>

የኦሕዴድ የቀጣይ ግማሽ አመት እቅድ (ኤርሚያስ ለገሰ)

በብዙዎች ዘንድ ኦህዴድ አሁን የያዘውን አቋም አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጣሉ። በአንድ በኩል አባዱላ የወሰደውን እርምጃ እና የለማ መገርሳ ካቢኔ ከአንደበታቸው የሚወጣውን ኢትዬጲያዊነት በመመልከት እድል ሊሰጣቸው ይገባል የሚሉ አሉ። በሌላ በኩል አሁንም ከጀርባ ያለው ህውሓት ስለሆነ የተቀነባበረ ድራማ ነው የሚሉ ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪም ” ፌንጣ ብትቆጣ ክንፏን ለመጣል ነው” በሚል የሚተርቱ አልጠፉም። የራሴን ቦታ ስመለከተው ኦህዴድ ዋነኛ የለውጥ ሐይል ባይሆንም በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ አመኔታ የሚፈጥሩ እርምጃዎችን መውሰድ ከቻለ ሊበረታታ እንደሚገባ ይሰማኛል። ኦሕዴድን ምንም ሳናስጨንቀው ህውሓት ከቀየሰው ህጋዊ ማእቀፍ ሳይወጣ የሚፈፅመው ቁልፍ ተግባራት የመበረታታቱ መነሻ ሊሆን እንደሚገባ እምነት አለኝ። በመሆኑም የሚከተሉትን ቀላልና ሕጋዊ ተግባራት በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ( ህዳር – ሚያዝያ) ይፈፅምና ማበረታታቱን ወደ ድጋፍ እንቀይርለት።

አንደኛ: የኢህአዴግ ሕገ ደንብ በግልፅ እንዳሰፈረው አባል ድርጅቶቹ በማንኛውም ወቅት ከግንባሩ ለቀው መውጣት ይችላሉ ። በመሆኑም ኦሕዴድ በግንባሩ ሕገ ደንብ መሰረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፍቺውን በሚቀጥለው ጉባኤ ላይ አቅርቦ መፈፀም ይኖርበታል ። ይሄን ማድረግ ሕጋዊ ነው። ቀላልም ነው።
ሁለተኛ: ኦሕዴድ ከኢህአዴግ ጋር ያለውን ፍቺ በሶስት ወር ውስጥ ከፈጣጠመ በኃላ ራሱን ወደ አገር አቀፍ ፓርቲ ማሳደግ ይኖርበታል። በፓለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ መሰረት አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ ከአራት ክልሎች እስከ 1500 ድጋፍ ካሰባሰበ በአገር አቀፍ ፓርቲነት መመዝገብ ይችላል። ኦሕዴድ ከኦሮሚያ ፣ ከአማራ፣ ከሱማሌ፣ አዲስ አበባ፣ ሐረሬ… ወዘተ የመሳሰሉት የኦሮሞ ተወላጆች ከሚገኙበት አካባቢዎች ድጋፍ ማሰባሰብ ይችላል። ይሄን ማድረግ ህጋዊ ነው። ቀላልም ነው ።
ሶስት: የኦሕዴድ ከኢሕአዴግ ተገንጥሎ መውጣት ፓርላማውን፣ አስፈጻሚ አካላቱን ፣ ፕሬዝዳንቱን፣ በሹመት የሚሰጡ ቦታዎችን ( የጦር ጄኔራሎቹን ጨምሮ) ህጋዊ በሆነ መንገድ ሽግሽግ መጠየቁ አይቀርም። በተለይ ፓርላማው ውስጥ አብላጫ ድምፅ ለመያዝ ጥምረት መፍጠር ይችላል። እንደ ኦህዴድ ሁሉ ብአዴን ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ከቻለ ከ547 ወንበር ውስጥ 316 በሁለቱ የተያዘ በመሆኑ በሁለቱ ድርጅቶች ጥምር መንግስቱ ሊመሰረት ይችላል።ይሄንን ማድረግ ህጋዊ ነው። ቀላልም ነው።
አራት: እስከ ቀጣይ ምርጫ የሚቆየው ጥምር መንግሥት የመንግስታዊ ስልጣኑን ማስተካከያ መስራት ሌላው ቁልፍ ተግባሩ ሊሆን ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፣የኢታማዦር ሹም፣ የደህንነት ሚኒስትር ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የኢኮኖሚ ሚኒስትር፣ የፋይናንስና ገቢዎች ሚኒስትር፣ የፌዴራል ፓሊስ ዳሬክተር ጄኔራል ፣ በፓርላማው የመንግሥት ዋና ተጠሪ፣ አፈጉባኤ ፣ የአቃቤ ህግ ዴሬክተር በሙሉ የጥምር መንግሥቱን በፈጠሩት ኦሕዴድ እና ብአዴን አመራሮች ብቻ ይያዛሉ። የጦር ጄኔራሎች ብዛትም ከአጠቃላዩ ሰባ በመቶው ብቃታቸው የተረጋገጠ የኦሮሞና አማራ ተወላጆች ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ሕገወጥነት አይደለም። በጣምም ቀላል ነው።
አምስት: የጥምር መንግስቱ የፓለቲካ እስረኞችን በመፍታት ስራውን ይጀምራል። ቀጥሎም የሚዲያ፣ የመያድ፣ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጐችን ሙሉ ለሙሉ በፓርላማ ይሽራል። በማስከተልም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በውጭም በውስጥም ለሚገኙ የፓለቲካ ድርጅቶች የብሔራዊ አገር አድን ጥሪ ያቀርባል። የእውነት አፈላላጊና የብሔራዊ እርቅ ጉባኤ ይጀምራል። ይሄ እርምጃ ህጋዊ ነው። ቀላልም ነው።
Filed in: Amharic