>
4:34 pm - Wednesday October 16, 8165

ራይላ ኦዲንጋ፣ኡሁሩ ኬንያታ እና ሳፋሪኮም! (ቅዱስ መሃሉ)

በኡሁሩ ኬንያታ የሚመራው የኬንያ መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ አሸነፍኩ ያለው ምርጫ በድጋሚ የሕገመንግስት ፈተናን ማለፍ እንደማይችል ከወዲሁ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ የሕዝቡን ድምጽ ይዘው በድጋሚ ወደ ሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማምራታቸውን ተከትሎ የኡሁሩ ኬንያታ የፕሬዝዳንትነት ቃለ መሐላ ትርጉም አጥቷል። ራይላ ኦዲንጋ ፈተና የሆኑት ለኡሁሩ ኬንያታ ብቻ አይደለም። በኬንያ ተወዳዳሪ የሌለው እና በአፍሪካ ትልቅ ለሚባለው የቴሌኮም ካምፓኒም ትልቅ ፈተና ጋርጠውበታል። ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎቻቸው ሳፋሪ ኮምን ለቀው ሌላ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭዎችን እንዲጠቀሙ ባስተላለፉት መልክት መሰረት ራሳቸውን ጨምሮ ደጋፊዎቻቸው ሳፋሪ ኮምን እርቃኑን ሊያስቀሩት እንደሚችሉ ይገመታል። እንደ ኤርቴል ያሉ በአነስተኛ ዋጋ ለሕዝቡ አገልግሎት ለሚሰጡ የቴሌኮም ኩባንያዎች ደግሞ ሲሳይ/እርዝቅ እየዘነበላቸው ነው። በቅርቡ የዚህ ካምፓኒ ዳይሬክተር ከሳፋሪኮም ጋር መወዳደር ፈተና ሆኖብናል ብሎ የሰጠውን ቃለ መጠይቅ አስታውሳለሁ። ሳፋሪኮም በበኩሉ የኦዲንጋ ልብ ይራራልኛል ብሎ ይሁን የደምበኞቹን ሆድ ለማባባት ደምበኞቹ ሳፋሪኮምን ከለቀቁ “ከኛ ጋር በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ የሚሰሩ በሞባይል ባንኪንግ ኤጀንትነት ጭምር የሚያገለግሉ አንድ ሚሊዮን ያህል ኬንያዊያን ስራ አጥ ይሆናሉ” እያለ ነው። ሰምሚ ያገኘ ግን አይመስልም። ሳፋሪኮም መጠንቀቅ እና ገለልተኛ መሆን የነበረበት መጀመሪያ ነበር። ቢዝነስ እየሰሩ ፖለቲካ ውስጥ መፈትፈት ነጻነት ባለበት ሃገር ትልቅ ዋጋ ምናልባትም ቢዝነሱን ሙሉ ለሙሉ ማጣትን ጭምር ዋጋ ያስከፍላል። ይህ ግን የሚሰራው አማራጭ እና ተወዳዳሪ (የቴሌኮም) ኩባንያዎች ባሉበት ሃገር ነው።ኡሁሩ ኬንያታ እና ቤተሰቡ በኬንያ በሃብት አምስተኛ ሲሆን የኡሁሩ ኬንያታ እናት እና የሃገሪቱ መጀመሪያ ፕሬዝዳንት ሚስት ደግሞ በኬንያ በሃብት ደረጃቸው አራተኛ ናቸው። የኬንያ የመመጀሪያም ምክትል ፕሬዝዳንት ልጅ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ ደግሞ ኬንያ ካሏት ቱጃሮች ውስጥ በ6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የናጠጡ ሃብታም ናቸው።

እንግዲህ ከላይ እንደተረዳነው አንድ ሕዝብን የሚበድል የንግድ ድርጅት ለመቅጣት በገበያ ላይ ተወዳዳሪ እና አማራጭ ድርጅቶች መኖራቸው አስፈላጊ መሆኑን አይተናል። ልክ እንደ ኬንያዊያን ደምበኛ የሆንነው ድርጅት ከመንግስት ጎን ቆሞ ሲበድለን ለመቅጣት እንድንችል በሁሉም መስክ አማራጭ (የቴሌኮም) ኩባንያዎች ያስፈልጉናል። እንዲያውም ኦሕዴድና ብአዴን የእውነት ነጻ እየወጡ ከሆነ በሁለቱ ክልሎች ሁለት የቴሌኮም ኩባንያዎች በራሳቸው ካልሆነም ደግሞ የውጭ ቴሌኮም ኩባንያዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ወይም ማዕከላዊ መንግስቱ የውጭ ድርጅቶች ገብተው ኢንቨስት ማድረግ የሚያስችላቸውን የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲቀርጽ ጫና መፍጠር ይኖርባቸዋል። በክልላቸውም ኢትዮቴሌኮምም እንደማንኛውም ቢዝነስ ከነሱ ጋር እንዲወዳደር ቢያደርጉ የሚመሩትን ሕዝብ ከብዝበዛ ያድናሉ፤አማራጭ ሲያገኝ ሕዝቡም እስከዛሬ እውነተኛ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቅሞ እንደማያውቅ ይረዳል። በተጨማሪም እነዚህ ሁለት ቡድኖች የእውነትም ቢሆን እንኳ “ተለውጠናል ብለው” ሊያመጡት ከሚችሉት የፖለቲካ ነጻነት የበለጠ ሕዝቡ በርካታ ጥቅም እንዲያገኝ እና የስራ ዕድል እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ኬንያዊያን ከዓለም ጋር ለመተሳሰር ባደረጉት ጥረት በአሁኑ ሰዓት በቴክኖሎጅ እና ኢኖቬሽን መስክ ከምስራቅ አፍሪካ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሃገር እና የኢንቨስትመንት መዳራሻ መሆን አስችሏቸዋል። ኢትዮጵያ ደግሞ የቴሌኮም ኩባንያዋ ከዓለም የመጨረሻ ኋላ ቀሩ ሲሆን ዋና ስራውም ገንዘብ መበዝበዝ ብቻ እንደሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ ‘ጥገት ላማችን ነው’ ሲሉ በተዘዋዋሪ የተጠቃሚዎቹን ኪስ እንደሚያልቡ በአደባባይ በቴሌቪዥን ነግረውናል። በኢንተርኔት ቴክኖሎጅ፣ከሕዝብ ብዛት አንጻርም የተጠቃሚ አናሳነት እና በኢኖቬሽን መስክም ከዓለም ኋላ ቀሯ ከሶማሊያም ጭምር ኢትዮጵያ ናት። ምክንያቱም ሕዝብ ሲበደል፣ሲገደል እንዳይገናኝ እና ተደዋውሎ እንዳይገናኝ ኔትዎርክ የሚዘጋው እና ኢንተርኔት የሚያጠፋው እንዲሁም ዓለም የደረሰበትን ይቅርና ጎረቤቶቻችን የሚጠቀሙትን የቴሌኮም አገልግሎት እንኳ መስጠት የማይችለው ኢትዮቴሌኮም ያለተፎካካሪ በመንግስት እጅ ሆኖ ከዚህ የተሻለ ሊያደርግ አይችልም፤ሊሻሻልም አይችልም። ስለዚህ ኦሕዴድና ብአዴን ሌሎች ተወዳዳሪ ኩባንያዎች ወደ ክልላቸው ወይም ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የሚያስችላቸውን ፖሊሲ ማዕከላዊ መንግስቱ ላይ ጫና በማድረግ መፍጠር ይኖርባቸዋል።ይሄን የምለው የሰሞኑ የሁለቱ ቡድኖች ሁኔታ የእውነት ይሆናል ብየ በቀናነት መንገድ ስለተመለከትኩት ነው። ሁለቱ ፓርቲዎች ቢፈልጉም ሊያመጡት የማይችሉት ነገር እንዳለ ግን ይገባኛል። ሆኖም ግን እንደ አቅጣጫ በጠቆምኳቸው መንገድ ቢሄዱ ሕዝቡን በዘለቄታዊ መንገድ ለመጥቀም ያስችላቸዋል። ኢትዮጵያዊያንም በሌላ ሃገር የስራ ገበያ ላይ ተፈላጊ እና ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉበትን መንገድም ይጠርጉላቸዋል።

Filed in: Amharic