>

የሟች እናት እያለቀሰች የገዳይ እናት እየሳቀች መኖር ይቻላል ብሎ ማሰብ ከንቱነት ነው! (ሃብታሙ አያሌው)

ዛሬ በደም የመነከር ተረኛዋ አምቦ ሆነች! ሃገር እየቀየሩ መግደል የነገስታት መብት መስሏል፨ ጥይታቸው የወገኖቻችንን ግንባር ሲነድል የኛ ልብ ይደማል ! በአራቱም ማዕዘን የሚወድቀው ወገናችን ለሃገሬ ያገባኛል ስላለ ብቻ ነው፤ የአባቱ ቤት ሲዘረፍ አብሮ ስላልዘረፈ ፨ ዛሬ በአሳዛኝ ሁኔታ መግባቢያችን ቋንቋው ጥይት ሆኗል…!!

በኢትዮጵያችን ሁኔታ አንድ ልጅ ወልዶ ለአቅመ አዳም ለማድረስ የሚያስከፍለውን ዋጋ ብረት አንጋች ሎሌም ሆነ “ገድለህ ና” ባይ ጌታ አያውቀውም – ብረት አንጋቹ ስላልወለደ ጌታው ልጅ ለማሳደግ ተጨንቆ ስለማያውቅ! በህዝብ ጫንቃ የተሳፈረ የደሃ ህዝብ ሃብታም ገዥ የልጅ ማሳደግን መስቀል የት ያውቀዋል? ! ቢያውቀውስ የድሃልጅ ሞተ ቀረ ምን ሊያጎድል ?! ማንንነገሬ ብሎ ሊጠይቀው ?!

በሁለት ቀን ከሃያ በላይ ወገኖቻችን ከመኖር ወደ አለመኖር ተቀይረዋል ፤ የእኩልነት ሃገር የማየት ጉጉታቸው መንገድ ቀርቷል! ሆኖም ህልማቸው አብሮሞቷል ማለት አይደለም ! የሟች እናት እያለቀሰች የገዳይ እናት እየሳቀች መኖር ይቻላል ብሎ ማሰብ ከንቱነት ነው ! ርካሽ በሆነ ጥይት ውዱን የሰው ልጅ ህይወት እየቀጠፉ በሰላም ውሎ ማደር የሰውነት መገለጫ አይደለም …. !!! በአንድ ቀን አስር ሰው የረፈረፈ ታጣቂ በፍቅር ይወደዳል ማለት ነፈዝነት እንጅ ሌላ አይሆንም ….! በሰው ልጅ ነፍስ እየቀለዱ የመኖሪያው ጀንበር ጠልቋል ….! አምቦ ፅናቱን ይስጥሽ …ሃዘንሽ ሃዘናችን ስብራትሽ ህመማችን ነው

Filed in: Amharic