ከለይ ለተጠቀሱት እያንዳንዱ ቀን የተሰጠው መሪ ቃል፣ እንዲሁም በመርሃ ግብሩ የተዘረዘሩት ተግባራት አንድነትን፣ የሀገር ፍቅርን እና ኢትዮጲያዊነትን አያንፀባርቁም። ለምሳሌ፣ በመርሃ ግብሩ መሰረት፣ ሀገራዊ አንድነትን ለማንፀባረቅ ከሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ “ትምህርት ቤቶችን እና የስራ ቦታዎችን በጋራ ማጽዳትና ማደራጀት፣ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን በአብሮነት ስሜት በጋር ማከናወን፣ እንዲሁም በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎችን መጎብኘት” የሚሉት ተጠቅሰዋል። በተቀሩት ሁለት ቀናት የሚከናወኑት ዝርዝር ተግባራት ደግሞ ከመሪ ቃሉ የባሰ አስቂኝና የተሳሳቱ ናቸው። በአጠቃላይ፣ “የአንድነት ቀን”፣ “የሀገር ፍቅር” እና “የኢትዮጲያ ቀን” በሚል የተዘጋጀው መርሃ ግብር የኢህአዴግ መንግስት የሚከተለውን የተሳሳተ የፖለቲካ አቅጣጫ በተጨማሪ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ያለበትን ስር የሰደደ የዕውቀት እጥረት (knowledge deficiency) በግልፅ ያሳያል። ለምን እና እንዴት የሚለውን ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር እንመለከታለን።
የሰው ልጅ አስተሳሰብ በወደፊቱ ግዜ ላይ የተመሰረተ ነው። ትላንትን የሚያስተወሰው የነገ ሕይወቱን ለማስተካከል ወይም ለማሻሻል ነው። ዛሬ ላይ የሚፈፅመው ተግባር ነገን ታሳቢ ያደረገ ነው። ምክንያቱም፣ ሰው የሚኖረው በወደፊት እና ለወደፊት ነው። “የሰው ልጅ የሚኖረው በተስፋ ነው” ወይም ደግሞ “Human being lives primarily in the future and for the future” የሚለው አባባል ይህን የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ይገልፃሉ። ስለዚህ፣ ከወደፊት ሕይወቱ የተነጠለ ወይም ተያያዥነት የሌለው ነገር ለሰው ልጅ ስሜት አይሰጥም። በዚህ መሰረት፣ ሀገራዊ አንድነት፥ ፍቅርና ዜግነት ትርጉም የሚኖራቸው በዜጎች የወደፊት ሕይወት ውስጥ ፋይዳ ሲኖራቸው ነው። በወደፊት ሕይወታችን ውስጥ ፋይዳ ከሌላቸው ግን ዛሬ ላይ ዋጋ አንሰጣቸውም። በቀጣይ ቀናት የሚከበሩት የአንድነት፣ የሀገር ፍቅር እና የኢትዮጲያ ቀናት ከዚህ አንፃር መታየት አለባቸው።
ብዙዎቻችሁ እንደምትታዘቡት እገምታለሁ፣ በተለይ ባለፉት አስርና አስራ አምስት አመታት የኢህአዴግ መንግስት ስለ “አንድነት፣ የሀገር ፍቅር ወይም ኢትዮጲያዊነት” ምንም ቢናገር፥ ቢያደርግ በብዙሃኑ ዘንድ ተዓማኒነት የለውም። የኢህአዴግ መንግስት ስለ ብሔሮች መብትና እኩልነት እንጂ ስለ ሀገራዊ አንድነት፣ ፍቅርና ዜግነት ቢናገር፥ ቢከራከር ተቃዋሚዎች ቀርቶ የራሱ ደጋፊዎች እንኳን በሙሉ ልብ አምነው አይቀበሉትም። ምክንያቱም፣ የኢህአዴግ መንግስት የፖለቲካ መርህና አመለካከት ሙሉ በሙሉ በትላንትና ዛሬ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። ከሕገ-መንግስቱ ጀምሮ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ መርሆችና ፖሊሲዎች በሙሉ ከቀድሞ ስርዓት ላይ ተነስተው የአሁኑ ስርዓት ላይ የሚቆሙ ናቸው። ከወደፊቱ ሕይወት ጋር ትስስር የላቸውም። ሃሳቡን ግልፅ ለማድረግ ከሀገር አመሰራረትና አንድነት አንፃር መመልከት ይኖርብናል።
በቀጣይ ሳምንት ከሚከበሩት አንዱ “የአንድነት ቀን” ሲሆን “ኢትዮጵያዊ ኩራቱ ህብረ-ብሄራዊነቱ” የሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ከላይ ተገልጿል። ነገር ግን፣ የኢህአዴግ መንግስት ሀገራዊ አንድነትን “ከህብረ-ብሔራዊነት ወይም ብዙሃንነት” አንፃር የሚገልፅበት ምክንያት ምንድነው? “ኢትዮጵያዊ ኩራቱ ህብረ-ብሄራዊነቱ” የሚለው መሪ ቃልስ ከአንድነት ፅንሰ-ሃሳብ ጋር አብሮ ይሄዳል? በእርግጥ የኢህአዴግ መንግስት ሀገራዊ አንድነትን ከህብረ-ብሔራዊነት ጋር አንፃር የሚገልፅበት ዋና ምክንያት ራሱን ከቀድሞ አህዳዊ ስርዓቶች ለመለየት ነው።
የኢህአዴግ መንግስት በተለይ በአፄ ሚኒሊክ ዘመን የተመሰረተችው የአሁኗ ኢትዮጲያ በአንድ ዓይነት ቋንቋ፥ ታሪክ፥ ባህል፥ ሃይማኖት፥… እንደሆነ ይገልፃል። በዚህ መሰረት፣ በቀድሞ ስርዓት “አንድነት” ማለት አማርኛ ቋንቋ፣ የአማራ ባህልና ሃይማኖት፣ እንዲሁም የአማራ የበላይነት የተረጋገጠበት አስተዳደራዊ ስርዓት እንደነበር ይገልፃል። በሕወሃት መሪነት የተጀመረው የትጥቅ ትግልም ይህን አህዳዊ ስርዓት በማስወገድ የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብትና እኩልነት የተረጋገጠበት ፖለቲካዊ ስርዓት ለመዘርጋት ዓላማ ያደረገ ነበር። የደርግን ስርዓት በማስወገድ የተዘረጋው በብሔር ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ስርዓት የዚህ ውጤት ነው። በመሆኑም፣ የኢህአዴግ መንግስት ሀገራዊ አንድነትን ከሕብረ-ብሔራዊነት ነጥሎ ማየት አይችልም። ሕብረ-ብሔራዊነትን ከቀድሞ ታሪክ፣ ከአሁኑና ከወደፊቱ ፖለቲካ አንፃር እንመልከት።
የኢትዮጲያ አመሰራረትና አንድነት
የኢህአዴግ መንግስት በተደጋጋሚ ኢትዮጲያ እንደ ሀገር መቀጠል የቻለችው በሕብረ-ብሔራዊነቷ፥ በብሔር ልዩነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት መዘርጋት በመቻሏ እንደሆነ ይገልፃል። እንደ ኢህአዴግ መንግስት አገላለፅ፣ በቀድሞ ስርዓት የነበረው የኢትዮጲያ አንድነት በአንድ ዓይነት ቋንቋ፥ ታሪክ፥ ባህል፥ ሃይማኖት፣ እንዲሁም በአንድ ብሔር የበላይነት ላይ የተመሰረተ ከነበረ፣ ሀገሪቱ የኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን እስከመጣበት 1983 ዓ.ም እንደ ሀገር መቀጠል አትችልም ነበር። አፄ ሚኒሊክ የአሁኗን ኢትዮጲያ ከመመስረታቸው በፊት ሆነ በኋላ በአንድ አይነት ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖት ሀገር ለመመስረት የተደረገው ሙከራ በተደጋጋሚ ውድቅ ሆኗል። በአጠቃላይ፣ በፍፁም አህዳዊ እሳቤ ሀገራዊ አንድነትን ማረጋገጥ አይቻልም።
“Jose Ortega y Gassett” የተባለው ፀኃፊ “THE REVOLT OF THE MASSES” በሚለው መፅሃፉ ስፔን በመካከለኛውና ደቡብ አሜሪካ ያጋጠማትን እንደ ማሳያ ይጠቅሳል። ከዚህ በተጨማሪ፣ እንደ እንግሊዝና ፈረንሳይ ያሉ ሀገራት በቅኝ-ግዛቶቻቸው በአንድ ዓይነት ቋንቋ፥ ታሪክ፥ ባህልና ሃይማኖት ላይ የተመሰረተ አንድነት ለመፍጠር የሚያደርጉት ሙከራ እንደማይሳካ መፅሃፉ በወጣበት እ.አ.አ. 1929 ዓ.ም ላይ ሆኖ በግልፅ ጠቁሟል። በተለይ ስፔን በመካከለኛውና ደቡብ አሜሪካ በነበሯት ቅኝ-ግዛቶች የጋራ ታሪክ፥ የጋራ ቋንቋና ዘር እንደነበራት ይገልፃል። ሆኖም ግን ሀገራዊ አንድነት ሊኖራት እንዳልቻለ እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-
“With the peoples of Central and South America, Spain has a past in common, common language, common race; and yet it does not form with them one nation. Why not? There is one thing lacking which, we know, is the essential: a common future.” The Revolt of the Masses, Ch. XIV: Who Rules the World?, Page 105.
ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ ስፔን በደቡብና መካከለኛው አሜሪካ በአንድ አይነት ታሪክ፥ ቋንቋና ዘር ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠር ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም። እንደ ፈረንሳይ ያሉ ቅኝ-ገዢ ሀገራት የራሳቸውን ቋንቋ፥ ባህል፥ ስነ-ልቦና፥ የትምህርት ስርዓት እና ሌሎች ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ስርዓቶችን በአፍሪካና ኢሲያ ሀገራት ላይ በመጫን አህዳዊ አንድነት እንዲኖር ያልተሳካ ሙከራ አድርገዋል። አንዳንድ አክራሪ ብሔርተኞች የአፄ ሚኒሊክን መስፋፋት ከቅኝ-ግዛት ጋር ያያይዙታል። ሕወሃት/ኢህአዴግ ደግሞ የኢምፔሪያሊዝም መስፋፋት እንደሆነ ይገልፃል። ሁለቱም ወገኖች ግን ከአፄ ሚኒሊክ ጀምሮ እስከ ኢህአዴግ መንግስት ድረስ በአንድ ቋንቋ፥ ታሪክ፥ ባህልና ሃይማኖት ላይ የተመሰረተ አንድነት እንደነበረ ይገልፃሉ። የስፔንና ፈረንሳይ ተሞክሮ የሚያሳየው ግን በዚህ ላይ የተመሰረተ አንድነት ቀጣይነት እንደሌለው ነው።
የአሁኗ ኢትዮጲያ ግን መመስረት ከተመሰረተችበት ግዜ አንስቶ የኢህአዴግ መንግስት እስከ መጣበት ድረስ አንድ መቶ አመት ያህል አንድነቷን አስጠብቃ ቆይታለች። ከዚህ በተጨማሪ፣ ገና በምስረታ ሂደት ላይ እያለች የኢጣሊያን የተቃጣባትን የቅኝ-ግዛት ወረራ መመከት ችላለች። በወቅቱ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የወደፊት አብሮነት “common future” ካልነበራቸው የኢጣሊያን ወራሪ ጦር በጋራ ተረባርበው አይመክቱም ነበር። እንደ ሀገር አብሮ ለመቀጠል፥ የጋራ ዓላማና ግብ ከሌላቸው የተለያዩ ብሔር ተወላጆች አደዋ ላይ ከኢጣሊያን ጋር የሚዋጉበት ምክንያት የለም።
የኢትዮጲያ ብሔሮች አድዋ ላይ የተዋደቁት የጋራ ዓላማ፣ የወደፊት አብሮነት ስላላቸው እንጂ በቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህል ወይም ሃይማኖት አንድ አልነበረሩም። በተቃራኒው፣ ኢጣሊያ ኢትዮጲያን የወረረችበት ዓላማ በአንድ አይነት ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት እና ግዛት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ለመዘርጋት ነበር። ይህን “
“If any quality typifies Italian colonial efforts it would not be jingoism but apathy. The Italian statesman Marquis d’Azeglio, after Italian unification, commented that “We have made Italy. Now we must make Italians.” Italy was divided along religious, political, and regional lines. It was hoped by some, such as Prime Minister Crispi, that imperialism would improve the standing of the Italian government within the nation and across Europe.” When Ethiopia Stunned the World: Cambridge, Massachusetts: Belknap Press, 2011
ኢትዮጲያ ከአደዋ ጦርነት በኋላም አንድነቷን የሚፈታተኑ ታሪካዊ ክስተቶች አጋጥመዋታል። ከእነዚህ ውስጥ የአምስት አመቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ እና የደርግ ወታደራዊ ፋሽስት አስተዳደር በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። በአጠቃላይ፣ ከኢህአዴግ መንግስት መምጣት በፊት አንድነቷን ሊያፈርሱ የሚችሉ ብዙ አስቸጋሪ ወቅቶችን አልፋለች። አፄ ሚኒሊክ የአሁኗን ኢትዮጲያ ለመመስረት ወደ ደቡብ፥ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫዎች ካደረጉት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮች ሊነሱ ይችላል። ሆኖም ግን፣ እንደ ስፔን፥ ፈረንሳይና ኢጣሊያ ካሉ የቅኝ-ግዛት ኃይሎች በተለየ፣ የአፄ ሚኒሊክ መስፋፋትና የዘረጉት የፖለቲካ አስተዳደራዊ ስርዓት ሕብረ-ብሔራዊ ነበረ።
ኢትዮጲያ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ አንድነቷን አስጠብቃ መቀጠል የቻለችበት ዋና ምክንያት ይሄ ነው። የአፄ ሚኒሊክ መስፋፋት ዋና ዓላማ እንደ አውሮፓዊያኑ የነባር ጎሳዎችን፥ ብሔሮችን ቋንቋ፥ ታሪክ፥ ባህልና ሃይማኖት በአህዳዊ አንድነት ለማጥፋት ሳይሆን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ለመመስረት እንደነበረ በወቅቱ ዓይን እማኝ የነበረው ሩሲያዊው ፀኃፊ “Alexander Bulatovich” እንደሚከተለው ገልፆታል፡-
“These are the motives which led Menelik to aggressive acts; and we Russians cannot help sympathizing with his intentions, not only because of political considerations, but also for purely human reasons. It is well known to what consequences conquests of wild tribes by Europeans lead. Too great a difference in the degree of culture between the conquered people and their conquerors has always led to the enslavement, corruption, and degeneration of the weaker race. The natives of America degenerated and have almost ceased to exist. The natives of India were corrupted and deprived of individuality. The black tribes of Africa became the slaves of the whites.” With the Armies of Menelik II, trans. Richard Seltzer, Journal of an expedition from Ethiopia to Lake Rudolf, an eye-witness account of the end of an era.
ከላይ እንደተመለከትነው፣ ኢትዮጲያ ከአመሰራረቷ ጀምሮ ሕብረ-ብሔራዊ እንደነበረች ተመልክተናል። ለዚህ ደግሞ ሀገሪቷ አንድነቷን ጠብቃ ለአንድ ክፍለ ዘመን መቀጠል መቻሏ፣ አህዳዊ ስርዓት ለመዘርጋት በሚሞክሩ ቅኝ-ገዢዎች የተቃጣባትን ወረራ በጋራ መመከቷ መቻሏ፣ እንዲሁም እንደ “Alexander Bulatovich” አገላለፅ፣ የኢትዮጲያ ነባር ጎሳዎች፥ ብሔሮች ወይም ሕዝቦች ልክ እንደ አሜሪካ ነባር ሕዝቦች (ቀይ ሕንዶች) የመኖር ሕልውናቸውን አለማጣታቸው፣ ቋንቋ፥ ባህልና እምነታቸውን እስካሁን ይዘው መቀጠላቸው በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።
የኢትዮጲያ አንድነት እና የኢህአዴግ አመለካከት
የኢህአዴግ መንግስት የዘረጋው ፖለቲካዊ ስርዓት “የቀድሞ ስርዓት አህዳዊ ነበር” በሚል አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ መሰረት፣ የሀገሪቱ አንድነት በአንድ ቋንቋ፥ ታሪክ፥ ባህልና ሃይማኖት ላይ የተመሰረተ፣ ወይም የአማራ የበላይነት የተረጋገጠበት ነበረ። የኢትዮጱያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብትና እኩልነት ስላልተረጋገጠ ሕብረ-ብሔራዊነት አልነበረም። የኢትዮጲያ አንድነት እና ሕብረ-ብሔራዊነት የተረጋገጠው በኢህአዴግ መንግስት አማካኝነት ነው። ስለዚህ፣ የአንድነት ቀን “ኢትዮጲያዊ ኩራቱ ህብረ-ብሔራዊነቱ” በሚል መሪ ቃል የሚከበርበት ዋና ምክንያት፤ ከአፄ ሚኒሊክ ዘመን ጀምሮ የነበረው ፖለቲካዊ ስርዓት አህዳዊ እንደነበርና ይህም ስርዓት በ1987 ዓ.ም በፀደቀው ሕገ-መንግስት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ እንደተወገደ ለማሳየት ነው።
በቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት ከአፄ ሚኒሊክ ዘመን ጀምሮ የነበረውን በመሻር ሀገሪቷን በአዲስ መሰረት ላይ እንዳቆማት ሲገልፅ ይስማል። በዚህ መሰረት፣ አንደኛ፡- ትላንት ላይ ሕብረ-ብሄራዊ ስርዓት ስላልነበረ ሀገራዊ አንድነት አልነበረም፣ ሁለተኛ፡- ዛሬ ላይ ሕብረ-ብሄራዊ ስርዓት ስለተዘረጋ ሀገራዊ አንድነት አለ። ነገር ግን፣ ዛሬ ኢትዮጲያ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲኖራት ትላንት ላይ ሕዝቦቿ የጋራ ታሪክና የወደፊት አብሮነት ሊኖራቸው ይገባል። ትላንት ላይ ሕብረ-ብሔራዊነት ካልነበረን የወደፊት አብሮነት አይኖረንም፤ የወደፊት አብሮነት ካልነበረን ዛሬ ላይ አንድነት ሊኖረን አይችልም። ሃሳቡን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ ሃሳቡን በዝርዝር መመልከት ያስፈልጋል።
በመጀመሪያ ደረጃ ከአፄ ሚኒሊክ ዘመን ጀምሮ ሕብረ-ብሔራዊነት ካልነበረ ሀገሪቱ ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል አንድነቷን ጠብቃ መቀጠል አትችልም ነበር። ምክንያቱም፣ አፄ ሚኒሊክ ወደ ደቡብ፥ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫዎች በመዝመት ከፊሉን በአስከፊ ጦርነት የተቀሩትን በሰላማዊ ድርድር የኢትዮጲያ አካል ያደረጓቸው የተለያዩ ጎሳዎች፥ ብሔሮችና ሕዝቦች ከተወሰነ ግዜ በኋላ ራሳቸውን ከአገዛዙ ነፃ ለማውጣት ትግል ይጀምራሉ። በተመሳሳይ ወቅት በአውሮፓ ቅኝ-ገዢዎች ስር የወደቁ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሕዝቦች ከግማሽ ክ/ዘመን በኋላ ራሳቸውን ከአገዛዙ ነፃ ማውጣት ችለዋል። የኢትዮጲያ ብሄሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ግን የኢትዮጲያ አካል ከሆኑ አስር አመት ሳሞላቸው የኢጣሊያን የቅኝ-ግዛት ወረራ ለመመከት በጋራ ወደ አድዋ ዘምተዋል።
ኢትዮጲያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልዩ የሚያደርጋት በአደዋ ጦርነት በነጮች ላይ የተቀዳጀችው ድል አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ከሌሎች አፍሪካዊያን በተለየ በኢትዮጲያ ስር የነበሩት ነባር ግዛቶች፡- ሸዋ፥ ጎንደር፥ ትግራይ፥ ጎጃምና ወሎ በደቡብ፥ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫ ከነበሩት ሌሎች ብሄሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በመቀናጀት የቅኝ-ገዢዎችን በጋራ ለመመከት መስማማታቸው ነው። ስለዚህ፣ ኢትዮጲያዊያን በኩራት የሚጠቅሱት የአደዋ ድል የመጨረሻ ውጤት እንጂ መነሻ ምክንያት አይደለም። ከአደዋ ድል እና ከኢትዮጲያ ነፃነት በስተጀርባ ያለው ሚስጥር የኢትዮጲያ ብሄሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በጋራ በመሆን ራሳቸውን ከቅኝ-ግዛት ወረራ ለመከላከል የፈጠሩት የወደፊት አብሮነት (common future) ነው። ሌሎች አፍሪካዊያን ይህን የወደፊት አብሮነት መፍጠር ስለተሳናቸው ለቅኝ-ግዛት ተዳርገዋል። ኢትዮጲያዊያን ግን ራሳቸውን ከቅኝ-ገዢዎች ወረራ መከላከልን ዓላማ አድርገው የፈጠሩት አብሮነት ለአንድነታቸው መሰረት ሆኗል።
በሌላ በኩል፣ የአፄ ሚኒሊክ አገዛዝ ልክ እንደ ቅኝ-ገዢ ኃይሎች አህዳዊ ፖለቲካዊ ስርዓት የመዘርጋት ዓላማ ከነበረው በተለያዩ ብሄሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ላይ አንድ ዓይነት ቋንቋ፥ ታሪክ፥ ባህልና ሃይማኖት ይጭኑ ነበር። ይህ ከሆነ ደግሞ በደቡብና መካከለኛው አሜሪካ እንደነበረው የስፔን አገዛዝ፣ እንዲሁም በአፍሪካ ኢሲያ እንደ ነበረው የፈረንሳይ አገዛዝ ለውድቀት ይዳረግ ነበር። አሊያም ደግሞ የሀገሪቱን ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድ ላይ በማቀናጀት የኢጣሊያን ወረራ መመከት ይሳነው ነበር። በመሆኑም፣ በአፄ ሚኒሊክ ዘመን የተዘረጋው አገዛዝ ሕብረ-ብሔራዊነት ካልነበረው፣ እንደ ኢህአዴግ መንግስት አገላለፅ ወይም እንደ ቀኝ-ገዢ ኃይሎች ፍፁም አህዳዊ ስርዓት ከነበረ ከግማሽ ከፍለ ዘመን በፊት በወደቀ፣ ሀገሪቷም አንድነቷን አስጠብቃ ማስቀጠል በተሳናት ነበር። ስለዚህ፣ ኢትዮጲያ እንደ ሀገር መቀጠል የቻለችው በሕብረ-ብሔራዊነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ስለነበራት ነው።
የፈረሰ አንድነት
የኢህአዴግ መንግስት “ዛሬ ላይ በሀገራችን የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብትና እኩልነት ተረጋግጧል” የሚለውን እውነት ነው ብለን እንቀበል። በሕገ-መንግስቱ መሰረት፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው ተከብሯል። የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በራሳቸው ቋንቋ የመናገር፥ የመማርና የመፃፍ መብት፣ ባህላቸውን መግለጽና ማሳደግ ችለዋል። በመሆኑም፣ ሀገራችን ብዙሃንነት የሚንጸባረቅባት ሕብረ-ብሔራዊ ሆናለች። ይሄ ዛሬ ላይ ያለው፥ የሆነውና እየሆነ ያለ ነገር ነው። ነገ ግን ሌላ ቀን ነው። ዛሬ ላይ ያለው፣ የሆነው ወይም እየሆነ ባለው ነገር ብቻ መኖር አይቻልም።
ትላንት ላይ ሆነን የዛሬውን ህብረ-ብሔራዊነት ስንመኝ፥ ስናስብና ስናቅድ ስለነበር በተግባር እውን ማድረግ ችለናል። ነገር ግን፣ በትላንት ሃሳብ፥ ዕቅድና ምኞት ዛሬን መኖር አንችልም። ምክንያቱም፣ የሰው ልጅ ትላንትን የሚያስታውሰው ሆነ የዛሬ ተግባሩን የሚፈፅመው ነገ ላይ የተሻለ ነገር ለማግኘት ነው። የቀድሞውን የኢትዮጲያን የቀድሞ ታሪክ የምናስታውሰው፣ የዛሬውን ህብረ-ብሔራዊነት የምናወድሰው፣ ነገ ላይ የተሻለ ፖለቲካዊ ስርዓት ለመዘርጋት እንዲያስችለን ነው። ይሁን እንጂ፣ የኢህአዴግ መንግስት ከቀድሞ ስርዓት ስህተት እና ከአሁኑ ስርዓት ፍፁማዊነት ትርክት ባለፈ ለነገ ምን ሰንቋል?
የኢህአዴግ መንግስት የዘረጋው ፖለቲካዊ ስርዓት፤ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች ትላንት ላይ የጋራ ታሪክና አብሮነት ወይም አንድነት አልነበራቸውም፣ ዛሬ ላይ ግን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት አላቸው፣ ነገ ላይ ደግሞ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 39(1) መሰረት በማንኛውም መልኩ የማይገደብ የራስ እድልን በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት አላቸው። ስለዚህ፣ ትላንት ላይ የጋራ አብሮነት አልነበረንም፣ ዛሬ ላይ በልዩነት አብረን አለን፣ ነገ ላይ መለያየት እንችላለን። በዚህ መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት አቋምና አመለካከት ስህተት ነው።
አንደኛ፡- ዛሬ ላይ አብረን እንድንሆን ትላንት ላይ አብረን መሆን ነበረብን። ምክንያቱም፣ ትላንት ላይ አብረው ያልነበሩ ወገኖች ዛሬ ላይ ስለ ወደፊት አብሮነት ሆነ መለያየት ለመነጋገር መሰረት የላቸውም። ዛሬ ላይ አብረን እንድንሆን ትላንት ላይ በወደፊት አብሮነት (common future) የተመሰረተ አንድነት ሊኖረን ይገባል። ትላንት ላይ የወደፊት አብሮነት ከነበረን ደግሞ የጋራ አንድነት እንደነበረን መገመት ይቻላል። ስለዚህ፣ የኢህአዴግ መንግስት በህብረ-ብሄራዊነት ላይ የተመሰረተ አንድነት በ1987 ዓ.ም እንደሆነ የሚገልፀው ፍፁም ስህተት ነው።
ሁለተኛ፡- ዛሬ ላይ አንድነት እንዲኖረን የወደፊት አብሮነት ሊኖረን ይገባል። የወደፊት አብሮነት እንዲኖረን ስለ ወደፊቱ ግዜ በጋራ ማሰብ፥ መመኘት፥ ማቀድ፥ መነጋገርና መግባባት አለብን። ይህን ለማድረግ ደግሞ ለወደፊት በአብሮነት ለመኖር መወሰን አለብን። ነገር ግን፣ የትኛውም ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ መቼና ለምን እንደሆነ ባልታወቀ ምክንያት ከሌሎች የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ጋር አብሮ መቀጠል ባለመፈለጉ ምክንያት ሊገነጠል ይችላል።
በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 39(1) ላይ በተደነገገው መሰረት፣ ማንኛውም የኢትዮጲያ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ በማንኛውም መልኩ ያልተገደበ የመገንጠል መብት አለው። በድንጋጌው መስረት፣ “የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል መብቱ በማንኛውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” እንደማለቱ፣ ሌሎች ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች፣ ወይም አግባብነት ያለው ማንኛውም አካል አንድን ብሔር እንዳይገነጠል ወይም ከሌሎች ጋር በአብሮነት እንዲቀጥል ሊያደርጉት አይችሉም። በአጠቃላይ፣ ትላንት ላይ አንድነት አልነበረንም፣ ዛሬ ላይ በልዩነት አለን፣ ነገ ላይ ግን ለመለያየት አቅደናል። ለመለያየት እቅዱ ባይኖር እንኳን መንገዱን አዘጋጅተናል። ስለዚህ፣ ዛሬ ላይ አብረን እያለን ነገ ላይ ተለያይተናል።
የኢህአዴግ መንግስት ስለ ቀድሞ ስርዓት የተሳሳ ተግንዛቤ አለው። ፖለቲካዊ ስርዓቱም በተሳሳተ መርህ ላይ የተመሰረተ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ፖለቲካዊ ስርዓቱ በትላንት እና ዛሬ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው። ይህ ማለት ስለ ትላንቱ የጋራ ታሪክ ወይም ዛሬ ላይ ስላለን የጋራ ጉዳይ አይደለም። “አንድነት” ማለት ነገ ላይ ያለን የጋራ ተስፋና አብሮነት ነው። በትላንቱ ወይም በዛሬ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት የሀገር አንድነትን፥ ፍቅርንና የዜግነት ክብርን ያጠፋል፡-
“If the nation consisted only in past and present, no one would be concerned with defending it against an attack. Those who maintain the contrary are either hypocrites or lunatics. But what happens is that the national past projects its attractions- real or imaginary into the future. A future in which our nation continues to exist seems desirable. That is why we mobilise in its defence, not on account of blood or language or common past. In defending the nation we are defending our to-morrows, not our yesterdays.” The Revolt of the Masses, Ch. XIV: Who Rules the World?, Page 103.
የሀገር አንድነት የወደፊት አብሮነት ነው። ወደፊት ለመለያየት እቅድ ያለን ወይም መንገዱን ያዘጋጀን ሕዝቦች የወደፊት አብሮነት የለንም። የወደፊት አብሮነት ከሌለን ሀገራዊ አንድነት የለንም ወይም ሊኖረን አይችልም። በአጠቃላይ፣ የአሁኗ ኢትዮጲያ አንድነት የላትም። አሁን ያለው ፖለቲካዊ ስርዓት እስካለ ድረስ አንድነት ሊኖራት አይችልም። በዚህ ሁኔታ፣ ዜጎች የሀገር ፍቅር ሆነ የዜግነት ክብርና ኩራት ሊኖራቸው አይችልም። የላቸውም! ምክንያቱም፣ ሀገር የሚመሰረተው፣ አንድነት የሚረጋገጠው፣ እንዲሁም ዜጎች ሀገራዊ ፍቅርና ክብር የሚኖራቸው በሌላ ሳይሆን የወደፊት አብሮነት ሲኖራቸው ነው። ለወደፊት ለመለያየት እቅድ ያለን ሕዝቦች የወደፊት አብሮነት የለንም!!!
በመጨረሻም፣ “ኢትዮጲያዊነት” ማለት በወደፊት አብሮነት ላይ የተመሰረተ አንድነት፣ የሀገር ፍቅር እና የዜግነት ክብር ነው። የኢህአዴግ መንግስት የሀገር አንድነት፣ ፍቅርና የዜግነት ክብር ከአብዛኛው ኢትዮጲያዊ አመለካከት ውስጥ ተፍቆ እንዲወጣ በማድረግ ይህን የአብሮነት መንፈስ ለማጥፋት ተቃርቧል። ጎጠኝነትና ጠባብ ብሔርተንነት ገኖ እንዲወጣ በማድረግ ኢትዮጲያዊነትን ትርጉም አሳጥቶታል። በአንፃሩ፣ የውስን አመለካከት ነፀብራቅ የሆነው ብሔርተኝነትና ጎጠኝነት በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። በመሆኑም፣ በግብዝ ዕውቀትና ግንዛቤ ላይ ተመስርቶ ሀገር ማፍረሱን ቀጥሎበታል።