>
10:41 am - Friday October 22, 2021

የእነ ሚሚ ስብሃቱ ወጥመድ (ሙሉነህ ዮሃንስ)

የቀድሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ

ጊዜው ይነጉዳል። ለውጡ ግን ሲንፏቀቅ ቆይቶ ገና አሁን ላይ ነው የቁርጥ ሰአት መድረሱን እኛም ጠላቶቻችንም እርግጠኛ የሆነው። የኢትዮጵያን ህዝብ ጥያቄ በማስተጋባት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንኳን የዩኒቨርሲቲ ተማሪወች ትዝብት ላይ እየወደቁ ነው። የወያኔ ከፋፍለህ ግዛው ዋና ተጠቂና ተጠማቂወች እየሆኑ ይገኛሉ።

ወደ ቀደመው ጉዳይ ልመልሳቹህና 17 አመታት የኋሊት ስንሄድ ታሪካዊውን የ1993 የተማሪዎች አመፅ እናገኛለን። ያኔ አንፈራም ነበር። ድፍረቱ ነበረን። ያኔ በዘር አልተቧደንም ነበር። በጋራ የሚያንቀጠቅጥ ነጎድጓዳማ ድምፅ ነበረን። ያኔ እከሌ ወያኔ ነው መባል እጅግ የሚያስነውርና የሚያሳፍር ነበር።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪወች ህብረት ነበረን ሊቀመንበራችንም አሁን በካናዳ የጥብቅና ባለሞያ የሆነው የያኔው የህግ ተማሪ የነበረው በድፍረቱ ወደር የማይገኝለት ተክለሚካኤል አበበ ነበር። ተክሌ ቤተሰቦቹ ከማሃል ሃገር ተነስተው በስራ ምክንያት ሄደው ሃገራቸው ሆኖ በሚኖሩበት የኦሮሞ ማህረሰብ ስላደገ ከማንኛውም ተማሪ ጋር በቀላሉ ይግባባ ነበር። አባ ኪያ ተብሎ ይታወቃል። ይህ ብርቱ ሰው መንግስት በሚቆጣጠረው የቴሌቪዥን ጣብያ ወጥቶ ከዩኒቨርሲቲው አስተዳዳሪወች ጋር ምግት ገጥሞ በዝረራ ጣላቸው። በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት አጋለጠ። የተማሪው ህብረትም በነፃነት ለመስራት መቸገሩን ለህዝቡ አሳወቀ። ህብረቱ የሚያሳትማትን ህሊና የተባለች መፅሄት እንኳን ለማሳተም መቸገራችንን አብራራ።

ፕሮፎሰር መስፍን ይመሩት የነበረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ(ኢ.ሰ.መ.ጉ.) የያኔውን የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሞያዎች ማህበር መስራች ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ሆነው የዩኒቨርሲቲውን ተማሪወች በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ ስብሰባ ጠሩን። ይህ የሆውነ ባልሳሳት እሁድ እለት ሚያዝያ 7 1993 ውነ። አዳራሹ በተማሩውም ተሸክሞት በመጣውም ሃሳብ ብዛት አብጦ ሊፈነዳ ቀርቦ ነበር። እናም ስለመብታችን እስከ በማይባል ደረጃ አጥግበው አጠመቁን። ሙቀት ተሰማን። ጀግንነት ሸተተን። ደረታችንን ነፍተን አንገታችንን አቅንተን የህዝባችንን የመብት ጥያቄ እያጉተመተምን ወደ ታሪክ ሰሪው ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ካምፓስ አመራን። የልደታ የአራት ኪሎና የአምስት ኪሎ ተማሪዎችም መመሪያ ለመቀበል በሚመስል መልኩ እኛኑ ተከትለውን መጡ። እንደ ቀልድ ጣል እንደሚደረገው ዝርዝሩን ስድስት ኪሎ ጠይቁ እንደሚባለው የሳይንስ ተማሪወች እኛው ጋር ተጣበቁ። ከነግርማ ሞገሳችን ጊቢውን አጥለቀለቅነው።

ሚሚ ስብሃቱ በእኛ ምክንያት ከቪኦኤ እንዴት እንደተባረረች የተማሪውም አመፅ የት ድረስ እንደሄደ እመለስበታለሁ። እንቀጥል። እናማ የተማሪው ህብረት ሰኞ እለት ሚያዝያ 8 1993 ይመስለኛል የተማሪውን መብትና ጥቅም ማስከበር አልቻልኩም ከዛሬ ጀምሮ ተማሪው የመብት ትግሉን እራሱ በተመቸው ይቀጥል በማለት መፍረሱን አወጀ። የተቀላቀለ ስሜት ቢኖረንም በአንድነታችን እንደምንፀና እርግጠኞች ነበርን።

እሮብ ሚያዝያ 10 1993 በፌደራል ወታደር ቅጥቅጥ ብለን የተደበደብንበት ቀን ነበር። የተማሪውን ትግል የቀየረ መራር ትዝታ ነበር። ስንደበደብ አርፍደን ወደ እኩለ ቀን አካባቢ ገነት ዘውዴ ታጅባ መጣች። ደም በደም የሆነውን መአት ተማሪ ስታይ እስሷን ይዛ “ወይኔ ልጆቼ እያለች አለቀሰች”። የዛኑ እለት ከሰአት በኋላ ምሳ ይቅርብን ተብሎ የተማሪው ደም ሳይደርቅ ከሚኒስትሯ ጋር ለመደራደት በልደት አዳራሽ ጢቅ ብለን ተሰበሰብን። ሶስት መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎች ይዘን ከያኔዋ የትምህርት ሚኒስትር ዮዲት ጉዲት ብለን ከምንጠራት ከገነት ዘውዴ ጋር ስብሰባው ቀጠለ። ጥያቄዎቻችንን አቀረብን።

ጥያቄወቻችን፦ አካዳሚክ ነፃነት ይኑረን፣ የተማሪው ህብረት ነፃ ሆኖ ይንቀሳቀስ ህሊና የተባለችውም መፅሄታችን በነፃነት እናሳትማት፣ የፖሊስ ጣብያው ከጊቢው ይነሳልን የሚሉ ነበሩ። ለዋቢነት በመብት ጥያቄ ምክንያት የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ለሁለት ጊዜ በዛ ፖሊስ ጣብያ ታስሬ ለድብደባና ለእንግልት ተዳርጌያለሁ። ታድያ ገነት ዘውዴ እስኪገርመን ድረስ በነፋስ ፍጥነት ምን ችግር አለው ይፈታሉ አለች። ወዲያውኑ አንድ ፀጉረ ልውጥ ሰው ወደ መድረኩ ተጠግቶ በጆሮዋ የሆነ ነገር ሹክ አላት። ጠብቁኝ መጣሁ ብላ ወደ ውጭ ወጣች። ተማሪው እርስ በርስ ይነጋገር ጀመር። ማን ሊጠራት እንደሚችልና ለምን እንደተጠራች ለብዙወቻችን መገመት አልከበደንም። ገነት ዘውዴ ተመልሳ ስትመጣ እውነተኛ ማንነቷንና ተላላኪነቷን አሳየች። ፊቷን ቅጭም አድርጋ አመፁን አቁመን ወደ ትምህርት ገበታችን እንድንመለስ መመሪያ አይሉት ማስፈራሪያ አስተላለፈች።

ተማሪው እጅግ ተቆጣ። ጥያቄም አቀረበላት። ምነው ልጆቼ ብለሽ አልቅሰሽ ጥያቄዎቻችንም እሽ ይፈታሉ ብለሽ ተስማምተሽ ስታበቂ እንዴት ትቀለብሻለሽ አልናት። ትንግርታዊ በሆነ ተውኔት እረ እኔ አላለቀስኩም ጥያቄወቹንም አልተቀበልኩም ብላ ሸመጠጠች። ተማሪው ተበሳጨ። የትምህርት ማቆም አድማውና የመብት ትግሉ ከሚያዝያ ተነስቶ ለሶስት ወራት እስከ ሰኔ ሲቀጥል የዩኒቨርሲቲው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ አመት ተማሪወች በሙሉ ለአንድ አመት ትምህርት ተቀጥተው ከፍተኛ ዋጋ ከፈሉ። ተመራቂወች ብቻ ጊቢውን ተመርቀው እንዲለቁ ተደረገ።

የተማሪውን ትግል እንመራለን ብለው ከታወቁት አንዱ የሆነው ፋሲል በደህንነት ተልጠፎ በኢቲቪ ቀርቦ ተሳስተናል እንዲል አስገደዱት። ሌላኛው መስፍን በማይችለው ቀጭን ሰውነቱ ላይ ድብደባ አድርሰውበት ከትግሉ ራቀን። ሊቀመንበር የነበረውን ተክሌን/አባ ኪያን ለመበቀል ቋምጠው በሄሊኮፕተር ጭምር ታግውዘ አሩሲ ድስረ ቤታውቸ ተበረበረ። በይፋ የሚታወቁት አመራሮች ሲሰደዱና ሲሰወሩ በብዙ ሽህ የሚቆጠር ተማሪ በታጠቅ ጦር ሰፈር ተግዞ ታሰረ። የተቀረነው ትግሉን ለመቀጠል ወስነን በህቡዕ አዲስ አመራር ፈጠርን። እኔም በዚሁ አመራር ውስጥ የሚዲያ ኮሚቴ አባል በመሆን ነፍሱን ይማውረና አማካሪያችን ከሆነው አዳነ ወንዴ ጋር ብዙ ሰርተናል። የጀርመን ድምፅ ጋዜጠኛ አሰገደች ይበርታን ሳሪስ ጎተራ አካባቢ ድስረ እየተሹለከለክን እናገኛትና ሪፖርት እንሰጣት ነበር። የቢቢሲ ጋዜጠኛዋን ስድስት ኪሎ ድስረ መጥታ እናስዘግባት ነበር። የአሶሼትድ ፕሬሱን ጋዜጠኛ ስሙን ከማልጠቅሰው ሆቴል ተደብቀን የተማሪውን ድምፅ እናስተጋባ ነበር። ዳእደ ደስታን፣ አዲሱ አበበን እንዲሁም ሚሚ ስብሃቱን ከቪኦኤ እንገናኝ ነበር።

ትግሉ እየጠነከረ ለወራት ሲዘልቅ ወያኔ ዘጋቢወቹ ከጎዳና ተማሪ ያልሆኑ ሰችወን ተጠቅውመ እያቀረቡ ረብሻውን አባባሱ ብሎ ስለወነጀለ የቪኦኤ ጋዜጠኞች የተማሪ መታወቂያ ካላሳያቹህ መዘገብ ይቸግረናል አሉ። ስለሆነም የዛኔው ዘጋቢያቸው ዳእደ ደስታ ቦሌ ኦሎምፒያ አካባቢ ቀጠረኝ። ስጋት ቢኖርም ሄድኩ ከቀጠሮው ሰአት ቀድሜ ብደርስም ውስጥ ሳልገባ አካባቢውን ማጥናት ያዝኩ። በመልክ የማያውቀኝ ዳእደ ሰትቱን እያየ ወደ ውስጥ የሚገባው ሰው ላይ ሲያማትር በመስታውት ከታጠረው ኬክ ቤት ውጭ ሆኘ በደንብ አስተዋልኩት። ከዛ በፊት በመልክ ባላውቀውም አለባበሱን ነግሮኝ ሰለነበር ለመለየት አልተቸገርኩም። ተስፋ ቆርጦ ወደ ውጭ ሲወጣ ማንም ተከትሎት አልወጣም። ትንሽ እንደተራመደ ከኋላው ተከተልኩትና “ዳእደ” ብየ ስጣራ ዞር አለ።

በግርምት አናገረኝ። ይዠ የመጣሁትን የተማሪ አቋም መግለጫ ሰጠሁት። መታወቂያየን አግጋገጠ። ይህን እኔ ከምዘግበው በምሽቱ ፕሮግራም አዲሱና ሚሚ በስልክ ቃለ መጠየቅ ያድርጉልህ ካልሆነ ማቅረብ አንችልም አለኝ። ተማሪው ደግሞ በነዚህ የአቋም መግለጫዎች ነበር መልእክት በሚዲያ የሚያገኘውና ምርጫ አልነበረኝም ሃላፊነቱን ልወጣ ብየ ቃለ ምልልስ ሰጠሁ ስሜ ሳይጠቀስ ተላለፈ።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚሚ ስብሃቱ ያኔ የተቀበሉኝን ስልኬን ተጠቅማ ደወለችልኝ። አዲስ አበባ ስለመጣሁ ስለተማሪው ትግል ሁኔታ ላናግርህ ብላ በቦሌ መድሃኒአለም መስመር የኡራኤል ድልድይ ዳር ጥቅጥቅ ባለ አፀድ ከተከበበው የብሄረ ፅጌ መናፈሻ መስራች ከሆኑት አባቷ ቤት ቀጠረችኝ። በተባለው ቀን ከተንጣለለው አልፋ ቪላ በሩ በዘበኛ ተከፍቶልኝ ስደርስ ሚሚ ጊቢው ውስጥ ከሆኑ ሰወች አፍ ገጥማ ስታወጋ ደስረኩ። እንዳሁኑ ባይብስባትም ያኔም ጎረድራዳ መልከ የለሽ ነበችረ። እዛው ጊቢ ውስጥ እንዳቆመችኝ የምጠላውልን ሲጋራ አቀጣጥላ ስትምግ ሴትም ታጨሳለች ብየ በግርምት አየትኋ። ጊዜ ሳትፈጅ ወደ ፈለገችው ነጥብ ገባች።

የተማሪው ትግል ይህን ያክል ጊዜ ከዘለቀ ለምን ሃገራዊ ጥያቄዎች አታነሱም አለችኝ። ግር አለኝና የምትህርት ፖሊሲ የመሳሰሉ ሃገራዊ እንምደታ ያላቸው ጥያቄዎች ማንሳታችንን ያልተመለሱት ጥያቄዎችም ሌላ እየወለዱ መሆኑን አስረዳኋት። እንደሱ አይደለም አለች ሲጃራ ያልያዘውን እጇን እያወራጨች። እኔ ምልህ ለምን መንግስት ስልጣን ይልቀቅ ብላቹህ አትጠይቁም አለችኝ። ይህን ስትል ድምጿን ከፍ አድርጋ ፈንጠር ብለው ያሉት “ሰወች” እንዲሰሙት አድርጋ ስለ ነበር ሰውነቴን ቀፈፈው። ቀስ ብየ “ሰወቹን” ሳያቸው ሙሉ ትኩረታቸው ወደ እኛ መሆኑን ተረዳሁ። ቅርቃር ውስጥ እየገባሁ መሆኔ ታወቀኝ። መዘየድና መሸሽ እንዳለብኝ ደመ ነፍሴ ነገረችኝ። እናም ለሚሚ የምመልሰው መልስ ለእሷ ሳይሆን በቅርብ እርቀት በአይነ ቁራኛ ለሚጠባበቁት “ሰወቹ” መሆኑን ተረዳሁ።

ድምፄን ዘለግ አድርጌ የተማሪው ጥያቄ ግልፅ ነው። መንግስት ይገልበጥ የሚል ድብቅ አጀንዳ የለውም አልኩ። መሄድ እንዳለብኝ ነግሬ በፍጥነት ጊቢውን ለቅቄ ወጣሁ። ክትትል እንዳይደረግብኝ በሚገርም የሩጫ ፍጥነት መንደር እያቆራረጥኩ ሸመጠጥኩት። በ5 ሽህ ሜትር ትምህርት ቤቴን ወክየ ስለምሮጥ እቃ አላልኩትም። ከመ ቅፅበት ሃይስኩል ከተማርኩበት ቦሌ ትምህርት ቤት ስርደስ ታክሲ ይዤ ከሚሚ ስብሃቱ ወጥመድ አመለጥኩ። ያሁኗ የወያኔ አሽከር ሚሚ ጭምብሏን ሳታወልቅ የዛን ሰሞን የአዲስ አበባ የመብት ጠያቂ ተማሪዎችን “እረብሸኞች” ብላ በመጣራቷ የተቆጣው ሃገር አፍቃሪው ዲያስፖራ በፈጠረው ጫና ከቪኦኤ እስከመጨረሻው ተሰናበተች። የጥላቻ መርዘኛ ምላሷንም እስከ አለቆቿና ቢጤወቿ የሃገሬ ህዝብ ሊላቀቀው ጫፉ ላይ ደርሷል። የቀራቸውን ሽራፊ ጊዜ ለማራዘም መርዛቸውን ጨርሰው እየተፉ ነውና ከወጥመዳቸው እንዳትገቡ በማስተዋልና በጥንቃቄ ተራመዱ።

Filed in: Amharic