>

እስራኤል 40ሺህ ስደተኛን ልታባርር ነው-27ሺህ ኤርትራዊያን ናቸው (በወንድወሰን ተክሉ) 

የእስራኤል መንግስት በሀገሩ  ያሉትን ከ40ሺህ በላይ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ሊያባርር መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ጽ/ቤት [UNHCR ] ስጋቱን አስታወቀ።

እንደ የተ.መ ድ የስደተኞች ጉዳይ ጽ/ቤት ስደተኞቹ በእስራኤል መንግስት በኩል ሀገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ወይም በግዳጅ ወደየሀገራቸው ታስረው እንደሚመለሱ የወጣውን ህግ “እጅግ አሳስቦኛል”ሲል ገልጻል።

በእስራኤል መንግስት  ሀገር ለቀው እንዲወጡ ወይም ተገደው እንደሚመለሱ ትእዛዝ ከደረሳቸው ውስጥ ከ27ሺህ በላይ ኤርትራዊያን እና ወደ 8ሺህ የሚጠጉ  ሱዳናዊያን ህይወት እጅግ ያሳስበኛል ያለው የስደተኞች ጉዳይ UNHCR ጽ/ቤት “የእነዚህ ሰዎች ወደ ሀገራቸው መመለስ ህይወታቸውን ለአደጋ ማጋለጥ ነው “ብሏል።

አብዛኞቹ ስደተኞች ማለትም ከሱዳን፣ኤርትራ፣ኢትዮጵያ የተሰደዱ የፖለቲካ ስደተኞች እንደሆኑ እየገለጹ ሲሆን በእስራኤል በኩል ግን የኢኮኖሚ ስደተኞች  እንጂ የፖለቲካ ስደተኞች አይደሉም  የሚል አቋም እንደተወሰደ ማወቅ ተችላል።

በጠ/ሚ ቤንጃሚን ኔታኒያሁ በሚመራ የካቢኔ ስብሰባ ላይ  በአንድ ድምጽ ከ40ሺህ በላይ ከአፍሪካ የፈለሱ ህገ-ወጥ ስደተኞችን ወደ፦የሀገራቸው በውዴታ ወይም በግዳጅ  ለመመለስ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን በደቡባዊ እስራኤል የሚገኘውን ሆሎት የተሰኘውን የስደተኞች ካምፕ  በመዝጋት ስደተኞቹ በ90ቀናት ውስጥ ከሀገር እንዲወጡ ቀነ ገደብ አስተላልፋል።

እንደ የህዝብ ደህንነት ሚኒስትሩ አገላለጽ “ሰርጎ ገቦቹ ሁለት አማራጭ አላቸው” ያሉ ሲሆን “ሀገሪቷን ለቆ መውጣት አሊያም መታሰር”ሲሉ ገልጸዋል።

አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ቢመለሱ ህይወታቸው በአደጋ ላይ እንደሚወድቅ ይናገራሉ።ይህንን ስጋታቸውንም የተ.መ.ድ የስደተኞች ጉዳይ ጽ/ቤት ይጋሯቸዋል። ሆኖም በእስራኤል መንግስት በኩል “የኢኮኖሚ ፍልስተኞችና ሰርጎ ገቦች”ተብለው በመፈረጅ ከሀገር እንዲወጡ የ90ቀን  ግዜ ገደብ ተስጥቷቸዋል።

ጠ/ሚ ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ከ40ሺህ በላይ ስደተኞች ያሉበትን ስደተኞች ካምፕ መዝጋት መንግስት ለካምፑ ሲያውል የነበረውን በጀት ለሌላ ነገር እንዲያውል ያደርገዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉበት ቢገለጽም በዋነነት ኤርትራዊያን 27494 እና ሱዳናዊያን 7869 ስደተኞች እንደሆኑ ተገልጻል።

Filed in: Amharic