>
6:57 am - Wednesday July 6, 2022

የሮማናቱ ሰለማዊ ሰልፍ (አምደጽዮን ገብረስላሴ)

ሰለማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ማሳወቅ ይጠብቅብን ነበር። ኣሳውቀናል። ሰልፉ እንዳናካሂድ ከተፈለገ ደብዳቤ ባስገባን በ12 ሰዓት ውስጥ ምላሽ መሰጠት ነበረበት።
የመቐለ ከንቲባ ኣቶ ዳንኤል ኣሰፋ (የደህንነቱ ሃላፊ ጌታቸው ኣሰፋ ታናሽ ወንድም) “ምን ያመጣሉ” ከሚል ትእቢት የሚነሳ ይሁን እንዝህላልነት ሰዓቱን
ኣሳለፉ። እኛም እውቅና እንደሰጡት ኣስበን (ህገመንግስቱ እንዲያ ስለሚል) ዝግጅታችን ቀጠልን።
እነሱ በፌስቡክ ተላላኪዎቻቸው በኩል ማህተም የሌለው ደብዳቤ በመለጠፍ ሰልፉን እንዳገዱት ኣስነገሩ።
እኛም ቢነገርም ባይነገርም፣ ደብዳቤ ቢደርሰንም ባይደርሰንም የሚቀየር ነገር እንደሌለና ሰልፉ ሕጋዊ እንደሆነ (ማርፈድ የሰነፍ ከንቲባ ምልክት ነው
ብለን lol) ገልፀን ስራችንን ቀጠልን።
በፌስቡክ ባስወሩት ትእዛዝ ተቀባይነት እንደሌለው ያወቁት ኣቶ ዳንኤል ኣሰፋ የትግራይ ቴሌቭዝንና ሬድዮ ጣብያዎች ጋዜጠኞች ጠርተው “ዓረና የጠራው ስልፍ ሕገ ወጥ ነው” የሚል መግለጫ ሰጡ።
እኛም “ሕገ መንግስት የሰጠን ሰለማዊ ሰልፍ የማካሄድ መብት ኣንድ የህወሓት ባለስልጣን መግለጫ በመስጠት ሊገድበው ኣይገባምም
ኣይችልምም” ከሚል ኣቋም ተነስተን በያዝነው መንገድ ቀጠልን።
፦ የኦሮምያ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ “በነቀምቴ በኣሰቃቂ ሁኔታ በግፍ የተገደሉ ዜጎች “ተጋሩ” ኣይደሉም ” የሚል ማስተባበያ እንዲሰጥ ተደረገ።
ለዚህ መግለጫም “እኛ ትግራዋይ ብቻ ተገደለ ብለን ኣይደለም ሰልፍ የጠራነው። የነቀምቴ ክስተት እንደ መነሻ በመጠቀም በሃገሪቱ እያጋጠሙ ያሉት ብሄር መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ነው እያወገዝን ያለነው” ብለን ቀጠልን።
(ብሄራቸው ስለተቀየሩ ሟቾች ተጋሩ መሆናቸው ተጨባጭ መረጃ በእጃችን ደርሶ ነበረ። ቄሱ ዓዲ ጉደም፣ ኣንድ መቐለ ኣቡነኣረጋዊ ቤተ ክርስትያን ሌላው ደግሞ ሓወዜን መሆናቸው ኣረጋግጠናል።)
ህወሓቶችም የኛ ኣቋምና የህዝቡ በሰልፉ ለመገኘት ያሳየው መነሳሳትና ጉጉት ክፉኛ ስላስደነገጣቸው ዓፈና ለማካሄድ ተግተው ሰሩ።
ህወሓት ስልፉ ለማክሸፍ ሶስት ስራዎች እየሰራ ነበረ።
ሀ) እኛን በማስፈራራትና ተፅእኖ በማድረግ ሰልፉ እንድናቋርጥ ማስገደድ
ለ) ሰልፉ የማይቀር ከሆነ ህዝቡ ቤቱ እንዲውል በውሸት ፕሮፖጋንዳ ማስፈራራት፣ ማሸበር
ሐ) ደፍረው ለሚወጡ ሰልፈኞችና ሰልፉን ማፈን የሚችል ግዙፍ የመከላከያ፣ የትግራይ ልዩ ሃይል፣ ፖሊስ፣ ሚልሻና ድህንነት ማሰማራት ናቸው።
የዓፋኙ ሃይል ሁኔታ
፦ መከላከያ ሰራዊት በእንዳየሱስ ቤተ ክርስትያን፣ ሰራዋትና መሳሕል(መሰቦ ኣጠገብ) በተጠንቀቅ ትእዛዝ እንዲጠባበቅ ተደርገዋል።
፦ የቀበሌ ሴቶችና ታማኝ የመንግስት ሰራተኛ ካድሬዎች ቤት ለቤት እየዞሩ ” ዓረና ከኦነግ፣ ሻዕብያና ጉንበት 7 በመሆን በመቐለ ዓመፅ ለማነሳሳት ሕገ
ወጥ ሰልፍ ጠርተዋል። ንብረት ሂወት ለማጥፋትና ለማውደም፣ ብጥብጥ ለማንሳት፣ ፈንጅ ለማፈንዳት ተዘጋጅተዋል፤ ራሳቹም እንዳትሄዱ፣ ልጆቻቹ
ከቤት እንዳይወጡ ጠብቁ ” ወዘተ የሚል ማስፈራርያና ትእዛዝ ኣስተላልፈዋል።
“ልጆቻቹ በሰልፉ ከተሳተፉ ከሶስት እስከ ኣምስት ኣመት ይፈረዳሉ፣ ሁመራ ተወስደው ይታሰራሉ” በማለት ሽብር ሲፈጥሩ ሰንብተዋል ።
፦ የመቐለ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በሰልፉ እንዳይገኙ “ክላስ ኣላቹ ማንም እንዳይቀር፣ ማንምኛውም ተማሪ ከግቢ እንዳይወጣ” የሚል ትእዛዝ ኣስተላልፈዋል። መውጫ በሮች በታጣቂዎች ታጥረው ውለዋል።
፦ የመንግስት ሰራተኞች የህወሓት ኣባላት ለብቻ፣ ኣባል ያልሆኑ ለብቻ ሰብስበው “ቅዳሜ ዓረና ከኦነግና ጉንበት 7 በመሆን በኦሮምያና ኣማራ ክልል እንደተነሳው ሽብር ለመፍጠርና ዓመፅ ለመቀስቀስ፣ ንብረት ለማውደም በመቐለ ሰልፍ ጠርተዋል። ልጆቻቹ ከቤት እንዳይወጡ፣ እናንተም በሰልፉ
እንዳትገኙ ተጠንቀቁ!” የሚል ዛቻ ኣስተላልፈዋል።
. በተለይ ኣባል ያልሆኑ ሰራተኞች “ስለተቀደማቹ ጨንቋቹ ነው። እናንተ መጥራት የነበረባቹ ሰልፍ ዓረና በመጥራቱ ሊመሰገን ይገባው እንደሆነ እንጂ
ሊኮነን ኣይገባውም ” የሚል ጠንካራ መልስ የሰጡ እንዳሉም ታወቀዋል።
፦ የኣንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ የግል ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች ሳይቀር ተማሪዎቻቸው ሰልፍ እስኪጨረስ ማንም ተማሪ ቅዳሜ ከቤቱ እንዳይወጣ ትእዛዝ እንዲያስተላልፉ ኣድርገዋል።
፦ በመቐለ ሁለቱ የኣውቶቡስ መናሃሪያዎች ግዝያዊ ኬላ በመክፈት ተጓዦች ተፈትሸው መታወቅያ የያዙ እስከ 6:00 ያልያዙ ወገኖች በዱላ እየተቀጠቀጡ
እስከ ከቀኑ 9:00 ታግተው ውለዋል ።
፦ የእንደርታ ወረዳ(መቐለ ዙርያ) ኑዋሪዎች በሰልፉ እንዳይገኙ ከፖሊስ፣ ምልሻ፣ ካቢኔ ኣመራሮች፣ ማህበራትና ካድሬዎች የተውጣጣ “መላሽ ግብረ
ሃይል” ኣቋቁመው መቐለ እንዳይሄድ ኣግደውት ውለዋል።
፦ ዓርብ ከቀኑ ስድስት ሰዓት እስከ ለሊት ታክሲዎችና ሌሎች መኪኖች መፈተሽ፣ በጎዳናው የሚንቀሳቀሱ ጎዳና ኣዳሪዎች ሲፈትሹ ነበር።
፦ በሰልፉ ይገኛሉ የተባሉ የከተማዋ ወጣቶች በተለይ የመቐለ ከነማ (ምዓም ኣምበሳ) ደጋፊዎችና የጎዳና ተዳዳሪዎች ዓርብ ምሽት በየፖሊስ ጣብያ ታስረው ኣደሩ።
፦ ለባጃጅና ታክሲ ኣሽከርካሪዎች ሰብስበው “በዓረና ሰልፍ ከተገኛቹ መንጃ ፍቃዳቹ እንቀማቹሃለን” ተብለዋል።
እነሱ ይህ ዝግጅት ሲያደርጉ እኛም ስራችን እየሰራን ነበር። በሰልፉ ይዘናቸው የምንወጣና በድምፅ ያምናሰማቸው መፎክሮቻንን ኣዘጋጅተን ነበር።
* ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ኣንድ ኣይደለንም !
* ኢህኣዴግ ኢትዮጵያውያንን መግደል ያቁም !
* በኦሮምያ በንፁሃን ዜጎች ወገኖቻችን እየተፈፀመ ያለው ኣሰቃቂ ግድያ እናወግዛለን !
* በሶማሌና ኦሮምያ ግጭት ምክንያት የጠፋው
ሂወትና ለተፈናቀሉ ወገኖች ምክንያት የሆኑ ኣካላት ለፍርድ ይቅረቡ።
* ብሄር ከብሄር ጋር ለማጋጨት የሚደረግ ሴራ ይቁም!
* የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ !
* ህወሓት/ኢህኣዴግ በፈፀመው ወንጀል የትግራይ ህዝብ ተጠያቂ ኣይደለም !
* ህውሓት/ኢህአዴግ ብዝፈፀሞ በደል ትግራዋይ ክቕፃዕ የብሉን !
* ኣብ ኦሮምያ ብዘይ ፍርዲ ዝተኣሰሩ ተጋሩ ብህፁፅ ይፈትሑ !
* ደም ንፁሃት ዜጋታት ደምና እዩ !
* ህወሓት ምበር ህዝቢ ትግራይ ኣይተጠቐመን!
* ልዕልነት ሕጊ ይከበር! ፋሉልነት ይቀበር !
* ሰብኣውን ዲሞክራሲያዊን መሰል ዜጋታት ይከበር!
* የኢትዮጵያ ህዝቦች ኣንድ ነን !
* ደም ንፁሃት ወገናትና ደምና እዩ !
* በብሄራችን ምክንያት ኣትግደሉን !
የሚሉ መፎክሮች ኣሰርተን ልንቀበለው ስንሄድ ኣሳታሚው ” 4 ድህንነቶች በኣካል መጥተው ስራህና ሂወትህን የማትፈልገው ከሆነ መፎክሮቹ ትሰጣቸዋለህ” ብለው ዝተውብኝ ሂደዋል። የሂወት ጉዳይ ነውና ትቸዋለው ሲል ሳይሰጠን ቀረ።
* ዳግም ፖስተሮቹ ሊፅፍልን የሚችል ሌላ ኣሳታሚ ኣግኝተን ተዋዋልን።
ሁሉንም ኣዘጋጅቶ እንደጨረሰ እንድንቀበለው ነግሮን ማታ 02:00 ስንሄድ ዓምዶም ገብረስላሴ፣ ገብረሚካኤል ተስፋይና ሰኣሊ ተወልደብርሃን ምሩፅ
በቢሮው እያለን የትግራይ፣ ልዩ ሃይል፣ ፖሊስ፣ ምሊሻ፣ ድህንነት፣ የሓድነት ካድሬዎች የተውጣጣ ኣፋኝ ግብረሃይል በመኪና ኣፍኖ ሓድነት ፖሊስ ጣብያ
ወሰደን።
በጣብያው ፖሊስና ድህንነት ህገ ወጥ ሰልፍ ከተካሄደ በሂወት እንደምንጠየቅ በየተራ ኣስፈራሩን።
ማታ 04:30 ኣከባቢ ክስ ተመስርቶብን ህግ ፊት እስክንቀርብ ቤታችን እንድንቆይ ነግረው ከጣብያው ኣስወጡን። ፖስተሮቹ ስጡን ስንላቸው ኣንሰጥም ብለው ከለከሉን።
ሰልፉ የግድ መካሄድ ስለነበረው በእጃችን የፃፍናቸው የተወሰኑ መፎክሮች ይዘን ለመውጣት ተገደናል።
ቅዳሜ ጥዋት በመቐለ ጎዳናዎች ፈሶ ያገኘነው የሰራዊት ዓይነትና ብዛት ለማመን የሚከብድና መቐለ በ26 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ቁጥር ያለው
የታጠቀ ሃይል ነበር።
ክልሎች ይህን ያህል የታጠቀ ሃይል ካዘጋጁ መከላከያ ሃይል ሃርድ ውስጥ መሆኑን ልንገነዘብ ችለናል። (ልዩ ሃይሉ ከሁሉም ዞኖች በኣስቸኳይ እንዲመጣ የተደረገ መሆኑ ኋላ ሰምተናል።)
፦ ቅዳሜ ጠዋትም ማንም ሰው በከተማ እንዳይንቀሳቀስ ታክሲና ባጃጅ ተከልክለው እስከ ከቀኑ 5 ሰዓት ታግተው ዋሉ ።
በመላው ትግራይ ያሉ ከተሞች ኑዋሪ ህዝብ ቅዳሜ ወደ መቐለ እንዳይሄድ ጥብቅ ትእዛዝና ቁጥጥር ሲደረግ ነበር።
በሽዎች የሚቆጠሩ የመቐለ ነዋሪዎች፣ የዩንቨርሲቲ ኣስተማሪዎች ፣ ተማሪዎች ፣ነጋዴዎች ወደ ሰልፍ ሜዳ ሮማናት ኣደባባይ ሲዘምቱም ፖለሶች፣
ድህንኖቶች፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወታደሮች በመላው ከተማ በየመኣዝኑ ዘግተው መንቀሳቀስ ሲከለክሉ ኣርፍደዋል።
ቅዳሜ
ታዳሚዎቻችን ከቤታቸው ደጃፍ የጀመረው “ወዴት ናቹ? ወደ ሰልፉ እንዳትሄዱ” የሚሉ ጥያቄዎችና ትእዛዞች በየኣምስት ሜትር ርቀት እያጋጠማቸው ሰልፉ ወደ ሚጀምርበት ኣደባባይ በእግራቸው ተጉዘው ደረሱ ።
መንጋ ፈደራል ፓሊስ፣ የትግራ ልዩ ሃይል፣ ፖሊሶች በክብ መልክ ኣዳባባይ እንዳይገቡ ከለከሏቸው።
የትግራይ ልዩ ሃይል የክልሉ ኮማንደር በማይክሮፎን “ሰልፉ ሕገ ወጥ ስለሆነ ወደየቤታቹ ተበተኑ” እያለ ኣወጀ። ህዝቡ ግን ሊበተን ኣልቻለም።
“እየተካሄደ ያለው ሰልፍ ሕገ ወጥ ነው። ስርዓት ለማስከበር በምንወስደው እርምጃ የሚጠፋ ሂወት ተጠያቂዎች ኣንሆንም። ለሂወታቹ ስትሉ ተበተኑ” እያሉ በማወጅና ሊገቡ ያሰቡትም ገፍተው ሲመልሱ ነበር።
በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች በኣደባባይ ዙሪያ በሚገኙ ህንጻዎች በመውጣት ሰልፉ ሲመለከቱ ነበር።
የዓረና ሰልፈኞች “ደም ንፁሃን ኣሕዋትና ደምና እዩ ! ህወሓትን ህዝቢ ትግራይን ዝተፈላለና ኢና ! የኢትዮጵያ ህዝቦች ኣንድ ነን ! በብሄራችን ምክንያት ኣትግደሉን ወዘተ የሚሉ መፎክሮች ኣሰምተናል።
በሰልፉ ለመሳተፍ የመጣውና በታጣቂዎች የተከለከለው ኣመስግነን ሰልፉ እንደጨረስን ስንሰናበት ቆሞ ይከታተለን የነበረው ህዝብ በጭብጨባና በፍጮት ገለፀልን።
ከሮማናት ልንንቀሳቀስ ስንል የትግራይ ቴሌቭዥን(ቶግ ቲቪ) ጋዜጠኛ ቃለመጠይቅ ላድርግልህ? ብሎ ጠየቀኝ። እኔም እሺ ግን በያዝኩት ድምፅ ማጉልያ ነው የምመልስልህ ብየው ተስማማን።
ብዙ ከጠየቀኝ በኋላ ሰልፉ ጥቂት ሰው ብቻ ነው የተሳተፈበት ምክንያት ምንድን ነው? ብሎ ጠየቀኝ።
እኔም “ክብ ሰርቶ እየተመለከተ ያለው ህዝብ ለመሰለፍ የመጣ ነው። እንደምትመለከተው ወታደር ከተሰለፍክ በህወትህ እንደፈረድክ ይቆጠራል፣ እንገድላለን እያለ እያስፈራራው ነው። እኝጂ የምታየው በሺዎች የሚቆጠር ህዝብ የኛ ታደሚ ነው። ብየ በመመለስ ለማረጋገጥ ወደ ሰልፋችን ለመሳተፍ ነው የመጣቺ ኣይደል?
ብየ ለህዝቡ ጠየቅሁ።
ህዝቡ በጭብጨባና ፍጮት ማረጋገጫ ሰጠን።
ዓረና ትግራይ ቅዳሜ 25/2/2010 ዓ/ም በመቐለ ሮማናት ኣደባባይ ያደረገው የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍ ከ26 ኣመት በኃላ የህወሓት የማይደፈር ምሽጉ መሰበሩ ትልቅ ድል ነው ።
ካሁን በኋላ ዓረና ትግራይ በመረጣቸው የትግራይ ከተሞች ህዝባዊ ሰለማዊ ሰልፍ በማደራጀት ህዝባችን ህገ መንግስታዊ መብቱ እንደሚያስከብር ያረጋግጣል።
ሰለማዊ ሰልፉ ሁለት ቁምነገሮች ኣሳይቶን ኣልፈዋል(ግቡን መተዋል)።
ሀ) ለ26 ዓመታት ህወሓት ዓፍኖ ይዞት የነበረው ሰልፍ የማካሄድ መብት መጠቀም መቻላችን(ፍርሃትን በመስበራችን)
ለ) ማስተላለፍ የፈለግነው መልእክት በተገቢው መልክ ማስተላለፍ መቻላችን ናቸው።
የሰልፍ ህጉ የማያውቁት(ማሳወቅ እንደሚጠብቅብን፣ በ12 ሰዓት ውስጥ ካልመለሱ እንደተፈቀደ እንደሚታሰብ፣ መፍቀድም ይሁን መከልከል እንደማይችሉ) የህወሓት ባለ ስልጣናት ተገቢው ግንዛቤ ጨብጠው እንደሚሆኑ ተስፋ እንደርጋለን።
በኦሮምያ የተለያዩ ኣከባቢዎች የሚገኙ ተጋሩ ኣሁንም ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን መረጃዎች እየደረሱን ነው። ኣሁንም የኦህዴድ ኣስተዳደር ቅቃቱ እንዲያስቁመው ጥሪያችን እናቀርባለን።
ድጋፋቹ ለሰጣቹን ሁሉ ምስጋናችን እናቀርባለን።
**** ነፃነታችን በእጃችን ነው

Filed in: Amharic