>
4:11 am - Tuesday January 31, 2023

በአማራ ትኩስ እሬሳ በባህር ዳር የለማ መገርሳ ሙገሳ!!! (ኢ/ር ይልቃል ጌትነት)

የአቶ ለማ ሙገሳ ያልኩት እንደ ታዋቂ ሙዚቀኛና ትያትረኛ “በመሳጭ የአንድነት ንግግራቸው የሚታወቁት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ” በሚል በባህር ዳር ወጣቶች ፌደሬሽን የማህበራዊ ድህረ ገፅ ማስታወቂያ ተሰርቶላቸው በማየቴ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሞ ነፃነት ታጋዮች ዘንድ የተቀየሰ አንድ አጠቃላይ ስትራቴጂ ያለ ይመስላል፡፡ ይኸውም “ለኦሮሞ ህዝብ የነፃነት ትግል በምናደርገው እንቅስቃሴ የባህሪ አባታችንና የግንባራችን አባል ሕወሐት የምንመኘውን የኦሮሞ ነፃነት በገባው ቃል ኪዳን መሰረት ቃሉን አላከበረም፡፡ ስለሆነም የኦሮሞን ህዝብ ሙሉ ብሔራዊ ነፃነት ለማጎናፀፍ ከሕወሐት ጋር ለምናደርገው የውስጥ ትግል እንዲረዳን በስልት ደረጃ አማራን ከጎን ማሰለፍ የሚል ነው፡፡” ይህንን ስትራቴጂ ወደ ተግባር ለመለወጥ በአማራ ስነ ልቦና በቀላሉ ተቀባይነት ያላቸውን ሃሳቦች ማለትም አንድነት፣የጥንታዊ ኢትዮጵያን ታላቅነት፣የሕወሐትን ጡንቻ ፈርተው በአደባባይ ባይናገሩትም ሕወሐት ከፋፋይ ስለሆነ ይህንን ተግባሩን ለማክሸፍ የኦሮሞ እና የአማራን ህዝብ አንድነት ማጠናከር ወዘተ የሚሉ የአየር በአየር ፕሮፓጋንዳ ይዞ ወደ አደባባይ መውጣት ነው፡፡
በዚህ ስትራቴጅው ኦነግ/ኦህዴድ ለሚያደርገው የኦሮሞ ነፃነት እንቅስቃሴ ለጊዜውም ቢሆን በማታለል የተሳካለት ይመስላል፡፡ ነገር ግን በተግባር ስንመለከተው የኦሮሞ ነፃነት እንቅስቃሴ በኦነግ ሲመሰረት በፀረ አማራና በአማራ አመለካከት ተፈጥራለች በሚላት ኢትዮጵያ ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይህ አመለካከት በተግባር ምንም ሳይለወጥና መሻሻል ሳያሳይ የአማራን ህይወት እየቀጠፈ እንደሚገኝ በኢሊባቦር የተፈፀመው አረመኒያዊ ደርጊት የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች ይህንን የአማራ ጭፍጨፋ ሃላፊነት ለሕወሐት በመስጠት እራሳቸውን ያታልላሉ፡፡ በእኔ እምነት በፖለቲካ አመለካከታቸው እና በአማራ ላይ ያላቸው አስተሳሰብ በሕወሐት፣ኦነግና ኦህዴድ መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ ልዩነት የሚመስል ነገር ካለም በስልትና ኦህዴድ ከኦነግ በበለጠ ለሕወሐት ያደረና ያጎነበሰ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ኦህዴድና ኦነግም በኦሮሚያ ክልል ያለውን አማራና ሌላውን ኦሮሞ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ የሚያዩት በኦሮሞ ነፃ መሬት ላይ የሚኖር ወንድም ህዝብ፣ኦሮሞ ሌላውን ለማቀፍና አብሮ ለመኖር የተዘጋጀ ኦሮሚያም ሰፊና አሁን ካለው ህዝብ በላይ ማስተናገድ ስለሚችል ከእኛ ጋር መኖር ትችላላችሁ የሚል እንጅ በኦሮሚያ ክልል የሚኖር ኦሮሞ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ከኦሮሞ ጋር የማይሸራረፍ እኩል የዜግነት መብት እንዳለው አስረግጠው አይናገሩም፡፡
በተጨማሪም በሕወሐት/ኢሕአዴግ ውስጥ ድርጅቱ በማርጀቱ ያጋጠመውን የውስጥ ሽኩቻ ለማባባስ በሚመስል መልኩ እንደ ስልት ኦሕዴድን የደገፉ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ኦሕዴድ ለውስጥ ሽኩቻው የሚጠቅመውን ስትራቴጅ ነድፎ እነሱን እያታለላቸው መሆኑን እረስተውት ሳያውቁት ኦሕዴድን እንዳበረታቱት አድርገው እራሳቸውን ያታልላሉ፡፡
ኦሕዴድ በአደባባይ የሚናገረውና እውነተኛ አጀንዳው ባይቃረን ኖሮ በአሁኑ ሰዓት ማድረግ ያለበት በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ ያለውን ፀረ አማራ አመለካከት በይፋ ማውገዝ፣ ፍቅርና አንድነትን ማስተማር፣የጥላቻ ሀውልቶችን በተግባር ማፍረስ፣ኦሮሞ ባልሆኑ ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸውን የመብት ጥሰት በአደባባይ እንዲቃወሙ መፍቀድ፣በአለፉት 26 ዓመታት በክልሉ ውስጥ በሚኖሩ አማሮች የደረሰውን ጭፍጨፋ ማመንና ለድርጊቱ በኦሕዴድ ስም ሃላፊነት መውሰድ፣በቅርቡ በኢሉባቦር ለተጨፈጨፉና ንብረታቸው ለመወደመባቸው አማሮች ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ለጋዜጠኞችና ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ እውነቱን እንዲያውቀው መንገዶችን መክፈትና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበረበት፡፡ ነገር ግን አሁን ይደረጋል የተባለው የአቶ ለማ መገርሳ የባህር ዳር ሽር ሽር እውነተኛ ማንነታቸውን ያጋለጠውን የኢሉባቦር የአማራ ጭፍጨፋ ለማስረሳትና ለዘላቂው “የኦሮሞ ቅድሚያ” እንቅስቃሴያቸው እንቅፋት እንዳይፈጠርባቸው ስለ አነድነትና የኢትዮጵያ ትልቅነት በማውራት የአማራን ህዝብ የእንቅልፍ ክኒን ለማስዋጥ የሚረዳ ከስትራቴጃቸው አንዱ አካል ነው፡፡
አሁን የሚደረገው የሕወሐትና የኦነግ የባህሪ ልጅ የሆነውን ኦሕዴድን መደገፍ ከትግራይ የበላይነት ወደ ኦሮሞ የበላይነት የሚደረግ ሽግግር አድርጌ አያዋለሁ፡፡ ምክንያቱም በሕወሐትና በኦሕዴድ መካከል የሚደረገው ሽኩቻ የደርሻዬን አላገኘሁም የሚል እንጂ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ምንም ልዩነት የለም፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አቶ ለማ በሚመሩት ድርጅትና አመለካከቱ ምክንያት አማራ ተገሏል፣ተሰዷል እንዲሁም ንብረቱ ወድሟል፡፡ ካዛ ውጭ በአድርባዩ ብአዴንም ሆነ በአማራ ህዝብ እሳቸው በሚመሩት የኦሮሞ ህዝብ ላይ የተሰነዘረ የጥላቻ አመለካከትም ሆነ ጥቃት የለም፡፡ ስለሆነም አሁን ለደረስንበት የተጠራጣሪነት አስተሳሰብ ችግሩም ሆነ መፍትሔው ያለው በእሳቸውና በድርጅታቸው በኩል ነው፡፡ በመሆኑም በአማራ ህዝብ ላይ ተማኒነት ለማግኘት ከፈለጉ የቤት ስራቸውን መስራት ያለባቸው አቶ ለማና ድርጅታቸው ናቸው፡፡ የአማራ ህዝብ ስለ ኢትዮጵያ አንድነትና በጋራ መኖር በንግግር ሳይሆን በደም መስዋዕትነት በስነ ልቦናው ተዋህዶታል፡፡ በጊዚያዊ የፕሮፓጋንዳ ግርግር የተፈጠረውን ጠባሳና የአመለካከት መራራቅ መጠገን አይቻልም፡፡
እዚህ ላይ በሕወሐት/ኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረው ሽኩቻ ለትግሉ አስተዋፅኦ የለውም ማለቴ አይደለም፡፡ ይህ የድርሻ ይገባኛል ሽኩቻ የማይቀር መሆኑን በመገንዘብ ለትግሉ የበኩላችንን አስተዋፅኦ እንዴት ማድረግ እንዳለብን ከስድስት ወር በፊት “አይቀሬው የለውጥ ማዕበል በኢትዮጵያና የህወሐት/ኢሕአዴግ የቁልቁለት ጉዞ” በሚል ርዕስ በዚሁ ማህበራዊ ሚዲያ ገልጫለሁ፡፡

Filed in: Amharic