>

መንገድ ጠራጊ ለመሲሁ - ኦህዴድ! እንደ መጥምቁ ዮሃንስ (ጉማ ሳቀታ)

(ፎቶ) ~ የኦህዴድ ታጋዮች (ኩማ ደመቅሳ፤ኢብራሂም መልካ፤ አባዱላ ገመዳ፤ ባጫ ደበሌ፤ ዲማ ጉርሜሳ፤ ዮናታን ዲቢሳ እና በቀለ በdhaadhaa) 1982 ዓ.

OPDO አዴት ላይ ሲመሰረት እነ ኩማ፣ እነ ኢብራሂም መልካ፣ እነ ባጫ ደበሌ፣ ዋና ተዋንያን ነበሩ። ኢብራሂም መልካ አንድ ጊዜ በሚዲያ፣ “ለኦሮሞ ህዝብ የማትሆን ኢትዮጵያ አስር ቦታ ትበጣጠስ!!” ብሎ በመናገሩ መለስ ደንግጦ አባረረው። ይህ ከሆነ 26 አመታት እንደዋዛ አልፈዋል።
ህወሃት አዴት ላይ የመሰረታት ኦህዴድ OPDO ዛሬ በህይወት የለችም። የዛሬው OPDO በመንፈስም ሆነ በአላማ የተለየ እንደሆነ ይሰማኛል። የቀድሞውን OPDO
አብርሃ ማንጁስ በቀላሉ ይነዳው ነበር። ሰለሞን ጢሞ ይቆጣው ነበር። አዲሱ ለገሰ እንደፈለገው ያንገላታው ነበር።የቀድሞዎቹ የOPDO አመራር አባላት ራሳቸውም እየተሰቃዩ
ስንቱን ሲያሰቃዩ ኖረዋል። ለማይረባ ስልጣን የህዝባቸውን መከራና አበሳ አራዝመዋል።
.
የዛሬዎቹስ? በርግጥ ካለፈው ስህተት ተምረዋል? ራሳቸውን እየሸወዱ ይሆን? ወይስ ለክብርና ለመስዋዕትነት ቆርጠው ተነስተዋል?በእርግጥም የOPDO የትንሳኤ ዘመን የደረሰ ይመስላል። አዎ የኦህዴድ ኦሮሞዎች ነጻነትን ደህና አድርገው ቀምሰዋታል። ቄሮ መስዋእትነት ከፍሎ ያቃመሰውን ነጻነት በርካሽ ዋጋ እንደማይወረውሩት እርግጠኞች ነን።
.
የኦህዴድ አባላት እንደ እነ ባሮ ቱምሳ፣ እንደ አቦማ ምትኩ፣እንደ ጃራ አባገዳ፣ እንደነ አብዱልሰመድ፣ እንደነ ማሞ መዘምር፣ እንደነ አብሼ ገርባ፣ እንደነ መገርሳ በሪ፣ እንደነ
ጄኔራል ታደሰ ብሩ ስማቸውን የሚተክሉበት ታሪካዊ መስቀለኛ መንገድ ላይ እነሆ ቆመዋል። የኦሮሞ ህዝብ አብዮት እስረኛውን OPDO ፈንቅሎ የነጻነቱን መንገድ አሳይቶታል።
በዚህ አብዮትም የኦህዴድ አባላት ራሳቸው ተሳታፊ ነበሩ። ዳር ቆመው ተመልካች አልነበሩም። ወያኔ ኦህዴድን እንደቀድሞው ህሊናውን አስሮ ሊነዳው መጣሩ አይቀርም።
ፈታኝ ቀናት በከፍተኛ ፍጥነት በመምጣት ላይ ናቸው።

OPDO በሽርፍራፊ ጉርሻዎች ተደልሎ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ላይ ቁማር ከተጫወተ የሚከፍለው ዋጋ ውድ ይሆንበታል። ለተሰው የኦሮሞ ልጆችም ስድብ ነው።
ወያኔ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰውም እጁን ተጠምዝዞና ተቀጥቅጦ እንጂ በልመና አይደለም። ዞረም ቀረ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የታሰሩት መፈታት አለባቸው። መብቱን በመጠየቁ ምክንያት የታሰረው ሰው ሳይፈታ የመብት ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ አይችልም።
በሚቀጥለው ዘመን ለማ መገርሳ በመላ ኦሮሚያ በኩራት ለመራመድ የዛሬው ተግባሩ ወሳኝ ይሆናል(ይበልጥ ደግሞ የነ አቦ በቀለ ገርባን የምስክርነት ጉዳይ እንደ ቀላል ሊያዩት አይገባም) ይህች እድል አቦ ለማ መገርሳ ላይ ወድቃለች ጥያቄአችንን ከግብ ካደረሰው ያኔ
ከልጅ እስከ አዋቂ፣ “ለማ! ለሚ! ለሜሳ!” እያለ በፍቅር ይጠራው ዘንድ ዛሬ እድል እጁ ላይ ወድቃለች። ለማ ከህወሃት ጋር ተጋፍጦ ማሸነፍ ይችል ዘንድ ግን መላው የኦህዴድ
አመራርና አባላቱ ከጎኑ ሊቆሙ ይገባል። ለማ ብቻውን ብዙ ሊገፋ አይችልም። የዙሪያው ድጋፍ ያስፈልገዋል። በዙሪያው ያሉት ደግሞ የOPDO አባላት ናቸው።
የኦሮሞ ህዝብም እንደ ህዝብ የኦህዴድን አባላት ነጥቆ ለመውሰድ በሙሉ ሃይሉ መግፋት አለበት።

– ኦህዴድ ህወሃት ለራሱ ሲል የዘረጋውን መዋቅር የራሱ ሊያደርገው ይችላል። ያኔ ለማ
መገርሳም እንደ ዮሃንስ መጥምቁ፣ “ከእኔ በሁዋላ የሚመጣውን ተመልከቱ!” እያለ በከፍተኛ ድምጽ በማወጅ መንገድ ጠራጊ ለመሆን ይበቃል።

Filed in: Amharic