>
9:47 am - Tuesday July 5, 2022

የሚበጀን የትኛው መንገድ ነው – የብቀላው ወይስ የይቅርታው መንገድ?

ምኒልክ አስፋው

” ………….. ኔልሰን ማንዴላ በ1962 ዓ.ም. በአገር ክህደት ክሥ ተወንጅለው ዕድሜ ይፍታ ተፈረደባቸው። ሥርዐቱም እነ ማንዴላን ወህኒ በመወርወርና በመከርቸም የነጻነት ዐመፁን ለጊዜውም ቢሆን የደቆሰና የቀለበሰ መሰለ። ሆኖም በሌሎች አገሮች እንደታየው ሁሉ በደቡብ አፍሪካም የተረጋገጠው ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ሰዎችን በማሰርና ከትግሉ ሜዳ በማግለል ማዳፈን አይቻልም። ማንዴላ በታሰሩ ማግሥት ትግሉ ይበልጥ ተፋፋመ።
ምንም እንኳ ማንዴላ አካላቸው ቢታሰርም መንፈሳቸውና ኅሊናቸው ግን አልታሰረም ነበር። ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ በሮቢን ደሴት የታሰሩት ማንዴላ በአንድ በኩል የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ እንዴት ነጻ እንደሚወጣ ሲያውጠነጥኑ በሌላ በኩል ደግሞ በነጻነቱ ማግሥት ሊፈጠር የሚችለውን ብጥብጥ (አንዳንድ ሠነዶች እንደሚጠቁሙት የእርስ በእርስ ፍጅት) እንዴት መግታት እንደሚቻል ያብሰለስሉ ነበር። ማንዴላ ወህኒ ከመወርወራቸውና ከብረት አጥር በስተጀርባ ከመከርቸማቸው በፊት አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል። “የነጮችን ጭቆና እፋለማለሁ፤ የጥቁሮችንም ጭቆና እፋለማለሁ፤ ጸንቼ የምቆመው ሰዎች ሁሉ በእኩልነት ለሚተዳደሩበት ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ነው፤ ለዚህ ፋይዳ ነው ካስፈለገም ሕይወቴን የምሰጠው”። ማንዴላ ታስረው ሳለም ከዚህ ጽኑ አቋም ከቶ ንቅንቅ አላሉም። ይልቁንም ይህ አቋም መሥራት አለመሥራቱን በዚያች ጠባብ ወህኒ ቤት ውስጥ ይፈትኑ ነበር። የሮቢን ደሴት ለማንዴላ ቤተ ሙከራ ነበር ማለት ይቻላል። ለደቡብ አፍሪካ የሚበጃት የትኛው መንገድ ነው – የብቀላው ወይስ የይቅርታው መንገድ? ጥላቻን በጥላቻ፣ ዘረኛነትንም በዘረኛነት መመለስ ወይስ ይቅር መባባል? እንግዲህ ማንዴላ ወደፊት ለሚጠብቃቸው ብርቱ ጥሪ መዘጋጀት የጀመሩት በሮቢን ደሴት ነው ማለት ይቻላል።
ከብዙ ውትወታና ጩኸት በኋላ ማንዴላ ከእስር ሲፈቱ የ71 ዓመት አዛውንት ነበሩ። የሕይወታቸውን አንድ አራተኛ ወህኒ ቤት አሳልፈው ሲወጡ በቀልን ሳይሆን እርቅን የትግላቸው መርሕ/ፋይዳ አድርገው ወጡ። መላው ዓለምም “እኚህን ሰው ለዚህ ያበቃቸው ምስጢር ምንድን ነው?” በማለት መጠየቅና መደነቅ ነበረበት። ከቶ ማንዴላን ምን ለወጣቸው? ብዙዎች የጠበቁትን ብቀላ ሳይሆን የዚያን ተቃራኒ መንገድ እንዲመርጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው? ሰይፍን ሳይሆን ይቅርታን እንዴት ሊያነሡ ቻሉ? እና እንግዲህ በብዙ የለውጥ ሐዋርያት ሕይወት እንደ ተመሰከረው ምርጥ ሰብእና የሚፈጠረው ከአሳዛኝ መከራ (tragedy) ሳይሆን አይቀርም በማለት መደምደም ሊኖርብን ነው። ደግሞም ከአሳዛኝ መከራ ተምሮ ለሌላ የመከራ ዑደት ምክንያት አለመሆን ትልቅ አስተዋይነት ነው። በቀለኛነትም ሆነ ደም መላሽነትና ብድር ከፋይነት ሌላ የብቀላ ዑደት ከመፍጠር በቀር ምንም አይፈይዱም። እንዲያውም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ክፉ ነቀርሳ ይሆናሉ።
ማንዴላ በቀልና ደም መላሽነት ደቡብ አፍሪካን ድምጥማጧን እንደሚያጠፋት በትክክል ተገንዝበዋል። ከበቀሉ ጎዳና ይልቅ የእርቁና የይቅርታው ጎዳና ይሻላል በማለት ባይሞግቱ ኖሮ አሁን የምናውቃት ደቡብ አፍሪካ ባልተገኘችም ነበር። እርግጥ ነው አፓርታይድ በደቡብ አፍሪካውያን በተለይም በነጮችና በጥቁሮች መካከል ብርቱ ጥላቻ እንዲሰፍን አድርጓል። የደቡብ አፍሪካን ጥቁሮች ከልክ በላይ አዋርዷል፤ ሰብእናቸውን አራክሷል። በአጭሩ በዘረኛነት ላይ የተመሠረተ ሥርዐተ ማኅበር እንዲንሰራፋ አድርጓል። ሰዎች የቆዳቸው ቀለም ጥቁር በመሆኑ ብቻ ተንቀዋል፤ እንደ ምናምንቴ ተቈጥረዋል። ጥቁሮች በገዛ አገራቸው ቁም ስቅላቸውን አይተዋል። ጭቆናው አንሶ አፈናውና ጭፍጨፋው መድረሻ አሳጥቷቸዋል። እናም ለደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ነጭ ማለት “ነፍሰ በላ ጨካኝ አውሬ ነው። ነጮች የሰይጣን ቁራጮች ናቸው፤ ነጮች ጣረ ሞት ናቸው። እናም ጥቁሮችን ቁም ስቅል እንዳሳዩ እነርሱም ቁም ስቅላቸውን ማየት አለባቸው፤ የክፉ ብድራታቸውን መቀበል አለባቸው፤ ለእነርሱ የሚገባውም ሞት ብቻ ነው” የሚል በቀለኛነት በመላው ደቡብ አፍሪካ አስተጋባ።
ኔልሰን ማንዴላ ሰው አንደ መሆናቸው መጠን ይህ ሌሎችን የወረሰው የበቀለኛነት መንፈስ እርሳቸውንም መውረስ ነበረበት፤ ነገር ግን በማንዴላ ሕይወት የተመለከትነው ይህን አይደለም። ማንዴላ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ እስር ቤት መከራ ቢቀበሉም መከራው ግን አንድ ወሳኝ ነገር አስተምሯቸዋል፤ ይኸውም በቀል ለማንም የማይጠቅም መሆኑን። ይልቁንም በቀል አገር ያጠፋል፤ ሕዝብ ይደመስሳል፤ ትውልድ ይጨርሳል። የሚሻለው ብቀላ ሳይሆን ይቅር መባባል ነው። ከዚህ ውጭ ተስፋም ሆነ መልካም መጻኢ ዕድል የለም። በእውነተኛው የማንዴላ አስተሳሰብ የተከረከመውና አዲስ መልክ የተላበሰው እስር ቤት ነው የሚሉ ወገኖች ትክክል ብለዋል። ማንዴላ በዚያች የሮቢን ደሴት እስር ቤት ውስጥ ጧትና ማታ የሚያሰላስሉት አገራቸው ደቡብ አፍሪካ ከእርስ በእርስ ፍጅት ልትድን የምትችለው የትኛውን መንገድ ብትከተል ነው? የሚለውን ነበር። ጥቁሩ በነጩ እንደ ተበላ ነጩም በጥቁሩ መበላት አለበት? ጥቁሩ በነጩ እንደ ተተለተለ ነጩም በጥቁሩ መተልተል አለበት? ጥቁሩ በነጩ እንደ ተጨፈጨፈ ነጩም በጥቁሩ መጨፍጨፍ አለበት? ጥቁሩ በነጩ እንደ ተወገደ ነጩም በጥቁሩ መወገድ አለበት? ከቶ ደቡብ አፍሪካን የሚታደጋት የትኛው አማራጭ ነው? በቀለኛነት ወይስ ይቅር ባይነት?
ማንዴላ ተራው የጥቁሩ ከሆነ አገር ሊደመሰስ ትውልድም ሊጠፋ እንደሚችል በሚገባ ተረድተዋል። ይህም ውሎ አድሮ ሌላ አካይስታዊ ዑደት እንደሚፈጥር አስተውለዋል። እንደ ማንዴላ ሁሉ ተራው የጥቁሩ መሆን የለበትም በማለት በብርቱ ከተሟገቱ ወገኖች መካከል አንዱ ሊቀ ጳጳስ ዴስሞን ቱቱ ናቸው። እንዲያውም ማንዴላ ከእስር ተፈትተው የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ፕሬዘዳንት ሲሆኑ “የእርቅና የሰላም ተቋሙን” በሊቀ መንበርነት እንዲመሩ የተደረጉት ቱቱ ነበሩ።እንደ ማንዴላ ሁሉ ቱቱም “ያለ ይቅርታ ተስፋ የለንም” የሚል ብርቱ አቋም ነበራቸው። እርግጥ እንደ ሰው ሲታሰብ ተራው የጥቁሩ መሆን ነበረበት። ይሁንና በቀል እማንዴላ ቀመርና ሒሳብ ውስጥ ስፍራ አልነበረውም። የደቡብ አፍሪካ መጻኢ ዕድል ፈንታ የተመሠረተው በዕርቀ ሰላሙ መንገድ ላይ ብቻ ነበር። ምንም እንኳ ብዙዎች በማንዴላና በቱቱ አቋም ደስ ባይሰኙም (የብዙዎች አቋም “ደም መመለስ፣ ብድርም መከፈል አለበት” የሚል ስለ ነበር) ማንዴላና ቱቱ ግን ብቀላ ምርጡ መንገድ እንዳልሆነ አስተውለዋል። ፍጹም ነጻነት በብቀላ አይገኝም ነው የማንዴላና የቱቱ ሙግት። እንግዲህ ማንዴላ ለበቀል ዕድል ፈንታ ባለመስጠት ሕዝቦች ሁሉ ሊከተሉት የሚገባ ምርጥ ጎዳና ለዘመንተኛው ትውልድ አመላከቱ ማለት ይቻላል። እንደ ማንዴላ እምነት ጥላቻ ጥላቻን ይወልዳል፤ ጥፋተኛን መቅጣትና ፍዳውን መስጠት ይቻል ይሆናል፤ ይህ ግን ምርጡ መንገድ አይደለም። ምርጡ መንገድ ይቅርታ ነው። እውነተኛ ሰላም ከበቀል ጋር አንዳች ዝምድና የለውም። እንዲያውም ሰላም የእርቅ እንጂ የበቀል ልጅ አይደለችም።
………….. ተረኛው በዳይ ወይም ተረኛው ተበዳይ ማን እንደ ሆነ ማንም የሚያውቅ የለም። ማን ያውቃል በሌሎች ስፍራዎች እንደታየው ሥልጣን የጨበጡ ተበዳዮች እነርሱ ራሳቸው በዳይ ሆነው ተገኝተዋል። ʻኧረ የሰማይና የምድር ጌታ እንዲህ ከሰውነት ተራ ሲያወጡን ዝም አትበል!ʼ በማለት ወደ ላይ የጮኹና የቃተቱ እነርሱ ራሳቸው ሌሎችን አበሳና ፍዳ አሳይተዋል። ታዲያ የሚሻለው ምንድን ነው? ግፍንና በደልን ቈጥሮ መበቀል? ብድሩን መክፈል? ደም መመለስ? ፍዳውን መስጠት? ወይስ ለማንዴላ የበራውን የዕርቀ ሰላም ብርሃን መከተል?
…………“ምርጡ መንገድ ሌላ ምንም ሳይሆን የሰላሙና የእርቁ መንገድ ነው” በማለት ተግቶ የሚሰብክልን? ማን ነው “በቀል በቀልን ይወልዳል፤ የሚሻለው መወጋገድ ሳይሆን መቀባበል ነው” በማለት የሚያውጅልን?እኔ የምመኘው የማንዴላን እሴትና ፋይዳ፣ እምነትና ጽናት ወኔና ቅን አሳቢነት የሚያስተጋቡ ሰዎች እንዲነሡ ነው። በቀልን ሳይሆን እርቅን፣ ሰይፍን ሳይሆን ምሕረትን የሚያነሡ ሰዎች እንዲወለዱ ነው። የሰው ልጆች ታሪክ የበቀልና የሰይፍ ታሪክ ነው። ይህ ደግሞ ከቶ አልጠቀመንም፤ ይልቁንም ይበልጥ አበጣበጠን፤ ይበልጥ አከፋፋን፤ ይበልጥ አራራቀን። ጭቆና፣ ብዝበዛና ብቀላ ምርጥ እሴቶች አይደሉም። ምርጡ እሴት ይቅርታና ምሕረት ነው። እንግዲህ ትልቅነት የሚለካው በላቀው እሴት ከሆነ ትልቆቹ ይቅር የሚሉና ምሕረት የሚያደርጉ ናቸው። እኔን አሁን በጣም የሚያስጨንቀኝ እንደ ማንዴላ ዐይነት ሰዎች በሌሉበት ዓለም “የሰዎች ሰውነትና እኩልነት” የሚረጋገጠው እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ ነው። ለራሳቸው ሳይሆን ለሌሎች የሚኖሩ ሰዎች እየጠፉ በመጡበት ዓለም እንዴት መኖር ይቻላል? ሰዎች በሰላምና በፍቅር ተከባብረው እንዲኖሩ የሚያስላቸውን መሠረት ድምጥማጡን እያጠፋን እንዴት ነው ወደፊት መራመድ የሚቻለው? ልጆቻችንና ቀጣዩ ትውልድስ ተስፋ የሚኖራቸው እንዴት ነው?…………….”

ሕንጸት መጽሔት- ምኒልክ አስፋው

 

Filed in: Amharic