>
6:48 am - Wednesday July 6, 2022

የአቶ ካሳን ንግግር ሳስብ | በጸሎት ፍ. (ስዩም ተሾመ)

በቅርቡ በድንገት ከሚኒስትርነት ወደ አምባሳደርነት የተመደቡት ነባሩ ታጋይ አቶ ካሳ ተክለብርሀን ለመንግሥታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲህ አሉ።
– ‘የኢህአዴግ አመራር….በጥልቅ ተሀድሶው ወቅት በነበረው ግምገማ ህዝባዊነት እና ጥርት ያለ የዓላማ ፅናትን ከመላበስ አኳያ ክፍተት የታየበት ስለመሆኑ፣
– …መደበላለቆች እየታዩ በመሆኑ ከስሜትና ከዘረኝነት የፀዳ አስተሳሰቦችን በማስረፅ ሰልፍን ማስተካከል እንደሚገባ….’

አዎ!.. አቶ ካሳ በገደምዳሜውም ቢሆን በአመራሩ ውስጥ የተከሰቱ ችግሮችን ሊጠቁሙን ሞክረዋል።
ቀለል ተደርገው የተነገሩ ችግሮችን አፍታተን እንያቸው።

የዘረኝነት ጉዳይ…
ምንድነው ዘረኝነት? መገለጫዎቹ ምንድናቸው? በአጭሩ ዘረኝነት ለራስ ብሄር፣ ጎሳ፣ ቀበሌ… ጥቅም መቆም፣ ሽንጥን ገትሮ መሟገት ነው። ጠንከር ሲልም የእኛ ብሄር ከሌላው የተሻለ ነው የሚል አስተሳሰብና ተግባርን ይዞ መገኘት ነው። ይህ የቆሸሸና የዘቀጠ ተግባር በአመራሩ ውስጥም እየተንጸባረቀ ነው መባሉ ደግሞ ያስደነግጣል፤ ሕክምናውንም ውስብስብና አስቸጋሪ ያደርገዋል።

የዚህ አስተሳሰብ መሠረቱ ምንድነው? አቶ ካሳ እንደሚሉት እንዲህ ዓይነት ሥር የሰደደ ቆሻሻ አስተሳሰብ በአንድና በሁለት ሣምንት ለብለብ ሥልጠና ማስወገድ ይቻላል ወይ? በአሰልጣኝነት የሚመደቡ አመራሮች በሥነምግባራቸው፣ በክህሎታቸው፣ ከሙስናና ብልሹ አሠራር ምን ያህል የጸዱና አርአያ መሆን የቻሉ ናቸው…? ነገሩ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያጭር ነው።

አዎ! ኢህአዴግ ባለፉት 26 ዓመታት ዘረኝነትን የሚያቀነቅኑ ሹሞች፣ ካድሬዎች እና ደጋፊ ነን ባይ ግለሰቦችን በብዛት ማፍራት የመቻሉ ጉዳይ እውነት ነው። ይህ የሆነው ለምንድነው? የግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ ወይንም ርዕዮተ ዓለም ስለሚፈቅድ? ከፍተኛ አመራሩ በዘረኝነት ችግር በመበከሉ ወይስ ሌላ… የሚለውን ለመመለስ የተጨበጠ ጥናትና ማካሄድን ይጠይቃል።

ከምንም በላይ ግን ይህን የዘረኝነት መርዛማ ቫይረስ የተሸከሙ ሰዎች ኢህአዴግ ውስጥ ምን ያደርጋሉ ተብሎ ሊጠየቅም ይገባል።
ዘረኛ አስተሳሰብና ተግባር የተጠናወተው ሹም ተለቅሞ ወደቤቱ ይሸኛል ወይንም በምግባሩ ይቀጣል እንጂ ከእነእድፉ እንዲቀጥል ዕድል እንዲሰጠው መታሰቡ ጤናማ መፍትሄ አይደለም።

ዘረኝነትን የሚሰብኩ የአስተሳሰብ ድኩማን ስለብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት፣ ሠላም፣ ወንድማማችነት ሊናገሩ፣ ሊያስተምሩ፣ አመራር ሊሰጡ አይችሉም። ግን እየሆነ ያለው በተጨባጭ ምንድነው? የለያቸው ዘረኞች ስለዘረኝነት አስከፊነት ሰባኪ እየሆኑ ነው። ከገቢያቸው በላይ ሀብት ያፈሩ የመንግሥት ሌቦች ማይክ ጨብጠው ስለሙስናና ኪራይሰብሳቢነት አስከፊነትና አደጋ ሲሰብኩ እያየን፣ እየታዘብን ነው። እንደእነዚህ ዓይነት እርኩሳንን በትምህርትም ሆነ በሥልጠና ማረቅ አይቻልም። በትምህርትማ ቢሆን ቀድመው የጫኑት ዲግሪና ማስተርስ ሰው ባደረጋቸው ነበር። ግን አልሆነም።

የሕዝባዊነት መጎደል ጉዳይ
አመራሩ ሕዝባዊነት ማጣት ወይንም የሕዝብ ጥቅምን ማስቀደም አለመቻል ተጠቅሷል። አሁንም በኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ውስጥ ጰረ ሕዝብ አጀንዳ በግልጽም ይሁን በህቡዕ ካለ ድርጅቱ በሞት አፋፍ ላይ ቆሟል ማለት ነው። ውስጡ ተበልቷል ማለት ነው። ለምን ቢባል ሀገር ሕዝባዊ አስተሳሰብ በራቃቸው ግለሰቦች ልትመራ አትችልምና ነው። የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ግልጽ ራዕይ፣… የሌላቸው መሪዎች ሆድ ከመሙላት የዘለለ ዓላማን ሊያራምዱ አይችሉምና ነው።

በጥቅሉ የአቶ ካሳ ለስላሳ ንግግር፤ ኢህአዴግ ‘ጥልቅ’ ያለውን ተሀድሶ ካወረደ ከዓመት በሀላም መታደስ አለመቻሉን ጮክ ብሎ የሚያሳብቅ ነው።
የአቶ ካሳ ንግግር ለየት የሚያደርገው በፈራ ተባም ቢሆን ግልጵነት የተንጰባረቀበት መሆኑ ነው። የኢህአዴግ ምክርቤት ጎምቱዎቹ አመራሮች አሁን ለታ ተሰብስበው ምን አሉን? ‘ጥልቅ ተሀድሶው በተያዘለት አቅጣጫ መሠረት በተሳካ ሁኔታ እየሄደ ነው….’ አሉን። ይህ እንግዲህ ዕቅድ ነዳፊውም፣ ፈጻሚውም፣ አፈጻጸም ገምጋሚውም አንድ አካል ሲሆን የሚያጋጥም የተለመደ በሽታ ነው። ስለራስ ደስኩሮ ራስ ማጨብጨብና ማስጨብጨብ።

አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ጥሩ ነገር ብለዋል። ‘ሥልጣን ሕዝብ የሰጠን ኮንትራት ነው’ ብለዋል። አዎ! እሳቸው እንዳሉትም ገዥው ፓርቲ ከሕዝብ በተቀበለው ኮንትራት ሊሰራበት ካልቻለ ሕዝብ ኮንትራቱን ሊሰርዘው ይችላል። በተራ አገላለጵ ‘በቃህኝ’ ሊል ይችላል።
ኢህአዴጎች እየተሰማችሁ ይሆን?

Filed in: Amharic