>
4:59 pm - Wednesday July 6, 2022

የኢትዮጵያ ፈተና— የኦሮሞ ጥያቄ ወይስ የህወሓት እብሪት? (ሰለሞን ስዩም)

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መመስረቷ ካልሆነ በብሔር ግንባታ እጅግ ብዙ ይቀራታል፡፡ እንደ ሀገር ህልው ሆና ለመቀጠል በሀገሪቱ የወደፊት ስዕል ላይ ያለው መሠረታዊ የኃይላት ቅራኔ መፈታት አለበት፡፡

ገዥው ቡድን ከመጀመሪያው ጀምሮ መሰረታዊ የታሪክ ተቃርኖዎችን ለመፍታት ፍላጎት አሳይቷል፤ የሚገርመው ግን ዛሬም ቢሆን በተግባር መሬት ላይ ያሉትን ተፃራሪ ፍላጎቶች እንጂ ነገ በተመሳሳይ ደረጃ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ቅምጥ መልስ ፈላጊ ተቃርኖዎችን አስተውሎ አሁን ካሉት ጋር አዳብሎ ለመፍታት አይሞክርም፡፡ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትም እስኪገደድ እየጠበቀ ነው፤ እኛም ተቺዎች ስለዛሬው እንጂ ነገ ሲለሚፈነዱት ቅምጥ ፍላጎቶች የሚጨንቀን አይመስልም፡፡

ሰለሞን ዴሬሳ ከብዙ አመታት በኋላ በ1991 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፤ ስለኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ተጠየቀ፣ እንዲህ አለ “ስለዚህ ጉዳይ ከውጭ መጥቼ …ኤክስፐርት መሆን አልፈልግም፤ ግን ካየሁትና ከምሰማው አንድ የሚታየኝ ትግሪኛ የሚናገሩ፣ አማርኛ የሚናገሩና ኦሮሚኛ የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን እዚህ ያሉት እነሱ ብቻ ሆነው እንደሚናገሩ ይመስላል፤ በርካታ ቁጥራቸው ትንሽ የሆኑ ህዝቦች መኖራቸውን የረሳነውና ውይይቱ በኛ መካከል ብቻ የሚካሄድ ይመስላል፤ እኔ ይኼ ጥጋብ ይመስለኛል፤ ምክንያቱም በቁጥር ብዛት እውነት አይቆምም፤ እውነቱ ደግሞ ቀላል ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦች አሉ፡፡”

ዛሬ ዛሬ ስለ የባህል ቡድን (ብሄር/ብሄረሰብ) ስትከራከር “ማን ወከለህ?” ትባላለህ፤ ለመሆኑ ስለ ግለሰብ ስታወራ ስለግለሰቦች መሆኑ ይቀራል? ታዲያ አንተንስ ማን ወከለህ? ማለት ይቻላል፤ ቁምነገሩ ስለፍትህ መቆም ይመስለኛል፡፡ ማንም ቢሆን እንደ ግለሰብም እንደቡድንም ከማንነቱ የተነሳ ግፍ መቀበል የለበትም፤

በኢትዮጵያ፣ እንኳን በሰፊው ድንበር ውስጥ ይቅርና፣ ምትሮፖሊታን የምንላት አዲስ አበባም፣ ዛሬም ፍራሽ አንጥፈው ሳምንት የሚያዝኑና የሚያስተዛዝኑ ህዝቦች ያሉባት ናት፤ አንድን ሟች ለመቅበር ብዙ መኪና ህዝብ ደብረሊባኖስ ይውላል፡፡ ባህላዊ ቡድናዊነትማ ዋነኛ ተፈጥሮዋ ነው፡፡ ስሙ የተረሳኝ አንድ የፖለቲካ ሳይንትስት ለቁጥር የሚያታክቱ ሊማዳዊ መስተጋብሮችን በማስተዋሉ “በየትኛውም ረገድ አለም ግለሰባውነትን አትቀዳጅም” ብሏል፡፡

እንኳን አንድ ትግሬ ቀርቶ፣ በአማራ-ትግሬ-ኦሮሞ መካከል ስምምነት ብሰፍን፣ ከቁብ ባልቆጠርናቸው ሌሎች ብዙ ቡድኖች ገና ተቃርኖ ይቀርብባታል፡፡ ከአዋሳ የማያልፈው የደቡብ ፖለቲካ (ማንም በሚያውቀው ኃ/ማርያምን ትቻለሁ)፣ የሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ… ተቃርኖዎች አሁን ከምናነሳቸው ጋር እግረ መንገድ ካልተፈቱ የዳግም ብያኔ ጥያቄ ማስነሳታቸው አይቀርም፡፡

ያ ትውልድ በኢትዮጵያ ድርብ ጭቆና መኖሩን ተቀብሎ ለመቀየር ተንቀሳቅሷል፤ የያ ትውልድ የተናቀ ክንፍ የነበረው ህወሓት የበኩሉን ለመቀየር ሞክሯል፤ ከላይ ባነሳኋቸው ምክንያቶች ግን አላሳካም፤ በሌላ መልኩ መደባዊ (ኢኮኖሚያዊ) ጭቆናውን ከንጉሱ ዘመን በባሰ መልኩ በዋናነት ከአንድ ዘውገ ብሔር የሚመነጭ አድርጎታል፤ የንጉሱ በዋናነት ከአማራ በተገኙ ግለሰቦች፣ የህወሓት በዋናነት ከትግሬ፡፡ ዘርዘር አድርገን እንይ

በንጉሱ ከስደት መልስ የመጀመሪያ አመታት በተለይ አዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ በአረቦች የገበያ ተፅዕኖ ስር ነበረች፡፡ የየመንደሩ ገበያ “ዓረብ ቤት” ይባል ነበር፡፡ “ለመሆኑ አረቦቹ ከጅምላ እስከ መንደር ችርቻሮ ሙሉ ቁጥጥር (monopoly) የያዙት በምን ምክንያት ነው?” ያልን እንደሆነ፣ በወረራው ዘመን በተደረገላቸው ያልተገደበ የፖለቲካ ድጋፍ የተነሳ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ እንደገና አረቦቹንም ከጨዋታ ያስወጣቸውም ለሀገሬው የተደረገ የፖለቲካ ድጋፍ ነው፡፡ ይኸውም ሩጋ አሻሜ የተባለ የጉራጌ ተወላጅ መፍትሄ እንዲያቀርብ በንግድ ሚኒስትሩ አቶ መኮንን ሀብተወልድ ከታዘዘ በኋላ ባቀረበው መፍትሄ፣ ሀምሳ (50) የሚደርሱ ጉራጌዎች በታታሪነታቸው ተመርጠው ከመንግስት ካዝና መነሻ ካፒታል አግኝተው ከየአረቦቹ ጎን ተመሳሳይ ሱቅ በመክፈት ከአረቦቹ በወረደ ዋጋ በመሸጥ ሀገሬውን በመሳብ ነበር፡፡

ዘውዴ ረታ በ “የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት” መፅሀፉ (ከገፅ 618-624) እንደጠቀሰው በርግጥ ሩጋ ጉራጌ ቢሆንም ከአረብ ነጋዴዎች ጋር ለሚያስፈልገው ‹ውድድር› “ተወላጆቼ ጉራጌዎች የተሸሉ ይሆናሉ ብዬ ስናገር ሞያቸውን እና ችሎታቸውን በመመርኮዝ እንጂ በተለይ ወገኖቼን ለመጥቀም … አለመሆኑን” በመግለፅ የብሔር ወገናዊነት እንዳልሆነ ይከላከላል፡፡

የሆነ ሆኖ መንግስት ባደረገው የፖለቲካ ድጋፍ ወደ ገበያው የገቡት ጉራጌዎች ቢያንስ ለ80 እና 90 ዓመታት የኢትዮጵያን ገበያ በተለይ ችርቻሮውን ተቆጣጥረው ቆይተዋል፡፡ መላኩ እንግዳ “Ethnicization of market share: the proportion of wholesale in merkato, 1998-2002” (G.C) ሲል በሰራው የዳሰሳ ጥናት ጉራጌዎቹ የበላይነት ቢይዙም የከፋ ተቃውሞ እንዳልገጠማቸው ፅፏል፡፡ ይኸ ድምዳሜ የሩጋን የታታሪነት መመዘኛ የሚደግፍ ይመስላል፡፡

አሁን ቁልጭ ያለው የኢኮኖሚ የበላይነት በበኩሉ የኢጣሊያ አሸናፊነት ለአረቦቹ እንደረዳው ሁሉ፣ የህወሃት በኢህአዴግ ግንባር የበላይ መሆን ወደ የህወሓት አባላት፣ የቀድሞ ታጋዮች እና ደጋፊዎች እንዲያደላ ራዳ፡፡

ብዙ ዝርዝር በሚያስፈልገው የፖለቲካ ሙስና ባንድ ጀምበር ብር የከመሩ፣ ከነሱ ውጪ ሌላ ህዝብ በኢትዮጵያ ያለ የማይመስላቸው እብሪተኞች ካሉ እነሱ በዋናነት የህወሓት ተጋሩ እንደሆኑ ብዙ ሰው ያምናል፡፡ የሀገሪቱን ህዝብ መቶኛ ብንወስድ በዚህ ሩብ ምዕተ ዓመት የተጋሩን ያክል ወደ አዲስ አበባ ተምሞ ዋና ዋና የንግድ ቀጠናዎችን የወረረ እንደሌለም በየአዳባባዩ ይነገራል፡፡

አበበ ተክለሀይማኖት (ጀቤ) ጳጉሜ 2008 አከባቢ አዲስ አድማስ ላይ ባስነበበው ሀተታ በትግራዋይነት የተገኛ ፖለቲካ ድጋፍ ያስከተለው ባይሆንም ፍልሰቱ ከፍ ያለ እንደሆነ አልካደም፡፡ እንደጀቤ ከሆነ ለፍልሰቱ ዋና ዋና የሚባሉ ገፊ ምክንያቶች በክልሉ እየከፉ የመጡት ረሃብ፣ ድርቅ፣ ስራአጥነት፣ የፖለቲካ አፈና … ናቸው፡፡ ሆኖም ትግራይ ከአፋር፣ ከሶማሌ … በበለጠ በተዘረዘሩት ችግሮች ያለመጠቃቷን ስናይ የጀቤ ምክንያት ውሃ አያነሳም፡፡ የሶማሌ እና የወላይታ ተወላጆችም መጠነኛ የፍልሰት መጠን አላቸው፤ ታዲያ ምነው ንግዱን አልተቆጣጠሩ? መልሱን ለናንተ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር አክዬ ላብቃ፡፡ አዳሙ አሸብር በ1990 ወደ አዲስ አበባ መጣ፤ በአንድ የገበያ ስፍራ የሚገኝ የወንድሙን ሱቅ ከትምህርት ቤት ውጪ ባለ ጊዜው ይጠብቃል፡፡ አዳሙ እንደሚለው አዲስ አበባ እንደደረሰ ሰሞን የገበያ ስፍራው ሱቆች ሙሉ በሙሉ የተያዙት በኦሮሞ፣ አማራ እና አልፍ አልፎ የደቡብ ተወላጆች ነበር፡፡ በተጨማሪም ከሁለት እና ሶስት የማይበልጡ የትግራይ ተወላጆች ከሱቆቹ ውጪ ራቅ ብለው መወልወያ፣ መጥረጊያ … መሬት ላይ ዘርግተው ይታዩ ነበር ፡፡

“በቀጣዮቹ አራት አመታት የገበያ ስፍራው የብሔር ስብጥር ውስጥ ትግሬዎች በፍጥነት እየጨመሩ መጡ” የሚለው አዳሙ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሀገር ሄዶ “ከሶስት ዓመታት በኋላ ሲመለስ የገበያው ስፍራው ፈፅሞ ከዚያ ቀደም የማውቀው አልሆነም፤ የትራይ ተወላጆች ሱቆቹን በዚህም በዚያም ብለው እየያዙ የበላይነታቸውን አስፍነዋል፡፡ በቀጣዮቹ አምስት አመታት ደግሞ እንደሮኬት እየተመነጠቁ በመሄዳቸው ሱቆቹን እያስተላለፉ ወደ ትልልቅ የ‹ንግድ› ዘርፎች ተሸጋገሩ” ሲል ደመድማል፡፡

የጋምቤላ የመሬት ቅርምት፣ የብሔራዊ ባንክ የብድር ቅሌት … ተጋሩነትን መሰረት ያደረጉ እንደነበር ለቁጥር ሚያታክቱ ሰነዶች አስፍረዋል፡፡

1. ለመሆኑ አዳሙ የሚለው ሁኔታ አልተስተዋለም?

2. ከተስተዋለ፣ እንዴት ሊከሰት ቻለ?

3. ንግድ ሚኒስቴር ይኸንን አያውቅም?

4. የህወሓቱ ሩጋ አሻሜ እነዚህን ያንድ ጀምበር ሚሊየነሮች በተወላጅነት ነው በትጋት መረጠ?

5. ቀድሞ ነገር ስርዓቱ ጉዳዩን ያምናል?

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተይዘን ተሀድሶ ስንወስድ አንዱ ርዕሰ ጉዳይ በዚች ሀገር የትግራይ በላይነት እንደሌለ ማመን ነበር፤ በርግጥ ‹የትግራይ የበላይነት› እና የህወሓት ተጋሩ የበላይነት ፈፅሞ ይለያያል፡፡ በፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል ውስጥ የአንድ ዘርፍ ዳይሬክተር የሆነ ኮማንደር አበበ የተባለ ትግሬ “የሚባለው ሁሉ ውሸት ነው፤ ጸረ-የትግራይ ህዝብ ፕሮፖጋንዳ ነው፤ በዚህች ሀገር የትግሬም የህወሓትም የበላይነት የለም” ብሎ ከደመደመ በኋላ ለኛ እድል ሰጠ፡፡

አንዱ ልጅ እንዲህ አለ፤ “እኔ ተይዤ ምርመራ ሲደረግብኝ ሁን ብዬ ትግሬ አይደለሁም አልሁ፤ ብዙ ሰው ትግሬነቴን ተናግሬ መፈታት እንዳለብኝ ብነግሩኝም በአቋሜ ፀናሁ፤ ይኸው እዚህ መጣሁ” ሲል ኮማንደር አበበን ሞገተ፡፡ የተፈጠረው ስሜት በግል ታታሪነታቸው የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆችንም ሰለባ አድርጓል፤ ይኸው ልጅ ሲናገር፣ “የምንኖርበት ግቢ ብዙ አባ ወራ አለ፤ ኩሽና በጋራ ነው፤ ይኸንን የተረዳችው እናቴ ያመት በዓል ዳቦ ለመጋገር ሌሊት ተነሳች፤ ደፍታ እያለ የተቀደሙት ሌሎች ተነሱ፤ አስቡ፤ እናቴ እንቅልፏን ሰውታ ነው የቀደመቻቸው፤ እኔ ግን ‹ምን ታድርግ፤ እሷማ ባለጊዜ ናት› ሲሉ ሰማኋቸው” ሲል ሌሎች ያመጡት ጣጣ በስመ ትግሬ ለናቱ እንደተረፈ ገለፀ፡፡

ህወሓት ቀደም ሲል፣ እንደ ነፃ አውጪ በምትታይበት ዘመንም ሆነ ሁሉም ነገር እርሷ ባለችው ብቻ እንዲሄድ የማድረግ አቅም በነበራት ጊዜ የህዝቦችን እኩልነት ተለማምዳ/አለማምዳ ቢሆን ኖሮ ዛሬ እነዚህ ጥያቄዎች ባልተነሱ፡፡ አሁንም ቢሆን የመደራደሪያ ጥይቶቿን ተኩሳ አልጨረሰችምና ነገሮችን ጤናማ ለማድረግ የሚጠይቀው ፍላጎቷን ብቻ ነው፡፡ የትግሉ ውለታም በኢትዮጵያ ማቀፍ ውስጥ በሚገኘው የብልፅግና ሽግግር መመለስ ነበረበት፡፡

የሚገርመው ደግሞ፣ በ1960ዎቹ የጎመራው የተማሪ ንቅናቄ ዛሬ እንኳ ያልተሻረ ሀገራዊ መፍትሄ አቅርቦ ነበር፤ ድርብ ጭቆናን የሚያምነው ያ ትውልድ “የቱ ቅድሚያ ያግኝ?” በሚለው ባይስማማም፣ የመጨረሻ የተባለውን መፍትሄ ግን ይጋራል፡፡ ሀገር የሚበትነው የብሔሮች የራስን መብት መወሰን ሳይሆን መብቱ እውቅና ካገነ በኋላ በፈጣን እና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ እድገትና ተጠቃሚነት አለመታጀብ ነው የሚል፡፡ ኢህአዴግ (‹የህዝብ ወኪሎች›?) በህገ መንግስቱ መግቢያ ላይ ያሰፈረው ዋነኛ ጉዳይም ይኸው ነው፤ በነፃ ፈቃድ፣ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት በማረጋገጥ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ መገንባት የሚል፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው ኢኮኖሚ በዚህ ረገድ ጤናማ ነው? መልሱን ለየራሳችን፡፡

ዋነኛ የኢትዮጵያ ችግርስ የኦሮሞ ጥያቄና መዘዙ ነው?

በግሌ አይመስለኝም፡፡ ኦሮሞ ወደ ውብ ማንነቱ ከተመለሰ፣ ከሚገባው በላይ ጠያቂ አይሆንም፤ በመሆኑም ህወሓት የድርሻውን ከተወጣ፣ በልህ ከማንነቱ ያፈነገጠው ውስን ኦሮሞም ወደ ማንነቱ ተመልሶ ሌሎችን (ለምሳሌ አማራን) ከጥርጣሬያቸው ለመፈወስ ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ መሀመድ ሀሰን በኦሮሞና አማራ መካከል የነበረው ግንኙነት ሺህ ዘመን ያስቆጠረ ዘርፈ ብዙ ቢሆንም የባህሬ አዘጋገብ ጦርነቱ ላይ ብቻ በማተኮሩ ቀጣዩን ዘመን በዚሁ ላይ መወሰኑን በመጨረሻ መፅሀፉ ገልጧል፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ወገን ከዚህ ውጪ ባሉ ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች ላይ ማተኮር ከቻሉ ያሁን እና የመጪ ዘመን ማይተካ ሚና መወጣት ይቻላቸዋል፡፡

ኦሮሞም ቢሆን ህወሓትን ወደ መስመር ለማስገባት በሚደረገው ግፊት ሁለት ነገር ማስተዋል አለበት፤

1. የህወሓትን ጨቋኝ አገዛዝ እና የትግራይን ህዝብ በተለያየ መንገድ ማየት አለበት፤ አጥፊ ግለሰቦች ሲገኙም ህግ ፊት እንዲቀርቡ ከማድረግ ያለፈ ሚና ሊጫወት አይገባም፤ ሌሎች ብሔሮችንም በሚመለከት፡፡

2. መተባበር፤ መተባበር ሁለት አይነት ነው፡፡

2.1. ተመሳሳይ የለውጥ ፍላጎች ካላቸው ብሄሮች/ ቡድኖች ጋር መተባበር፤ የ1953ቱን መፈንቅለ መንግስት በዋናነት ያከሸፈው የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አዛዥ የወቅቱ ኮሎኔል ታደሰ ብሩ ነው፤ በኋላ ብቻውን ሆኖ ቀደም ሲል የተከላከለውን ስርዓት ለመገርሰስ ቢሞክርም አልቻለም፡፡

2.2. ኦሮሞው እርስ በርስ፤ ኦሮሞ በትግሉ ግብ ላይ ቢስማማም ወደዚያ በሚወስደው መንገድ ላይ ቢያን ሁለት ወገን ተፈጥሯል፤ በአፋጣኝ መፍትሄ ማግኘት አለበት፡፡

በአጠቃላይ ለተፈጠሩት ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ፣

1. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ?

2. የፀጥታና ደህንነት ም/ቤት?

በፍፁም ጥላቻ መስበኬ አይደለም፤ እንዲያውም ተሳስቶ ያሳሳተው ስዓርቱ ነው፡፡ የከፋ ደረጃ ላይ የደረሱ ስርዓቱ ሰዎች ግፋ ቢል በህግ ከመጠየቅ ያለፈ ባይሄዱ እመርጣለሁ፤ ማንም እነሱንም ሆነ የተገኙበትን ብሔር እንዲያንጓጥጥ በግሌ አልፈቅድም፡፡

የተሻለው መፍትሄ ግን ፖለቲካዊ ነው፤ ከተከፈተላቸው የፖለቲካ ሙስና ታቅበው ወደ ህጋዊ የገበያ ፉክክር/ወሰኝነት እንዲመጡ በመጀመሪያ ህወሐት ከኢትዮጵያ ህዝቦች ሞግዚትነት በስምምነት ይልቀቅ፡፡ ከመንግስት መዋቅር ውጪ ሆነው ሌላውን ከፀጥታ ስም የሚያፍኑ፣ የሚያሰቃዩና የሚያሳድዱ ህገወጥ ቡድኖች ይፍረሱ፡፡ የፌዴራል እና የአዲስ አበባ እስር ቤቶች ‹አስተዳደር›ን ከቀድሞ የህወሓት ታጋዮች የብቻ ግዛትነት በማላቀቅ መጀመር ምኑ ይከብዳል?

ነገር ግን ለአነዚህ ወገኖች ያለፈ ጥፋት፣ ደህንነት መተማመኛ የሚሰጥ ድርድር እንዲያደርግ መፍቀድ ግድ ነው፡፡ “politics is the art of negotiation’’ እንዲሉ፡፡ በቀጣይ ለሚያገኙት ቦታ እና ለሚያፈሩት የልፋታቸው ውጤትም የዚህ ታሪክ ጥላሸት እንዳይከተላቸው የሁላችንም በጎነት ያስፈልጋል፡፡ ለራሳችን ስንል፡፡

ማስገንዘቢያ

ይኸን ስል በቅናሽ የሸጣትን መፅሀፍ ሂሳብ ሲቀበል ስጋ ጋብዞ 100 ብር ለመጓጓዘዣ የሚለኝን ለፍቶ አዳሪ ወዳጄ Asrat Abreham፣ በወር ከሚያገኘው ደሞዙ የዩንቨርስቲ ወጪዬን ሁለት ሶስቴ የተጋራኝ Tekle Bekele፣ ስናገኝ አብረን በልተን ስናጣ አብረን የምንራበውን የቀድሞ ታጋይ ተወልደ (Tewe Tewe) እና መሰሎቻቸውን የምረሳ እንዳይመስላችሁ፡፡

(መታሰቢያነቱ—በግፍ እስር ቤት ህይወቱ ላለፈው እና ትኩረታችን ለተነፈገው ተስፋሁን ጫመዳ (ኢን/ር)፡፡)

Filed in: Amharic