>
3:35 pm - Saturday October 23, 2021

አህመዲን ጀበል ያቺን ሰዓት! (ክፍል ሦስት፤ ሃብታሙ አያሌው)

…የሀገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊ የነበረው ወልደስላሴ ወልደ ሚካኤል ቁመቱ አጭር ከመነፅር ስር የሚቁለጨለጩ ትንንሽ ተጠራጣሪ አይኖች ያሉት ከሲታ እና ባለ ቁጡ ፊት ተብሎ የሚገለፅ አይነት ነው። ደጋግሜ ለመግለፅ እንደሞከርኩት አህመዲን መረጃ የሚያገኝበትን መንገድ ተመራምሮ ማግኘት ለማናችንም አልተቻለንም። ቀንም ለሊትም ከጎናችን ሳይለይ አብሮን ከርሞ ሳለ ባለ ስልጣናቱ በቢሮ የዶለቱትን ጉዳያቸውን ብቻ ሳይሆን ክፉ የመከሩበትን የቢሮ ቁጥር ጭምር በይፋ ይናገር ነበር። ወልደስላሴን ለማስደንገጥ የተጠቀመው መረጃም እንኳን ሰውዬውን እኛንም አስደንግጦናል። ዞን 3 አራተኛ ቤት መግቢያ ላይ ባለወንፊቱ ሽቦ አጥር ስር እኔና ዮናታን ወልዴ በወሬ ጠምደነው ሳለ አህመዲን ከ2ኛ ቤት ወጥቶ ተቀላቀለን። ወልዴ “በማረሚያ ቤቱ የፖለቲካ እስረኞችን እና ቤተሰቦቻቸውን የማስጨነቅ፤ ተለይቶ የሙስሊም በዓል እንዳይከበር በመከልከሉ ጉዳይ የመንግስት ኃላፊዎች ድርሻ የለበትም፤ የማረሚያ ቤት ሹመኞች የተሳሳተ አቋም ነው። ” የሚል መከራከሪያ አቅርቦ እኛ ደግሞ የባለ ስልጣናት እጅ ስለመኖሩ የራሳችንን እውነት አቅርበን ጦፍ ያለ ሙግት ይዘን ነበር።

አህመዲን የወልዴን መከራከሪያ ወደ ድንጋጤ የሚቀይር መሞገቻ ሃሳብ በመሰንዘር የሞቀ ክርክራችንን ተቀላቀለ።
“የምናውቀውን ትተህ የማናውቀውን ብትነግረን ጥሩ ይመስለኛል፤ እዚህ ያሉት ኃላፊዎች በሙሉ ከላይ እስከታች እሰሩ ሲባሉ የሚያስሩ ፍቱ ሲባሉ ሚፈቱ ግደሉም ሲባሉ የሚገድሉ ሙሉ በሙሉ የትግራይ ሰዎች ቢሆኑም በራሳቸው ሳይሆን በበላዮቻቸው ጭንቅላት የሚኖሩ አሽከሮች እንደሆኑ በሚገባ ታውቃለህ። ዛሬ ቀን ጥሎህ የነሱ መቀለጃ ብትሆንም ትላንት ስታዛቸው የነበርከው አንተ እራስህ ነበርክ። በ97 ምርጫ ቃሊቲ አመፅ ተነሳ ሲባል የመለስን ትዕዛዝ ይዘህ “ሻዕቢያ” በሚል ስም በሚታወቀው ጨካኝ የአድዋ ሰው በኩል ስንት የደሃ ልጅ እንዳስረሸንክ ውስጥህ ያውቀዋል። ሌላው ይቅር አንተ አሁን ቀን ጥሎህ ስንት ወጣት ባመከንክበት ማዕከላዊ ሲያስሩህ አለቃ ፀጋዬ መጥቶ ቆሞ እንዳስገረፈህ አውቃለሁ። ሊከሱህ የነበረው በመለስ ትዕዛዝ አፋር ባስፈፀምከው በጅምላ ገድሎ በጅምላ በመቅበር ወንጀል ነበር፤ ይሄ ክስ የቀረልህ ከከሰሳችሁኝ ግድያውን መለስ ትዕዛዝ የሰጠበትን መረጃ ለፍርድ ቤት አቀርባለሁ ስላልክ አይደለም ? ”

የወልዴ ፊት ላብ አቸፈቸፈ ድንጋጤው ቅልብልብ ምላሱን ቆለፋት፤ መስማማትም መቃወምም ትቶ ዝምታ መረጠ። ነገሩ ለኛም ግራ ገባን አለቃ ፀጋዬ ቆሞ ሲያስገርፈው፤ በአፋሩ የጅምላ መቃብር ሲከራከሩ ገራፊ መርማሪ ከራሱ ከተገራፊው እና ከአለቃ ፀጋዬ በቀር ማንም በሌለበት ሚስጥሩ እንዴት ወጣ ? አህመዲን ጋርስ እንዴት ሊደርስ ቻለ ? እስካሁንም እንቆቅልሽ ነው። አህመዲን መረጃ ከማግኘት ባሻገር አንድም ቀን ለራሱ ታስሬያለሁ የሚለውን ነግሮት አያውቅም፤ ማለዳ ተነስቶ “ውዱ” አርጎ ሶላት ካደረሰ በኋላ በወጉ አጣጥፎ ያስቀመጠውን ንፁህ ልብስ ቀያይሮ ሽቶ ተቀብቶ ሲዘጋጅ ፈፅሞ ማረሚያ ቤት የሚውል አይመስልም። እረፍት የማይሰጡ ተባዮች “ትኋኖች” ሲርመሰመሱበት አድሮ በአሳሪዎቹ ፊት ምቾት ያንገላታው መስሎ ተሞሽሮ ተሽቀርቅሮ ይወጣና በንዴት ያጦፋቸዋል።

ፈራኦን የአምባገነኖች ተምሳሌት የሚለው መፅሐፉን በፃፈበት ጊዜ ለሊት ሲፅፍ ያመሽና ሲጠራቀም እንዳርመው (አርትዖቱን እንድሰራ) ያቀብለኛል። አርሜ የሚጨመር ጨምሬ የሚቀነስ ቀንሼ መልሼ አቀብለዋለሁ። አንድ ቤት ውስጥ ሆነን እሱ ሲደብቀው አይገኝም እኔጋር ሲሆን ፈልፍለው ያወጡታል፤ በእጅጉ ይገርመኝ ነበር፤ እናም የፈለገውን ያህል አምሽቼ የሱን አርሜም ሆነ የራሴን ፅፌ ስጨርስ በማንኛውም ሰዓት ቢተኛም ቀስቅሼ እንዲደብቅ ሰጥቼው እተኛለሁ እንጂ እኔው ጋር መደበቅ እርግፍ አድርጌ ትቼ ነበር። በእርግጥም በዚህ መንገድ የሱ መፅሐፍ ተጠናቀቀ የሽፋን ስዕሉን በእጄ ስዬ አማራጭ አቀረብኩ ተስማማበት፤ በዘዴ ወደውጭ ወቶ በኮምፒውተር ተሰርቶ መጣ በጋራ አሳለፍነው መፅሐፉ ለህትመት በቃ።

እኛ ወደ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ ማንኛውም የሙስሊም በዓል እንዳይከበር ይደረግ ነበር። ለክርስቲያኖች በዓላችን በደረሰ ጊዜ በሽሮ ማፍያው ጎላ ስጋ ጣል ጣል መረቅም ቢሆን ይቀርባል፤ ቤተሰብ የሚያመጣው ያለገደብ ይገባል ይህ በሙስሊም በዓል አይደረግም፤ ልብ ይሰብር ነበር። ህሊና ይጎዳል የሚያመጡት ባይጠቅምም ተንኮልና ሴራቸው ግን ያበግናል። በሙስሊም በዓል የኛ ቤተሰቦች ዳቦ አስጋግረው እንዲያመጡ ቄጤማ እንዲያቀብሉን እያደረግን በዓሉን በዓል ልናደደርግላቸው እንጥር ነበር።

በአንድ ወቅት ምሬቱ ሲበዛ በሚስጥር መልዕክት በመላላክ አድማ ተመታ። ለሙስሊሙ በዓል የቀረው ‘ስጋ ጣል ጣሉ መረቅ’ ለክርስቲያኖች በዓል ቀን ሲመጣልን ሙስሊም ወንድሞቻችን አንበላም ሲሉ በአንድነት አደሙ ምንም እንኳን ቀድሞም የመረቁ ተቋዳሽ ባንሆንም አድማውን ግን ብዙዎቹን ክርስቲያኖች አስተባብረን ተቀላቀልን። ቂሊንጦ ተጨነቀች… ስብሰባ ግምገማ ማስፈራርያ መረቁን ከመደፋት ሳያያስጥሉት ቀሩ።

እኛም ወደ አህመዲን አልጋ ሁለተኛ ቤት ግራ ጥግ ሰብሰብ ብለን ቀኑን በደስታ አሳለፍን። አህመዲን ጀበል፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ሼህ መከተ ሙሄ፣ ካሚል ሸምሱ፣ ካሊድ ኢብራሂ፣ መሐመድ አባተ፣ ናቲ፣ ዮናታን ወልዴ፤ የሺዋስ አሰፋ፣ መሐመድ አብዱልቃድር…የህወሓት ጉጅሌዎች ደማቸው ተንተከተከ ቅጥ ያጣ የበቀል እርምጃቸው ቀጠለ የሚንበረከክ ግን አልተገኘም። እናም የመጨረሻ አማራጫቸው እኛን መበታተን ሆነ፤ ምን እንደታሰበ መረጃው እንደተለመደው ከአህመዲን አላመለጠም እኛ ግን ለሚሆነው ሁሉ እንግዳ ነበርን። አህመዲን አንድ ምሽት እንደተለመደው እራቱን ከጀማው ጋር 6ኛ ቤት ሳይበላ ድርሻውን ይዞ መጣ። ማታ ከሶላት በኋላ ወደ ቦታው ጠራኝ እና ዛሬ እራት አብረን መብላት አለብን አለኝ፤ ለምን የሚለው የዓዕምሮዬ ጥያቄ ሳይመለስ አደርን ለካ የመጨረሻ እራት ጋብዞ እየተሰናበተኝ ኑሮአል፤ ማለዳ እነዚያ የክፋት መልዕክተኞች መጥተው እነ አህመዲንን ወደ ቃሊቲ ወሰዷቸው ።
በዚህ ሁኔታ ተለያየን፤ ከአመታት ተጨማሪ ግፍ በኋላ አህመዲንን እነዚያ የህወሓት ጭፍራዎች እንዲህ አድርገውት ማየት ለኔ ምን አይነት ስቃይ እንደሆነ የሚገልፁ ቃላቶች የሉኝም። አምላክ ምህረቱን ይላክለት !!

Filed in: Amharic