>
5:13 pm - Thursday April 19, 6012

“በማያዳምጡ ተናጋሪዎች” እና “በማይናገሩ አድማጮች” መካከል መግባባት አይኖርም! (ስዩም ተሾመ)

ሕወሃት/ኢህአዴግ መስራችና ከፍተኛ አመራር አቦይ ስብሃት ነጋ ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስከተለመደው ወጣ ያለና በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ላይ ጠንከር ያለ ትችት የሰነዘሩበት ነው። አቦይ ስብሃት ከሁሉም ባለስልጣናት በተለየ ሃሳባቸውን በነፃነት ሲገልፁ በተደጋጋሚ ይስተዋላል። አሁንም የገዛ ፓርቲያቸውን ልክ-ልኩን ነገሩት እኮ! መቼም እንደሳቸው የተሰማውን በነፃነት መናገር የማይሻ ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም። ይሁን እንጂ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ልክ እንደ እሳቸው በነፃነት ወይም በድፍረት ለመናገር የሚደፍር ሰው መኖሩን እጠራጠራለሁ። በእርግጥ “ከሁላችንም በተሻለ ኢህአዴግን ያለ ስጋት የመተቸት ዕድል ያለው እሳቸው ብቻ ናቸው” ብል ማጋነን አይሆንም።

ይህ ፅኁፍ አቦይ ስብሃት “ለእኔ ብሔራዊ መግባባት ያለ አይመስለኝም። አሁን ላይ ያለው ትምክህት፣ ጠባብነት እና አክራሪነት ነው” በማለት በሰጡት አስተያየት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። በእርግጥ እሳቸው እንዳሉት በሀገራችን ብሔራዊ መግባባት የለም። ነገር ግን፣ ብሔራዊ መግባባት እንዳይኖር ያደረገው ዋና ምክንያት ምንድነው? አቦይ ስብሃት የጠቀሱዋቸው የትምክህት፣ ጠባብነት እና የአክራሪነት አመለካከቶችን ከብሔራዊ መግባባት አለመኖር ጋር ተያያዥነት አላቸው? እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን እንደሚከተለው ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

በመሰረቱ በአንድ ሀገር ብሔራዊ መግባባት ሊኖር የሚችለው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ የሆነ አቋምና አመለካከት ሲኖር ነው። ለዚህ ደግሞ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ግልፅና ነፃ የሆነ ውይይት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ ሊፈጠር ይገባል። በመሆኑም፣ ብሔራዊ መግባባት እንዲኖር ዜጎች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት የሚያደርጉበት፤ ሃሳብ የሚለዋወጡበት፣ እምነትና አመለካከታቸውን የሚያንፀባርቁበት፣ ያሏቸውን ጠቃሚ ልምዶች፥ ዕሴቶችና ባህሎች የሚጋሩበት…ወዘተ፣ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የፀዳ የጋራ የሆነ መድረክ ሊኖራቸው ይገባል።

ይህ ካልሆነ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ የሆነ ግንዛቤ በዜጎች ዘንድ መፍጠር አይቻልም። በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በቂ የሆነ ግንዛቤ የሌላቸው ዜጎች ብሔራዊ መግባባትን በሚያሳይ መልኩ የጋራ አቋምና አመለካከት እንዲያንፀባርቁ መጠበቅ “ላም ባልዋለበት…” የሚሉት ዓይነት ነው። ስለዚህ፣ በሀገራችን ብሔራዊ መግባባት ላለመኖሩ በዋና ምክንያትነት ሊጠቀስ የሚገባው ነገር ነፃና ገለልተኛ የሆነ የውይይት መድረክ አለመኖር ነው።

በተመሣሣይ፣ እንደ ትምክህት፥ ጠባብነትና አክራሪነት ያሉ ፅንፈኛ አመለካከቶች በሀገሪቱ ውስጥ እንዲስፋፉ ያደረገው ነፃ የውይይት መድረክ አለመኖሩ ነው። በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት፤ ስለ ብሔራዊ አንድነትና የቀድሞ ታሪክ የሚናገሩትን ወገኖች “ትምክህተኞች”፣ የብሔርተኝነትና እኩልነት ጥያቄ የሚያነሱትን ወገኖች ደግሞ “ጠባቦች”፣ እንዲሁም ስለ ሃይማኖትና እምነት ነፃነት የሚጠይቁትን “አክራሪዎች” ብሎ በጅምላ በመፈረጅ ያላቸውን የተለየ ሃሳብና አመለካከት በነፃነት እንዳያንፀባርቁ ተደርገዋል።

ነገር ግን፣ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት የሚያንፀባርቁበት የጋራ መድረክ አለመኖሩ ወይም መነፈጋቸው ይበልጥ ፅንፈኛ እየሆኑ እንዲሄዱና ይህንንም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በማህብረሰቡ ውስጥ ለማስረፅ ጥረት እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በውይይት ያልዳበረና በምክንያታዊ ዕውቀት ላይ ያልተመረኮዘ ግንዛቤ የሌለው ማህብረሰብ ለፅንፈኛ አመለካከቶች ተጋላጭ ቢሆን ሊገርመን አይገባም። ስለዚህ፣ ከብሔራዊ መግባባት በተጨማሪ፣ ለትምክህት፥ ጠባብነትና አክራሪነት አመለካከቶች በሀገሪቱ እንዲስፋፉ በዋና ምክንያትነት ሊጠቀስ የሚገባው ነገር በድጋሜ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የውይይት መድረክ አለመኖሩ ነው።

ከላይ በዝርዝር ለመጥቀስ እንደተሞከረው፣ ለብሔራዊ መግባባት መጥፋት እና ለትምክህት፥ ጠባብነትና አክራሪነት መፈጠር ዋና ምክንያቱ ነፃና ገለልተኛ የሆነ መድረክ አለመኖር ነው። ነፃና ገለልተኛ የሆነ የውይይት መድረክ እንዲኖር ደግሞ በቅድሚያ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ያለ ምንም መሸራረፍ ሊከበር ይገባል። ምክንያቱም፣ ስለ ራሱ ችግር በግልፅ ለመናገር የሚፈራ ሰው ስለ ሌሎች ሰዎች ችግር ለመስማት ፍላጎት አይኖረውም። ስለ ራሱ መብትና ነፃነት መከበር በግልፅ ለመናገር ዕድል የሌለው ዜጋ ስለ ሀገር አንድነትና ልማት እንዲናገር መጠበቅ “የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች” የሚሉት ዓይነት ይሆናል።

በፅሁፉ መግቢያ ላይ የሕወሃት/ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቦይ ስብሃት ነጋ “ከሁላችንም በተሻለ ኢህአዴግን ያለ ስጋት የመተቸት ዕድል ያላቸው እሳቸው ብቻ ናቸው” ብዬ ነበር። ነገር ግን፣ እንደ ችግር ለጠቀሷቸው የብሔራዊ መግባባት አለመኖር ሆነ ለትምክህት፣ ጠባብነት እና አክራሪነት አመለካከቶች መስፋፋት ዋናው ምክንያት አብዛኞቻችን ልክ እንደ እሳቸው የመናገር ነፃነት ማጣታችን ነው። ስለዚህ ችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙት እኛም እንደ እሳቸው ሃሳብና አመለካከታችንን በነፃነት መግለፅ ስንችል ነው፡፡ 

Filed in: Amharic