>

የሃሳብ ነፃነት እና የአስተሳሰብ ባርነት (ስዩም ተሾመ)

አንዳንድ ወዳጆቼ በESAT ሲጠብቁኝ በOBN መምጣቴ አልተዋጠላቸውም። የኦሮሞና አማራ ሕዝብን፤ “ማን አስታራቂ አደረገህ?”፣ “ለምን 2/3ኛ አልክ?”፣ “የኦህዴድ/ኢህአዴግ ደጋፊ ሆንክ?”፣ “ጠቃሚ ደደብ ነህ?” እና የመሳሰሉት ሲሉ አያለሁ። “ጉድጓድ ውስጥ ያለች አይጥ የሰማዩ ስፋት ካለችበት ከጉድጓዱ አፍ ስፋት የሚበልጥ አይመስላትም” እንደሚባለው ሁሉ “በጎሳ ፖለቲካ” ውስጥ የተዘፈቁ ሰዎች ሁሉንም ነገር በብሔር ምንፅር ነው የሚመለከቱት።

Photo credit: Milkeessaa Midhagaa (Dr.)

የፖለቲካ አቋምና አመለካከታቸው በብሔር ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም አንድን ነገር ሲደግፉ ሆነ ሲቃወሙ በብሔር ነው! ሃሳብና አስተያየት ሲሰጡ በብሔር ነው! የሌሎችን አቋምና አመለካከት ሲተቹ በብሔር ነው። እንደ ብሔር ካልሆነ እንደ ሰው በራሳቸው ማሰብ ሆነ መናገር አይችሉም።
ከብሔርተኝነት ባለፈ ሰብዓዊነት የሚባል ነገር አለ። እንደ ሰው ስታስብ፣ ሁሉም ሰዎች ልክ እንደ አንተ የተሻለ ነፃነትና ተጠቃሚነት እንደሚሹ ትረዳለህ። ይህን ስትረዳ “ሁሉም ሰው በሰውነቱ እኩል መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ይገባዋል” የሚል እምነት ይኖርሃል። የፖለቲካ አቋምና አመለካከትህ ከዚህ አንፃር የተቃኘ ይሆናል። ከአባይ ማዶ፥ ከተከዜ በላይ፥ ከአዋሽ በታች፥ ከኦሞ ግርጌ፣ … በየትኛውም አከባቢ ይስፈር፣ ሁሉም ሕዝብ እንደ ሕዝብ የተሻለ ልማት፥ ሰላምና ዴሞክራሲ ይገባዋል። ኦሮሞ፥ አማራ፥ ጉራጌ፥ ትግሬ፥ ሶማሌ፥ ወላይታ፥ ከንባታ፥…. ሁሉም ትላንት ላይ የጋራ የሆነ አኩሪና አሳፋሪ ታሪክ አላቸው፣ ዛሬ ላይ በአንድ ሀገርና ስርዓት ስር ናቸው፣ ነገ ላይ የጋራ ተስፋና ስጋት አላቸው።ስለዚህ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች፤ ስለ ቀድሞ ታሪካቸው፣ ስለ ዛሬው ሁኔታ እና ስለ ነገ ተስፋና ስጋታቸው እርስ በእርስ መነጋገር አለባቸው። ባለመነጋገር የአለመተማመንና ጥርጣሬ ይሰፍናል። በመነጋገር መተማመንና መግባባት ይሰፍናል። በዚህ መሰረት፣ በመግባባትና ትብብር ላይ የተመሰረተ አንድነት ይኖራል።

በሕወሃት መሪነት የተዘረጋውና ላለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን በተግባር ላይ የቆየው ፖለቲካዊ ስርዓት፤ ከቀድሞ ታሪክ ጥሩውን እያጣጣለ፥ መጥፎውን እያጋነነ፣ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ትላንትን ሲዖል፣ ዛሬን ገነት አስመስሎ እውነትን እንደ ምፅዓት ሩቅ አደረጋት። በእውን የኖርነውን በውሸት ሊያሳምነን ይጥራል፡፡ በተግባር የምናቀውን እውነት በቴሌቪዥን ይዋሸናል፡፡ በዚህ መሃል “#OBN እስኪ በተግባር የምታቀውን፣ ሰሞኑን የታዘብከውን ነገረን?” ሲለኝ መልሴ “እሺ” ነው፡፡

ባለፈው አመት በዚህ ሰዓት ጦላይ ነበርኩ፡፡ አምና ሃሳቤን በነፃነት ስለገለፅኩ አሰረኝ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ሃሳብህን በነፃነት ለOBN ስጠን ብሎ ጠየቀኝ፡፡ አምና ፀረ-ሰላም ነበርኩ፣ ዘንድሮ ሰላማዊ ሆንኩ፡፡ ይሄ ልዩነት ከየት መጣ? ከእኔ አይደለም! ከኦህዴድ ነው! አምና የፃፍኩት “የዜጎች መብት፥ ነፃነትና እኩልነት ይከበር!” እያልኩ ነበር፡፡  ዘንድሮ “OBN”  ላይ የተናገርኩት ስለ ዜጎች መብት፥ ነፃነትና እኩልነት ነው፡፡ የእኔ አቋም አንድ ነው፦ “ሁሉም ሰው እኩል መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ይገባዋል” የሚል ነው፡፡

እኔ የምናገረው ስለ ኢትዮጲያ ህዝብ መብትና ነፃነት እንጂ ስለ አንድ ብሔር ጥቅምና ተጠቃሚነት አይደለም፡፡ የህዝብ ደጋፊ እንጂ የአንድ ፓርቲ ወይም መንግስት አገልጋይ አይደለሁም፡፡ የህዝብን ጥያቄ ለተቀበለ ሁሉ ደጋፊ ነኝ፡፡ የህዝብን ጥያቄ ለገፋ ሁሉ ተቃዋሚ ነኝ፡፡ ህዝብን በሃይል ለማፈን የሚታትርን ደግሞ ውድቀቱ እንዲፋጠን ሃሳብ አዋጣለሁ፡፡ እኔ የምደግፈው አንድ ነው፦ እሱም የኢትዮጲያ ህዝብ ነው! ነገር ግን፣ በጎሳ ፖለቲካ እሳቤ ከአንዱ ጎጥ ስር ለተወሸቀ ሰው ይሄ አንዱን ብሔር ደግፎ ሌላውን “መጥላት” ነው፡፡ ጫን ሲል ደግሞ “የአንድ ፓርቲ አገልጋይነት ነው” ይለሃል፡፡ እኔ የማገለግለው ህዝብ እንጂ አንድ የፖለቲካ ቡድን አይደለም!

እንደ ሰው ለሚያስብ፣ ህዝብ ለሚያከብር ሰው ይህ ፖለቲካ ሳይሆን የሞራል ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህ ራሱን ከእንዲህ ያለ የአስተሳሰብ ባርነት ነፃ ሳያወጣ የእኔን የሃሳብ ነፃነት ከብሔርተኝነትና አገልጋይነት ጋር ለማያያዝ መሞከር ከጉድጓድ ውስጥ እንዳለችው አይጥ ራስን ማስገመት ነው!

Filed in: Amharic