>
4:34 pm - Sunday October 16, 5707

‹ሕዝባዊት ዲሞክራሲያዊት ኬንያ› የምትባል ሌላ ሐገር ?!?! (ዮናስ ሃጎስ)

የሆማ ቤይ ካውንቲ የፓርላማ ተወካይ ከኬንያ 47 ካውንቲዎች 40ዎቹ ተገንጥለው ‹ሕዝባዊት ዲሞክራሲያዊት ኬንያ› የምትባል ሌላ ሐገር መመስረት እንደሚፈልጉ የሚጠይቅ ረቂቅ አዋጅ ለምርጫ ቦርዱ አቀረበ። ይህ ረቂቅ አዋጅ በኬንያ ሕገ መንግስት አንቀፅ 256(መ) መሰረት የተረቀቀ መሆኑን የምርጫ ቦርድ በትላንትናው እለት በማረጋገጡ ፓርላማው ውስጥ ወደሚገኙት ሁለት ምክር ቤቶች እንዲያቀርብ ይሁንታውን ሰጥቶበታል።
***

እንደ ፒተር ካሉማ የሆማ ቤይ የፓርላማ ተመራጭ አነጋገር በተለይ በባለፈው የጥቅምት 26 ምርጫ ላይ ያልተሳተፉ አራት ግዛቶች ባልመረጡት ፕሬዝዳንት መተዳደር አይፈልጉም። ይህን አባባሉን የሚያረጋግጠውም ደግሞ እስካሁኗ ቅፅበት ድረስ የ7 ካውንቲ ምክር ቤቶች ኡሁሩ ኬንያታን እንደ ፕሬዝዳንትነት እንደማይቀበሉ ወስነዋል። በሌሎችም ካውንቲዎች በኡሁሩ ኬንያታ ፕሬዝዳንትነት ዙርያ የመተማመኛ ድምፅ ውሳኔ የመስጠት ስብሰባ በቀጣይ ቀናት እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል። በመሆኑም በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 256(መ) መሰረት የኬንያ ሕዝብ ባልመረጠው ፕሬዝዳንት የመተዳደር ግዴታ ስለሌለው፤ ፕሬዝዳንቱ የመረጣቸውን ክልሎች መምራት እንደሚችልና ፕሬዝዳንቱን ያልመረጡት (ድምፅ ያልሰጡት) ክልሎች የራሳቸውን ሐገር መስርተው የራሳቸውን ፕሬዝዳንት መምረጥ እንደሚፈልጉ ተናግሯል።
***
መንገዱ ምን ይመስላል?
***
ፒተር ካሉማ ያቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከፍፃሜ ለምድረስ ሁለት ዓይነት መንገድ ይኖረዋል። የመጀመርያው ረቂቅ አዋጁን ፓርላማው ውስጥ ላሉ ሁለት ምክር ቤቶች አቅርቦ ባንዱ ምክር ቤት ብቻ 2/3ኛ ድምፅ ማግኘት አለበት። ከዚያ በኋላ የፕሬዝዳንቱን ይሁንታ ተከትሎ ለመላው የፓርላማ ተወካዮች ውይይት ይቀርባል። ውይይቱን ካለፈ ከ30 ቀናት በኋላ ዓዋጅ ይሆንና የኬንያ ሕዝብ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 255(2) መሰረት በ90 ቀናት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ ይገደዳል ማለት ነው።
***
ፒተር ካሉማን ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ የሚያድነው ሁለተኛ አማራጭም ከፊቱ ይገኛል። ሁለተኛው አማራጭ የ1 ሚልዮን መራጮችን ፊርማ ማሰባሰብ ያካትታል። ከዚያም እነዚህ ፊርማዎች ትክክለኛ ስለመሆናቸው በምርጫ ቦርድ ከተረጋገጡ በኋላ ይህ ረቂቅ ለ47ቱም ካውንቲ ምክር ቤቶች እንዲወያዩበት ይተላለፍላቸዋል። ምክር ቤቶቹ በ90 ቀናት ውስጥ ተወያይተውበት ውሳኔ ማሳለፍ ይጠበቅባቸዋል። ከ90 ቀናት በኋላ አብዛኛው ምክር ቤት ካፀደቀው ለፕሬዝዳንቱ ይቀርብለትና የኬንያ ሕዝብ በ90 ቀናት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ያካሂዳል ማለት ነው።
***
ረቂቁ ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ ዓዋጅ የመሆን እድል ባይኖረው እንኳን የኬንያ ሕዝብ በቀጥታ በረቂቁ አዋጅ ይሁን ወይንም አይሁን ላይ ድምፅ እንዲሰጥበት ሊደረግ ይችላል።
***
እንግዲህ ይህ ረቂቅ ከተሳካና በዓዋጅነት ፀድቆ ስራ ላይ ከዋለ ወደፊት ከታች በምስሉ ላይ የምታዩዋቸውን ሁለት ጎረቤት ሀገራት እናገኛለን ማለት ነው።
***
ይህ በእንዲህ እንዳለ … እንዲል ተመስገን በየነ… ኬንያውያን ኡሁሩ ኬንያታን ከስቴት ሐውስ ለማስወጣት የሚያደርጉት ዘርፈ ብዙ ትግል በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥም ቀጥሏል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ትላንትና ጀምሮ በከሳሾችና(ተቃዋሚዎች) በመልስ ሰጪዎች (ምርጫ ቦርድና የጁቢሊ ጠበቆች) መሐከል ኃይለኛ ክርክሮችን እያስተናገደ ይገኛል። የፍርድ ቤቱ ሂደት በቀጥታ ስርጭት በሲቲዝን ቲቪ ዌብሳይት ላይ እየተላለፈ ስለሆነ ማየት ትችላላችሁ።
***
ተቃዋሚዎች ሐሙስ እለት ከአሜሪካ ለሚመለሰው መሪያቸው ራይላ ኦዲንጋ ታላቅ የሚባል አቀባበል እያዘጋጁ ቢሆንም ፖሊስ ደግሞ ለሰልፍና እንደዚህ ዓይነት ሥነ ሥርዓት ፈቃድ አልሰጥም ብሎ ፍጥጫ ላይ ናቸው። እንደሚታወቀው ሰልፎችና የዚህ ዓይነት ስነ ስርዓቶች ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ ስለማይጠበቅባቸው ተቃዋሚዎች የፖሊስ ጄኔራሉን መግለጫ ከቁብም የጣፉት አይመስልም።
***
ምስል ቁ. 1 – ፒተር ካሉማ
ምስል ቁ.2 – ረቂቅ አዋጁ በካርታ ላይ ሲታይ…
Filed in: Amharic