>
4:34 pm - Sunday October 18, 5485

ዩንቨርስቲዎቻችን እና የብሄር ግጭቶቹ (ደረጀ ገረፋ ቱሉ)

1993 ወረሃ ታህሳስ ነው።በAAU ዋናው ጊቢ (ግን ማነው ዋናው ጊቢ ያደረገው? ደግሞ ይህንኑ ለምን ጠየክ ብላችሁ ፀብ እንዳታነሱ?) ነው።
አሁን በዘነጋሁት በአንዱ ዲፓርትመንት አንድ የራያ ተማሪ የጥናት ወረቀት ሲያቀርብ የኦሮሞን ህዝብ በማይሆን ስም ይጠራል።አስቡት ራያ ኦሮሞ ነው እያልን እየተከራከርን እንደገና በራያ ልጅ የጥናት ወረቀት ላይ ፀብ ተፈጠረ።በኃላ ላይ ብዙዎቻችን ተቆጭተናል።
ለማንኛውም በወቅቱ ክፍል ውስጥ የነበረው አስተማሪ ነገሮችን ማረጋጋት ይሳነው እና ፀብ ይፈጠራል።
ፀቡ ከዲፓርትመንት ዛሎ ዩንቨርስቲውን በማካለል ከብሄር ግጭትነት ዘሎ በፌደራል ፓሊስ እና በኦሮሞ ተማሪዎች መካከል ይሆናል።
ፌደራል ፖሊስ ከውጭ ገብቶ ከተማሪዎች ጋር ግብግብ ገጠመ።መከታከቱ እስከ ሌሊቱ 7 ሰዓት ቀጥሎ በፌደራል ፖሊስ አሸናፍነት ተጠናቀቀ ።በወቅቱ ሞባይ ያለ አይመስለኝም።ቢኖርም ሞባይ ለመያዝ የቤት ካርታ ስለሚያስፈልግ ቢያንስ በተማሪው እጅ አልነበረም።
የሆነው ሆኖ በዋናው ጊቢ 12 ሰዓት አከባቢ በኦሮሞ ተማሪዎች እና በፖሊስ መካከል የጀመረው ግብግብ አድማሱን እያሰፋ መልዕክተኞች ወደየ ካምፓሱ ተልከው ከሁሉም ካምፓስ የኦሮሞ ተማሪ ተፋፍሶ ወደ ዋናው ጊቢ ተመመ ።ጉዞው ግማሹ በእግሩ ግማሹ በባስ ነው።በታክሲ የመጣ ቱጃርም አይጠፋም።
መጀመሪያ የ FBE ተማሪዎች ደርሰው የዋናውን ግብ ታቀላቀሉ።
ቀጥሎ አምስት ኪሎዎች ደረሱ።
አራት ኪሎዎች ስደርሱ ፖሊስ መቋቋም አቅቶት አፈገፈገ።
በአሸናፊነት መንፈስ ተመሪው ተዘናግቶ ጊቢ ውስጥ እያቅራራ ከዬት መጣ ሳይባል ጊቢው በወታደር ተጥለቀለቀ።
ወታደሮች በየጓዳ ጎድጓዳው እየገቡ የኦሮሞ ስም በአይዲ ላይ እያሰሱ መነረት ጀመሩ።የቻልቱንም ጫኑ።
ሸነግ ነኝ (የሸገር ልጅ ለማለት ነው እንጅ እንዲህ የሚባል ነገር ያኔ አልነበረም።) እያለ ቤሄርተኞችን ስያንጎጥጥ የነበረ በአያቱ ወይም በአባቱ ጫላ እና መገርሳ ወይም ሳ መታወቂያው ላይ የተገኘ በሙሉ እየታሰሰ ተነረተ።
አልዋሻችሁም ።
ውስጥ ውስጡን ዋናው ቤሄርተኞች በፖሊስ ስራ ተደሰትን።
እኛ የከተማ ልጆችን ወደ ብሄርተኝነት ለመሳብ ያደረግነው እልህ አስጨራሽ ትግል ብዙም ፍሬ አልነበረውም።
ፖሊስ ግን በአንድ ሌሊት ብዙ ብሄርተኛ ፈልፍሎ አደረ።
ከተሜ ነኝ እያለ ሲያበሽቀን የነበረውን የያሬድ አይነቱን ትራንስ-ኤቴንክ ፖሊስ በአባቱ እና በአያቱ ስም እያሳደደ ነረተው።
ያኔ ኤትአባቱ ብለን ነበር።
ዛሬ ላይ ግን ብዙ ነገር ልክ እንዳልሆነ ይገባኛል።የፖሊስ ስራ ብቻም ሳይሆን የኛም ደስታ ጤነኛ አልነበረም።
ለማንኛውም ትራንስ ኤቴንኮች በአንድ ሌሊት ወደ ኤቴንክስ ከፍ (በኛ አተያይ) ወይም ዝቅ (በነሱ እተያይ) ብለው አደሩ።
ከሁሉም ካምፓስ ጉዞው ቀጥሏል።
ተማሪዎች ከጥቁር አንበሳ እና ከአርክቴክቸር ካምፓስ ዋናው ጊቢ ከሌሊቱ አምስት ሰዓት አከባቢ ደረሱ።
ኮተቤዎች ከሌሊቱ 7 ሰዓት አከባቢ ስደርሱ ቢሾፍቱ ካለው የእንስሳት ህክምና ካምፓስ ሊነጋጋ ስል ተማሪዎች ስድስት ኪሎ ደረሱ።
በእርግጥ አራት ኪሎዎች ከገቡ በኃላ ተጨማሪ ወታደሮች የጊቢውን በር መዝጋት ስለቻሉ ወደ ውስጥ መዝለቅ አልተቻልም።
መፈክሮች በየበሮቹ ቀለጡ።
ከእኩለ ሌሊት በኃላ ተማሪዎች በኦራል ተጭነው ወደ ኮልፌ ተጓጓዙ።
በማግስቱ ያልታሰርነው ዘመቻ አካሄድን።
በየ ሚዲያው ዞርን።
ኤምባስዎችን አሰስን።
ሸገር ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር ከሆነ 10 ዓመት ሞልቶታል።
ተማሪዎች የኤርትራን መገንጣል በመቃም በወቅቱ የተ.መ ዋና ፃሃፍ የግብፃዊውን ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊን አአ መጎብኘት አስታከው ሰልፍ እንደወጡ እና ሰው እንደሞተ ሰምተናል።
ይህ ለኛ ትውልድ ታሪክ መሆኑ ነው።
ልክ እኛ ያደረግነው ለዛሬው ትውልድ ታሪክ እንደሆነው።
ያው የአጭር ጊዜ ታሪክ መሆኑ ነው።

ለማንኛውም ከ10 ዓመት በላኃ የሆነውን ታሪክ የሸገር ነፃ ፕሬሶች እንደየ ፖለቲካ ግባቸው አራገቡት።
ሴይፋ ነበልባል የገረሱ ቱፋን “እኛስ የማን ልጆች ነን ?” የሚል አርዕስት በፊት ገፅ ይዛ ወጣች። የፅሁፉ መነሻ ፖሊሶች ስማቸው ኦሮሞ ያልሆኑትን ተማሪዎች እነሱ የኛ ናቸው ስሉ ስለነበረ ነው ገረሱ አርዕስቱን ለፅሁፉ የመረጠው ።
ፅሁፉ እጅግ ብዙ የሸገር ኦሮሞዎችን ከጎናችን አሰለፈ።የኦሮሞ ተማሪዎች ትግልም ደግም ላይነልቀ ስር ሰደደ።
በወቅቱ የአማራ ብሄርተኝነትን ሲያቀነቅን በነበረው እና የኦሮሞ ብሄርተኞች ታክትካል አጋር በነበረው እስክንድር ነጋ ባለቤትነት ይታተሙ የነበሩት ምንሊክ፣ሳታናው እና አስኳል የአማራ ብሄር ተማሪዎችን እልህ ውስጥ አስገብተው ለመቀስቀስ ተጠቀሙበት ።
ምኒልክ ጋዜጣ “የኦሮሞ ተማሪዎች በድንጋይ ጠመንጃ ስፋለሙ የአማራ ተማሪዎች ደንግጠው እራሳቸውን ሳቱ” ብሎ በፊት ገፁ ይዞ ወጣ።
እስክንድር ያሰበው ተሳክቶለት የከተማው እና የአማራ ተማሪዎች ሚያዝያ ላይ መሬት አንቀጥቅጥ ሰልፍ አደረጉ።( በሌላ ክፍል እመለስበታለሁ።)
የሙሉጌታ ሉሌዋ ጦቢያ ፣የሲሳይ አጌናዋ ኢትኦጵ እና ሌሎች የአንድነት ኅይሉ ደጋፍ ሚዲያዎች ሰልፉን አጣጣሉት።
“ከሰው በታች መሆን አሉት።”
ደህንነት የነበሩ ተማሪዎች “ህንፃን ( መስታውት) ያንቀጠቀጠ ትውልድ ” ብለው አላገጡ።እኛ ተራራን ያንቀጠቀጥን ነን ለማለት ነው።ያሁኑን አያርገው እና በወቅቱ ተስፋዬ ገብረዓብ የፃፈው “ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” እና የክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” መፅሃፍቶች እጅግ ተነባቢ ነበሩ።
ከዚያ ጋር እያወዳደሩ ተዘባበቱ።
ያኔ መስታውት ያንቀጠቀጠው ትውልድ እሄው እስከዛሬ ጎዳና ላይ ነው።
በትንሽ በትልቁ ጎዳናውን ያምሰዋል።አሁንም ወደ ቤት አልመለስ እያለ ነው።
ታሪኩን ለማጠቃለል በማግስቱ ያልታሰርነው አንማሪም አልን።
የታሳሩት ተለቀቁ ።
ለሁለት ወር ትምህርት ቀጠለን በሚያዝያ ውስጥ ህወሃት ለሁለት ተሰነጠቀች። ዶር ብራሃኑ እና ፕሮፌሰር መስፍን ተማሪውን ብሄራዊ ሎቶር አደራሽ ስብሰባ ጠሩ።
ሚያዚያ 10 ተማሪው እንደገና አመፀ።
ህዝቡም ተቀላቀለ።
ሸገር በአንድ እግሯ ቆመች።
መንግስት በመነው መሰረት 31 ሰው ሞተ።
ዋናው መልዕክት የብሄር ግጭት በኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች ውስጥ አዲስ አይደለም።በትንሽ በትልቁ ይነሳል።
አንዳንዴ በቀላሉ ይረግባል።ሌላ ጊዜ ደግሞ የሰው ህይዎት እንደዋዛ ይበላል።
እሄው እስከዛሬ መፍትሄ ሊናገኝለት አልቻልንም።
ብዙም የተለወጠ ነገር የለም።
ምናልባት የተለወጠ ነገር ካለ ያኔ ሲያረጋጋ የነበረው ዛሬ ያራግባል።ያኔ ሲያራግብ የነበረው ደግሞ ዛሬ ለማረጋጋት ይፍጨረጨራል።ወይ ጊዜ ማለት ነው።
በጣም ወሰኙ እና መታለፍ ያሌለበት ነጥብ አለ።
የፀጥታ ኃይሎች የብሄርን ግጭት ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጥረት እጅግ ጠንቃቃ መሆን አለባቸው።
ስምን ከተከተልን ትልቅ ጥፋት እናስከትለላን።
ቋንቋን ከተከተልን የማይሽር ጠባሳ እናኖራለን።
ከተቻለ በሌላ ክፍል እመለሳለሁ።

Filed in: Amharic