>
4:16 pm - Monday February 6, 2023

እንደምን አመሻችሁ ዜና እናሰማለን! (ዮናስ ሃጎስ)

የዛሬው አበይት ዜናችን ‹ኢትዮጵያዊነት ሱሴ› ድራማ ክፍል ሁለት በነገው ዕለት በጎንደር ሲኒማ ቤት መመረቁን የተመለከተ ነው። ዘጋቢያችን እንደሚከተለው አቅርቦታል።
***
ክፍል አንድ ላመለጣችሁ ወገኖች ዩትዩብ ሄዳችሁ የባሕር ዳሩ ‹ኢትዮጵያዊነት ሱሴ› ብትሉ ማንም ያሳያችኋል።
***
በቅርቡ የጀመረውና ባጭር ጊዜ ውስጥ በጣም ተወዳጅነት ያተረፈው ‹ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ክፍል ሁለት ድራማ› በነገው ዕለት በጎንደር እንድሚለቀቅ የከፍታ ዘመን ፕሮሞሽን ትላንት አመሻሹ ያስታወቀ ሲሆን በዚህ ሁለተኛው ክፍል ላይ በክፍል አንድ ላይ ረዳት መሪ ተዋናይ ሆኖ በመስራት ‹የላቀ የተዋናይነት ዘርፍ› ሽልማትን የተቀዳጀው ገዱ አንዳርጋቸው እንደሚሳተፍበት የታወቀ ሲሆን በዚሁ ክፍል ላይ አባይ ወልዱ የተባለ አዲስ ተዋናይ እንዲካተት መደረጉንም ታማኝ ምንጮች ነግረውናል። በባለፈው ክፍል አንድ ድራማ ላይ ‹ምርጥ መሪ ተዋናይ› ዘርፍን ያለ ተቀናቃኝ ያሸነፈው ለማ መገርሳ በሌላ ‹ኦሮሞ ሶማሌ እርቅ› የተሰኘ ድራማ ላይ እየተወነ በመሆኑ በዚህኛው ክፍል ላይ እንደማይሳተፍ ተረጋግጧል። የለማ አድናቂዎች ለማን በኢትዮጵያዊነት ሱሴ ድራማ ላይ ለማየት የሚታደሉት በክፍል ሶስቱ ድራማ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
***
‹ለመስማት የሚፈልጉትን እናሰማቸው› በሚል ይዘት የተጀመረው ይህ ድራማ እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ወደፊት የሚታዩ የተለያዩ ክፍሎች እንደሚኖሩት የሚጠበቅ ሲሆን የተመልካች ቁጥሩ እንደሚጠበቀው የሚጨምር ከሆነ ‹ትግራይና ኦሮሞ›፣ ‹ኦሮሞና ጋምቤላ›፣ ‹አማራና ቤኒሻንጉል› … እያለ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
***
ሪፖርተራችን ከፕሮሞሽኑ ባለቤት አቶ ስብሐት ነጋ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ቀንጭበን እናስነብባችሁ፦
***
ሪፖርተር – ይህ ድራማ እስካሁን ድረስ ፕሮሞሽናችሁ ሲሰራቸው ከነበሩት ‹አግዓዚ› ተከታታይ ድራማ፣ ‹ኢኮኖሚክ ሪቮልዩሽን በPPP ስታይል›፣ ‹የወጣቶች ስራ ፈጠራ ፈንድ› … የመሳሰሉት ድራማዎቻችሁ በይበልጥ የተወደደ ይመስላል። ምክንያቱ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
አቶ ስብሐት ነጋ – በእውነቱ ፕሮሞሽናችን ባለፉት 26 ዓመታት ውስጥ ብዙ ተከታታይ ድራማዎችን በመስራት ይታወቃል። ይህንኑ ድራማ ራሱ ከአንድ ዓመት በፊት ‹የአማራና የትግራይ ሕዝብ እርቅ› ብለን አቅርበነው ብዙ ተመልካች እንዳላገኘ አንተም አትረሳውም። ሆኖም የባለፉት ድራማዎቻችን እምብዛም ያለ ተመልካች የቀሩት ጥናት ተደርጎባቸው ስላልተሰሩ ነው። ያሁኑን ድራማ ለየት የሚያደርገው ደግሞ ካንድ ዓመት በላይ የፈጀ ጥናት ተደርጎ ህዝቡ ባሁኑ ሰዓት ምን መመልከት ይፈልጋል የሚለውን መሰረት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው። ለዚያም ይመስለኛል ተወዳጅ የሆነው።
***
ሪፖርተር – እሺ… ግን ብዙም ባይሆን የዚህ ድራማ የመጀመርያው ክፍል አድናቂ የነበሩ ሰዎች ሁለተኛውን ድራማ ገና ሳያዩት እንደ መጀመርያው አይሆንም የሚል አስተያየት እያስደመጡ ይገኛል። በተለይ በመጀመርያው ድራማ በመሪ ተወናይነት የተሳተፈውና ሕዝቡን ‹ኢትዮጵያዊነት ማለት ልክ እንደ ሱስ ነው› በሚል ንግግሩ እንባ ያራጨው ለማ መገርሳ ያለመሳተፍ በተመልካች ቁጥር ማነስ እንደምክንያት ሊታይ የሚገባው ነገር ይመስለኛል። እርስዎ ከዚህ አንፃር ምን የሚሉን ነገር ይኖራል።
አቶ ስብሐት – አዎ በእውነቱ ለማ መገርሳ ለመጀመርያው ድራማችን ብዙ ተመልካች ማግኘት ወሳኝ ሚና የተጫወተ መሪ ተዋናይ ነው። ለዚያም ነው ባለፈው ኦስካር የመሪ ተዋናይነት ዘርፉን ያለ ተቀናቃኝ ሊያሸንፍ የቻለው። ግን ያው አንተም እንደምታውቀው አሁን ለማ ‹ኦሮሞ-ሶማሌ› የሚል ድራማ ቀረፃ ላይ ነው። ያኛውም ድራማ በኛው ፕሮሞሽን የሚሰራና የዚሁ ‹ኢትዮጵያዊነት ሱሴ› ፕሮጀክት አንዱ አካል ስለሆነ ነው በዚህ ሁለተኛው ክፍል ልናሳትፈው ያልቻልነው። በዚያ ላይ ደግሞ ለማ በሶስተኛው ‹ትግራይ-ኦሮሞ› በሚለው ድራማ ላይ እንደተለመደው መሪ ተዋናይነቱን በመያዝ ይተውናል። ለዚያ ድራማ የሚሆኑን አንዳንድ ቅድመ ዝግጅቶች ገና አላጠናቀቅንም። ለምሳሌ በመቱ ዩኒቨርሲቲ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎችን አደጋ ላይ በመጣል እያደረግነው ያለው ቀረፃ ገና አላለቀም። ከዚህም ቀረፃ በተጨማሪ እዚህ መቀለ ላይ እኔና ሌሎች የፕሮሞሽኑ አመራሮች አንዳንድ አለመግባባት ላይ ስለሆንን ሶስተኛው ክፍል ትንሽ ሊንጓተት ይችላል። ግን ያው እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ሕዝቡ በሚፈልገው መጠን በቅርቡ እንደምናደርሰው አልጠራጠርም…
***
ሪፖርተር – ከዚሁ ከመቀለ የፕሮሞሽናችሁ ስብሰባ ጋር በተያያዘ አንደኛዋ ባለድርሻ ስብሰባ ረግጣ ወጥታለች እየተባለ ነውና ችግሩ በቀላሉ ይፈታል ብለው ያምናሉ?
አቶ ስብሐት ነጋ – ችግሩ ኦልሬዲ ተፈትቷል። ስብሰባ ረግጣ የወጣችው ፕሮሞሽናችን ምን ያህል ዴሞክራሲያዊ እንደሆነ ለተመልካቾቻችን ለማሳየት እንጂ ብዙም የአቋም ለውጥ የለንም እኮ። እሷ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ የፕሮሞሽኑ አመራሮች በድራማችን ላይ የሚተውኑት መሪ ተዋንያን የክፍያ ጭማሪ ሊደረግላቸው ይገባል አይገባም በሚለው ጉዳይ ላይ እየተነታረክን ነው። ይህን ችግር የፈጠረው ያ ለማ የሚሉት ተዋናይ ነው። የክፍያ ጭማሪ አልተደረገልኝም በማለት በኦሮሚያ የሚገኙ የፕሮሞሽኑን የግል ንብረቶች በግል ፈቃዱ እየወሰደ ስላስቸገረን ነው ስብሰባው ምን መደረግ አለበት የሚለውን ነገር ለመወሰን ስብሰባው እንዲረዝም የተደረገው።
***
ሪፖርተራችን ከአቶ ስብሐት ጋር ያደረገው ቆይታ ረዘም ያለ ስለሆነ ከዜናው በኋላ ሙሉውን እንደምናቀርብ ቃል እንገባለን። የዛሬው የመወያያችን አርዕስት ‹ኢትዮጵያዊነት ሱሴ› በተመልካቹ ዘንድ ያለው እይታ የሚል ስለሆነ ስለ ክፍል አንዱም ሆነ ነገ ስለሚለቀቀው ክፍል ሁለት ድራማ ያላችሁን አስተያየት ኮመንት ብላችሁ እንድትልኩልን እያሳሰብን ወደ ሌላ ዜናዎች እናልፋለን….

Filed in: Amharic