>

ጸሐፍያኖቻችንን፣ተንታኞቻችንን፣ ፖለቲከኞቻችንንና ስሉጣኖቻችንን ደጋግሞ እያሳሳታቸው ያለው ጉዳይ ምንድን ነው?

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ጥቂት የማይባሉ ጸሐፍያኖቻችን፣ ተንታኞቻችን፣ ፖለቲከኞቻችን (እምነተ አሥተዳደራውያኖቻችን) እና ስሉጣኖቻችን (አክቲቪስቶቻችን) ሕዝባዊ ዐመፁንና እምቢተኝነቱን ተከትሎ ወያኔ ሲጨንቀው ሁኔታውን ለመቆጣጠር በማሰብ ሕዝቡን “እንዲህ ሆነ እንዴ! ውጤቱ እንዴት ይሆን? ምን ይከተል ይሆን? ይሄን ተከትሎ ምን ይፈጠር ይሆን?” አሰኝቶ እንዲሁም “ወያኔ በራሱ ጊዜ መፈራረስ መናቆር ከጀመረማ ለምን በከንቱ መሥዋዕትነት እከፍላለሁ? አርፌ ውጤቱን አልጠብቅም እንዴ?” አሰኝቶ ሕዝቡ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በማስጣል በማስመሰል የፈጠራቸውን ችግሮች ውጤት እንዲጠብቅ በማድረግ አፍጥጦ ከመጣበት ሕዝባዊ ዐመፅ አደጋ ለማምለጥ በሚቆምራቸው ቁማሮችና በሚጫወታቸው ድራማዎች (ትውንተ ኩነቶች) በተደጋጋሚ መሳሳታቸው መሸወዳቸው እጅግ እየገረመኝ ነው፡፡ እነኝህ ወገኖቻችን ለዚህ የተሳሳተ ድምዳሜ የሚዳረጉት በሦስት ምክንያቶች እንደሆነ አምናለሁ፦
1. የአቅም ማነስ
2. የምኞት ተጽዕኖ
3. ክህደት ወይም ቅጥረኝነት ናቸው፡፡
የአቅም ማነስ፦ ይሄ ችግር ያለባቸውን ወገኖች አቅማቸው እንዲጎለብትልን ከመመኘት በቀር ምንም ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ትንሽ ብቻ ቅር የሚለው ነገር እራሳቸውን እንደ ከባድ ፖለቲከኛ፣ ጸሐፊ፣ ተንታኝና ስሉጥ የሚቆጥሩ ሆነው ሳለ የቱንም ያህል ለፖለቲካው ቅርብ የነበሩና የሆኑ ቢሆንም ግን ያላቸው የመረዳት፣ የማሰላሰል፣ የአስተውሎት አቅም (perception) ደካማ በመሆኑ እውነታውን መረዳት፣ እውነታው ላይ መድረስ የማይችሉ መሆናቸውንና ይሄንንም የአቅም ደካማነታቸውን አለማወቃቸው ነው ትንሽ ገረም የሚለው፡፡

በምኞት ተጽዕኖ፦ በዚህ ምክንያት ለተሳሳተ ድምዳሜ እየተዳረጉ ያሉ ወገኖቻችንንም ሊከሰት የሚችልና የሚጠበቅ በመሆኑ “ለምን እንዲህ ትሆናላቹህ?” ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ምክር ግን ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ፈጣሪን አማኝነት (አምላኪነት አላልኩም) ሰብእና የሚጎላባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ይሁንና ከፈጣሪ ጋር ያላቸው የግንኙነት መስመር ግን የተሳሳተ ነው፡፡ ከእነኝህ ሰዎች ውስጥ ከፊሎቹ በፈጣሪ መኖር የማያምኑ እንደሆኑ አድርገው የሚያወሩም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ውስጣቸው ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ሰብእናቸው በእጅጉ ሲበዛ በፈጣሪ ወይም በተአምር ላይ ጥገኛ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት ሰዎች ብዙ ጊዜ ሊያስተካክሉት የሚገባቸው ነገር ግን ከአቅም በላይ የሆነ ፈተና ወይም ችግር ሲያጋጥማቸው በቁማቸውም ሆነ በመኝታቸው ከገጠማቸው ችግር ለመውጣት “እንዲህ ቢሆንልኝ ወይም ቢሆንልን!” ብለው የሚመኙትን መልካም ምኞት በማሰብና በመመኘት ነው ዘወትር ጭንቅላታቸው የሚባዝነው፡፡ ታዲያ በአጋጣሚ ያንን ምኞታቸውን ሊያሳካ የሚችል የሚመስል አንዳች ነገር ባጋጠማቸው ጊዜ ስለ ትክክለኛነቱ ስለ እውነተኛነቱ ልመርምር ልጠራጠር ሳይሉ እውነት እንደሆነ ፈጥነው ያምናሉ ይቀበላሉ፡፡ ተቀብለውም ይፈነጥዛሉ፡፡

የሚገርመው ሐሰት ወይም ማጭበርበር እንደሆነ ካወቁና ዋጋ ከከፈሉበትም በኋላ በሌላ ጊዜ ከቀደመው ስሕተታቸው የሚማሩ አለመሆናቸውና ተመሳሳይ ስሕተት በተደጋጋሚ የሚፈጽሙ መሆናቸው ነው፡፡ ለነኝህ ሰዎች ምኞታቸውን የሚያሳካ መስሎ የታያቸውን ነገር “ሌላ ገጽታ፣ ተልእኮ፣ ዓላማ ሊኖረው ይችል ይሆን?” ብሎ መጠራጠር ፈጣሪን እንደማሳዘን ወይም እንደመቃወም መስሎ ነው የሚሰማቸው፡፡ የሰብእና ጉዳይ ነውና ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ማድረግ የምንችለው ነገር ቢኖር እንዲህ ዓይነት ሰብእና ያላቸው ግለሰቦች በተሳሳተ ድምዳሜያቸው ሌላውንም አሳስተው ለችግር ስለሚዳርጉ እንዲህ ዓይነት ችግር ከመፍጠራቸው በፊት እየለየን በእነሱ ላይ ጆሮን መቆለፍ ብቻ ነው መፍትሔውና ከእኛ የሚጠበቀው ነገር፡፡

ክህደት ወይም ቅጥረኝነት፦ በዚህ ወቅት ይሄ ችግር ያለባቸውን ግለሰቦችንና ቡድኖችን በይፋ እያስተዋልን ነው፡፡ ወቅታዊ ሁኔታውም ይህ ይሆን ዘንድ ግድ የሚል በመሆኑ ነው፡፡ እነኝህ ግለሰቦች አስቀድሞ በተቃዋሚነታቸው በተችነታቸው የሚታወቁ የነበሩና አሁን አሁን ላይ ግን ወያኔ በጥቅም እየለወጣቸው ያሉ ናቸው፡፡ ስለዚህም ከሀዲዎች ናቸው፡፡ የተቃዋሚነት ገጽታቸውን ሳይቀይሩ አስቀድሞ የነበራቸውን የሕዝብ አመኔታ በመጠቀም አሁንም ተቃዋሚ መስለው ሕዝብን ወያኔ በሚፈለገው አቅጣጫ ለመንዳት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነኚህ ውስጥ በግል የተደለለ አለ በቡድን የተደለሉም አሉ፡፡ በግል የተደለሉትን ለጊዜው እንተዋቸውና በቡድን ወደተደለሉት ሳመራ የእነ ጃዋር መሐመድን ቡድን እናገኛለን፡፡ ወያኔ በኦሕዴድ በኩል እነ ጃዋርን ማርኮ በእጁ አስገብቷል፡፡

“ምን ብሎ? ምን ቃል ገብቶላቸው? ለምን?” የሚለውን ጉዳይ ግን አሁን በዚህ ሰዓት እንቅጩን ለመናገር ያለው ዕድል ጠባብ ይመስለኛል፡፡ ይሁንና ፍላጎታቸው አስቀድሞ ይታወቃልና የትኛው ፍላጎታቸው ሊፈጸምላቸው እንደተስማሙ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ቀድሞ ከነበረው ፍላጎታቸው ከፊሉ ወይም ሙሉ ለሙሉ ሊፈጸምላቸው እንደተስማሙ ግን መገመቱ ቀላል ነው፡፡

ይህ የተስማሙበት እስኪፈጸምላቸው ድረስ ግን ለወያኔ ሥልጣን ሥጋትና አደጋ የሆነው ሕዝባዊ ዐመፅና እምቢተኝነት ተወግዶ ሁኔታዎች ወደነበሩበት መመለስ አለባቸው በመባሉ “ሀገርን በማረጋጋቱ ሥራ ላይ ተባበሩ!” ተብለው አስቀድሞ ከነበራቸው “ኦሮሚያ ለኦሮሞ ብቻ! ፣ ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም፣ እንገነጠላለን …” ከሚሉ ጽንፈኛ አቋም አስተሳሰቦቻቸው የሚቃረኑና የማይስማሙ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ አቋም አስተሳሰቦችን እያንጸባረቁ ይገኛሉ፡፡ ሁኔታዎች ወደነበሩበት ተመልሰው የወያኔ እና የነጃዋር ጥምረት እዚህ ሀገር ውስጥም እውን ከሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ደግሞ ለአማራ ሕዝብ አደገኛና ከእስከ አሁኑም የከፋ ሁኔታን የሚፈጥር ለመሆኑ የሚጠራጠርና የማይረዳ ካለ የዋህ መሆኑን ይወቅ፡፡

እነኝህ በሦስት የተከፈሉት ፖለቲከኞቻችን፣ ጸሐፍያኖቻችን፣ ተንታኞቻችንና ስሉጣኖቻችን (አክቲቪስቶቻችን) ሕዝባዊ ዐመፁንና እምቢተኝነቱን ተከትሎ ወያኔ ሁኔታውን ለመቆጣጠር የሚያደርጋቸው ነገሮች የማስመሰያ ድራማ (ትውንተ ኩነት) እና ሸፍጥ ያዘሉ ድርጊቶች፣ ቁማሮች እንደሆኑ ሲነገራቸው አንድ በተደጋጋሚ የሚሉት ነገር አላቸው “ወያኔን ይሄንን ያህል የተወሳሰበ ሸፍጥ ሴራ መቀመር የሚችልና ጠንካራ ኃይል አድርጎ ማሰብ ከራስ ደካማነትና ተስፋ ቆራጭነት የሚመነጭ የተሳሳተ አመለካከት ነው! ፣ ጨለምተኝነት ነው!” በማለት ጠርጣሮችንና ነቄዎችን ለማሸማቀቅ ጥረት ሲያደርጉና ወያኔ በዚህ ጉዳይ ጠንካራ እንዳልሆነ እንድናስብ በማድረግ መውሰድ ያለብንን ጥንቃቄና የዝግጅት እርምጃ እንዳንወስድ ለማድረግ ሲጥሩ ይስተዋላሉ፡፡

እነኝህን ወገኖች ልጠይቃቸው የምፈልገው ቁልፍ ጥያቄ አለኝ፡፡ ታዲያ ወያኔ የምትሉትን ያህል ደካማ ከሆነ ከአናሳ ጎሳ የመጣ አናሳ ቡድን ሆኖ እያለ፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ከመጀመሪያው ጀምሮ በሰብአዊ መብት ገፈፋውና ኢሰብአዊ ግፎቹ በዝርፊያዎቹ የሚታወቅ ተኮናኝ፣ ተወጋዥ የወንበዴ ቡድን ሆኖ እያለ፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ በኢትዮጵያ ሕዝብ የተጠላ፣ የማይፈልግ፣ የማይወደድ እንደባዕድ የሚቆጠር ሆኖ እያለ እንዴት ሆኖ ነው ታዲያ 27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደገል ቀጥቅጦ እንደሰም አቅልጦ ሊገዛ የቻለው የሚመስላቹህ??? የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ እንደመርገም ጨርቅ ከሚጠላውና በወራዳነቱ ከሚንቀው አገዛዝ ለመላቀቅ የተቻለውን ያህል ሳይጥር፣ ዋጋም ሳይከፍል ቀርቶ ነው ወይ??? በፍጹም!!! መልሱ ወያኔ ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ቁማርተኛ፣ ክፋተኛ፣ ተንኮለኛ በመሆኑ ነው፡፡

* ወያኔ ሸፍጠኛ ሴረኛ ስለሆነ አይደለም ወይ መልካም ስም የሌለው ሆኖ እያለ የሰብአዊ መብቶችና የዲሞክራሲ (የመስፍነ ሕዝብ) ጠበቃና ጠባቂ ነን ብለው የሚመጻደቁትን ምዕራባውያን መንግሥታትን ምን እንደሚፈልጉ አጥንቶ ጥቅማቸውን ስለጠበቀላቸው ለቃላቸው ታማኝ እንዳይሆኑና በዚህ አሳፋሪ ተግባራቸው ሳያፍሩ እንዲደግፉት ከጎኑ እንዲቆሙ ያደረጋቸው???

* ወያኔ አጋንንትን የሚያስንቅ የተዋጣለት ሸፍጠኛና ሴረኛ ቡድን ስለሆነ አይደለም ወይ የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘር በሃይማኖት ከፋፍሎ እያናቆረ አንድ እንዳንሆን እንዳንስማማ እርስ በእርስ እንዲፈራራ አድርጎ ከፋፍሎ እንደመጠላቱ ቶሎ ሳይወገድ የአገዛዝ ዕድሜውን ለማራዘም የቻለው???

* ወያኔ ቁጥር አንድ ሴረኛና ሸፍጠኛ ስላልሆነ ነው ወይ ሹመኛና አባሎቹ በሙሉ እንዳይሸሹትና በነጻ ሕሊናቸው እንዳያስቡ፣ አቤት ወዴት እያሉ ሳይወዱ በግድ እንደባሪያ ተገጥበው፣ እራሳቸውን አዋርደው እንዲገዙለት ለማድረግ በሙስና እንዲጠለፉ አድርጎ፣ ካለባቸው ወንጀል ከተጠያቂነት ነጻ አድርጎ እነኝህን ሁለት ችግሮቻቸውን በማስፈራሪያነት በመያዝ የዘለዓለም ባሪያው አድርጎ ሰብእናቸውን፣ ሕሊናቸውንና አምላካቸውን አስጥሎ በነፍሳቸው የሚጫወትባቸው???

* ወያኔ ዋና ሸፍጠኛና ሴረኛ ስላልሆነ ነው ወይ ኢሕአዴግ የሚባል አሻንጉሊት የፖለቲካ ፓርቲ (የእምነተ አሥተዳደር ቡድን) መሥርቶ በውስጡም የየብሔረሰቦችን ተወላጆች ካላካተተና እነሱን ካልተመረኮዘ በስተቀር በአናሳነቱ ኢትዮጵያን የመግዛት አቅምና ዕድል ፈጽሞ ሊኖረው እንደማይችል ተረድቶ ከየብሔረሰቡ መልምሎ የመለመላቸውንም ከገዛ ወገናቸውና ከሕሊናቸውም አቆራርጦ ለራሱ ብቻ ፍጹም ታማኞች እንዲሆኑ አድርጎ በአሻንጉሊት ድርጅቶች አደራጅቶ በማቀፍ ከአናሳነቱ የተነሣ ሊገጥመው የሚችለውን ሁሉን አቀፍ የአቅም ውስንነት ቀርፎ ሰፊውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በመቆጣጠር ጨቁኖ እየገዛ ያለው???

* ወያኔ እርኩስ፣ ክፋተኛ፣ ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ ባይሆን ነው ወይ እሱና ሸአቢያ ከሱዳንና መሰል ሀገሮች ያገኙ የነበረውን ተገን፣ የስንቅና ትጥቅ አቅርቦት… የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢያገኝ ለአንድ ወር እንኳ የመግዛት ዕድል እንደማይኖረው በመረዳት ጎረቤት ሀገራትን መሬት በመስጠት፣ በጥቅም በመያዝ የኢትዮጵያን ሕዝብ መሸሻ መሸፈቻ አሳጥቶ፣ አማራጭ አሳጥቶና አፍኖ የግዱን እንዲገዛለት ማድረግ የቻለው???

* ወያኔ እናንተ እንደምትሉት ቂልና ደካማ ስለሆነ፣ ሸፍጠኛና ሴረኛ ስላልሆነ ነው ወይ ሕዝቡ ሲበቃው በጣጠሰው እንጅ ስለችግሮቹ እንዳይመክር፣ መላ እንዳይመታ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት አፍኖት የቆየው???

* ወያኔ ደሙን እያፈሰሰ አጥንቱን እየከሰከሰ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመጠበቅ የጋለ ፍቅርና ፍላጎት ስላለው ነው ወይ የመከላከያና የደኅንነት ኃይሉን የኃላፊነት ቦታዎች በሙሉ በትግሬ ቁጥጥር ስር አድርጎ ከነዚህ ክፍሎች ሊመጣ ከሚችል ሥጋት እራሱን ነጻ አድርጎ እያስጨፈጨፈ ወደን ሳይሆን ተገደን እንድንገዛለት ያደረገን???

* ወያኔ ክፉ ሸፍጠኛና ሴረኛ ሳይሆን ደካማ፣ ቅን፣ ለሕዝብና ለሀገር አሳቢ ሆኖ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ ሕዝቧንም ለመጥቀም ስላሰበ ነው ወይ የፓርቲ የንግድ ድርጅቶችን አቋቁሞ የሀገሪቱ ሀብት እየዘረፈ ወገኖቹንና ትግራይን እየገነባ ያለው???

* ወያኔ ደካማ ቂል የዋህ ስለሆነ ነው ወይ ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ የመሬት ፖሊሲውን (መመሪያውን) ወዘተረፈ ሀገርንና ሕዝቧን ሳይሆን እራሱን ብቻ ሊጠቅም በሚችል ሕዝቡን ግን አቅም ሊያሳጣ፣ ሊያዳክም እንዲችል አድርጎ የደነገገው???

* ወያኔ ቅን የዋህ ደካማ ስለሆነ ሸፍጠኛ ሴረኛ ስላልሆነ ነው ወይ በዚህች ሀገር ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሲቪክ (ሕዝባዊ) ማኅበራት እንዳይወጡ በርካታ እንቅፋት፣ መሰናክል፣ ማነቆ መንገድ ላይ ገጥግጦ እንዳይወጡ ያደረገው?፣ መሀላቸው ላይ ካድሬዎቹን (ወስዋሾቹን) አስርጎ በማስገባት የሚያፈርስ የሚበታትናቸው???

* ወያኔ እርጉም፣ ሰይጣን፣ አረመኔ ሸፍጠኛና ሴረኛ ስለሆነ አይደለም ወይ ጠላቱ ያደረገውን የአማራን ሕዝብ ከአጋሮቹ ጋር ሆኖ በሚታይና በማይታይ ጭካኔ የተሞላባቸው የጥቃት ዓይነቶች እየፈጀን ያለው???

* ወያኔ ክፉ ጨካኝ አረመኔ እርኩስ ሸፍጠኛና ሴረኛ ስላልሆነ ነው ወይ ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ለደርግ የጦር አለቆች በሚስትነትና በወሲብ ባሪያነት አስርገው አስገብተው በመሰለል፣ የደርግ ጄኔራሎችንና (ራሶችን) የጦር አለቆችን በዶላር በመግዛት የደርግን ሠራዊት ሽባ ያየረገው፣ ሀውዜንን አስደብድቦ ደርግን በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ በማሳጣትና በማስወገዝ የፖለቲካ ኪሳራ እንዲደርስበት ለራሱም ሰፊ ድጋፍ ለማግኘት እንዲችል ያደረገው???

* ወያኔ ሴረኛ ሸፍጠኛ ስላልሆነ ነው ወይ በደርግ ውድቀት መቃረቢያ ላይ እነ አቶ መለስ ከደርጎች ጋር ሮም ለድርድር በተቀመጡበት ሰዓት የሔሊኮፕተር (የደውደዊት) ድምፅ ሲሰሙ እነ አቶ መለስ ተደናግጠው የተደነባበሩ በመምሰል በጠረጴዛ ስር የተወሸቁትና “ምን ሆናቹህ ነው?” ተብለው ሲጠየቁ “በረሃ ላይ በየዕለቱ እየመጡ የሚጨፈጭፉን ሔሊኮፕተሮች (ደውደዊቶች) ታውሰውን ነው በጣም ይቅርታ እንጠይቃለን!” ብለው ምዕራባውያኑን አደራዳሪዎች በማጃጃልና አንጀት በመብላት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማግኘት የቻሉት???

* ወያኔ ሴረኛ፣ ሸፍጠኛ፣ አጭበርባሪ፣ ይሉኝታ ቢስ፣ ቀሳጢ ባይሆን ነው ወይ ሱዳን በማዳበሪያ ከረጢት አሸዋ እየሞላ ሜዳ ላይ ከደረደረ በኋላ “ይሄው በረሀብ ለተጎዳው የትግራይ ሕዝብ የእርዳታ እህል ገዝተን እንድናሳያቹህ ባዘዛቹህን መሠረት በሰጣቹህን ገንዘብ ከሱዳን ገበያ ገዝተን የከማቸነው እህል ይሄ ነው በአስቸኳይም ለሕዝባችን እናደርሳለን!” በማለት ገንዘቡን ለወያኔ ስንቅና ትጥቅ መሸመቻ ያዋሉት??? የወያኔ ሸፍጥ፣ ሴራ፣ ተንኮል፣ ቁማር፣ ክፋት፣ ተንኮል ተቆጥሮ የሚዘለቅ አይደለምና ወዘተረፈ. ብየ እንድዘጋው ፍቀዱልኝ?

ልብ እንድትሉልኝ የምፈልገው ጉዳይ ግን ወያኔ ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ቀሳጢ፣ ተንኮለኛ፣ ክፋተኛ፣ ወንበዴ ነው ማለት ብልህ ነው፣ አስተዋይ ነው፣ ሀገርን ለማሥተዳደር፣ ሕዝብ ለመምራት የሚያስችል ብቃት፣ ችሎታ፣ አቅምና ጥንካሬ ያለው ቡድን ነው ማለቴ አለመሆኑን ነው፡፡

ወያኔ በዓለም ተስተካካይ የሌለው የደናቁርት ቡድን፣ የጥፋት ኃይል መሆኑን ማረጋገጥ ከፈለጋቹህ ወያኔ በትግሬ ሕዝብ ስም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እጅግ ዘግናኝና ይቅር የማይባል ግፍ ሰቆቃ ዝርፊያ እየፈጸመ “ሕዝቤ ነው እወደዋለሁ እሞትለታለሁ!” የሚለውን የገዛ ወገኑን በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ እንዲጠላና ወያኔ በወደቀ ጊዜም የበቀል እርምጃ እንዲወሰድበት አድርጎ ማመቻቸቱን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ መልካም ሊሠራለት እንደሚችል አሳምኖ ሳይሆን አስገድዶ በዘር በሃይማኖት ከፋፍሎ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር አድርጎ ለሀገርም ለሕዝቧም በማይጠቅም አኳኋን መግዛቱን፣ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” በሚለው መሠረታዊ መመሪያው የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም አሳልፎ መስጠቱን ማሰቡ ብቻ ከበቂ በላይ ነው፡፡

እናም ወያኔ ማለት ይሄንን ነው፡፡ እኔ እንዲያውም ወያኔን በሸረኝነት፣ በሸፍጠኝነት፣ በሴረኝነት በዓለም ላይ የሚስተካከለው ያለ አይመስለኝም፡፡ ወያኔን ሆን ብለው ደካማ እንደሆነ እንድናስብ የሚፈልጉት ከላይ በሦስተኛ ላይ የተጠቀሱት ወገኖች እንዲህ የሚሉት እውነቱ ጠፍቷቸው ሳይሆን ሕዝቡ ተዘናግቶ የተቀጠሩበት ዓላማ እንዲሳካላቸው ለማድረግ ከመፈለግ ስለሆነ አሁን ባልኩት ነገር ሁሉ የምገልጥላቸው እውነት የሚኖር አይመስለኝም፡፡

የተቀረኸው ሕዝብ ግን ወያኔ እነኝህ ወገኖች እንዳሉት ደካማ ሳይሆን የመጨረሻ ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ የአጋንንት ቡድን እንደሆነ አውቀህ ለፀረ ወያኔ ትግሉ ምን ያህል በልጠህ ራስህን በማዘጋጀት ወያኔን ድል ለመምታት እንድትታገል ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ትግሉ የግድ መደረግ ያለበትና አማራጭ የሌለው የህልውና ትግል ስለሆነ የግድ ታደርገዋለህ፡፡ የጠላትን አቅም በስሕተት አሳንሶ ገምቶ ለፍልሚያ መውጣት ለታላቅ ሽንፈት ይዳርጋል፡፡ የወያኔን አቅም አሳንሰን እንድንመለከት የሚፈልጉት ቅጥረኞች የሚፈልጉት ይሄንን ነው፡፡ ስለሆነም እንጠንቀቅ!!

ወያኔ የተንኮል፣ የክፋት፣ የሸፍጠኛ፣ የሴረኛ ብቃቱ ቁጥር አንድ ነው፣ የሚስተካከለው የለም፣ ሰይጣን ነው ማለት ወያኔን ማቄል፣ ማጃጃል፣ ማሸነፍ አይቻልም ማለት አይደለም፡፡ ሰይጣን የቱንም ያህል ቢበረታ፣ ሸፍጠኛ፣ ክፋተኛ፣ ሴረኛ ቢሆን ይሄ ሁሉ አቅሙ በመላእክት ፊት ሲቆም ባዶ ነው ከምንም አያድነውም፡፡ በመሆኑም ወያኔ እንደሰይጣን ቢሆንም ያለውን የሸፍጠኝነት፣ የሴረኝነት፣ የክፋት፣ የተንኮል ብቃቱን በማክሸፍ መቅጣት፣ ማዋረድ፣ ማሸነፍ ካስፈለገ እንደመላእክት ብርቱ፣ ጽኑ፣ ኃይለኛ፣ ለሰይጣን ክፉ በመሆን ማሸነፍ ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ነንና እንችላለንም!!! ወያኔ እንደ ሰይጣን ክፉ፣ ሴረኛ፣ ሸፍጠኛ፣ ኃይለኛ መሆን እንደቻለ ሁሉ እኛም እንደመላእክት ጽኑ፣ ብርቱ፣ ኃይለኛና ለሰይጣንም ክፉ መሆን እንችላለን!!!

ከመቋጨቴ በፊት ጥብቅ ማሳሰቢያ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፦ እባካቹህ በተለይ ነጻ የብዙኃን መገናኛዎች ኢሳትን ጨምሮ ወያኔ ሆን ብሎ እንዲስተጋባለት በማሰብ የሚፈጥራቸውን አዘናጊ የፖለቲካ ድራማዎችንና ቁማሮችን፣ አፈትልከው የወጡ ምሥጢሮች አስመስሎ የሚያቀብለንን ወሬዎች መልሰን ማስተጋባታችን ለሸፍጠኛ ዓላማው አጋዥና ተባባሪ እያደረገን፣ ዘወትር ወሬዎቹን በማውራት እኛን ቢዚ (ባተሌ) በማድረግ መሥራት ያለብንን እንዳንሠራ፣ ማተኮር ባለብን ጉዳይ ላይ እንዳናተኩር አድርጎ እየተጫወተብን ስለሆነ እባካቹህ ከዚህ ታቅበን ሕዝባችን አትኩሮቱ ሳይሰረቅ፣ ጊዜውን በወሬ ሳያባክንና ሳይዘናጋ ትግሉ ላይ ብቻ እንዲያተኩር በሚያስችል ሥራ ላይ ሕዝባዊ ትግሉ ስኬታማ ሊሆን የሚችልበትን ስልት መንደፉ ላይ፣ ሕዝቡን ማንቃቱ ላይ፣ ሕዝቡን ማደራጀቱ ላይ፣ ሕዝቡን ማታገሉ ላይ እንድናተኩር አበክሬ አጥብቄ ማሳሰብ እወዳለሁ! አመሰግናለሁ!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

Filed in: Amharic