>
7:25 pm - Tuesday October 19, 2021

እውን ሙጋቤ ስልጣን ይለቃሉ? (ቅዱስ መሃሉ)

የሮበርት ሙጋቤ መጨረሻ ምን ይሆናል?
“ለሰዳቢ ሚስቱ አሳልፎ ሰጥቶናል፤ እንድንዋረድ አድርጓል” ያሉ እና ከሳምንት በፊት የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ከስልጣን በማባረራቸው የተቆጡ የዚምባቡዊ ጦር ሃይል አባላት ሙጋቤን እና ቤተሰቡን ለጊዜው ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ በቁም እስር ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል። የዚምባቡዌ ህዝብ ከእንግሊዝ ነጻ ከወጣ ወዲህ የሃገሪቱ ትልቁ መንበረ ስልጣን ላይ ከሙጋቤ ውጭ ሌላ ሰው አይቶ አያውቅም። የዚምባቡዌ ዜጎች ለሙጋቤ ያላቸው ስሜት ድብልቅልቅ ያለ ነው። የነጻነት አባታቸው ስለሆነ ይወዱታል፤አምባገነን ስለሆነ ይጠሉታል። ይህ ስሜት አሁን “መንፈንቅለ መንግስት ሳይሆን በሙጋቤ ዙሪያ ያሉትን ወንጀለኞች እያደንን ነው” በሚሉት በሃገሪቱ ወታደራዊ አመራሮች ሳይቀር ይንጸባረቃል። ምክንያቱም አብዛኛው የዚምባቡዌ የገጠር ነዋሪ እና የወታደሩ ክፍል ሙጋቤን ይወዳል። የሃገሪቱ የጦር ሰራዊት አባላት እና የነጻነት ተዋጊዎች ማህበር አሁን በዚምባቡዌ የተደረገውን እና እየተደረገ ያለውን የወንጀለኞች ምንጠራ እንደሚደግፍ ገልጾ የዚምባቡዌ ፕሬዝዳንት ግን አሁንም ሮበርት ሙጋቤ ብቻ እንደሆኑ ተናግሯል። የሃገሪቱ ጦር ሃይል ቃል አቀባይ “ሮበርት ሙጋቤ አሁንም የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ናቸው። መፈንቅለ መንግስት አላደረግንም” ቢልም እየሆነ ያለው ግን መፈንቅለ መንግስት ከመባል ውጭ ሌላ ስም የለውም። ይሁን እንጅ ከሁሉም በላይ የዚምባቡዌ ወዳጅ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተልኩ ነው ብላለች። የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ከሙጋቤ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ተናግረው መከላከያ ሚንስትራቸውን ጨምሮ ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የጸጥታ ሃይል አማካሪዎቻቸውን ወደ ዚምባቡዌ መዲና ልከዋል። በዚያም ከሮበርት ሙጋቤ እና ከወታደራዊ ሹማምንቶች ጋር በመማከር ለጉዳዩ መፍትሄ ያመጣሉ ተብሏል። ባለፉት አመታት የዚምባቡዌ ኢኮኖሚ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ የገንዘብ ግሽበት በተመታበት ወቅት ለዚምባቡዌ የመንግስት ሰራተኞች እና ወታደሮች በአሜሪካ ዶላር ደሞዝ ስትከፍል የቆየችው ደቡብ አፍሪካ መሆኗ የሚዘነጋ አይደለም።

የሮበርት ሙጋቤ መጨረሻ ምን ይሆናል? በእኔ እይታ ሮበርት ሙጋቤ በሁሉም አማራጮች ወደ መንበረ ስልጣናቸው ይመለሳሉ። ይህ ምናልባት በቀጣዩ የፕሬዝዳንታዊ ውድድር ራሳቸውን ለማግለል በመስማማት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ምናልባት ያባረሩትን ባለስልጣን ወደ መንበረ ስልጣኑ ለመመለስ ቃል በመግባት ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ወታደሮቹ ‘ወንጀለኞች’ ያሏቸው ሰዎችን ከስልጣን ሊያባሩም ይችላሉ። ስልጣን ለመልቀቅ ከተስማሙም የሚሆነው መጀመሪያ ወደ ስልጣን መመለስ ይኖርባቸዋል። አለዚያ ግን የለቀቁት ተገደው ነው ማለት ነው። በደቡባዊ አፍሪካ ሃገራት ወታደሮች ማዕከላዊ መንግስትን ከገለበጡ በአካባቢው የሚገኙ ሃገራት በሰላማዊ መንገድ በድርድር ችግሩን ከመፍታት ጀምሮ የኢኮኖሚ ማዕቀብ እና ወታደራዊ ዘመቻ እስከማድረግ ድረስ በጋራ ያጸደቁት ስምምነት አላቸውም።

የዚምባቡዌ ወታደሮች በድርድር ሮበት ሙጋቤን በሰላም ወደ ስልጣን ለመመለስ ካልፈለጉ ወይም እነሱ የፈለጉትን ለመሾም ከወሰኑ ወይም ራሳቸው ስልጣን ላይ መቆየት ከፈለጉ በምህጻረ ቃሉ SADC የተባለው የ15 ደቡባብዊ አፍሪካ ሃገራት ጥምረት የዚምባቡዌን ድንበሮች ሙሉ ለሙሉ በመዝጋት ወደ ዚምባቡዌ የሚወጡም ሆነ የሚገቡ ሸቀጦች እና ምርቶች ላይ እገዳ በመጣል የዚሚባቡዌን ሕዝብ ህልውና በመፈታተን ሙጋቤን በገለበጡት ወታደሮች ላይ ሕዝቡን ያሳምጹበታል። የሃገሪቱ የስለላ ድርጅት እስካሁን ከሙጋቤ ጎን መቆሙ እና ከወታደሮች ጋር ለመተባበር አለመፈለጉ ደግሞ አሁንም ቢሆን ወታደሮቹ በሃገሪቱ ሁከት ተነስቶ ሌሎች ሃገራት በቀጥታ የጉዳዩ ተዋናይ ይሆናሉ በሚል ስጋት ላይ ናቸው። ዜምባቡዌ አባል የሆነችበት የ15 ደቡባብዊ አፍሪካ ሃገራት ጥምረት የሆነው SADC ግን ከዚህም በላይ የማድረግ አቅም እና ስልጣን አለው። እሱም በዚምባቡዌ ጦር ሃይል ላይ ወታደራዊ ዘመቻ በመክፈት የዚምባቡዌ ጦር ወደነበረበት ስፍራ እንዲመለስ ማስገደድ አሊያም መማረክን የሚያካትት ሲሆን ይህ ጥምር ሃይል ጦር የሚመራው ደግሞ በአፓርታይድ የመከራ ዘመን የሙጋቤን ድጋፍ ባገኙት ቀኝ እጃቸው እና ጓደኛቸው በሆኑት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ነው። ስለዚህ የ SADC ጥምር ጦር ወታደሮች ወደ ሃራሬ የሚያደርጉትን ዘመቻ ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ድጋፍ በመስጠት የዚምባቡዌ ወታደሮችን ብቻቸውን ነጥሎ እንደሚያስቀራቸው ይገምታል። የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት “የዚምባቡዌ ጦር ሃይል እስካሁን ካደረገው በላይ ተጨማሪ ምንም ነገር ለማድረግም ሆነ የዚምባቡዌን መንግስት ለመገልበጥ እንዳያስብ ምክንያቱም ጎረቤታችን የሚነሳን ማንኛውም ኢሕገመንግስታዊ ሃይል አካሄድ እንቆጣጠራለን።” በማለት መልክቱን አስተላልፏል። ሆኖም ግን ይህን የተለመደ የሪጅናል መንግስታት አካሄድ በተዘዋዋሪ በመቃወም እና የሮበርት ሙጋቤን ወደ ስልጣን አለመመለስ የሚፈልጉ የውጭ ሃይሎች ለዚምባቡዌ ጦር ድጋፍ ካደረጉ በኢኮኖሚ መቅሰፍት የምታጣጥረው ዚምባቡዌ ወደማያባራ ጦርነት የመግባት ዕድል ይኖራታል። እነዚያ የውጭ ሃይሎች ግን ምንም ጥይት ሳይተኩሱ ዚምባቡዌን እስካሁን ከበቂ በላይ የቀጧት ስለሆነ እና በዚምባቡዌ የማያባራ ጦርነት ቢከሰት በደቡባዊ አፍሪካ ሃገራት ላይ ያላቸው ጥቅም በሰላም እጦት ስለሚደፈርስ ያን ያደርጋሉ የሚል እምነት የለኝም።

Filed in: Amharic