>
3:35 am - Wednesday May 18, 2022

አንድ ነገር ይገርመኛል (ሉሉ ከበደ)

ይሄ መንግስት መውደቁ ነው፤ መንኮታኮቱ ነው፤ ማክተሙ ነው፤ ሞት አፋፍ ላይ ነው…ወዘተ ይባላል። ይደንቀኛል። እየወደቅን ፤ አየተንኮታኮትን ፤ እያለቀልን ያለነው እኛ ነን። ኢትዮጵያ ነች። ይህማ መንግስት እስከሚበቃው የሚያደርገውን ካደረገ በኋላ ፤ እስከሚችለው ሀገሪቱን ከዘረፋት ካራቆታት በኋላ፤ምንም ማድረግ የማይችልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ የሚሄድበትን ቦታ አዘጋጅቷል። በተደላደለ ኢኮኖሚ ላይ የሚያርፍበትን ሀገር ገንብቷል። የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ አስተዳደራዊ ቀውሶች ሁሉ በሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች እንጂ ትግራይ ውስጥ የሉም። የመብራት ችግር የለም።የስኳር እጥረት የለም። የውሀ ጀሪካን ሰልፍ የለም። የዳቦ ሰልፍ የለም። የህክምና ችግር የለም። የትምርት ጥራት ችግር የለም፤ ጅምላ እስር የለም።የኢኮኖሚ ቀውስ የለም ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎች እየተንቀሳቀሱ ነው። የሰላም ችግር የለም። መፈናቀል የለም።በየእለቱ በህዝቡ ላይ ወታደራዊ ጥቃት እንዲፈጽም የተሰማራ ሰራዊት የለም። በኦሮሞ በአማራና በሌሎች አካባቢዎች ላይ እንደሚደረገው ዘመናዊ ሰራዊት ህዝቡን እንዲያጠቃ ታዞ፤ ሰላማዊ የለትተለት ተግባራቸውን በማከናወን ላይ ያሉ አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎች እየተጨፈጨፉ፤ ቤታቸው ንብረታቸው እየተቃጠለ ፤ እየተዘረፈ፤ ብሄር ተብሄር ተጋጨ እየተባለ ውሸት የሚነዛበት ሁኔታ ትግራይ ውስጥ የለም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብ ከህዝብ ጋር አይጋጭም። ባለፉት 27 አመታት ህውሀት እያደረገ ያሳየን ነገር የሰለጠነ ሰራዊት በህዝብ ላይ ጥቃት እንዲከፍት ትዛዝ መስጠትና እንደየ ሁኔታው በመደበኛው ሰራዊትና በደህንነት ክፍሉ እርምጃውን ማስፈጸም ነው።የተረጋጋና የተደላደለ ህዝብ አንዲት ትንሽ የተረጋጋች የተደላደለች ሃገር ትግራይ ውስጥ ብቻ መኖር ይዟል። ለሌላው ኢትዮጵያ ሲኦል ሆናለች።እናት አደገልኝ ደረሰልኝ ያለችው ልጇ በወንጭፍ እንደተመታች ወፍ አይኗ ስር በጥይት ተመቶ ሲወድቅ ማየት የለት ተለት ድርጊት ሆኗል። አባት የልጁን ገዳይ የሚበቀልበት አቅም ወይም ዳኝነት የሚያገኝበት ህግ የለም። ወያኔ የፈለገውን ግፍ ሁሉ ፈጽሞ የቀሩት የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዳለቀላቸው ሲያረጋግጥ ወደተስፋዪቱ መሬቱ ሽግግር ያደርጋል።ከዚያ በኋላ ሳይሰራ ሶስት አራት አመት ሊያስተዳድረው የሚያስችለውን በውጭ የደበቀውን ሃብታችንን እየመነዘረ ለራሱ የሰላም ኑሮውን ይቀጥላል።ከኢትዮጵያ መንግስትነት ወደ ትግራይ መንግስትነት ይሸጋገራል እንጂ ወያኔ አያበቃለትም። እስራኤሎች ፍልስጤሞችን እያደረጉ እንዳሉት እኛን ማተራመሱንም ይቀጥላል። የሚያበቃልን እኛ ነን። በገባበት ገብተን ፤ተከትለን የተዘረፈውን ሃብትም ሆነ ሃገሪቷን እራሷን እንዳናስመልስ አንድ የሚያደርገን ፍቅር መኖሩን እጠራጠራለሁ።የወያኔን ህልም የሚያልሙና ያልተሳካላቸው ግን ከሁኔታ ጋር መልካቸውን እየቀያየሩ የተቀመጡ ሌሎቹም የሃገራችንና የአንድነታችን ጠላቶች የሆኑ ወገኖቻችንም ባህሪና ሁኔታ የሚተነበይ አይደለም። ሌላው የውድቀታችን ምክንያት እዚህ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የወደቀችውን ሃገራቸውን ለማዳን ምንም አስተዋጾ የማያደርጉ ዜጎች መብዛት ነው። በተለይም ተምረዋል የሚባሉ ወይም ተምረናል የሚሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች እንደኤሊ ጭንቅላታቸውን ቀብረው የተቀመጡትን መቁጠር ያታክታል። የሚጨነቁት፤የሚቆረቆሩት፤ ሀገር ሀገር እያሉ ያለመታከት ሲጮሁ የምናያቸው በጣት የምንቆጥራቸው ናቸው። እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደዶክተር ታደሰ ብሩ ህይወያቸውን ለመስዋትነት ያቀረቡ ምሁራንን ማየት ብርቅ ነው።
እርግጥ ኢትዮጵያዊ ሲማር አብዛኛው ከተጣባው ቁሳዊ ድህነት ለመላቀቅ እንጂ ለሃገሬ ለወገኔ ይህን ለማድረግ ነው ብሎ የሚማር አይደለም። ካለም ጥቂት ስለሆነ ተምሮ ዶክተርም ሆነ ማስተር ትምርቱ ባስገኘለት ጥቅም ሆዱን እየሞላ ከመኖር በቀር ፍትህ ተጓደለ፤የወገኔ መብት ተነካ፤ ሀገሬ ተደፈረች ብሎ ለትግል ህብረተሰቡን የሚያንቀሳቅስ በጣት የሚቆጠር ነው። ይልቅስ አንባገነን ገዢዎችን ተለጥፎ የዘረፋና የጭቆና አባሪ የሚሆነው ይበዛል። የኢትዮጵያ ህዝብ ስቃይ የሚባባሰው ገዢ በሚፈጽመው ግፍ ውስጥ የምሁሩ ተሳርፎ ስላለበት ነው።ከቅርብ ወራት ወዲህ ባገራችን ይህ ብቅብቅ ያለው በኦሮሞና በአማራው መካከል አብሮ የመሆን ዝንባሌ ንፋስ ካልገባው፤ሳጥናኤል ጆሮ ካልደረሰ፤ የነጃዋር ቡድን መግቢያ በር ከተዘጋ ተስፋ አለ። የአማራውና የኦሮሞው አንድ መሆን ሌሎቹንም በፍጥነት በቀላሉ ያሰባስባል።ህውሃቶችን የበሉትንም አስተፍተን፤ የደበቁትንም አስወጥተን፥ ረግጠን ቀጥቅጠን እንዲታረሙ ልናደርግ እንችላለን። የትግራይን ህዝብም ከቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነጻ ልናወጣው እንችላለን።ሃገራችንን አድነን ሰላማችንን መልሰን እንኖር ይሆናል። አለበለዚያ ግን እኛ ያልቅልናል። እነሱ መኖር ይቀጥላሉ።
ምሁራን በያላችሁበት ተንቀሳቀሱ። ኢትዮጵያ ለጥሩውም ለመጥፎውም ነገር ከተማረው ይልቅ ያልተማረው ቀድሞ የሚገኝባት ሃገር ሆናለች። ስንት ሊቃውንት፥ ስንት ምሁራን ያሏትን ሃገር ነው እነመለስ ዜናዊ እነሳሙራ ዮኒስ የተቆጣጠሯት። ምሁራን ይህንን ኡደት ከንግዲህ በኋላ መስበር አለባችሁ። ከያላችሁበት ድምጻችሁን አሰሙ ። ወጣቱ በአር አያነት የሚከተለውን ይሻልና።ኢትዮጵያ ለዘላለም በነጻነት ትኑር።
Filed in: Amharic