>
3:31 am - Wednesday February 1, 2023

ብአዴን ማን ነው? 

(ምንጭ፡የመጀመሪያው የኢህዴን ሊቀመንበር ያሬድ ጥበቡ )

ጊዜው በ1973 ዓ.ም. ነው። ኢህአፓ በከተማ የትጥቅ ትግል ተሸንፎ ከወጣ በኋላ ጫካ ገብቶ የትጥቅ ትግሉን ለመቀጠል ኢህአሰ [የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ሰራዊት] በሚል ስያሜ የመሰረተውን ወታደራዊ ክንፍ ይዞ ትግራይ አሲምባ እንደከተመ በጫካ ትግሉ ብዙም ሳይገፋ ድርጅቱ በውስጥ ክፍፍል መታመስ ጀመረ። ድርጅቱ የተተራመሰው አፈ ጮሌ የድርጅቱ ታጋዮች ከድርጅቱ መርህ ውጭ የሆነ ጽሁፍ በመበተናቸው ነው ተብሎ አራት ፋኖዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ። የነዚህ አራት ፋኖ ጽሁፍ በታኞች ቡድን አስተባባሪ በበረሀ ስሙ «አንበርብር» እየተባለ ይታወቅ የነበረው የድርጅቱ አስኳድ ነው። አንበርብር ከኢህአፓ ስነስርዓት ውጪ ድርጅቱን የሚጎዳ ጽሁፍ የበተነው ከወያኔና ከሻብያ በተሰጠው ድርጅቱን የማፍረስ ተልዕኮ እንደሆነ የትግል አጋር ፋኖዎቹ ይናገራሉ። በመጨረሻም የአንበርብር ቡድን ከህዳር 7 ቀን እስከ ህዳር አስራ አንድ ቀን 1973 ዓመተ ምህረት በትግራይ ውስጥ በተምቤን አውራጃ አምበራ ወረዳ ሽልም እምኒ ቀበሌ ተክራርዋ በተባለች መንደር ከኢህአፓ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የአፈነገጡት ተጨማሪ ፋኖዎችን በመያዝ ቀደም ብሎ ወያኔ ወዳዘጋጀላቸው ቦታ ተወስደው በወያኔ አጋፋሪነት «ጉባኤ» ዘርግተው አዲስ ፓርቲ ለመመስረት «መከሩ»።

በነአንበርበር ስብሰባ ላይ የነበሩ የህወሀት ሰዎች እነአንበርብርን በህወሀት ህግ መሰረት አግባብተው በስብሰባው መጨረሻ በህዳር 11 ቀን 1973 ዓመተ ምህረት ከኢህአፓ አፈንግጦ የወጣውን የነአንበርብር ቡድን በህወህት አዋላጀት የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ [ኢህዴን] የሚባል ፓርቲ ተመሰረተ። ህወሀት ከኢህአፓ የውስጥ ደንብ ውጭ ኢህአፓን የሚያፈርስ ጽሁፍ እንዲጽፍና እንዲያሰራጭ በኋላም በህወሀት ፕሮግራም ኢህዴንን እንዲቋቋም በማድረግ ትልቅ ሚና የነበረውና «ድርጅቴን አዳክሞ አባላቶቼን አስከዳብኝ» ብሎ በወቅቱ ኢህአፓ መጀመሪያ ያሰረውና ቀጥሎም ከእስሩ ካመለጠ በኋላ በይፋ ያወገዘው «ከሀዲው» ግለሰብ በብዕር ስሙ አንበርብር ተብሎ ይታወቅ የነበረው የወያኔ «ተላላኪ» እንደሆነ ከፍ ብዬ ገልጫለሁ። ይሄ በበረሀ ስሙ አንበርብር በመባል ይጠራ የነበረው የወያኔ «ተላላኪ» እና የኢህአፓ «ከሀዲ» ዛሬ በሚንስትር የማዕረግ ስሙ በረከት ስምዖን ተብሎ ይጠራል።

ኢህዴን እዚያው ትግራይ ውስጥ የህወሀት «የጡት ልጅ» ሆኖ እንደተመሰረተ ለነአንበርብር ቡድን በመጀመሪያ ወታደራዊ ስልጠና የሰጣቸው የወያኔው የቀድሞ መከላከያ ሚንስትር የነበረው ስዬ አብርሀ ነበር። የስዬን ስልጠና እንደጨረሱ ኢህዴኖች መሳሪያ ታደላቸውና በአማራ አገር ለሚደረገው የህወሀት ትግል በመንገድ መሪነትና በአማርኛ አስተርጓሚነት ታጩ። ይሄንን ታሪክ የሚነግረን የያኔው አንበርብር ወይንም የዛሬው በረከት ሰምዖን ሳይሆን የመጀመሪያው የኢህዴን ሊቀመንበር ያሬድ ጥበቡ ወይንም በትግል ስሙ ጀቤሳ ነው። የውቤ በረሀው ልጅ ያሬድ ጥበቡ አስቀድሞ ያልተገነዘበውን የወያኔ ስውር ደባ ውሎ አድሮ ሲገለጥለት «ኢህዴን ነጻ የነሆነ ድርጅት ሳይሆን የህወሀት ጉዳይ አስፈጻሚ፣ ለህወሀት ያደረና የህወሀት ጉዳይ ፈጻሚ ነው» በማለት ፊቱን ወደ ሱዳን አዙሮ ኢህዴንን ሙሉ በሙሉ ለነአንበርብር ጥሎ አሜሪካ ገባ።

ኢህዴን ከተመሰረተ ዘጠኝ አመት ከአምስት ወር ሲሆነው ወያኔ ኢህዴንን አማርኛ እያስተረጎመ ጎጃምና ጎንደር ተሻግሮ አዲስ አበባ ገባ። ወያኔ አዲስ አበባ እንደገባ የአማራ ጥላቻ የወለደው ኦነግ የሚባለው ድርጀት የሽግግር መንግስቱ አካል ሆኖ ያገኘውን ስልጣን በመጠቀም በወለጋ፣ በአርሲ፣ በሀረር፣ በባሌና በሎሎች ኦነግ በስፋት በሚንቀሳቀስባቸው ከተሞች ሁሉ ለዘመናት አገር ሰላም ብለው ይኖሩ የነበሩ አማሮችን ያለርህራሄ ማረድና መጨፍጨፍ ጀመረ። አማራው በያለበት ደሙ ደመ-ከልብ መሆኑ እንቅልፍ ያሳጣቸው እጀ መድሀኒቱ ታአምረኛ ሀኪም ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ በየተገኘበት ይታረድ የነበረውን የአማራ ህይወት ለመታደግ «መአህድ» [የመላው አማራ ህዝብ ድርጀት] የሚባል ህይወት አድን ድርጅት አቋቋሙ። ይህንን ተከትሎ መአህድ ባጭር ጊዜ ውስጥ እልፍ አእላፍ አባላትና ደጋፊዎችን ከጎኑ አሰለፈ። በኢትዮጵያ ህዝብ ባጠቃላይና በተለይም በአማራው ዘንድ የመአህድ ተሰሚነትና የፕሮፌሰር አስራት ቅቡልነት እንቅልፍ የነሳው ወያኔ ኢህአዴግ ውስጥ በአማራ ብሔረሰብ ስም የሚጠራ ድርጅት ስለሌለው [የኢህአዴግ አካል የሆነው የነ አንበርብሩ ኢህዴን ህብረ ብሔራዊ ድርጅት እንደነበር ልብ ይሏል] መአህድ አማራውን ከጎኑ አሰልፎ ሳይጨርሰው ከመአህድ የአማራውን ውክልና ለመጫረት ሲባል ህብረ ብሔራዊው ድርጀት የሆነውን ኢህዴን ወደ ብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ [ብአዴን] ተለውጦ የፕሮፌሰሩን መአህድ እንዲውጥ ትዕዛዝ ሰጠ።

ኢህዴኖች እነ አንበርብርም ከኢህዴን ወደ ብአዴን እንዲያንሱ የተሰጣቸውን የወያኔ ትዕዛዝ ሰጥ ለጥ ብለው በመስገድ በይሁንታ አስተናግደው የህብረ-ብሔራዊውን የኢህዴን ድርጅት የፖለቲካ ፕሮግራም ሳይቀይሩ «ወደ ብሔረሰብ ድርጅትነት» ተለወጡ። በ1973 ዓ.ም. ኢህአፓን ከድቶ ለወያኔ ያደረው ኢህዴን በ1985 ዓ.ም. ደግሞ ራሱን ኢህዴንን ከድቶ ብዓዴን ሆነ። ዛሬ «ብዓዴን ነን» ከሚሉን የድርጅቱ እንደራሴዎች ይልቅ የብአዴንን እውነተኛ ታሪክ ከስር መሰረቱ ለምን አላማ ድርጅቱን እንደመሰረተው የሚያውቀው ወያኔ ብቻ ነው። ይህንን ለማየት ድርጅቱን ወያኔ እየሾማቸው ይመሩት የነበሩት ሰዎች ስለብዓዴን የተናገሩትን መውሰድ በቂ ነው። ለምሳሌ ኢህዴን ወደ ብአዴን ከመቀየሩ በፊት ዋናው ኢህአፓ «ለወያኔ ያደሩ ከዳተኞች ብሎ» ክስ አቅርቦባቸው ኖሮ የወቅቱ የደርጅቱ መሪ የነበሩት የዛሬው ፓስተር ታምራት ላይኔ ኢህአፓ በኢህዴን ላይ ላቀረበባቸው አስተያየት ተጠይቀዉ ሲመልሱ «እኛ ከኢሕአፓ ተለይተን የወጣን ትክክለኛ ኢሕአፓዎች ነን» ብለው ነበር። በሌላ ጊዜ ደግሞ የዚሁ ድርጅት መሪ የነበሩት አዲሱ ለገሠ የድርጅቱን በዓል ሲያከብሩ ለአማራ ህዝብ መብት የተፈጠሩ መሆናቸዉን ተናግረዉ ነበር። ዛሬ ለድርጅቱ መሪነት የተወከሉት ደመቀ መኮነን ቢጠየቁ ሌላ እንደሚመልሱ እርግጠኛ ነኝ። ኢህዴን/ብዓዴን ይህን ሁሉ የክህደት ውል ለወያኔ እየፈረመ ሲገለባበጥ የኖረው በኢትዮጵያና በተለይም በአማራው ውርደት፣ ድህነት፣ ባርነት፣ ስደት፣ ግድያና ሰቆቃ ላይ የወያኔን የግዛት ዘመን ለማራዘም ነው።
የወያኔን ሀያ ስድስተኛው ዓመት የንግስ በዓል ተከትሎ ሰመኑን ደግሞ የኢህአፓና የአማራ ህዝብ ከሀዲዎች ማህበር የሆነው ጉደኛው ብዓዴን ዛሬም እንደ ወትሮው ሳያፍር «የ37ተኛ ዓመት ልደቴን ላከብር ነው» እያለ ህዝቡን በመዋጮ ከማስጨነቁም አልፎ «በአለም ላይ የመጨረሻ ድሀ ክልል» የተባለውን የአማራ ክልል ከፍተኛ በጀት ለበዓሉ ማክበሪያ መድቦ እየተራወጠ ይገኛል። ገንዘብ ከማዋጣት በተጨማሪ የፈረደበት የአማራ ህዝብ በአሉንም እንዲያጅብ በየቀበሌውና በየመስመሪያ ቤቱ ቀጭን ትእዛዝ ደርሶታል። አማራው የሀገሩንና የራሱን አራጆች ድግስ እንዲያሞቅና ለዲስኩራቸው እንዲያጨበጨብ እየተደረገ ያለው ሠራተኛው በሚያገኛት ኩርማን ደሞዙ፤ ሌላው ከቀበሌ በሚያገኘው ስኳር፣ ዘይትና በሌሎች መሰረታዊ አግልግሎት በኩል በሚመጣበት ማስፈራሪያ ነው። ላለፉት ሀያ ስድስት አመታት አማራው በኢህዴን/ብዓዴን አማካኝነት በአገሪቱ ውስጥ ላለው ብቸኛው ቀጣሪ፤ ስኳርና ዘይት አከፋፋይ፤የሚነበበውንና የሚደመጠውን መራጭ፤ የእድገትና የከፍተኛ ትምርት እድል ደልዳይ፤ ፍትህንና የባንክ ብድርን ፈቃጅ ለሆነው ወያኔ ተላልፎ ተሰጥቷል። ለዚህ ውለታው ነው እንግዲህ ብዓዴን የአማራ ህዝብ 37ተኛ አመት ውልደቱን እንዲያከብር እያስገደደው ያለው።

Filed in: Amharic