>

ሽንፈት የወለደው የፖለቲካ አድርባይነትና የኢትዮጵያ ፈተና!!! (ኢ/ር ይልቃል ጌትነት)

በኢትዮጵያ ፖለቲካ በቆየሁባቸው ጊዚያት እኔ እንደተረዳሁት የችግሮች መወሳሰብና የውጤት ርሃብ በመኖሩ ከየት ተነስተን የት እንደምንደርስ፣ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ችግሮቻችን በቅደም ተከተል ምን እንደሆኑ፣ የምንታገላቸውና የምንታገልላቸው ሃሳቦች ምን እንደሆኑ ግልፅ አቋም የወሰድንባቸውና ለይተን ያስቀመጥናቸው አይመስለኝም፡፡ የእነዚህ ነገሮች ጠርቶ አለመውጣትና መደበላለቅ መንስኤው ተደጋጋሚ ሽንፈትና የፖለቲካ አድርባይነት ይመስለኛል፡፡ በአቋም ከመበየን ይልቅ ለውይይትና ለመማማር እንዲመች የአድርባይነት አመለካከቶች ታይቶባቸዋል ብየ በማምንባቸው የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄ አዘል አስተያየቶችን አቀርባለሁ፡፡

1ኛ. በቅርብ ጊዜ ካስተዋልኩት ብጀምር በነቀምት ከተማ ሶስት የትግራይ ተወላጆች በድንጋይ ተቀጥቅጠው ተገደሉ የሚል ወሬ በማህበራዊ ሚዲያ መናፈሱን ተከትሎ በአብዛኛው ትግሬ ያልሆኑ ሰዎች ጉዳዩን በተመለከተ ያልነው ደረሰ፣ይህንን ፀረ ትግሬ አመለካከት በሌላው ዘንድ እንዲፈጠር ያደረገው የሕወሐት የዘር ፖለቲካ ነው፣ይህ በጊዜ ካልታረመ በትግሬ ላይ አስከፊ ችግር ይመጣል ወዘተ የሚሉ አስተያየቶችን ተመልክቻለሁ፡፡ የዚህ አስተሳሰብ መነሻው
1.ትግሬዎች በራሳቸው ላይ የሚመጣውን ችግር መረዳትና መገንዘብ አይችሉም ነው?
2.በትግሬዎች ሊመጣ ባለው ችግር ላይ ከትግሬዎች የበለጠ ትግሬ ያልሆኑ ሰዎች ሃላፊነት አለባቸው ማለት ነው?
3.ስለ ትግሬዎች ቀና የሚመስል አስተያየት በመስጠት የትግራይ ባለስልጣናት እንዲለወጡ ለማባበልና ለመማፀን ነው?
4.እንዲህ ዓይነት አስተያየቶችን በመስጠት ትግሬዎችን በማስፈራራት ጫና ለመፍጠር ነው?

2ኛ. ኦነግ 40 ዓመታት በአካሄደው የፖለቲካ አመለካከት ምክንያት በአማራ ህዝብ ላይ በተፈጠረው ጥላቻ በኦሮሚያ ክልል ለሚኖሩ ለብዙ አማሮች ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ ምክንያት ሆኗል የሚለውን አቋም ብዙ ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች በዚህ ሰዓት መነሳቱ አያስደስታቸውም፡፡ የዚህ አስተሳሰብ መነሻው
1.በአሁኑ ሰዓት ኦነግን መተቸት በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ አማሮችን የበለጠ ያስጠቃል ነው?
2.ኦነግ ድሮ የነበረው አመለካከት ታሪክ ሆኖና አስተሳሰቡ ተቀይሮ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን የሚስማማ ሆኗል ነው?
3.ኦነግን በዘዴ አታለን ሕወሐት/ኢሕአዴግ እንዲወድቅ ካደረግን በኋል ኦነግ የእኛን አመለካከት እንዲቀበል የምናደርግበት የአደረጃጀትና የፖለቲካ ቁመና ላይ ነን ነው?
4.ኦነግ በአዲሱ የቁቤ ትውልድ ላይ የፈጠረው አመለካከት ለኢትዮጵያ ከሕወሐት የበለጠ አደገኛ አይደለም ነው?
5.እውነቱን ከተናገርን ለጊዜው ያለን ታክቲካል ግኝኙነት ይበለሻል በሚል ነው?

3ኛ. በሕወሐት/ኢሕአዴግ ግንባር ውስጥ የተፈጠረውን ሽኩቻ ተከትሎ ብዙ ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች የኦህዴድን እንቅስቃሴ ሲደግፉ ይታያል፡፡ የዚህ አቋም መሰረቱ
1.ከሕወሐት/ኢሕአዴግ ይልቅ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ለኢትዮጵያ ይሻላል ነው?
2.ኦሕዴድ የያዘው የፖለቲካ አስተሳሰብ ሕወሐትን በማሸነፍ ለኢትዮጵያ የሚበጅ አዲስ አስተሳሰብ ይፈጥራል ነው?
3.ኦሕዴድ በሚያደርገው የፖለቲካ ጫና ሕወሐትን ካሸነፍን በኋላ የኦሕዴድን ሀሳብ የሚያስቀይር የፖለቲካ አደረጃጀትና ተክለ ሰውነት አለን ነው?
4.ኦሕዴድ አሁን ባለው ተክለ ቁመና ድሮ ከነበረው አስተሳሰብ በተግባር ተለውጧል ነው?
5.ምንም ይሁን ምን ሕወሐትን እስከገፋ ድረስ መደገፍ አለብን ከዛ በኋለ የመጣው ይምጣ ነው?

4ኛ. ብዙ ሰዎች የሌሎችን ብሔረሰቦች በማንነት መደራጀት ደግፈውና እውቅና ሰጥተው አብረው እየሰሩ አማራ በተግባር ብዙ ጥቃት እየደረሰበት እያዩ የአማራን በአማራነት መደራጀትን ይቃወማሉ፡፡ የዚህ አመለካከት መንስኤው
1.ኦነግና መሰሎቹ ተደራጅተው ሌላውን እስከማጥቃት ሲሄዱ አማራ ቢገደልም መደራጀት የለበትም ነው?
2.አማራ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የበለጠ የዜግነት ሃላፊነት አለበት ነው?
3.አማራ በማንነቱ ሲደራጅ እኛ የምንፈልገው የፖለቲካ ግብ እንዳይመታ እንቅፋት ይሆንብናል ነው?
4.የአማራን ሲቃይ ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ስብስብ ካለ የእኛ ድምፅ አይሰማም ነው?

5ኛ. የብሔራዊ እርቅና የሀገር አንድነትን በተመለከተ ተደጋግሞ የሚነሳው የዜግነት ፖለቲካ በሚያራምዱ ሃይሎች ነው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ መነሻው
1.ሕወሐትን ጨምሮ በብሔረሰብ የተደራጁ ደርጅቶች የብሔራዊ እርቅን አስፈላጊነት አይረዱትም ነው?
2.በኢትዮጵያ አንድነትና ብሔራዊ እርቅን በተመለከተ የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች የተለየ ሀላፊነት አለብን ነው?
3.አሁን ባለው የፖለቲካ አሰላለፍ የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች እራሳቸውን እንደጥፋተኛ ቆጥረው የብሔረሰብ ድርጅቶችን ለመለመን ነው?
በእኔ አስተያዬት ከላይ በጥያቄ መልክ ላነሳኋቸው ሃሳቦች ግልፅና ቀጥተኛ መልስ መስጠት ያልቻልነውና ግልፅ የፖለቲካ አቋም ለመውሰድ የተቸገርነው ከባህላችን በወረስነው መሸፋፈንና ማድበስበስ ምክንያት የፍርሃትንና የትግስትን እንዲሁም አድርባይነትንና ሆደ ሰፊነትን መለየት የማንችልበት ከባድ የፖለቲካ በዥታ ውስጥ በመሆናችን ይመስለኛል፡፡ ፖለቲካ በባህሪው ቀጥተኛ ለሆኑ የፖለቲካ ጥያቄዎች ግልፅ የሆኑ አማራጮች ቀርበው በድርድርና በውይይት የተሻለውንና የሚያቀራርበውን አማራጭ መውሰድ ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ባለንበት ሁኔታ በማድበስበስና በመሸፋፈን እየሄድንበት ያለውን መንገድ ቆም ብለን አስበን እውነቱን ለመጋፈጥ እስካልወሰንን ድረስ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት የፖለቲካ ቀውስ የመፍትሔ አካል መሆን የምንችል አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም በአሁኑ ሰዓት ቀላል የሆኑና በግልፅ ብንነጋገርባቸው መፍትሔ ልናበጅላቸው የምንችላቸው የፖለቲካ ጉዳዮች ባለመነጋገራችንና በያዝነው የፖለቲካ አድርባይነት ምክንያት ችግሩን የበለጠ እንዳናበብሰውና የጥፋቱን መንገድ እንዳናፋጥነው እሰጋለሁ፡፡

Filed in: Amharic