>

ህውሃት የአረጀ ዶሴ እያገላበጠች አሮጌ ስልቶችን አሁንም እየተጠቀመች ነው (ቬሮኒካ መላኩ)

ሀ ~ ዛሬ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በእጅ ፅሁፍና በፊርማ ወደ ሳይበሩ አለም የለቀቃት ቀቢፀ ተስፋ አስቂኝ ናት። ፅሁፏ ለቀጣይ 25 አመታት ድርጅታቸው ያለውን ራእይ ልትነግረን ትሞክራለች ። ይሄ ስልት የአረጀ የአፈጀ መንግስታት ለመውደቅ አንድ ሀሙስ ሲቀራቸው የሚጠቀሙበት ስልት ነው።
የዚች ስልት አላማ በህዝቡ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ውሃ ለመቸለስ ። በለውጥ ስሜት የሻፈደውን ህዝብ ተስፋ ለማስቆረጥ የምትነዛ ስልት ነች። ህውሃት የአረጀ ዶሴ እያገላበጠች አሮጌ ስልቶችን አሁንም እየተጠቀመች ነው። ስልቱ “አሁንም ጠንካራ ነን ” የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ነው።
የ1997 ምርጫን ተከትሎ ህውሃቶች በጣም ተስፋ ቆርጠው በነበረበት ወቅትና መለስ ዜናዊም ከ4 ኪሎ ቤተመንግስት ወጥቶ ደብረዘይት አየር ሀይል ውስጥ የሚበርበትን አውሮፕላን አዘጋጅቶ በነበረበት ወቅት ለሪፖርተርና ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ የላኳት ዜና እንደዚሁ ያለች ነበረች ። ይች ዜና ” ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚሆን አዲስ ቤተ መንግስት እየተገነባላቸው ነው ።” የሚል ነበር።

ሁ ~ የኦሮሚያው የተቃውሞ አመፅ አዲስ ህቡእ አመራር ያገኘ ይመስላል። ውስጡም ብዙ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ሳይቀላቀሉ አይቀርም። ጃዋር መሀመድ ” ይሄን ተቃውሞ እነሱ እንደሌሉበትና ሌላ ድብቅ አጀንዳ ባላቸው ሰዎች እየተዘወረ እንደሆነ ተናግሯል። ይሄንጉዳይ እውነት የሚያስመስሉ በቂ ምልክቶች አሉ።
ወያኔ የኦሮሚያው ተቃውሞ ሰልፍን ለማክሰም የተጠቀመችበትን ስልት ወደ ኋላ ተመልሰን ካስታወስን ምክንያቱ ሊገለፅልን ይችላል። ይሄ የአሁኑ የቄሮ ሰልፍ የደህንነት እጅ እንዳለበት ምልክቶች አሉ። ወያኔ የኦሮሚያን ተቃውሞ ለማቀዝቀዝ የተጠቀመችበት ስልት ” የቄሮን አጀንዳ ነጥቆ መልሶ ማስተጋባት” የሚል ስልት ነው።
ጃዋር መሀመድ “Oromo Revolution ” ብሎ ለኦሮሚያ ትግል አዲስ ምእራፍ መጀመሪያ ፊሽካ ሲነፋ ህውሃት ደሞ በኦፒዲኦ አማካኝነት ከጃዋር ” Rovolution ” የሚለውን ከባድ የመታገያ ስልት ቀምታ ” Economic Revolution ” በማለት የኦሮሞ ህዝብን ስሜት ለወራትም ቢሆን እንዳቀዘቀዘችው እናስታውሳለን ። አሁንም ተመሳሳይ ስልት ይመስላል ። እነ ጃዋር የሚመሩት ቄሮ ኦሮሚያን በተቃውሞ ሲንጣት ህውሃትም በጎን የራሷን የኦሮሞ ክንፍ አዘጋጅታ ጀዋርን ከጨዋታ ውጭ የማውጣት ስትራቴጅ ቀይሳ ሊሆን ይችላል።
ይሄ የአሁኑን ተቃውሞ ለመጠራጠር ከሚያበቁት ምክንያቶች አንዱ በኦሮሚያና በአማራ ኩታ ገጠም አካባቢዎች መደረጉ ነው። እዚህ ላይ በአማራና በኦሮሞ መካከል እየጎለበተ የመጣው መደጋገፍ ቆሽቱን ያሳረረው ወያኔ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ክብሪት ለመጫርና ቤንዚን ለመርጨት ወደ ኋላ ስለማይል ህዝቡ በከፍተኛ ብስለትና ስክነት መከታተል አለበት።

~ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ምክንያት አድርጎ” የኦሮሞ ፕሮቴስት ” ከሁለት አመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የፈነዳ ሰሞን ኢታማዥር ሹሙና “ችፍ ኦፍ ስታፍ ” ሳሞራ የኑስ በሚዲያ ቀርቦ ” ይሄ የክልሎች አከላለል እኮ የሀሳብ መስመር ነው። እኛ ከፈለግን ይሄን አከላለል አፍርሰን እንደገና በሚያመች መልኩ ማካለል እንችላለን ።” ማለቱን አስታውሳለሁኝ ።ዛሬ ደሞ ከሁለት አመት በኋላ የኢትዮጵያ ካርታ ስራዎች ባለስልጣን የሆነው ሰው የአሁኑን ፌደራላዊ አከላለል ህጋዊ መሰረት የለውም እያለ ነው። ይሄ በጣም አስገራሚና ሰዎቹ አሁንም ሌላ እቅድ ያላቸው መሆኑን እያመለከተን ነው።

Filed in: Amharic