>
7:49 pm - Wednesday February 8, 2023

አሕያ ከአሕያ ቢራገጥ ጥርስ  አይሳበር (ዮናስ ሃጎስ)

የባሕር ዳሩ ‹ኦሮማራ› ስብሰባና የጎንደሩ ‹ትግማራ› ስብሰባ ሁለቱም የኢሕአዴግ ድራማዎች እንደሆኑ ስንናገር አምነው መቀበል ያቃታቸው የ‹ኦሮማራ› ስብሰባ ደጋፊዎች የመከራከርያ ሐሳብ ቢያጡ ምን የምትል አዲስ ግኝት አመጡ መሰላችሁ?

***
አቦይ ስብሐት በጎንደሩ ስብሰባ ላይ ‹ለምንድን ነው ከኦሮሞ ጋር የተሰበሰባችሁት?› ብሎ ጠየቀ…
***

በቃ ዛሬ ሰው ሁሉ ሲቀባበላት የዋለችው ይህችን ግኝት ነው። As in ሕወሐት አለው የሚመራው የደህንነት መ/ቤት ስለ ጉዳዩ ምንም የማያውቅ እና ለአቦይ ሪፖርት የማያደርግ ይመስል አቦይ ከእንቅልፋቸው እንደነቁ ሁሉ ይህን ጥያቄ ለመጠየቅ ጎንደር ድረስ ሲጓዙ አስቡት… ከቢሯቸው ሆነው በቀጭን ስልክ ትዕዛዝ ኦሮሚያ ውስጥ የኦነግ ባንዲራ ይዞ የተገኘ የትግራይ ተወላጅን ማስፈታት የሚችሉ ሰውዬ ጠፍጥፈው ሰሩት የሚባለውን  ብዓዴንን አዲስ አበባ አሊያም መቀለ ድረስ አስጠርተው አሊያም በስልክና ቪድዮ ኮንፈረንስ ደውለው መጠየቅ የሚችሉትን ጥያቄ መቶ ምናምን ሰው ከትግራይ ድረስ ይዘው ሲጠይቁት አስቡት እንግድህ… ‹ስማ እስቲ ገዱ… ባለፈው ከኦሮሞዎቹ ጋር ለምድን ነው ግን እኛ ሳንሰማ የተሰበሰባችሁት?›
***
FYI አብዛኛው የክልል ካቢኔ አባላት፣ ፕሬዝዳንቶች፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶች… ቅብርጥሶ ለስብሰባ ምናምን የሚሄዱት ሳይቆጠር ለእረፍትና መዝናናት እንኳን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት አዲስ አበባ ነው። አዲስ አበባ ስል ደግሞ ያው እነዛን ፕሪቪሌጅድ የሆኑ መዝናኛዎችና ክለቦችን ማለቴ መሆኑ አይጠፋችሁም። እነ ለማ ሕወሐት ላይ መዶለት ሲፈልጉ የሚዶልቱት እዚያ ነው እንጂ መቶ ምናምን ሰው በሚሳተፍበት በቴሌቭዥን እየተቀረፀ ባለ ኮንፈረንስ ላይ አይደለም።
***
እንደገና በኢሕአዴግ አሰላለፍ ውስጥ ብዓዴን እና ኦሕዴድ ባይዋደዱም ቅሉ አንድ ላይ ሲሰለፉ ዛሬ የመጀመርያቸው አይደለም። መለስ ዜናዊ የሞተ ጊዜ ሕወሐት ሌላ የትግራይ ተወላጅ በጠ/ሚ/ርነት ለመተካት የነበራትን ፍላጎት ሁለቱ ድርጅቶች ናቸው ገትረው ያቆሟት። በመጨረሻ ምንም እንኳን ደኢሕዴን በአሰላለፉ ውስጥ የሕወሐት ደጋፊ መሆኑ ቢታወቅም ቅሉ ከሕወሐት ይሻላል በሚል ነው የሐይለማርያም መተካት እንዲፀድቅ የተስማሙት። እና የኦሕዴድና የብዓዴን አንድ ላይ መሰለፍ ድሮም የነበረ ነው። ዛሬ አዲስ የመጣ ነገር አይደለም። ሕወሐት አብላጫውን ኃይል ይዞ እየመራ ያለው ከደኢዴን ውጭ ሁሉንም አጋር ድርጅቶች ጠቅልሎ በመያዙ ሳቢያ ነው። ይህ መንግስት እየተዳከመ የመጣውም ሕወሐት ከደኢሕዴን ጋር 18 ድምፅ ኦሕዴድ ከብዓዴን ጋር 18 ድምፅ ይዘው በመሐል ገላጋይ ስለጠፋ ነው። አሁንጅ ሕወሐት እንደ እቅድ የያዘችው አንደኛ አማራጭ የሶማሌ አጋር ፓርቲውን ወደ ኢሕአዴግ ድርጅት አባልነት የማሳለፍና በምክር ቤቱ ውስጥ ያላትን ፈላጭ ቆራጭነት የማስቀጠል እቅድም በዚሁ ምክንያት የመጣ ነው።
***
ኢሕአዴግ ስርዓት ነው። በውስጥ ያሉ ድርጅቶቹ ቢሿከቱ ለተቃዋሚው ጠብ የሚልለት አንዳችም መና አይኖርም –

አሕያ ከአሕያ ቢራገጥ ጥርስ  አይሳበር ። ብዓዴን እና ኦሕዴድ ተሳክቶላቸው የበላይነቱን በምክር ቤቱ ውስጥ ቢይዙ ስርዓቱ የተሻለ ነገር ይገኝበታል ብሎ መጠበቅ ትልቅ የዋህነት ነው። ለተቃዋሚው ከዚህ ስርዓት አጠቃላይ መውደቅ መታገል ውጭ ምንም ዓይነት አማራጭ የለውም። በአንዱ ድርጅት ተንጠላጥሎ ራስን ወደስልጣን ማስጠጋት ይቻል ይሆናል። (ልክ ኦሕዴድ ተቃዋሚዎችን ወደ ስልጣኑ ማዕድ እንዳቀረበችው ማለት ነው) ከዚያ ውጭ ግን ለተራው ሕዝብ ምንም ጠብ የሚል አንዳችም ፋይዳ አይኖርም።

***
ለነገሩ እኔን በዚህ ሁሉ ትንተና ምን እንደሚያደክመኝ እንጃ… የድራማውን ቀጣይ ክፍል ‹ኦሮትግ› በቅርብ ጊዜ ወይ በአዳማ አሊያም መቀለ ስናይ የዛኔ ወይ በደንብ እንተማመናለን አሊያም እኔ በናንተ ተስፋ እቆርጣለሁኝ።
Filed in: Amharic