውንድሜ Afendi ይህ ዓይነት አይነኬ ግን በጣም ወቅታዊና ሁላችንም አንዲት የጋራ ሃገር እንድትኖረን የምንፈልግ ወገኖች ተወያይተን ወደ ጋራ ግንዛቤ ልንደርስበትት የሚገባ እጅግ አስፈላጊ ርእስ ለውይይት በማቅረቡ ሊመሰገን ይገባል። በዚህ ርእሰ ጉዳይም ማለት የትግራይ ህዝብና ህወሓት ምንና ምን ናቸው በሚለው ምሁራን በጥናትና በምርምር ሰፋፊ ትንታኔውችን አቅርበውበት ሁሉም በእኩልነት በጋራ ልንኖርባት የሚንችል የጋራ አንዲት ኢትዮጵያ የምንፈልግ ወገኖች ተወያይተንበት የጋራ ግንዛቤ ልንይዝበት ይገባል።
— በሃገራችን ባለፉት 26 ዓመታት በተለያዩ ክልሎች ለተፈጸሙት ግዲያዎች፣ እስራቶች፣ ማፈናቀሎች፣ ስደቶች፣ በህዝቦች መካከል ለተፈጠሩ የርስበርስ ጥርጣሬዎች፣ ጥላቻዎች፣ . . . ወዘተ.ና ዛሬ ሃገራችንና ህዝቦቿ ገብተውበት ላለው ወዴት እየተጓዝን መሆናችን በውል ያልታወቅ ምስቅልቅል ሁኔታ ላይ ያደረሰን የህወሓት/ኢህ ኢህ አዴግ አፋኝ አገዛዝ ነው በሚለው ከገጂው ፓርቲ አባላት፣ ድጋፊዎችና ተጠቃሚዎች ውጭ ያለነው ኢትዮጵያዊያን የጋራ ስምምነት አለን ብል ብዙ ስህተት አይመስለኝም። ይህ በእንዲህ እያለ ግን ገጅውን ግንባር/ኢህ አዴግ ውስጥ ያሉት 4ቱ ድርጅቶች በግንባሩ ውስጥ ያላቸው ሚናና በትክክል ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው ማን ነው በሚለው እጅግ የተራራቀ አመለካከትና ግንዛቤ አለን። ግንባሩን በተመለከተ በጣም ከተራራቁት አመለካከቶች/ግንዛቤዎች ዋናዋናውቹም፣
1. ኢትዮጵያን ላለፉት 26 ዓመታት በግንባሩ/ኢህ አዴግ ስም እየገዛ ያለው ህወሓት ነው፣ ግንባሩ ስም ብቻ ነው፣
2. ኢትዮጵያን ላለፉት 26 ዓመታት እየገዛ ያለው ግናባሩ/ኢህ አዴግ ሆኖ በግንባሩ ውስጥ የአንባሳውን ድርሻ የያዘው ህወሓት ነው፣
3. ኢትዮጵያን ላለፉት 26 ዓመታት እየገዛ ያለው ግንባሩ ኢህ አዴግ ነው የሚሉ ናቸው።
አንዲት የጋራ ሃገር ኢትዮጵያ እንድትኖረን ኡነት ከልብ የምንፈልግ ከሆነ በጋራ ጠላታችን ላይ አንድ ዓይነት ግንዛቤ ሊኖረን እየተገባ እስከ ዛሬ ድረስ ተቃዋሚ የምንባል ድርጅቶችም ሆኑ አክቲቭስቶች የጋራ ግንዛቤ የለንም። ለምን ይሆ ሆነ፣ የሚለውና በትክክል ኢትዮጵያን ዛሬ እየገዛት ይለው ገጂ ክፍል ምሁራን በጥናትና በመረጃ የተደገፈ ትንታኔ በማቅረብ ሊመልሱት የሚገባ በውል ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።
ከሁሉም በላይ እጅግ የሚያሳዝነውና የሚያሳስበው ደግሞ ዛሬ በብዙ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ነን በሚሉና በብዙ አባሎቻቸውና ደጋፊዎች እንዲሁም በበርካታ አክቲቭስቶች በስፋትና በተከታታይ ስለተቀሰቀሰበት በትግራይ ህዝብና በህወሓት መካከል ያለው እጅግ ግዙፍ ልዩነት ድብዝዞ የትግራይ ህዝብ እንዳለ የህወሓት ደጋፊ አድርገው ስላቀረቡት በአብዛኛው ከትግራይ ህዝብ ውጭ በሆነው ህዝባችን የትግራይ ህዝብ በጥላቻና በጥርጣሬ ዓይን እንዲታይ መደረጉና የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ጋራ አንድ በማድረግ ህወሓት ለፈጸማቸው ጥፋቶች ተጠያቂ የማድረግ አዝማሞያዎች በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ተቀባይነት እንዲያገኙ የሚደረገው ሩጫ ነው።
— በትግራይ ህዝብና በህወሓት መካከል ያለው ግዙፍ ልዩነት እንደዚህ እንዲደበዝና የትግራይ ህዝብ በስሙ ህወሓት ሲነግደበት እንዴት እንደዚህ በዝምታ ሊመለከተው ቻለ፣ የሚለው ጥያቄ በውል ተጠንቶ መልስ የሚሻ መሰረታዊ ጥያቄ ነው። ለዚህ ጥያቄ ተገቢ መልስ በመስጠት ሁሉም የኢትዮጵያ ወጣት ምሁራን የየድርሻቸውን ሊያበርክቱለት የሚገባ ሆኖ በተለይ ከትግራይ ህዝብ አብራክ የተፈጠሩት ወጣት የትግራይ ምሁራን ደግሞ ከህወሓት መነጽር ወጥተው ማእከላቸው የትግራይ ህዝብን ብቻ በማድረግ በጥናት ላይ ተመስርተው ሊመልሱት የሚገባ ከባድ ጥያቄ ነው። በተለይ ከ1966ቱ አቢዮት ማግስት ጀምሮ ያለው የትግራይ ህዝብ ከ40 ዓመት በላይ ጉዞ በጥልቀት መጠናትና መመርመር ያለበት ነው። ከ1966ቱ አቢዮት ማግስት በትግራይ የጀመረው ትጥቅ ትግል በተመለከተ በቂ ጥናትና ምርምር ተደርጎ ሁሉም በትጥቅ ትግሉ የተሳተፉ ሃይሎች በትክክል ባደረጉት ጥሩ ስራና በፈጸሙት ስህተት የየድርሻቸው መሰጠት መቻል አለበት። ህወሓት እንደሚለው መል አክ ሌሎቹ ደግሞ ሰይጣን ተደርገው የሚነገረውና የሚጻፈ መቆም አለበት። ምክንያቱም ለዚህ አሁን የደርስንበት ምስቅልቅል ሁኔታና የትግራይ ህዝብ በስሙ ሲነገድበት እንደዚህ በፍርሃት ተሸብቦ ዝም እንዲል የተደረገበት ጉዞ ከያኔ ተጀምሮ የቀጠለ በትግራይ ህዝብ ላይ በህወሓት የተጫነ ግፍ ውጤት ስለሆነ።

— ወንድማችን Afendi በራሱ ትንታኔ በህወሓትና በትራይ ህዝብ መካክል ይለውን ልዩኔት እንዳስቀመጠው ሁሉ እኔም የትግራይ ህዝብና ህወሕትን እንዴት ለይቼ እንደማይ ላስቀምጥ። ዛሬ ስልጣን ላይ ያለው የህወሓት ቡድን/የነ አቶ መለስ ቡድን ማለቴ ነው አንድ ጊዜ ሲባል እንደሰማሁት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ አባላት አሉት። እነዚህ የህወሓት ቡድን አባላት በሙሉ ተጋሩና በክልሉ የሚኖሩ የሌሎች ብሄረሰቦች/ኩናማና ኢሮብ ተወላጆች ናቸው። በግምት በክልሉ የሚኖሩ ወደ 4.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ተጋሩና የሌላ ብሄረሰቦች/ኩናማና ኢሮብ ብሄረሰብ ተወላጆች ግን ከህወሓት ጋራ የሚጋሩት ትግራዋይነታቸው፣ ኩናማነታቸውና ኢሮብነታቸው ብቻ ሆኖ በዓላማ ሆነ በጥቅም መጋራ ከህወሓት የተለዩ ናቸው። እነዚህ በግምት ወደ 4.5 ሚሊዮን የሚጠጉት ተጋሩ ኩናማና ኢሮብ ዛሬ ልክ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በህወሓት ቡድን ተረግጠው የሚገዙ ጭቁኖች ናቸው። ስለሆንም ዛሬ የኒዚህ ወደ 4.5 ሚሊዮን ተጋሩና በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ቢሄረሰቦች/ኩናማና ኢሮብ ጭቆና ያንገበገባቸው የተወስኑ ወጣቶች ቁጥራቸውን የፈለገው ይሁን ከ9 ዓመት በፊት ፍርሃትና ዝምታን ሰብረው ዓረና በሚል ተደራጅተው በሰላማዊ መንገድ እየታገሉ ናቸው። እንድሁም ዛሬ በሶሽያል ሚዲያ በሚደረገው ትግልና እንቅስቃሴ ፍርሃት ሰበረው ጸረ ህወሓት/ኢህ አዴግ በሚደረገው የኢክቲቭስቶች ትግልና እንቅስቃሴ ቁጥራቸው የማይናቅ ተጋሩ እየተሳተፉና ደፍሮውና አምርረው ዛሬ በስልጣን ላይ ያለውን የህወሓት ቡድን እየታገሉት ነው ይህ ግን በሚዲያ መግኘት የሚገባውን ያህል ቱክረት እያገኘ አይደለም።

በሃገርቤት/በትግራይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ከላይ ባጭሩ ለማሳየት የሞከርኩት ሆኖ ሳለ፣ በኔ እይታ ዛሬ በሃገራችንና በህዝቦቿ ላይ አንጃቦ ላለው አደጋ ተጠያቂው በህወሓት የሚመራው የኢህ አዴግ አገዛዝ ነው። ስለሆነም ሃገራችንና ህዝቦቿን ከአገዛዙ ባርነት ነጻ አውጥተን እንደ አንዲት ሃገር ለመቀጥል የምንፈልግ ኢትዮጵያዊያን ቆም ብለን አስበን የጋራ ጠላታችንን ማን ነው የሚለውን በጥናት ላይ በተደገፈ ምርምት በግልጽ ማወቅ አለብን። የጋራ ጠላታችን በትክክል ከለየንና ክወቅን በኋላ ደግሞ በዚህ በጋራ ጠላታችን ላይ ብቻ ማተኮር እንጂ አንድን ህዝብ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጋራ ጨፍልቅን በማቅረብ፣ በህዝቡ ላይ ጥላቻ መስበክ ጉዳት እንጂ ምንም ዓይነት ጥቅም ስለሌለው ሁላችን ማቆም አለብን። የዛሬው የውይይት ርእሳችን የትግራይ ህዝብ ስለሆነ ሁላችሁ በትግራይ ህዝብና በህወሓት መካከል ያለውን እጅግ ግዙፍ ልዩነት በተመለከተ የተዛባ/የተሳሳተ አመለካከት ያላችሁና በዚህ መሰረት የተለያየ የጥላቻ ቅስቀሳ በህዝቡ ላይ የምታደርርጉ ያለኣችሁ ወገኖች ሁላችሁ ቆብ ብላችሁ ልታስቡ ይገባል። በየተኛውም ዓለም፣ በየተኛውም ሃገር አንድ ህዝብና አንድ የፖለቲካ ድርጅት ፈጽመው አንድ ሊሆኑ አይችሉም፣ አንድ ህዝብ በተለያየ ምክንያት በስሙ ሲነገድበት፣ በስሙ ጥፋት ሲፈጸም ራሱን አጎንብሶ ዝም ሊል ይምችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፣ በትግራይም ይህ ሁኔታ በዚህ ባሳለፍነው 40 ዓመታት በህዝቡ ላይ በተፈጸመው ግዲያና ብረይን ዎሽ ለማድረግ በመሞከር ተፍጽሟል። ክቡር ወንድሜ Afendi Muteki እንዳለው ድርጅት ጊዜያዊ ህዝብ ግን ዘለዓለማዊ ነውና ለዘለዓለም የኢትዮጵያ መሰረት ሆኖ የኖረውና ለወደፊትም ከህወሓት መወገድ በኋላ የሚኖውን የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ለይታችሁ በማየት ቱክረቱና ዱላዉን በህወሓትና ህወሓት ላይ ብቻ ማነጠጠር መቻል አለባችሁ። ዛሬ የትግራይ ወጣቶች ህወሓትን በተለያየ መንገድ በግልም በተደራጀ መልክም እየታገሉት ስለሆነ ከተጋሩ ውጭ የሆናችሁ ታጋዮች፣ አክቲቭስቶች እነዚህ የትግራይ ታጋዮችና አክቲቭስቶች የሚበራከቱበት፣ የሚጠናከሩበትና የሚሰፉበት ሁኔታ ከመፍጠርና ከማመቻቸት ይልቅ እነዚህ ፍርሃቱን ሰብረው አገዛዙን ለመታገል የቆረጡትን፣ ሁላችን በእኩልነት በጋራ ልንኖርባት የምንችል ኢትዮጵያ ለመፍጠ የራሳቸውን ድርሻ የማበርከት የሚፈልጉ ተጋሩ ከሚያሸሽና የአገዛዙ ዕድሜ ከሚያረዝም ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ለዘመናት የኖረችውን የጋራ ሃገራች ህልውናን ከማሳጣት የዘለለ ፋይዳ ስለሌለው ሰክን ብለን እናስብበት እላለሁ።
— በመጨረሻም፣ ምን መደረግ አለበት በሚለው በግሌ የሚታዩኝ አጭር ሶስት መልእክቶች ለሃገርቤት ታጋዮችና አክቲቭስቶች ላስቀምጥ፣
1. አሁን ስልጣን ላይ ያለው የህወሓት ቡድን የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው የምትሉ የክልሉ ተወላጆች በሙሉ አሁን ተደራጅቶ በሰላማዊ መንገድ እየታገለ ያለውን ዓረና ችግሮችና ድክመቶች ቢኖሩትም ተቀላቅላችሁ ችግሮቹንና ድክመቶቹን እየፈታችሁ ለማጠናከር ተቀላቀሉት፣ ይህ አይሆንም የራሳችን ድርጅት መስርተን ነው የምንታገለው ካላችሁ ደግሞ መደራጀትና መታገል ያለባችሁ ዛሬ ኣንጂ ነገ አለመሆኑ እወቁ።
2. ለትግራይ ህዝብም ለቀሩት የኢትዮጵያ ህዝቦችም ዋናው ጠላት በህወሓት የሚመራው የኢህ አዴግ አገዛዝ መሆኑ አውቃችሁ በሰላማዊ መንገድ ህወሓት/ኢህ አዴግን እየታገላችሁ ያላችሁ የትግራይ ታጋዮችና አክቲቪስቶች እንደ Afendi Muteki ዓይነት ትልቁን ስዕል/ኢትዮጵያን ማየት ከሚችሉ ታጋዮችና አክቲቭስቶች ጋራ ትግላችሁን ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ ማቀናጀትና አብሮ መታገል መቻል አለባችሁ።
3. ህወሓት/ኢህ አዴግ በዚህ ባሳለፍነው 26 ዓመታት በኢትዮጵያ ባጠቃላይ በፈጸመው ጭፍጨፋና የአፈና አገዛዝ የተማርርረው ህዝብ ዛሬ በተለያየ ቦታ ተቃውሞዉን በተለያየ መንገድ እያነሳ ነው። በተለይ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ. . ወዘተ. የባርነቱ አገዛዝ በቃን፣ ነጻነታችንን እንፈልጋለ፣ ህወሓት/ ኢህ አዴግ ከጀርባችን ውረድልን እያለ ነው። ይህ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ. . . ወዘተ. እየተቀጣጠለ ያለው የህዝብ ትግል እንደዚህ በተናጠል ከቀጠል ውጤቱ ምን ሊሆን እንደምችልና ጊዜው ሲደርስ መወገዱ የማይቀርለት ኢህ አዴግ ከስልጣኑ በራሱ ውስጥ በሚፈጠረው ቀውስ ወይም በህዝባዊ አመጹ ሲወገድ የሃገሪቷና ህዝቦቿ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደምችል አሁን ለመተንበይ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለን ይመስለኛል። ዛሬ ትግሉን ሀገራዊ የማድረግና ከኢህ አዴግ መወገድ በኋላ ሀገሪቷንና ህዝቦቿን እንዴት እናስቀጥል የሚለው ትልቁ ዕዳ ዛሬ ትልቁን ስዕል/ኢትዮጵያ ማየት በምትችሉ በቦታው/ሃገርቤት ባላችሁ የተለያየ ብሄር ብሄረሰቦች ተወላጆች ታጋዮችና አክቲቪስቶች ጀርባ ላይ የወደቀ ትልቁ ዕዳ መሆኑ ተንዝባችሁ በተበታተነ ደረጃ እየተደረገ ያለውን ትግል አንድ ጃንጥላ ስር አስባስባችሁ ሃገሪቷና ህዝቦቿ ላይ አንጃቦ ያለውን አደጋ በጋራ ለማስቀረት መሰባሰብና መስራት የግድ የሚበት ወቅት ላይ መሆናችን መገንዘብ አለባችሁ እላለሁ።
ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ፈጠሪ ይባርክ፣ ይጠብቅ።

Filed in: Amharic