>
8:08 am - Sunday January 29, 2023

የኛ ሰው በሄግ ችሎት - (ክንፉ አሰፋ - ዘ ሄግ)

ለ25 ዓመታት በኔዘርላንድ ውስጥ ሲኖር ሰብዓዊነት ማለት ምን እንደሆነ በደንብ የተረዳ ይመስላል። ምዕራባውያን ለሰብዓዊ ፍጡር የሚሰጡትን ዋጋ ሳይገነዘብ አልቀረም። አምላክ በአምሳሉ የፈጠረው የሰው ልጅ ህይወት ቀርቶ ለእንሰሶች ህይወት የሚሰጠውን ክብር ሌት ተቀን እያየ የአመለካከት ለውጥ አያደርግም ብሎ ለመናገር ይከብዳል።  እዚህ ሰብአዊ ፍጡርን በፖለቲካ አመለካከቱ መግደል ከቶውንም አይታሰብም።  መግደል አይደለም የሰው ልጅ ላይ እጁን የሚያነሳ፣ ጸያፍ ስድብ ከአንደበቱ የሚያወጣ እንኳ ባለስልጣን ቢኖር ዋጋ ይከፍላል።

መቶ አለቃ እሸቱ  በዚህ ሕብረተሰብ ውስጥ ለ25 ዓመታት ዘልቋል።   ከ25 ዓመት በፊት የነበረውን ትውስታ ሁሉ አጭንቅላቱ ሰርዞ አዲስ የስነልቦና ተክለሰውነት ይዞ እየኖረ ነው። በሌላ አገላለጽ ከ30 ዓማታት በፊት የተከሰተውን ሁሉ እንዳያስታውስ ሜሞሪው ሙሉ በሙሉ ታጥቧል።    ‘ወጣቱ የደርግ አባል’ ተብሎ ይጠራ የነበረው መቶ አለቃ እሸቱ አለሙ ዜግነቱ ወደ ሆላንዳዊነት ሲቀየር በሱ አመለካከት ሁለ ነገሩ ተቀይሯል።  ከዚያን ግዜ በኋላ  እያቆራረጠ መተንፈስን አቆሞ የነጻነት አየር ያገኘ መስሎት ነበር።  እንደማንኛውም የደች ዜጋ ይኖራል፣ ይዝናናል፣  የዜግነት መብቱን ያስከብራል።

“የተሳሳተ ሰው ነው የያዛችሁት” ነበር ያለው መቶ አለቃ እሸቱ ዓለሙ በዘ-ሄግ ከተማ የዓለም አቀፍ ወንጀል ችሎት ላይ ቀርቦ ቃሉን ሲሰጥ። እርግጥ ነው። አሁን “ነጻ ሰው ነኝ” ብሎ ራስን ላሳመነ ሰው ከዳይኖሰር የገዘፈ ወንጀል ከላይ ሲጫንበት ማስደንገጡ አያስገርምም።  “አቃብያነ-ሕግ በምን እንደከሰሱኝ ስሰማ እጅግ ተደናግጫለሁ”  በማለት ለፍርድ ቤቱ የተናገረው ቃል ይህንኑ ያረጋግጥልናል።

ወንጀሉ ከበድ ይላል። በሆላንድ ሃገር (ዓለማቀፉን ችሎት ሳይጨምር)  እንዲህ አይነት የወንጀል ጉዳይ ሲቀርብ የመጀመርያው መሆኑን ነው መገናኛ ብዙሃን የሚነግሩን።   75 ወጣት እስረኞችን መግደል፣  9 እሰረኞችን ማሰቃየት፣  240 እስረኞች ላይ ከባድ ግፍ መፈጸም፣ … ከተዘረዘሩት ክሶች ዋነኞቹ ናቸው።  በሆላንድ የሰብአዊነት አስተሳሰብና ስነልቦና ውስጥ ለሚገኝ ሰው ይህንን ዱብ እዳ በአንድ ግዜ መቀበል ቢከብድም ምላሹ ግን ያስደነግጣል።  “ጎጃም ውስጥ እስር ቤቶች አይቼ አላውቅም!” ብሏል እሸቱ።  የሚደብር አካካድ። መካድ ካልቀረ በደንብ አድርጎ መሸምጠት ነበረበት።   “እኔ መቶ አለቃ እሸቱ አለሙ አይደለሁም። ተሳስታችኋል!” ቢል ነበር ጥሩ ክህደት የሚሆነው።  ከጉዳዩ ባያመልጥም!  “ላታመልጪኝ አታሯሩጭኝ”  ይል የለ ያገሬ ሰው።

በስልጣን ስካር ውስጥ በነበረበት ግዜ ያደረገው የነበረው ነገር  ሁሉ ላይታወሰው ይችላል።  በወቅቱ አይኖቹ ሁሉ ተጋርደው  የሚታየው ከፍ ብሎ የወጣበት የስልጣን ማማ  እና በዜጋው ላይ ሊፈርድ የተቀመጠበት ወንበር ብቻ ነው።  ቀይ ሽብርን ደርሼ በአይኔ ባላየውም በታሪክ አንብቤያለሁ።  የወጣቱ ደም እንደ ጎርፍ መፍሰስ  በወታደሮቹ  እንደጀብድ የሚታይበት ግዜ ነበር።  በስልጣን ለመቆየት ሲሉ ብቻ አንድን ትውልድ እንደዋዛ አጠፉት።  የሚገርመው የአሁኖቹ ባለተራዎች ከዚህ ያለመማራቸው ነው። እነሱም ደም ማፍሰሱን አላቆሙትም።  ስልት ቀየሩ እንጂ  ትውልዱን  አሁንም እየፈጁት ይገኛሉ። የቤተ መንግስቱን ቁልፍ በእጃቸው ሲያስገቡ የሚታወሩበት አዚም ግራ ይገባል። ሌላው ቀርቶ የሚያንማርዋ መሪ ኡን ሳን ሱ ቺ – ተቃዋሚ ሳለች  የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ጀግና ነበረች።  ቤተ መንግስት ስትገባ  በአለም አንደኛዋ የተባለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ ተዘፍቃ እየዋኘች ትገኛለች።

ልብ ያለው ልብ ይበል። በህይወት ዘመናቸው ክቡሩን ህይወት የቀጠፉ ሁሉ ደም ይጠራቸዋል። ግዜው ሊቀርብም ሊርቅም ይሽላል።  በመጨረሻ ግን… ማንም ከፍትህ አያመልጥም።  የሰው ደም አይለቅቅም!

እነሆ የ63 አመቱ  እሸቱ አለሙን በሆላንዱ ፍርድ ቆሞ አየሁት። ይህንን ሰው ከዚህ ቀደም አንድ ግዜ ብቻ በአካል አግኝቼ እንዳነጋገርኩት ትዝ ይለኛል። ቀደም ሲል በሆላንድ ላይ “ኢትዮጵያ ወዴት?” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ በነበር ትልቅ ስብሰባ ላይ ሃሳብ ሲሰጥ በቪድዮ አይቼዋለሁ። ስለ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ግንባታ ሲናገር በጣም ያስደምማል።  በእሸቱ ንግግር የተመሰጡት ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ “… አነጋገርርህን  ስሰማ ስልጣኑን ለደርግ መልሰህ ስጥ ስጥ አለኝ” ሲሉ በዚያው ስብሰባ ላይ የተናገሩት የምጸት ቃልም ታወሰኝ።  ከዚያን  ግዜ ወዲህ  እሸቱ በኢትዮጵኖች ስብስብ ላይ ታይቶ አይታወቅም።

ባለፈው ሃሙስ ተጠቂዎች  በ ዘሄግ ፍርድ ቤት ቀርበው ቃል ሲሰጡ በስፍራው የነበረው ስሜት የተለየ ነበር። ሰውን  ሁሉ ስሜታዊ ያደረገው  የተጎጂ ወገኖች ምስክርነት ከተሰማ በኋላ፣  መቶ አለቃ እሼቱ 30 ዓመት ወደኋላ በትውስታ ተጉዞ ወደ አእምሮው  የተመለሰ ይመስላል።     እንባ እየተናነቀውም፣    “በወቅቱ እጅግ አስከፊ ነገር ተፈጽሟል።  ይህ ስርዓት ለፈጸመው በደል ሁሉ በጉልበቴ ተንበርክኬ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ”  ሲል ተናገረ። በዚህ ግን አላበቃም።  ወዲያው አንድ ነገር ትዝ አለውና እንዲህ አለ።

“የሚነገረውን ወንጀል ሁሉ ግን  እኔ አላውቀውም!”

ይቅርታው እና ክህደቱ ትንሽ ግራ ያጋባሉ። ድርጊቱን አልፈጸምኩም ካለ – ሰው ራሱ ላልሰራው ወንጀል እንዴት ይቅርታ ይጠይቃል? ወይንስ  በውክልና  ይቅርታ እንዲጠይቅ ደርግ ሃላፊነት ተሰጥቶታል?

እ.ኤ.አ. ጥቅምት 16 ቀን 2018  የሆላንድ ፖሊሶች  የፍርድ ቤት ማዘዣ  በመያዝ  አምስተልቪን በሚገኘው መኖርያው እሸቱ አለሙን እስካገቱት ድረስ ድምጹም ተሰምቶ አያውቅም።     በደርግ ዘመን  በጎጃም ክፍለ ሃገር ዜጎችን በመግደል፣ በማሰርና በማሰቃየት ተከስሶ በወያኔ የሞት ፍርድ የተበየነበት መቶ አለቃ እሸቱ አለሙ  በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ ሁለት አመት ሞላው።

እሸቱ አለሙን ለፍርድ የማቅረብ ሂደቱ የተጀመረው ከዛሬ 18 አመት ገደማ  ነበር።  በወቅቱ ከገዥው ፓርቲ ደህንነት ሃላፊ የነበሩት አቶ ክንፈ ገብረመድህን ሆላንድ ሃገር ባሉ ተወካዮቻቸው አማካይነት እንቅስቃሴ ተጀመረና  ግፊቱ ወደ ሆላንድ የኢትዮጵያውያን ማህበር ጽህፈት ቤት ደረሰ። በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ ማህበር አመራሮች ጉዳዩን ከግምት ውስጥ አላስገቡትም ነበር። ለዚህም በቂ ምክንያት ነበራቸው።   በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከደርግ የባሰ ወንጀል እየፈጸመ ነበርና።

ወያኔ በቀጥታ የሆላንድ መንግስትን መጠየቅ ሲችል ለምን በዚህ መንገድ መጣ የሚለው ጥያቄ በወቅቱ በእምሮዬ መጣ።  ሁለት ምክንያት አለው።   አንደኛው ሁለቱ ሃገራት ወንጀለኛን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ስለሌላቸው እና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ የሞት  ቅጣትን ስላካተተ ነው።

በወቅቱ የነበረው የማህበሩ አመራር፣  “ግለሰቡ መዳኘት ካለባቸው ዘ ሄግ ያለው አለም አቀፉ ፍርድ ቤት ነው” ሲል ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

እ.ኤ.አ. በ1998 ዩዲት ኑሪንክ የምትባል ታዋቂ የሆላንድ ጋዜጠኛ  ቢሮዋ ጠርታ ስለዚህ ጉዳይ  አነጋገረችኝ። እሸቱ አለሙ የጎጃም ነዋሪ ወጣቶች እንዲገደሉ እና እንዲታስሩ የፈረመበት ክምር ዶሴ በእጅዋ ነበር።  እንደ ጋዜጠኛ ሃላፊዋነትዋን ብቻ መወጣት እንደሚገባት ተነጋግረን ተለያየን። ጋዜጠኛ  ዩዲት – የኢትዮጵያ ማህበር አመራሮችን  (ጸጋ ታክሉን እና ወንድም አስረስን) እያጣቀሰች መረጃውን በአንድ ተነባቢ መጽሄት ላይ ለቀቀችው። …  ከዚያም ጉዳዩ በሆላንድ የአለማቀፍ ወንጀሎች ምርመራ ቡድን አይን ውስጥ ሊገባ ቻለ።

የሆላንዱ ፍርድ ሂደት ለእሸቱ አለሙ ህልም ሊመስል ይችላል።  የሚወዱትን ለተነጠቁት ለሟች ቤተሰቦች ግን እውን ነው።  እሸቱ አለሙን በባእድ ሃገር ፍርድ ቤት ብቻውን ቆሙ ለሚያየው ሰው እጅግ ያሳዝናል።    ከጎኑ አንዳች ሰው የለም።

በአይኑ ሳይሆን በልቦናው አትኩሮ ለሚመለከተው ሁሉ የሚነግረን መልእክት ግን አለ። … “እኔን ያየህ ተቀጣ!”

ይቀጥላል….   የፍርድ ሂደቱ ማክሰኞ ይቀጥላል።  ካቻልኩ በምስል ለማቅረብ እሞክራለሁ!

Filed in: Amharic