>
10:26 pm - Wednesday February 1, 2023

እዚህ መተንፈስ ካልተቻለ፣ነፃ ሀገር መምረጥና እዚያ መተንፈሱ ሰብአዊ ነው (አቶ ግርማ ሰይፉ)

በአለማየሁ አንበሴ

• የፓርቲዎች ዓላማ መሆን ያለበት፣ ተተኪ መሪዎችን ማፍራት ነው
          • የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል የምንል ሰዎች ተሰባስበን ልንወያይ ይገባል
          • አሁንም የተሻለ የፌደራል ስርዓት መገንባት የሚቻልበት ዕድል አለ

በቅርቡ “የተከበሩት!” የተሰኘ በተወካዮች ም/ቤት (ፓርላማ) ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ያሳተሙት የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ፤ወደ አሜሪካና ካናዳ ተጉዘው የፖለቲካ ሥራ ሲሰሩ እንደቆዩና እግረ መንገዳቸውንም መጽሐፋቸውን እንዳስተዋወቁ  ይናገራሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ አቶ ግርማ ሰይፉን በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣በኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ፣በፌደራሊዝም፣ በፓርቲዎች ድርድር፣በኦህዴድ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በቢሮአቸው ተገኝቶ አነጋግሯቸዋል፡፡
የአሜሪካ ቆይታዎ ምን ይመስላል? ውጤታማ ነበር?
አሜሪካ የሄድኩት ለእረፍት ነበር፡፡ እግረ መንገዴን ግን “የተከበሩት” የሚለውን መፅሐፌን ፅፌ ስለነበር፣ እዚያው ታትሞ ቢሰራጭ የሚል ሃሳብ ይዤ ነበር የሄድኩት፡፡ በዚያውም ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ የፖለቲካ ሥራዎችንም ስሰራ ነበር። ከተለያዩ ሰዎች ጋር ተገናኝቼ፣ የዚህችን ሀገር ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ሃሳብ ተለዋውጫለሁ፡፡
ዳያስፖራው አሁን በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዴት ያየዋል?
ዳያስፖራው የተለያየ አመለካከት ነው ያለው፡፡ ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት አላቸው፡፡ ያንን የሀገር ፍቅር ስሜት የሚገልፁበት ሁኔታ እና ለወደፊት የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ እንዴት ይሁን በሚለው ነገር ላይ ግን የወደፊት ራዕይ ባለው አቅጣጫ እየተንቀሳቀሰ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይሄ ትልቁ የታዘብኩት ነገር ነው፡፡ እርግጥ ብዙ ኃይል ነው እዚያ ያለው፤ ነገር ግን ያንን ኃይል ለለውጥ ለመጠቀም የሚደረግ እንቅስቃሴ አይታይም። ተዘበራርቆ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ይሄ በደንብ ሊገራ የሚገባው ኃይል እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ደንብ ሊገራ ይገባል ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አሁን እዚያ ያለውን ኃይል እዚህ ካለው ጋር በማስተሳሰር የለውጥ ኃይል ማድረግ ይገባል፡፡ መንግስት ዳያስፖራው ለፖለቲካም፣ ለኢንቨስትመንትም ያለውን ኃይል አውጥቶ ለሀገሩ እንዲያውል ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ማመቻቸት አለበት፡፡ ይሄን ለማድረግ በሀገር ውስጥ ያለውን ፖለቲካ በስርአት መምራት ያስፈልጋል። ሀገር ውስጥ ያለው ፖለቲካ ስርአት ሲኖረው ዳያስፖራውም በዚያው መስመር ውስጥ ገብቶ ለሀገሩ ለውጥ ሊሰራ ይችላል፡፡ አሁን ግን በሀገሩ ጉዳይ በዝምታ የተቀመጠው የመብዛቱን ያህል በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በማንኛውም መልኩ መውረድ አለበት የሚለውም ቀላል አይደለም፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ግን መንግስት ነው፤ ፖለቲካውን ባለማስተካከሉ፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ለሁሉም ዜጎች ክፍት ቢያደርግ፣ እዚያ ያለው ህመም ይታከማል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ብዙ ፖለቲከኞች በአንድ አጋጣሚ ከሀገር ከወጡ በኋላ የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ይስተዋላል። ይሄን ሁኔታ ሽሽት ልንለው እንችላለን ወይስ ተስፋ መቁረጥ?
እኔ ተስፋ መቁረጥ ነው ብዬ ለማለት አልችልም። የአንዳንዶችን የፖለቲካ መስመርና የሄዱበትን መንገድ ለመተቸትም ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በአጠቃላይ ስናየው ግን እዚህ መተንፈስ ካልተቻለ ነፃ ሀገር መምረጥና እዚያ መተንፈሱ ሰብአዊ ነው። ሰዎች ትግላቸውን፣ ከሰላማዊ ትግል ወደ ሌላ የትግል አቅጣጫ ቢቀይሩ ምክንያት የሚሆነው ሀገር ቤት ያለው የፖለቲካ ስርአት እንጂ እዚያ ሀገር በሚያገኙት ጥቅም እንዳልሆነ መናገር እችላለሁ፡፡ ዋናው ችግር እዚህ ያለው የፖለቲካ ስርአት ትክክል ያለመሆኑ ነው፡፡
እርስዎ ደጋግመው ወደ አሜሪካ እንደሚጓዙና እንደሚመላለሱ ይታወቃል፡፡ ሃገር ቤት ያለው የፖለቲካ ስርአት እርስዎ ለሚያደርጉት ትግል ምቹ ነው ማለት ነው?
እዚህ ስለሚመቸኝ አይደለም፤ እዚያም ስለማይመች ነው ወደዚህኛው የማደላው፡፡ እዚያው ሀገር ሆኜ መፅሐፌን እያስተዋወቅሁ ሳለ አንዲት ሴት፤ “ይሄን መፅሐፍ ፅፈህ ወደ ሀገር ቤት ትመለሳለህ?” ስትለኝ “አዎ” ስላት “በቃ አንተ ውሸትህን ነው፤ ወያኔ ነህ ማለት ነው” ነበር ያለችኝ። ጠንከር ያለ ነገር ተናግረህ፣ ሃገር ውስጥ ስትኖር በቃ ወያኔ ሆነህ ነው የምትታየው፡፡
ከሁለት ዓመታት በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ሲናጥ የከረመው የሀገሪቱ ፖለቲካ አሁንም ከቀውስ አልወጣም፡፡ የአገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
እኔ በአንድ ነገር አምናለሁ፡፡ ሠላም ሲደፈርስ ሀገር ሲተራመስ የሚጠቀም ኢትዮጵያ ያለ አይመስለኝ። የትኛውም ኃይል ከዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ የተለየ ጥቅም አያገኝም፡፡ ሌቦችና ዘራፊዎችም ቢሆኑ ለመስረቁ ሀገር ሠላም ሲሆን ነው የሚሻለው፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም፤በሀገራችን መዳከም የሚጠቀሙና መዳከሟን የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ግብፅ አለች። ግብፅ የሀገሯን ጥቅም ለማስጠበቅ ከሚነገረውም በላይ ልታደርግ ትችላለች፡፡ ይሄን ሴራ ማክሸፍ የምንችለው ሀገር ውስጥ ሠላም ሲኖረን ነው። ሠላም እንዲመጣ ደግሞ በስርአት የሚመራ መንግስት፣ በስርአት የሚመራ ህዝብ እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡ ይሄንን ነው ማሟላት ያለብን፡፡ ዝም ማለት በራሱ ሰላም እንዳልሆነም መታወቅ አለበት። የምንመኘውን አይነት ሠላም ለማምጣት ደግሞ ስላለፈው፣ ስለጠፋው፣ ስለሞተው ብቻ መነጋገር ሳይሆን ለወደፊት ስለምናደርገው መወያየት መነጋገር ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከአሁን በኋላ ሰው እንዳይሞት፣ ከአሁን በኋላ ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ከፍ ወዳለ ደረጃ እንድትሄድ ምን ማድረግ እንዳለብን መነጋገር አለብን። ይሄን ኢህአዴግ ማድረግ እንደማይችል፣ ከዚህ በፊት በሆነውም ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ስለዚህ የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል የምንል ሰዎች ተሰባስበን፣ ልንነጋገርና ልንወያይ ይገባል፡፡ የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሰዎች ሀገር ውስጥ የመኖራቸውን ያህል በውጪ ሀገራትም አሉ። ስለዚህ ከእልህ በመውጣት መነጋገር አለብን፡፡
በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች የፖለቲካ ቀውስ፣ በተወሰኑት ደግሞ ዝምታ ሰፍኗል። እርስዎ አሁን ያለውን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
አሁን ጫፍ ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡ ዝምታው ሰላም ነው ወይም ወደ ቀድሞ የመመለስ ምልክት ነው ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ፕ/ር መስፍን አሁን “እንዘጭ- እምቦጭ” በሚል ርዕስ ባወጡት መፅሐፋቸው ላይ “ማድፈጥ” ያሉት ነገር አለ፡፡ የሚገርም ሃሳብ ነው፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ማድፈጥ ነው፡፡ ማድፈጥ ደግሞ ቀጥሎ የሚያመጣው በቀለኝነትን ነው፡፡ ስለዚህ አሁን በተደራጀ ሁኔታ መነጋገር ያልቻለው ሰው በኋላ ላይ ጎንበስ ማለት ሲመጣ ወደ በቀል ይወርድና ሌላ አምባገነን የሚመጣበትን ሁኔታ ይፈጥራል ማለት ነው፡፡ አሁን ሠላም ሳይሆን ማድፈጥ ነው ያለው፡፡
መንግስት የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራሁ ነው ይላል፡፡ እርስዎ እንደ ፖለቲከኛ ምን አዲስ ለውጥ ታዘቡ?
ለኔ ተሃድሶ፣ ጥልቅ ተሃድሶ የሚባሉት ተረት ተረት ናቸው፡፡ በስብሰባ የሚፈታ ችግር የለም። የፖለቲካ ችግሩን የፈጠሩት አሁን ሃገሪቱን እየመሩ ያሉት ሰዎች ናቸው፡፡ ሙሉ ለሙሉ እነሱ ናቸው የፈጠሩት ባይባልም የችግሩ ምንጮች እነሱ ናቸው፡፡ እነሱ ራሳቸው ደግሞ ተሰብስበው መፍትሄ ሊያገኙ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ከውጭ ሆኖ ሲያያቸው የነበረውም ተሣትፎ አድርጎ፣ የራሱን አስዋፅኦ ማድረግ አለበት እንጂ ካድሬዎች እርስ በእራሳቸው እየተሰባሰቡ የሚያደርጉት ነገር ውጤት አያመጣም፡፡ እርስ በእርሳቸውም አዲስ ሃሣብ ተቀብለው የሚያስተናግዱ አይደሉም፡፡ አመራሮች የሚባሉትንም ስንመለከት፣ የእውቀት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆነ፣ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ከአዲስ ራዕይ መፅሄት ውጪ የማያውቁ ሰዎች ይበዛሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ታዲያ እንዴት ነው አዲስ ነገር ሊያመጡ የሚችሉት?! አሁን እነሡ አዲስ ነገር የሚመጣበትን፣ አጠቃላይ የሃገሪቱን አቅም ነው መጠቀም ያለባቸው፡፡ የለውጡ ኃይል ህዝቡ መሆኑን አውቀው፣ ራሱ ህዝቡ የሚፈልገውን እንዲወስን ማድረግ አለባቸው፡፡
በሌላ በኩል አዲሱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት እና አመራራቸው የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ ነው፡፡ እርስዎስ ምን ይላሉ? የለውጥ ተስፋ ይታይዎታል?
አዎ ተስፋ ይታየኛል፡፡ ከብዙዎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተሻለ አዲስ ፊት ለማምጣት የቻለው ኦህዴድ ነው፡፡ ተስፋው የሚታየኝ አይዲዮሎጂያቸውን ባይቀይሩ እንኳ በውስጣቸው መተጋገል ሊያደርጉ ይችላሉ ከሚለው አንፃር ነው። ለምሣሌ ኦሮሚያ አካባቢ ማንም እንዳይንቀሣቀስ ተብሎ የተገደበን ነገር “አይ መንቀሳቀስማ መብቱ ነው” ማለት ከጀመሩ ነው ተስፋ የሚኖረው፡፡ እነዚህ አዲሶቹ አመራሮች ይሄን ለማለት እየሞከሩ ነው፡፡ ነገር ግን እነሱም እንደቀድሞ “እኛ ብቻ ነን ለሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመት ልንመራችሁ የምንችለው” የሚሉ ከሆነ፣ ፕ/ር መስፍን እንዳሉት ያው እንዘጭ- እምቦጭ ነው የሚሆነው፡፡  በቋንቋ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ብዝሃነት እንዳለ ተረድተው ለውጥ እናደርጋለን ካሉ ተስፋ ነው፡፡
በአማራ እና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል የተደረገው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በሌሎችም ክልሎች እንደሚቀጥል ተነግሯል፡፡ የዚህ ዓይነት ግንኙነት ፋይዳው  ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ ከመፈራራትና ከመጠራጠር አልፎ መተማመን የሚያመጣ ማንኛውም አይነት እርምጃ ሊበረታታ ነው የሚገባው፡፡ ሁልጊዜ የኦህዴድ ሰዎችን የምላቸው ነገር ነበር፡፡ የኦህዴድ ፕሮግራም የኦሮሞ ልጆች ችግር የሚፈታው በኢትዮጵያ ጥላ ስር ነው ብሎ ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን እነሱ ይመሩ የነበረው በኦነግ ፕሮግራም ነው። ወጣቶቹን የኦሮሞ ልጆች፣ በዚህ ፕሮግራም “ኦሮሙማ” በሚል አስተሳሰብ ተብትበው ነበር የያዙት፡፡ የኦሮሞ መሬት፣ የኦሮሞ ሃብት የመሣሠሉት ጠባብ አስተሳሰብ ውስጥ ነበር የነበሩት። ይሄንን ነው አዲሶቹ አመራሮች የቀየሩት። ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ ሃገር አለችን ወደሚል ነው ያሳደጉት። እኛም ስንል የነበረው ይሄንኑ ነው፡፡ ኦሮሞ መሆን ኢትዮጵያዊ መሆንን አይከለክልም፡፡ ትልቅ መሆን እየተቻለ ለምን ትንሽ ይኮናል? እነዚህ አመራሮችም እያመጡ ያሉት ትልቅ መሆንን ነው። ኦሮሚኛ ቋንቋ ሊሰፋ የሚችለው ኦሮሚያ ውስጥ ባሉ ኦሮሞዎች ብቻ ስለተነገረ አይደለም፡፡ ሌላውም ሊናገረው ይገባል። ለምሳሌ በአማራ ክልል ኦሮሚኛ እንደ አንድ የቋንቋ ትምህርት ሊሰጥ ይገባል ሲባል፣ የአማራ ክልል ጉዳዩን እሠይ ብሎ ነው መቀበል ያለበት፡፡ እኔ በግሌ የአማራ ክልል ፖሊሲ አውጪ ብሆን፣ የቋንቋ ትምህርቱ ይሠጥ፤ ነገር ግን በግዕዝ ፊደላት ነው የሚሰጠው እል ነበር፡፡ የኦሮሚያ ልጆች ደግሞ ከአንደኛ ክፍል ጀምረው የአማርኛ ቋንቋን እንዲማሩ አስደርግ ነበር፡፡ ምክንያቱም ልጆቹ በዚህ ፌዴራሊዝም ስርአት ውስጥ ቦታ የሚያገኙት ሁለቱንም ቋንቋ አቀላጥፈው መናገር ሲችሉ ነው፡፡ ሰውን ከአንድ አካባቢ እንዳይወጣ አድርጎ መፍጠር ማለት ኢ-ሠብአዊ የሆነ ጭካኔ ነው፡፡ በተለይ ኦሮሚያ ከትግራይ ክልል በስተቀር ከሁሉም ጋር ይዋሰናል፡፡ ስለዚህ የኦሮሚያ ስቴትን በዚህ ሁኔታ ራሱን ችሎ ማብቀል አይቻልም፡፡
25 ዓመት የተጓዘው የፌደራል ሥርአት አሁን በምን ደረጃ ላይ ነው ማለት ይቻላል?
እስካሁን የተሠራው በዜጎች መካከል ግንብ ነው፡፡ ግን ግንቡ ዝም ብሎ አርቴፌሻል ነው አልተሳካላቸውም። ለዚህች ሃገር የፌደራል አስተዳደር ስርአት አሁን አዋጭ የሆነ ስርአት ነው። ራስን በራስ ለማስተዳደር አመቺ የሆነ ስርአት ነው፡፡ በኛ ሃገር የተተከለው የፌዴራል ስርአት ግን ይሄንን የሚያረጋግጥ አይደለም፡፡ በመንግስት ተኮር ሚዲያዎች “ፌደራሊዝሙ ለውጥ አምጥቷል” እየተባለ በየቀኑ የሚለፈለፍበት ምክንያት ደግሞ ፌዴራሊዝሙ ውጤት ባለማምጣቱ ነው፡፡ ውጤት አላመጣም። ውጤት ቢያመጣማ ከመናገር ይልቅ በተግባር ነበር የምናጣጥመው፡፡ በ25 ዓመት ውስጥ ፌደራሊዝም አንድ ውጤት ማምጣት ካልቻለ የውሸት ነበር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም የተሻለ የፌደራል ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ መገንባት የሚቻልበት እድል አለ፡፡ ስለዚህ በመፅሃፌም እንዳስቀመጥኩት፤ አሁን ያለው የፌደራል ስርአት ሪፎርም መደረግ (እንደገና መደራጀት) አለበት። ፌደራሊዝም ምን መሆን እንዳለበትም በመፅሃፌ ላይ ጠቅሻለሁ፡፡
እርስዎም የማህበራዊ ሚዲያ (facebook) ተጠቃሚ ነዎት፡፡ በአሁን ወቅት ይህ ሚዲያ በፖለቲካችን ላይ ያለው ተፅዕኖ ምን ድረስ ነው?
እንዴ! ራሱን ችሎ መንግስት ሆኗል‘ኮ፡፡ መንግስት ሆኗል ስል ግን ጥሩ መንግስት ሆኗል ማለቴ አይደለም። ዱርዬ የፌስቡክ መንግስት ነው ያለን፡፡ እኛም ልክ ያልሆኑትን ልክ አይደለም ለማለት ነው እዚያ ውስጥ የተገኘነው፡፡
ፌስቡክ ይሄን ያህል በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ኃይል ያገኘበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
መደበኛ ሚዲያዎች ህዝብ የሚፈልገውን እያቀረቡ ባለመሆኑ ነው፡፡ ብዙ ኤፍኤም ሚዲያዎች ቢኖሩም ከስፖርትና ከመዝናኛ አያልፉም፡፡ ህዝብ ግን መስማት የሚፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የእነሱ መሸበብ ነው ፌስቡክን ያጀገነው፡፡
ከሰሞኑ የክልልና የፌደራል ብሄራዊ ደህንነት ም/ቤት፣ የተቃውሞ ሰልፍን እስከ መከልከል የሚደርስ አዲስ የደህንነት እቅድ ማውጣቱ አንደምታው ምንድን ነው?
ለምዕራባውያን አጋሮቻቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስተናል እያሉ፣ለኛ ግን አዋጁ እንዳልተነሳ በጥቅሻ መልዕክት እያስተላለፉልን ነው፡፡ ይፋዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አልታወጀም እንጂ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ነው ያለነው የሚል መልዕክት አለው፡፡ ሌላው መልዕክቱ፣መንግስት ሠላም እንደሌለ ያምናል ማለት ነው፡፡ በዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስፈልግበት ሁኔታ ውስጥ ነን ማለት ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ማረጋጋት የፈለገው በኃይል እንደሆነ በደህንነት ም/ቤቱ የተሳተፉ አካላትን አይቶ መረዳት ይቻላል፡፡ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ፣. ደህንነት ከሆነ ተሳታፊው፣ በጉልበት ነው የምንቀጥለው እንደ ማለት ነው፡፡
ከህገ መንግስቱ አንፃርስ ይህ አይነቱ የመንግስት አቋም እንዴት ይገመገማል?
በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ መንግስት ተከብሮ አያልቅም፡፡ የምንመራው በህገ መንግስት ሳይሆን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፕሮግራም ነው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ደግሞ ህገ መንግስት፣ ደንብ፣ መመሪያ አያውቅም፡፡
ህዝብን የማደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ የማዘጋጀትና የመሳሰሉ የፖለቲካ ሥራዎችን ተቃዋሚዎች እንዴት ነው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ማከናወን የሚችሉት?
በመጀመሪያ ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስራ ማደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ነው ብሎ ማሰብ በራሱ ስህተት ነው፡፡ ህዝብን ሰብስቦ ማወያየት፣ የሲቪክ ማህበራትና ተቋማት ሥራ ነው መሆን ያለበት። የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና ስራቸው መሆን ያለበት ተተኪ መሪ ማፍራት ነው፡፡ ማደራጀት ማስታጠቅም አይደለም፤ ይሄ የሶሻሊዝም አስተሳሰብ ነው፡፡ መደራጀት የሶሻሊስት አስተሳሰብ ነው። መሆን ያለበት ድምፅ የሚሰጥ መራጭን ድጋፍ ለማግኘት መጣር ብቻ ነው፡፡ ፓርቲዎች ዓላማቸው ሊሆን የሚገባው ሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ እየጠሩ ዘራፍ ማለት አይደለም፤ተተኪ መሪዎችን ማዘጋጀት ነው፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የፖለቲካ ትግል ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ አለ ብለው ያምናሉ?
በአይዲኦሎጂ (ርዕዮተ አለም) ለመታገል አሁን በሀገራችን ምቹ ሁኔታ የለም፡፡ መንግስትን ማስገደድ የሚቻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሰልፍ እየጠሩ በሚደረግ እንቅስቃሴ አይደለም። በቃ ህዝብ በራሱ መብቴን አስከብራለሁ እያለ መንቀሳቀስ ሲጀምር ነው፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያ ላይ ቄሮ የሚባል አንቀሳቃሽ ኃይል አለ። የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሄን ማድረግ አይጠበቅባቸውም። ኢትዮጵያ ውስጥ በአይዲኦሎጂ ፖለቲካን የማራመድ ሚና የተወጣ አለ ወይ ከተባለ፣ እስካሁን የለም ነው መልሴ፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲም በሀገራችን የለም። ቀለብ የሚሰፈርላቸውና በድርድር ላይ ያሉትን እንደ ፓርቲ የምንቆጥር ከሆነ ስህተት ነው፡፡ ራሱ መንግስት አብሯቸው ቁጭ ብሎ እንደ ፓርቲ እንደማይቆጥራቸው አውቃለሁ። አንዳንዶቹ ራሳቸውም እኮ “እንረባለን” ብለው ደፍረው አይናገሩም፡፡ ጭራሽም አያስቡትም፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲ የለም ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ተቃዋሚ ፓርቲ የለም፡፡ በተለይ ለስልጣን እመጥናለሁ ብሎ ስልጣን ለመያዝ የሚጥር ፓርቲ የለም። ሰዎች ጠፍተው ሳይሆን የፖለቲካ ምህዳሩ ስለሌለ ነው ይህ የሆነው፡፡
በነገራችን ላይ ገዢው ፓርቲዎች እያደረጉ ባሉት ድርድር ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ድርድር የሚባለውን እንተወውና መንግስት የምርጫ ስርአቱን ለመቀየር ካሰበ፣ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን የአብላጫ የምርጫ ስርአት መቀየር አለበት ማለት ነው፡፡ ይህን ደግሞ ለማከናወን የራሱ ህገ መንግስታዊ ሂደት አለው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሂደት ነው መቀየር ያለባቸው እንጂ አሁን በሚሉት ደረጃ ቀይረነዋል ካሉን ሊያደርጉት አይችሉም፡፡
ግን ፓርቲዎቹ ቅይጥ በተባለው የምርጫ ስርአት ተስማምተው ተግባራዊ ይደረጋል እየተባለ ነው?
ተስማሙ እንጂ ተግራዊ አያደርጉትም፤ ይሄ የህገ መንግስት ጥሰት ነው የሚሆነው፡፡ መንግስት ራሱ ከማንም ጋር ሳይደራደር አስተካክያለሁ ተቀበሉ ቢለን እኮ እንቀበል ነበር፡፡ መደራደር ማለት ግን ሁሉም እኩል ሆነው፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚከናወን ሥርአት ነው፡፡
አሁን የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት ድርድር ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ?
አዎ! ያስፈልጋል ነገር ግን ድርድር ሲባል የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያገባናል የሚሉ፣ በህዝብ ተዓማኒነትና ተቀባይነት ያላቸው ዜጎች ሲኖሩበት ነው ድርድር የሚባለው፡፡
ድርድር ለምንድን ነው የሚያስፈልገው? 
ድርድሩ ስልጣን ለመከፋፈል አይደለም የሚያስፈልገው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋና ለሁሉም እንዲለቀቅ ነው መደራደር የሚያስፈልገው፡፡ ድርድሩ ምህዳሩ እንዲከፈት እንጂ የምርጫ ስርአት ለማሻሻል አይደለም፡፡
ኢህአዴግ የምርጫ ስርአቱን ለመቀየር የፈለገው ለምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
አንደኛ አሁንም እኔ እያሸነፍኩ ነው ብሎ ያስባል፤ ስለዚህ ለማስመሰል የተወሰኑ ተቃዋሚ ግለሰቦች በተመጣጣኝ ውክልና ገብተው እንዲቀልዱ ይፈልጋል። አንዳንዶቹ ተቃዋሚዎች ደግሞ በዚህ ይረካሉ። በድርድር ለመግባት የሚደሰቱ ተቃዋሚ የሚባሉ ሰዎች፣ ም/ቤት ቢገቡ ደግሞ ከኢህአዴግ በላይ ኢህአዴግ ካልሆንኩ እንደሚሉ መጠራጠር አያስፈልግም፡፡ ኢህአዴግ የምርጫ ሥርዓቱን ለመለወጥ የፈለገውም ከኢህአዴግ በላይ ኢህአዴግ ሆነው የሚያገለግሉትን ተላላኪዎች ወደ ም/ቤት ለማስገባት ነው፡፡
በመፅሐፍዎ ላይ ፓርላማው አስፈፃሚውን አካል ተቆጣጣሪ አለመሆኑን በስፋት ገልጸዋል፡፡ ለምንድን ነው ተቆጣጣሪ ያልሆነው?
የምክር ቤት አባላት ለህሊናቸው፣ ለመረጣቸው ህዝብና ለራሳቸው ታማኝ መሆን አለባቸው፡፡ የኛዎቹ በራሳቸው ላይ እንኳ ውሣኔ ሲተላለፍባቸው ያላቸው ምርጫ መቃወም ሳይሆን መቀበል ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው በሙስና የተጠረጠሩት ግለሰብ ያለመከሰስ መብታቸው ሲነሳ ተቃውሞ እንኳ አላሰሙም፡፡ ይሄ የሚያሳየው፣ ም/ቤት የሚገቡ ሰዎች ለህሊናቸው፣ ለመረጣቸው ህዝብ ጥቅምና ለህገ መንግስቱ ታማኝ ከመሆን ይልቅ ለፓርቲ ፕሮግራም ታማኝ መሆናቸውን ነው፡፡
እርስዎን ጨምሮ በርካታ የቀድሞ “አንድነት” አባላት “ሰማያዊ” ፓርቲን መቀላቀላችሁ ተገልጿል…
እርግጥ በሃሳቡ ላይ አለሁበት እንጂ እኔ አልተቀላቀልኩም፡፡ ጥንቅቅ ብሎ ፓርቲው እኔ የምፈልገው ደረጃ ላይ ከደረሰ ለመቀላቀል ችግር የለብኝም፡፡ ያው እንደሚታወቀው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ—- ጩኸት በመፍጠር ነው የሚታወቀው፤ እንደሱ አይነት ፓርቲ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ እኔ የዚያ ፓርቲ አባል አልሆንም። መሪዎችን ለማፍራት የሚጥር ፓርቲ ከሆነ ግን ለመቀላቀል አላመነታም፡፡
“ብሔራዊ የዜጎች ንቅናቄ” የሚል ፓርቲ የመመስረት እቅድ ነበራችሁ፡፡ ዕቅዱ  አልተሳካም ማለት ነው?
ዜጎችን ማዕከል ያደረገ ፓርቲ ለመመስረት ሲጥር የነበረ ኃይል ነው “ሰማያዊ”ን ተቀላቀለው። አዲስ ፓርቲ መመስረት ለጊዜው አያስፈልግም የሚል ስምምነት ላይ በመድረሳችን ነው የቀረው፡፡
የአቶ አባዱላ እና የአቶ በረከት ከስልጣን መልቀቅን እንዴት ይመለከቱታል?
እነዚህ ሰዎች በእርግጥ ለቀዋል? የሚለው ለኔ አሁንም ጥያቄ ነው፡፡ አቶ በረከት ከንግድ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢነታቸው ወይም ከፖሊሲ ጥናት ምርምር ለቀቁ አለቀቁ የሚለው ብዙም ትርጉም የለውም። ዋናው ከፓርቲው ጀርባ አሉ ወይ የሚለው ነው። ይሄንን ነው ማረጋገጥ የሚያስፈልገው፡፡ አቶ አባዱላን በተመለከተ አንደኛ፣ ም/ቤት ውስጥ ሆኖ ም/ቤቱን የእውነት ም/ቤት ማድረግ ነበረበት፤ ምናልባት ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ተመካክረው ም/ቤቱን በመበተን በአስቸኳይ ሌላ ምርጫ የሚካሄድበትን መንገድ መፍጠር ነበረበት፡፡ አንድ ነገር አውቃለሁ፤ አቶ አባዱላ  በቀጣይ የሚመጣው ም/ቤት ጠንካራ አደረጃጀት ይኑረው የሚል ሀሳብ ነበረው፡፡ ይሄ የማደንቅለት ሀሳቡ ነው፡፡ ም/ቤቱን አፍርሶ ሌላ ምርጫ እንዲከናወን ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቶ ከሆነ መልቀቁ መልካም ነው፡፡ ታመምኩ ብሎ ከመልቀቅ ይልቅ ግን አሰራሩ አልተመቸኝም ብሎ መልቀቅ የተሻለ ነው፡፡
ህዝቡ የቀጠለበት ተቃውሞ፣ የተቃዋሚዎች ደካማ መሆን፣ የኢህአዴግ አዲስ መፍትሄ ያለማመንጨት ሁኔታ ሀገሪቷን በቀጣይ ወዴት ሊወስዳት ይችላል?
ህዝቡ እየጠየቀ ያለው የስርአት ለውጥ ነው። ኢህአዴግ እየመለሰ ያለው ደግሞ ለህዝቡ ጥያቄ አይደለም፤ ሌላ ነገር ውስጥ የገባው፡፡ ሰካራም ቁልፉን የጣለበት ቦታ ሳይሆን መብራት ያለበት ቦታ ሄዶ ነው የሚፈልገው፡፡ ኢህአዴግ አሁን ህዝቡ እየጠየቀ ያለውን የስርአት ለውጥ እንዴት ላምጣ ሳይሆን ምን ባደርግለት ጥያቄውን አረሳሳዋለሁ የሚል ጨዋታ ውስጥ ነው የገባው፡፡ የራበውን ልጅ የእንጀራ እናት ጡጦ ማጉረስ ይቻላል፤ ነገር ግን ምግብ ሲያጣ ለቅሶውን ይቀጥላል። ለራበው ልጅ ወተት ያለው ጡጦ ነው መስጠት የሚያስፈልገው። ተቃዋሚው ፓርቲ የለም፡፡ ግን ሀሳብ ያላቸው ሰዎች ጠፍተው አይደለም፤ ምህዳሩ እስኪከፈት ጥግ ይዘው ሊሆን ይችላል፡፡
እርስዎ በፓርቲ ፖለቲካ ተስፋ ቆርጠዋል እንዴ?
ለምን ተስፋ እቆርጣለሁ፡፡ ተስፋ አልቆርጥም፤ መስራት ያለብኝን ስራ እየሰራሁ ነው፡፡ ዛሬ ምሳዬን አልበላም ማለት ነገ አልበላም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ዛሬ ላይ “የፖለቲካ ፓርቲ የለም” የሚለው አቋሜ ነው፡፡
“የተከበሩት” የሚለው መፅሐፍዎ ተቀባይነቱ እንዴት ነው?
በሀገር ውስጥ ጥሩ ተቀባይነት አግኝቷል፤በውጪ ግን የተጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡ ይሄ መፅሃፍ ድርሰት አይደለም፡፡ ሰነድ ነው፤ የእውነት ሰነድ ነው፡፡ ክርክሮችም በእነዚህ እውነታዎች ላይ ነው የሚሆነው። መፅሐፉ “የተከበሩት” የሚለው ማዕረግ፣ ለም/ቤት አባላቱ ይመጥናል ወይ? የሚል ነው በዋናነት የሚያሳየው፡፡ በተለይ የም/ቤት አባላት ቢያነቡት ጥሩ ነው፡፡ ሌላውም ማወቅ አለበት፡፡
ም/ቤቶች በሦስቱ መንግስታት እንዴት ነው የሚያነፃፅሩት?
ይሄን በመፅሃፌም አስቀምጨዋለሁ፡፡ የንጉሡ ም/ቤት ሲታይ አሁን ካሉት አባላት የተሻሉ ናቸው ቢያንስ ለራሳቸው ክብር ያላቸው፣ በአካባቢያቸው የሚከበሩ ናቸው፡፡ አሁን ያሉት ግን እንደዚያ አይመስሉኝም፡፡ ለራሳቸው ክብር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ እኔ ከዚህ አንጻር ከአሁኑ የንጉሱን ጊዜ ም/ቤት እመርጣለሁ፡፡

ምንጭ:- አዲስ አድማስ

Filed in: Amharic