>

ኬንያ 132 ኢትዮጵያውያንን እስር ቤት ከተተች (BBN)

በኬንያ 132 ኢትዮጵያውያን ለእስር ተዳረጉ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ለእስር የተዳረጉት እንደተለመደው በህገ ወጥ መንግድ ድንበር አቋርጣችሁ ገብታችኋል በሚል ምክንያት ነው፡፡ ስደተኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በአንድ ቤት ውስጥ ተቀምጠው ሳለ ሲሆን፣ ባይያዙ ኖረ ወደ ታንዛንያ የማቅናት ዕቅድ ነበራቸው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ከሀገራቸው ተነስተው መንገድ የጀመሩት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማቅናት ሲሆን፣ ሆኖም ወደ ታንዛንያ ከማቅናታቸው በፊት ናይሮቢ ላይ በቁጥጥር ስር ለመዋል ተገድደዋል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ከሀገራቸው የተነሱት በደላሎች አማካይነት ሲሆን፣ ደላሎቹ እስከ ደቡብ አፍሪካ እንደሚያደርሷቸው ውል እንደነበራቸውም ታውቋል፡፡ ስደተኞቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላም፣ በድለላ ስራው ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ ሁለት ኬንያውያንም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ስደተኞቹ በቀጣይ ፍርድ ቤት ቀርበው ቅጣት ሊተላለፍባቸው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ቅጣቱ ወደ ገንዘብ ተቀይሮ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ሊደረግ እንደሚችልም ተገምቷል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች በሀገራቸው ያለውን የስራ አጥነት፣ የአገዛዙን አምባገነንነት እና መሰል ጉዳዮች ሸሽተው እንደሚሰደዱ ይታወቃል፡፡ ፊደል ያልቆጠረውን ጨምሮ እስከ ባለ ድግሪ ድረስ በስራ አጥነት የተነሳ ሀገር ጥሎ የሚሰደድባት ኢትዮጵያ፣ ለዜጎቿ አጅግ አስከፊ ሀገር እየሆነች መምጣቷን በሀገር ቤት ያሉ ዜጎች ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በሀገር ቤት ያለው ኑሮ ከአቅም በላይ ባይሆን ኖሮ፣ ሰው እንደ ቅጠል የሚረግፍበትን በረሃ እና ውቅያኖስ አቋርጦ ስደት የሚወጣ አይኖርም ነበር፡፡›› ይላሉ-በሀገር ቤት ኑሮ የተማረሩ አስተያየት ሰጪዎች፡፡ በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ በኑሮውም በፍትሐዊ አስተዳር በኩልም ያልተዋጣለት እና ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት የመጣ ስርዓት መሆኑን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ የአገዛዙ ዕድሜ ካላጠረ በቀር በቀጣይ ዛፍ እና ወንዙ ጭምር ሳይሰደድ አይቀርም እንኳን ሰዉ ይላሉ- አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡

Filed in: Amharic