>
8:46 am - Tuesday July 5, 2022

የ ቴዎድሮስ ካሳሁን “ሆያ ሆዬ!”

ዚህ ትውልድ መሀከል ካሉ ሙዚቀኞች ሁሉ በተለየ የዘርፉ የንግስና ዙፋን ላይ እንዲቀመጥ ያደረገው ድምፁ፣ የግጥም አፃፃፍ ችሎታው እና የዜማ አወጣጡ ነው የሚል ድምዳሜ መስጠት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ጎሳዬና ማዲንጎም መረዋ ነው ድምፃቸው… ቢበልጥ እንጂ አያንስም… ጂጂም ስትፅፍ ልብ ታደክማለች በችሎታዋ የእዮብም ጥበብ ገራሚ ነው! ዘሪቱ ስትዘፍን ደመናውን ጠርጋ የአደይ ሰማይ ታመጣለች… ሌሎችም ድንቅ ልጆች አሉ! ታዲያ የዚህ ሰው ልዩነቱ ምንድን ነው? በእኔ አመለካከት በዚህ ደረጃ ሊገን የቻለበትን ነጥቦች አስቀምጣለሁ፡፡

1. በቅድሚያ

በሀገራችን ባህል ሰው ከሞተ በኋላ እንጂ በህይወት እያለ ማወደስ አልተለመደም፡፡

በህይወት እያለን የሰራናቸው ታላላቅና ጥሩ ስራዎቻችን ደብዝዘው ትንሽ ያጠፋናቸው ውስን ጥፋቶች ይደምቁብናል፡፡ ነገር ግን ከሞትን በኋላ በቀብራችን እለት ከሚነበበው የህይወት ታሪካችን ጀምሮ የሰራናቸው ትላልቅ መጥፎ ነገሮች ይደበዝዙና በተገላቢጦሹ ትንሽም ብትሆን የሰራናት ጥቂቷ ነገር እንድትደምቅ ይደረጋል፡፡

ይህ የተዛነፈ የማህበረሰባችን ባህል ከድምፁና ከችሎታው ባሻገር ለቴዎድሮስ ካሳሁን መግነን ቀዳሚውን ሚና ተጫውቷል፡፡ በህይወት ካሉት ይልቅ ለሞቱት የዘፈነው ይበዛል!

ጥያቄው እዚህ ላይ ነው፤ የሞቱት ነገስታት በነበሩበት ዘመን ቴዲ በህይወት እያሉ ቢዘፍንላቸው ህዝቡ ልክ እንደ አሁኑ ያደንቀው ነበር?

መልሱ አይድለም ነው! በህይወት ያሉትን ማሞገስ ካለመቻላችን ባለፈ በጨረፍታ ተጨማሪ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡

1.1 አፄ ቴዎድሮስ

ይህ ንጉስ ኢትዮጵያ ተበታትና በአካባቢ አለቆች ትተዳደር በነበረበት ወቅት ብቅ ያለ ሲሆን፤ ዘመነ መሳፍንትን ለማስቆም የተለያየ የሀይል እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ከዛም ባለፈ “የቤተክርስቲያን የገንዘብ ወጪ እና የያዘችው መሬት ስፋት ተገቢ አይድለም…!” በሚል መሬቷን ቀንሶ የዲያቆናትና ቀሳውስቱንም ቁጥር ገደብ አበጅቶለት ነበር፡፡ በወቅቱ የመንግስታችን ሌላኛዋ መንግስት የነበረችው አትነኬዋን ቤተክርስቲያን በመንካቱ በንጉሱ ላይ ከፍተኛ ቂም አሳድሮ ነበር የሀገሬው ህዝብ፡፡

በሀይለኝነቱ የተረገመ፣ የኮሶ ሻጭ ልጅ በመሆኑ የተናቀ፣ በተራማጅ አመለካከቱ የተነሳ ደግሞ በጊዜው እጅግ የተጠላ መሪ ሆኖ አልፏል፡፡

አሁን ደግሞ፤ እድሜ ከሞተ በኋላ ማሞገስ ለሚወደው ህዝብ ይሁንና…

በሀይለኝነቱ ተመረቀ፣ የኮሶ ሻጭ ልጅ በመሆኑ የህዝብ ተባለ፣ በተራማጅ አመለካከቱ የተነሳ ደግሞ ስልጣኔን ናፋቂነቱ ተደንቆ ለመወደስ በቃ!

ታዲያ ያን ጊዜ በብሪታንያ የጦር አዝማቾች እየተነዱ የመጡት ህንዳዊ የእንግሊዝ ባንዳዎች የሀገራችንን ድንበር አቌርጠው ንጉሱ እስካሉበት ድረስ ሲመጡ ያለ ምንም መንከራተት በገዛ የሀገራችን ዜጎች እንክብካቤ እየተመሩ ነበር፡፡

እናሳ ቴዎድሮስ ካሳሁን ለአፄ ቴዎድሮስ በወቅቱ ቢዘፍን አድናቂው ይበዛል ወይንስ ሰዳቢው?

1.2 አፄ ዳግማዊ ምንሊክ

እኚህ ንጉስ እንኴ በዘመናቸውም በስማቸው ሲማል የነበሩ ናቸው፤ ቁም ነገሩ ግን ወዲህ ነው፡፡ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጨው” የለመድን እኛ ነገሮችን ከስራቸው ጠለቅ ብለን ማየት አንፈልግም፡፡ አፄ ቴዎድሮስን የገፋው ህዝብ ነው ለምንሊክ በስሙ የማለለት፡፡ ቴዎድሮስ ካሳሁንም ስለሁለቱ ነገስታት ባህሪና የአገዛዝ አካሄድ ጠለቅ ብሎ ቢረዳ በአንድ ልብ ለሁለቱም መዝፈን አይችልም፡፡ በአንድ አፍ ሁለት የተለያየ ምላስ ይሆንበት ነበር፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ለህዝብ የቆሙ መሪ ነበሩ በተቃራኒው ደግሞ ምንሊክ ለአካባቢ ነገስታ የወገኑ ናቸው፡፡ በሀገራችን እስከ አሁን ፍዳ የምናይበትን አካሄድ ጥመት የፈጠሩትና መሰረት ያበጁለት እኚሁ ምንሊክ ናቸው፡፡

ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ ዘመቻ ሲያካሂዱ፤ ለመግዛት እንዲመቻቸውና ለራሳቸው የስልጣን መርዘም ጥቅም ሲሉ በየአካባቢው ላሉ ነገስታትን “ከእኔ ጋር ከተስማማችሁ እዛው ባላችሁበት ህዝቡን እንድትገዙ ፈቃድ እሰጣለሁ!” በማለት የመደብ ገዢነትነን አስፋፍተዋል፡፡ በእርሳቸው የተነሳ ገበሬ፣ አንጥረኛ፣ ሸክላ ሰባሪ በአጠቃላይ ሰራተኛው መደብ እንዲናቅ ሆኖ ለአጤ ምንሊክ ግብር የሚሰበስብላቸው ገዢ መደብ፡- መሪ ጌታ ቀኝ አዝማች ግራዝማች እየተባለ ቁጭ ብሎ የሚበላው እንዲከበር ሆኗል፡፡

ሁሉም በየአካባቢው ሆድ የባሰውን አፍኖ እየያዘ ታሪክም የጉልበተኞች ናትና ደግ ደጉ ብቻ እየተፃፈላቸው ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ሰርቶ የመላብት ጥላቻውና ገንዘብ እየሰበሰቡ ሰርቆ የመክበር ቁስሉ ግን አልሻረልንም፡፡

በግብር ሰብሳቢዎቹ የምንሊክ ሹመኞች ቢጨቆንም ለሀገሩ ግን “እምቢ!” ብሎ የተመመው ወርቅ የሆነ የሰራተኛውን መደብ ዜጋን ደም የጠጣችው የሀገራችን መሬት አድዋ ምስክሬ ናት! በጦርነቱ ላይ ማን ከፊት ማን ከኋላ እንደነበር የኢትዮጵያ አምላክ ይመሰክራል፡፡

ታዲያስ አሁን ያለው ይሄ ሰራተኛ መደብ በሟች ላይ መጨከን አይሆንለትም እንጂ ታሪኩን እያወቀ ጥቁር ሰው ሲባል አብሮ ይዘላል ወይ? አባተ ቧ ያለው ተኩሶ የጣለውን መድፍ ቴዎድሮስ ካሳሁን ግጥሙ ቤት እንዲመታለት ብቻ ሲል “ባልቻ አባ ነፍሶ መድፉን ጣለው ተኩሶ!” እያለ በንቀት ዘፈነ! ይሄም ህዝብ ጨፈረ! ታሪክ ማዛባቱ እየተነገረውም ቢሆን ብዙ አድናቂ ስላለው ብቻ ይቅርታ ለመጤቅ አልፈለገም፤ ንጉሱ! የሀዲስ አለማየሁን እንቁ ድርሰት ፍቅርን እስከ ገዳም አድርጎበት እንዲያ ለፍቅር ሟች የሆነ በዛብህን አዲስ አበባ አስገብቶ ሲያስለቅሰው “የሚገርም ልጅ!” እያለ የሚያደንቅ አንባቢ ህዝብ ተፈጠረ!

እመነኝ፤ ይሄ የሚያነግስህ በስሜቱ ልክ እንጂ በጭንቅላቱ ልክ አይድለም!

1.3 አፄ ሀይለ ስላሴ

የሙታን አድናቂውና ንጉሱን በተመለከተ አንዲት መsጫ ነው ያለኝ፤

ደርግ ንጉሱ መውረዳቸውን ያወቀ እለት እንደዛ በአዲስ አበባ ላይ ጉንዳን መስሎ የወጣው ህዝብ አፄ ኃ/ስላሴ በመንበረ ስልጣናቸው እያሉ ቴዎድሮስ ካሳሁን ቢዘፍንላቸው ኖሮ ከሰልፉ በኋላ “አንተ አሽቃባጭ ይሀው ንጉሱ ወረዱ!” እያለ ቀጥቅጦ ነበር የሚገድለው… ያ የተጨቆነ ህዝብ! እንኴን አልነበረ ወይንም ያኔ የነበሩት ጭቁን ህዝቦች እንኴን አለቁለትና እንኴን ከሰማንያዎቹ ወዲህ የተወለደ አድናቂ በዛለት!

2. በቀጣይ

በወቅቱ የነበሩትን የሀገራችን ህዝቦችን ያላማከለ የሙታን አደናነቁን ከማየት ስንሻገር ደግሞ የእኛን ሰው የነፃነትን ኑሮ ከማጣጣም ይልቅ ነፃነትን የመለመን ስነልቦናዊ ዝንፈትን እናገኛለን፡፡ ለቴዎድሮስ ካሳሁን መግነን ሁለተኛው አንኴር ምክንያትም ይሄ ነው፡፡

በመሰረቱ ነፃነት የሚለመን ነው ወይንስ የሚኖር?

እስከሚገባኝ ድረስ ነፃነት “ስጡኝ!” ተብሎ የሚታደል ነገር አይድለም፤ በትግልም ቢሆን የሚኖሩት አንጂ!

በጥቁር ህዝቦች ታሪክ በተለያየ አካሄድ ታግለው ነፃ ወጡ እንጂ ለምነው ነፃ አልወጡም፡፡ በዘመናችን ያለነው የሀገራችን ዜጎች አካሄድ ግን በየ-ማህበረሰብ ድረ-ገፁ ላይ ነፃነታችንን ስጡን አያልን መለመኑን ተያይዘነዋል፡፡ በተግባር ስንፈተን ግን የነፃነት ትግል ቁርጠኝነት የለንም፤ አስመሳይና ፈሪዎች ሆነናል፤ ቴዲ ደግሞ ለማስመሰልና ለፍርሀታችን ትልቁ ዋርካ!

በእርግጥ በነፃነት እየኖሩ ይሄ መንግስት ስላልፈለገ ብቻ እስር ቤት የገቡ አሉ፡፡ እነርሱ እጃቸው ታሰረም አልታሰረም ነፃ ናቸው!!! እዚህ ሆኖ ውጪ ሀገር ሆኖ የሚጮሀው ሁላ ግን እጅ እግሩ ባይታሰርም የህሊና እስረኛ ነው፡፡

የዘንድሮ ታጋይ “ከህሊናውና ከእጅ እግሩ የቱ ይታሰር ምረጥ?” ብትለው “ህሊናዬ ይታሰር!” ይልሀል፡፡ መብላቱን ማቆም አይፈልግማ!!!

በዘጠና ሰባቱም እንዳየነው፤ ይቅርታ ጠይቀው ከቃሊቲ ይወጡና አሜሪካ ሄደው ይታገሉልናል! ከዛም ቴዎድሮስ ካሳሁን ስለሆነ ጉዳይ በመንግስት ላይ ቃል ሲያወጣ ለአፍታም ቢሆን ከህሊናቸው እስር ለመላቀቅ ሲሉ አብረውት ይጮሀሉ፡፡ እጅ እግራቸው ሳይታሰር መዝፈን እንጂ በህሊና ነፃነት በነፃነት መኖር አይችሉማ!

ነፃነት የሚያጎናፅፈን የአኗኗር ዘይቤያችን እንጂ የአገዛዝ ስርአት አይድለም!

እየታመምንም ቢሆን በመኖራችን እንጂ ቴዎድሮስ ካሳሁን በዘፈነው አይድለም ነፃነትን እንድታብብ የምናደርጋት!

3. ደግሞ በሶስተኛነት

ቴዎድሮስ ካሳሁን የነገሰበት ቁልፍ ምክንያት ሙገሳ ብቻ የመውደድ የዘገመ ማህበረሰባዊ አመለካከት ባህላችን ነው!

ጎጃሙም ጎንደሬውም… ሰሜን ደቡብ… ኦሮሞ ጋምቤላም እንዳለ የአይዞህና የሙገሳ አድናቂ ነው፡፡ ህፃናት እንኴን ሳይቀር ይህንን ስነልቦና አውቀው በ“ሆያ ሆዬ!” ትንሽ ሳንቲም ስንሰጣቸው ሙገሳውን ሞቅ ያደርጉትና ገንዘብ ያስጨምሩናል፡፡

ምንም መጠለያ ሳይኖርህ “የኔማ እንትና የዚህ ቤት ጌታ!” ሲሉ ፈገግ ትልና በኩራት ብር ትሰጣለህ!

ቴዲም በ “ሆያ ሆዬ!” ስታይል ቀልባችንን ነድፎታል!

እየደጋገመ “ፍቅር ያሸንፋል!” ማለቱ ጨዋታ ነው ለእኔ፤ በቃል ደረጃ ካየነው ጥላቻም ሆነ ፍቅር እኩል ናቸው፡፡

ልዩነታቸው የሚጀምረው ስጋ ከሚለብሱበት ቅፅበት ጀምሮ ነው፡፡ ያኔ መንገዳቸው ለየቅል ይሆናል፡፡ እናስ ይሄ ህዝብ ፍቅርን እሺ ብሎ በራሱ ላይ ማንገስ፤ ቃሉን ስጋ ማድረግ ካልጀመረ ግዑዙ ፍቅር እንዴት ነው ብቻውን የሚያሸንፈው?

በወገንተኝነት ተበክለን…
በህይወት ያሉትን በመጥላት ሰልጥነን…
ዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ የምንለው ማንነታችን ሳንተው….
ሰርቶ መብላትን ንቀን…
ዘርፎ በአንድ ጀንበር መክበር ላይ ተጣብቀን…

ይሄ ሁሉ ጉድፍ ተከምሮብን እያለ ቴዎድሮስ ካሳሁን ደካማ ማንነታችንን ሳይወቅስ ከነ እድፋችን የወርቀዘቦ ካባ ቢያለብሰን ሰርጋችን ለአይን ያምራል እንጂ ስንጨፍር እያደር ጠረናችን አይከረፋም ወይ?

እንግዲ ይህን ብያለሁ!

ፈጣሪ የኢትዮጵያን ህዝብ በማስተዋል ይባርክ!

Filed in: Amharic