>

እነዚህ እንግሊዛዊያን ቅርስ ብቻ ሳይሆን የዘረፉን ነፍስም ጭምር ነው!(ጥበቡ በለጠ)

 ልዑል ዓለምአየሁ አስከፊ ስደቱና ሞቱ

Inline image 1ልዑል ዓለማየሁ የተወለደ ሰሞን አባቱ አፄ ቴዎድሮስ እጅግ የተደሰቱበት ጊዜ ነበር። ቴዎድሮስ ደስ ያላቸው ቀን ባለሟሎቻቸውን ሰብሰብ አድርገው መጫወት፣ ማውጋት፣ ጥያቄ መጠየቅ ይወዱ ነበር ይባላል። ታዲያ እርሳቸው የሚጠይቁት ጥያቄ መልሱ አይገኝም። በመጨረሻም መልሱ ሲጠፋ የሚመልሱት ራሳቸው አፄ ቴዎድሮስ ናቸው። የአብራካቸውን ክፋይ ልዑል ዓለማየሁን በአይናቸው ያዩ ሰሞን ባለሟሎቸውን አንድ ጥያቄ ጠየቁ

“ለመሆኑ በዓለም ላይ ደስ የሚል ጠረን ያለው ምንድን ነው?” አሉ ቴዎድሮስ፡

ቶሎ ብሎ ለመመለስ ባለሟሎቻቸው ይጣደፉ ገቡ። አንዱ ከመቀመጫው ተነሳ። እጅ ነሳ። በሕይወት ዘመኑ ያያቸውን የጥሪኝ አይነቶች ዘረዘረና ከእነርሱ እንዴት ያለ መልካም መዓዛ ያለው ነገር እንደሚሰራ ተንትኖ እጅ ነስቶ ቁጭ አለ።

መልሱ ግን አልተመለሰም።

አንደኛው ደግሞ ተነሳ። የሚያውቃቸውን የዱር አበባዎችና ጠረናቸውን ዘርዝሮ እጅ ነስቶ ቁጭ አለ።

አሁንም መልሱ አልተመለሰም።

ሌላኛውም ተነሳ። የጥንታዊያኖቹን የፋርስና የመካከለኛውን ምስራቅ ሽቶዎች እየጠቀሰ፣ በዓለም ላይ አሉ የተባሉትን መልካም መዓዛዎች ተነተነላቸው።

አሁንም መልሱ የለም።

ብዙ ሙከራዎች ተደረጉ። አፄ ቴዎድሮስ የጠየቁትን ጥያቄ የሚመልስ ጠፋ።

“አባ ታጠቅ፤ በቃ አንተው መልሱን ንገረን” አሏቸው።
አፄ ቴዎድሮስም የሚከተለውን መለሱ፡-
“በዓለም ላይ እጅግ ደስ የሚል ጠረን ያለው አራስ ልጅ ነው” አሉ።
አፄ ቴዎድሮስ በዓለማየሁ መወለድ የተሰማቸውን ወሰን የሌለውን ደስታቸውን ከዚህ በላይ የሚገልፀው አባባል ያለም አይመስለኝም። እንዲህ የአራስነት ጠረኑ ከሚያማልላቸው ልጃቸው ጋር መለያየታቸው፣ ዓለማየሁም እንዲህ በጠረኑ ብቻ ፍቅራቸውን ከሚገልጹለት አባቱ ይለያል ብሎ የሚያስብ ሰው በወቅቱ ያለ አይመስለኝም።

ቴዎድሮስ ለሀገራቸው ኢትዮጵያ እና ለራሳቸውም ክብር ብለው ራሳቸውን መስዋዕት ሊያደርጉ በተዘጋጁ ጊዜ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተለምነው ነበር።

“እባክዎን በሚወዱት በልዑል ዓለማየሁ ይሁንብዎ፤ በራስዎ ላይ አይጨክኑ!” እያሉ ተማጠኗቸው።

አይበገሬው ቴዎድሮስ ቆም ብለው ለአፍታ አሰቡ። ወዲያውም እንዲህ አሉ፡-

“ለዓለማየሁ ምንም የማወርሰው ነገረ የለም። ሲያድግ ግን አባትህ አንዲት ኢትዮጵያ በአይኑ እንደዞረች ሞተ በሉት” አሉ ቴዎድሮስ።

የመቅደላው ጀግና ራሱን ሰዋ። መቅደላ ማማዋ ተናደ። በየቦታው ፍንዳታና እሳት ይጋዩ ጀመር።

Captain Hozier, laid mines under the gate and other defenses, as well as Tewadros’s artillery which had been cast with great difficulty by Emperor’s European artisans. The fort was the blown up. The Emperor’s palace and other buildings, including the church of Medhane Alem, were next set of fire. . . . spread quickly from habitation to habitation and set a heavy cloud of dense smoke which could be seen for many miles. . . . Three thousand houses & a million combustible things were burning.

ይህ ከላይ የተገለፀው፣ የእንግሊዝ ወታደሮች አፄ ቴዎድሮስ ከተሰው በኋላ መቅደላን እንዴት አድርገው እንዳወደሟት የሚተርክ ነው። መቅደላ ላይ የተሰራው የመሳሪያ ግምጃ ቤትና ማምረቻ በፈንጂ ጋይቷል። የቴዎድሮስ ቤተ-መንግስትና ታሪካዊው መድሃኒዓለም ቤተ-ክርስቲያንም ከተቃጠሉት ውስጥ ጥቂቶች ናቸው። ከሶስት ሺ በላይ የመቅደላ ቤቶች እንዲሁም አያሌ የመቅደላ ንብረቶች ሰደድ እሳት ተለቆባቸዋል። የመቅደላ ቃጠሎ ጭሱ ከብዙ ማይሎች ርቀት ላይ ሁሉ ይታይ እንደነበር በወቅቱ በአይናቸው ያዩ የታሪክ ፀሀፊዎች ገልፀውታል

ለመሆኑ ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ከዚህ ሁሉ ቃጠሎ ውስጥ እንዴት ወጣ?
መቅደላ ከቴዎድሮስ ሞት በኋላ የሲኦል ምሳሌ ትመስል ነበር። ልዑል ዓለማየሁ እናቱ እቴጌ ጥሩወርቅም ይህን መከራ ለማምለጥ ተደብቀው ነበር። በኋላ አንድ የእንግሊዝ ወታደር አያቸው። ለጦሩ መሪ ለጀነራል ናፒር ነገረው። የአፄ ቴዎድሮስ ሚስትና ልጅ እነዚህ ናቸው ብሎት አሳየው። ናፒርም ሌላ አደጋ እንዳይደርስባቸው ተገቢው ከለላ እንዲሰጣቸው አደረገ።

የስድስት ዓመት እድሜ ያለው ዓለማየሁ እና እናቱ እቴጌ ጥሩወርቅ ምርኮኛ ሆኑ። ከእነርሱ ጋርም አንድ የሶስት ዓመት ሕፃንም ምርኮኛ ሆኖ መጣ።

እንግሊዞች ለዓለማየሁ ቴዎድሮስ ሻለቃ እስፒዲን እና ኢትዮጵያዊውን ደብተራ ዘነብን ሞግዚት አደረጉ። ለዚያ ለሶስት ዓመት እንቦቀቅላ ደግሞ ኮሎኔል ቻርልስ ቻምበርሊን የተባለ እንግሊዛዊ ሞግዚት ሆነ። መቅደላ አምባ በቃጠሎ ከጋየች በኋላ፣ በውስጧ ያሉት አንጡረ ሀብቶች በሙሉ ተዘርፈው በበርካታ ዝሆኖችና በቅሎዎች ተጭነው፣ ከነልዑል ዓለማየሁ ጋር አድርገው እግሊዞች ጉዞ ወደ ብሪታኒያ ማድረግ ጀመሩ።

አርማጭሆ በረሃ ሲደርሱ እቴጌ ጥሩወርቅ በጠና ታመው። መጓዝ አልቻሉም። የባለቤታቸው ሞት፣ የወንድሞቻቸው ሞት። የጦርነቱ መከራ፣ ምርኮኝነቱ፣ ከትልቅ ወደ ትንሽ መውረዱ ሁሉ ክፉኛ የከበዳቸው እቴጌ ጥሩወርቅ ከሀገራቸው ሳይወጡ ግንቦት 15 ቀን 1860 ዓ.ም ሕይወታቸው አለፈች። በሕመም እያቃሰቱ ሳሉ ግን ስለ ልጃቸው ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ጀነራል ናፒርን አስጠርተው የሚከተለውን ነገሩት።

“እኔ እንግዲህ መሞቴ ነው፤ የዓለማየሁን ነገር አደራ፤ አባቱ ከመሞታቸው በፊት እንግሊዝ ሀገር ሔዶ እንዲማር ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው ደጃዝማች ዓለማየሁን ውሰዱና አስተምራችሁ ወደ ሐገሩ ላኩልን። ውለታችሁን ግን አምላክ በሰማይ ቤት ይክፈላችሁ” ብለው በተናዘዙ በሁለተኛው ቀን አረፉ።
አስክሬናቸውም ወደ ሸለቆት ገዳም ሔዶ እናታቸውና ዘመድ አዝማድ በተገኘበት ቀብራቸው ተፈፀመ። ታዲያ በዚህ ወቅት የእቴጌ ጥሩወርቅ እናት የልዑል ዓለማየሁ አያት አንድ ደብደቤ ለእንግሊዟ ንግስት ላኩ። ደብዳቤው የልዑል ዓለማየሁን ጉዳይ መሠረት ያደረገና አያቱ ምን ያህል እንደተጨነቁለት የሚያሳይ ነው። ተክለጻዲቅ መኩሪያ ይህን ደብዳቤ አፄ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ አንድነት በተሰኘው መፅሐፋቸው ውስጥ በሚከተለው መልኩ አቅርበውታል።

“በስመ አብ. . . ከወይዘሮ ላቂያዬ የእቴጌ ጥሩወርቅ እናት፣ የደጃዝማች ዓለማየሁ አያት የተላከ። ይድረስ ለእንግሊዝ ንግሥት። አንባቢው እጅ ይንሳልኝ፤ መድኃኒዓለም ጤና ይስጥልኝ፤ መንግሥትዎን ያስፋ፤ ጠላትዎን ያጥፋ። ሶስት ደጃዝማቾች፣ አራተኛ እቴጌ ጥሩወርቅ ሞተውብኝ የቀረኝ ደጃዝማች ዓለማየሁ ነው። አደራዎን ይጠብቁልኝ። እግዝአብሔር አባቱንና እናቱን ቢነሳው እርስዎን ሰጥቶታል። እኔም ካላየሁት ከሞቱት ቁጥር ነኝ። እርስዎን እናቴ ይላል እንጂ እኔን እናቴ አይለኝም፤ አላሰደግሁትምና። እርስዎ ያሳደጉት ስለ እግዚአብሔር ብለው”
በማለት የልዑል ዓለማየሁ አያት ለእንግሊዟ ንግሥት ቪክቶሪያ ደብዳቤ ላኩ።

የእንግሊዝ ሠራዊት ከእቴጌ ጥሩወርቅ ቀብር በኋላ ጉዞውን ቀጠለ።

ስለ ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ታሪክ በስፋት ከፃፉ ሰዎች መካከል አንዱ ለንደን ውስጥ የሚገኘው ፈቃድ ሀብቴ የተባለ ኢትዮጵያዊ ነው። ፈቃድ ሐብቴ በእንግሊዝ ነገስታት ማሕደር ውስጥ የሚገኙትን ሰነዶች መርምሮ ስለ ልዑል ዓለማየሁ በጻፈው ጥናት “ባይተዋሩ መስፍን” በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ ዝርዝር አቅርቧል።

የእንግሊዝ ጦር የመጀመሪያውን ጉዞ ወደ ፓርት ሱዳን አደረገ። ከዚያም ሰኔ 3 ቀን 1860 ዓ.ም (ልክ በዛሬዋ ዕለት) ፌሮዝ እየተባች በምትጠራ የእንግሊዝ የጦር መርከብ ወደ እንግሊዝ አገር ለመመለስ ከፖርት ሱዳን ለቀቁ።

ከአንድ ወር የባህር ጉዞ በኋላ ዓለማየሁ ቴዎድሮስ፣ ሻለቃ እስፒዲ እና ደብተራ ዘነብ ወደ ለንደን ሲደርሱ፣ አብሯቸው የነበረው የሶስት ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ህጻን ደግሞ ከሞግዚቱ ከኮሎኔል ቻርልስ ቻምበርሊን ጋር ሆነው ወደ ሕንድ ሐገር ጉዞ ጀመሩ። በወቅቱ ሕንድ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነበረች። ያ የሦስት ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ሕፃን በኋላ ሐኪም ወርቅነህ እሸቱ /ዶ/ር ማርቲን/ እየተባሉ የሚጠሩት ታላቁ የህክምና ሊቅ፣ ዲፕሎማትና የኢትዮጵያ ሪፎርሚስት የነበሩት ሰው ናቸው።

ልዑል ዓለማየሁ ለንደን ከገባ በኋላ ሻለቃ እስፒዲ ወደ ዊንድሶር ቤተ-መንግሥት ንግስቲቷ ዘንድ ይዞት ሔደ። ንግሥቲቷም ዓለማየሁን ትክ ብለው አዩት። አቀፉት። ከዚያም የተሰማቸውን ስሜት በሚከተለው መልኩ እንደገለፁት አጥኚው ፈቃድ ሐብቴ ፅፎታል።

“ጊዜው በጋ ነበር። ውድ ዓለማየሁ! የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ፣ ያጌጡ የአብሲኒያ ልብሶችን ለብሶ ከሻለቃ እስፒዲ ጋር ብቅ አለ። ከፍ ያለ ደስታ ተሰማኝ። ቀረብ ብዬ አቀፍኩት። ሁል ጊዜ ስለ አባቱ የምንሰማው ቁጣ ግን ከፊቱ አይነበብም። በጣም አይናፋር ሆኖ አገኘሁት። በእንግሊዝኛም ትንሽ አነጋገርኩት”
በማለት ንግሥት ቪክቶሪያ ፅፈዋል።

ሻለቃ እስፒዲ የአለማየሁ ሞግዚት በመሆኑ ባለው የወር ደሞዝ ላይ 400 ፓውንድ በየዓመቱ ተጨመረለት። ካፒቴን እስፒዲ ስለ ዓለማየሁ ሁኔታ በየጊዜው ለንግሥቲቱ የሚያቀርበው ሪፖርት በጣም ጥሩ ነው። እርሱም ደስተኛ መሆኑን ይገልጽላቸው ነበር። ካፒቴኑ ወደ ሕንድ ሀገር በስራ ተቀይሮ ሊሔድ መሆኑ ሲታወቅም ችግር ሆነ። ዓለማየሁ ቴዎድሮስም ሕንድ ሊሔድ ሆነ። በመጨረሻም ወደ ሕንድ ሐገር ተጓዙ። ይሕን ጉዟቸውን የእንግሊዝ ባለስልጣናት መቃወም ጀመሩ።

የእንግሊዝ ሊብራል መንግሥት የገንዘብ ሚኒስትር ሮበርት ላው ጉዞውን በግልጽ ከተቃወሙት ውስጥ አንዱ ነበሩ። ዓለማየሁ ከሕንድ ሐገር እንዲመለስ ሚኒስትሩ ሮበርት ላው ለእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ለግላድስተን ታህሳስ 18 ቀን 1870 ዓ.ም የፃፉትን ደብዳቤ ፈቃድ ሐብቴ አግኝቶት ይፋ አድርጎታል። ደብዳቤው ወደ አማርኛ ሲመለስ እንዲህ ይላል፡-

“ጠቅላይ ሚኒስትር ግላድስተን

10 ዳውኒንግ መንገድ ለንደን

በመጀመሪያ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጤንነት እየተመኘሁ ስለ ዓለማየሁ ጉዳይ ይህን መፃፍ ተገድጃለሁ።

በአሁኑ ሰዓት ግልጽ ሊሆንልዎት የሚገባው ነገር ቢኖር ዓለማየሁን በሞግዚትነት የተረከቡት ሻለቃ እስፒድና ሚስቱ ሳይሆኑ መላው የእንግሊዝ ሕዝብ ነው። ስለ ዓለማየሁ የወደፊት ሕይወት እነ ሻለቃ እስፒዲ ከሚሰጡን ሃሳብ ወጣ ብለን መንግሥታችን ዘላቂ መፍትሔ መሻት ያለበት ይመስለኛል።

በመጀመሪያ ዓለማየሁን ከሕንድ አገር ማስመጣት ይኖብናል፤ ለወደፊቱ በአብሲኒያ ፖለቲካ ከፍተኛ ሚና ይጫወታልና። የኛ መንግሥት ጥሩ ጓደኛና ጥቅም አስጠባቂ ይሆናል ብለን የምንጠብቀው ዙፋን ወራሽ ስለሆነ እንደ ሕንድ በመሰለ በሽታ፣ ድንቁርናና ኋላ ቀርነት የፊጥኝ ባሰረው ኅብረተሰብ መካከል ማቆየቱ ተገቢ አይመስለኝም። አሁንም ቢሆን እስካሁን ድረስ እዛው እንዲቆይ “መደረጉ በጣም አዝናለሁ። በአስቸኳይ ወደ እንግሊዝ ሐገር እንዲመጣ ካልተደረገ ግን መጀመሪያውኑ ዓለማየሁን ለማሳደግና ለማስተማር ከአገሩ ማስወጣቱ ቁም ነገር አልነበረውም ማለት ነው።

ሻለቃ እስፒዲና ሚስቲቱ አንዳንዴ የሚናገሩት ገና የሚያደርጉትን አያውቁም። እኔ እርስዎን ብሆን ባልና ሚስቱ የሚሉትን አልሰማም። የዓለማየሁ ከነሱ ጋር መቆየት ከራሳቸው የኢኮኖሚ ጥቅም ጋር የተገናኘ በመሆኑ መቼውኑ ቢሆን እውነትንና ለዓለማየሁ የሚበጀውን ነገር መናገር አይፈልጉም።

ለዓለማየሁ እንግሊዝ አገር እንደተመለሰ የሚገባበት ት/ቤት አዘጋጅቼለታለሁ። ብራይተን የሚገኘው የቻልተንም ኮሌጅ ርዕሰ መምህር የሆነው ጂክስ ብሌስ በራሱ የግል ቤት አስቀምጦ እንዲያስተምረው ተስማምተናል። ጂክስ ብሌስ ዘጠኝ ሴቶች ልጆች ስላሉት ዓለማየሁ መቼውንም ቢሆን ብቸኝነት አይሰማውም ብዬ አምናለሁ።

ዓለማየሁን ይህንን የምንኮራበትን የበለፀገ ባህላችንን የምናስተምርበት ከዚህ የበለጠ ዕድል የሚያጋጥመን አይመስለኝም። ከዚህ በተረፈ ግን የርስዎን ትዕዛዝ ለመፈፀም ዝግጁ ነኝ።

ታዛዥዎ
ሮበርት ላው፣ ቻንስለር
ግልባጭ
– ለንግሥት ቪክቶሪያ
ዊንድሶር ቤተመንግት
ዊንድሶር

በዚህ ደብዳቤ ሃሳብ ንግሥት ቪክቶሪያ መበሳጨታቸው ይነገራል። ድፍረት የተሞላበት ደብዳቤ መሆኑ አስቆጥቷቸዋል።

ሕንድ ሐገር የሚገኘው ካፒቴን እስፒዲ ደግሞ የተፈጠረውን ጉዳይ አያውቅም። እንደውም ለንግሥቲቱ ደብዳቤ ፃፈ። ዓለማየሁ ወደ እንግሊዝ ሀገር መጥቶ ትልቅ ት/ቤት መማር አለበት፣ ስለዚህ ለእኔም ቅያሬ ይሰጠኝ ብሎ ፃፈ።

የልዑል ዓለማየሁ ጉዳይ የእንግሊዝን ባለስልጣናት ያጨቃጭቅ ገባ። ይባስ ተብሎ ሻለቃ ስፒዲ ወደ ማሌዥያ ተቀየረ። በዚህ ወቅት እነ ሮበርት ላው ልዑል ዓለማየሁን ከካፒቴን ስፒዲ እጅ ለመንጠቅ ምቹ ጊዜ ተፈጠረላቸው። ሮበርት ላው ለባለስልጣናቱ የሚከተለውን ደብዳቤ መፃፉም ይነገራል፡-

“የዓለማየሁን የወደፊት ሕይወት በሚመለከት ቋሚ መመሪያ ሊኖር ይገባል። ይህ ምስኪን ልጅ አጋጣሚ ሆኖ መጀመሪያ በአንድ ወታደር እጅ በመውደቁ እሱ ዛሬ አፍሪካ፣ ነገ ሕንድ፣ ከነገ ወዲያ ቻይና ይሄድ ተብሎ በተወሰነ ቁጥር አብሮ መንገላታት የለበትም።
በአሁኑ ሰዓት ሻለቃ እስፒዲ ወደ ማሌቪያ ፒናንግ እንዲሔድ በመታዘዙ ቀደም ሲል ዓለማየሁን እንዲያስተምር ያደረግነውን ስምምነት እዚህ ላይ ለማስቆም ወስኛለሁ።

በተረፈ ግን ሻለቃ እስፒዲ ዓለማየሁን ወደ እንግሊዝ አገር አምጥቶ ለርዕሰ መምህሩ ለጃክሰን ብሌክ እንዲያስረክብ አስፈላጊውን ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ”

በማለት ፃፈ።

ከብዙ ጭቅጭቅና የደብዳቤ ልውውጦች በኋላ ልዑል ዓለማየሁ ወደ ጃክስ ብሌስ ዘንድ ተዘዋወረ።

ለአራት ዓመታትም ማለትም እስከ እ.ኤ.አ. 1875 ዓ.ም ከጃክስ ብሌስ ጋር በት/ት ቆየ። ልዑል ዓለማየሁ በተማሪዎች፣ በመምህራንና በባለስልጣናት ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ልዑል ነበር። የጦር አካዳሚ ትምህርቱንም በሚገባ ተከታትሎ ነበር።

ዓለማየሁ ፈረንሳይንና ሌሎች ከተሞችንም ከጎበኘ በኋላ መታመሙ ተሰማ። ንግሥት ቪክቶሪያ ይህን የዓለማየሁን ጤና ማጣት ሲሰሙ ደንግጠው ወዲያው ከሚማርበት ከሳንድረስት ጦር አካዳሚ ወጥቶ ከልዩ ፀሐፊያቸው ቤት ሆኖ ሕክምናውን እዲከታተል የዓለማየሁ ጉዳይ ለሚመለከታቸው ባለስልጣኖች ቴሌግራም ማድረጋቸው ተፅፏል። ሳምንት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ዓለማየሁን ከነበረበት ኮሌጅ አውጥተው ወደ ንግስቲቱ ልዩ ፀሐፊ ቤት ወሰዱት። ሕመሙ እየጠናበት ሄደ። ልዕልት ቪክቶሪያ ይህን ሕመሙን አስመልክተው የሚከተለውን ደብዳቤ ፃፉ፡-

“ውደ ዓለማየሁ በጣም ታሟል። በመጨረሻ የተደረገው ምርመራ ትንሽ የተስፋ ፍንጭ የሚሰጥ ይመስላል። ነገር ግን ሕይወቱ አደገኛ ጊዜ ላይ ነው ያለችው። በሳንባ በሽታ በጣም ይሰቃያል። ዓለማየሁ መርዝ አቅምሰውኛል ብሎ ስለሚጠራጠር ምግብና መድሃኒት የመውሰድ ፍላጊቱ ቀንሷል። በዚሁ ምክንያት በየዕለቱ ሰውነቱ እየደከመ በመሔድ ላይ ነው። ከቅርብ ቀናት ጀምሮ ግን ዶክተሩ ያዘዘለትን መድሃኒት መውሰድ ጀምሯል። መርዝ አብልተውኛል የሚለውን ሃሳቡን ትቷል። በተረፈ ግን ለልጅ ዓለማየሁ እንፀልይለት”
መረጃዎችን ከእንግሊዝ ቤተ-መንግሥት የሰበሰበው ፈቃድ ሐብቴ ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን ሁኔታ በሚከተለው መልኩ ይገልጸዋል።

“የዓለማየሁ ዶክተር የንግሥቲቱን የግል ሐኪምና ሌሎች የታወቁ የህክምና ሰዎችን አነጋገረ። ለንግሥት ቪክቶሪያ የዓለማየሁን ሕይወት ማዳን የማይችል መሆኑን ኅዳር 11 ቀን 1879 ዓ.ም ተነገራቸው። በጣም በጣም በማዘን አንድ የመጨረሻ ደብዳቤ ፃፉለት። ዓለማየሁ አልጋ ላይ ተኝቶ እያቃሰተ የንግሥት ቪክቶሪያን ደብዳቤ ለማንበብ ጥረት አደረገ። የነበረውን ሁኔታ የንግሥቱቱ ልዩ ፀሐፊ ሚስት እንዲህ ብለው ይገልጹለታል. . .

“ዓለማየሁ ደብዳቤው ከማን እንደተፃፈ ለማወቅ የደብዳቤውን አድራሻ መፈለግ ጀመረ። የንግሥት ቪክቶሪያን ስም እንዳየ ፈገግ አለ። ፖስታውን ቀደደና ወረቀቱን ወጣ አድርጎ ትንሽ መስመሮች እንዳነበበ በጣም ስለደከመው ደብዳቤውን ሊያነብ በሚችልበት ቦታ ላይ እንዳስቀምጥለት ጠየቀኝ። አንገቱን ወረቀቱ ወደተቀመጠበት ዘወር አድርጎ የጀመረውን ለመጨረስ ታገለ። አልቻለም። በመጨረሻ እጄን ይዞ ማቃሰት ጀመረ”
በመጨረሻ የሻለቃ እስፒዲንና የጃክስ ብሌስን ሚስት እጃቸውን እንደያዘ በ19 ዓመቱ ኅዳር 14 ቀን 1879 ዓ.ም ከጥዋቱ 3 ሰዓት ላይ ዐረፈ። በንግሥት ቪክቶሪያ ትዕዛዝ ዓለማየሁ ዊንድሶር በሚገኘው የጊዮርጊስ ቤተ- ክርስትያን እንዲቀበር ተደረገ። በሞተ በሶስተኛው ቀን ንጉሣዊ ቤተሰቦችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣኖች በተገኙበት የቀብሩ ስነ-ሥርዓት ተፈፀመ።

የታላቁ ንጉስ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁ ይህችን አለም በሞት ሲለይ ንግስት ቪክቶሪያ የሚከተለውን ፃፉ።

“የዓለማየሁን መሞት ዛሬ ጠዋት ሰማሁ። ጥልቅ ሀዘን ተሰማኝ። ባይተዋር እንደነበር ባይተዋር ሆኖ ሞተ። ከመጀመሪያ ጀምሮ ደስተኛ ልጅ አልነበረም። በወጣትነቱ ካሳደጉት ዘመዶቹና ወገኖቹ ርቆ መኖር ለወጣት ዓለማየሁ ከባድ ፈተና ነበር። ጥቁርና (አፍሪካዊ) ሆኖ መኖር በእኛ ኅብረተሰብ አስቸጋሪ መሆኑንም ተረድቶታል። አንድ ቀን ሊያየኝ የመጣ ቀን “ለምን አንዳንድ ሰዎች ትኩር ብለው ያዩኛል?” ብሎ የጠየቀኝ ትዝ ይለኛል። መልስ አልነበረኝም። ወጣቱ ዓለማየሁ ቆንጅዬና ተናፋቂ ወጣት እንደነበር ቆንጅዬና ተናፋቂ ወጣት ሆኖ ሞተ”።

Filed in: Amharic