>

"እንኳን ሰው ዝንብ አልገደልኩም!" ኮ/ል መንግሥቱ የ‹‹60ዎቹ›› ባለስልጣናት ግድያ 43ኛ ዓመት መታሰቢያ

በውብሸት ሙላትና በአምደጽዮን ሚኒሊክ

ደርግ በቁጥጥር ስር አውሏቸው የነበሩት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለስልጣናት (‹‹60ዎቹ››) የተገደሉት ከዛሬ 43 ዓመታት በፊት (ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም) ነበር፡፡

 “እንኳን ሰው ዝንብ አልገደልኩም!”ያሉት ኮ/ል መንግሥቱ የዛሬ 43 ዓመት እነ አክሊሉ ሀብተወልድ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ትእዛዝ የሰጡበትን ሰነድ ዘንግተውት ይሆን?

‹‹ደመወዝ አስጨምሬ ወደመጣሁበት የጦር ክፍል እመለሳለሁ›› ያለው የወታደሮች ስብስብ እርጅና ተጫጭኗቸው ሁሉም ነገር እንደወትሮው አልሆን ያላቸውን ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ከዙፋናቸው አወረደ፡፡ ውሎ አድሮም ስብስቡ ‹‹እኔ ሀገር መምራት ያቅተኛል እንዴ?›› አለና ሀገር ሊመራ ተሰየመ፡፡

ጀኔራል አማን ሚካኤል አንዶም የደርግ ሊቀ-መንበር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ከደርጉ አባላት መካከል ጋር መስማማት አልቻሉም፡፡ ይባስ ብሎ ወደለየለት ስድብና አተካራ ውስጥ ገቡ፡፡ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያምም ስለ ጀኔራል አማን ጉዳይ ለመወያየት የደርጉን አባላት ሰበሰቡ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ከአንደኛው ብርጌድ ስድስተኛ ክፍለ ጦር የተውጣጡ ወታደሮች ጀኔራል አማንን በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ ቢታዘዙም ‹‹እንዴት አማንን በሚያህል ጀግና ላይ አፈሙዝ እናነጣጥራለን? … አናደርገውም!›› ብለው እምቢታቸውን ገለፁ፡፡

በዚህ ምላሽ ክፉኛ የደነገጠው ደርግ ጦሩ አፈሙዙን ወደ ደርግ ሊያዞር እንደሚችል ስጋት ቢገባውም የመጣው ይምጣ በማለት በቅርብ የተገኙ የደርግ ጥበቃ ኮማንዶዎችን ከጥቂት የቡድኑ አባላት ጋር በማጣመር በሻለቃ ዳንኤል አስፋው መሪነት ወደ አማን መኖሪያ ቤት ላከ፡፡ ጀኔራል አማን እጅ እንዲሰጡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከነሻለቃ ዳንኤል ጋር ተኩስ ገጠሙና የተወሰኑትን ገድለው በመጨረሻ ተገደሉ፡፡

ከደርግ አባላት ጋር ስብሰባ ተቀምጠው የነበሩት ሻለቃ መንግሥቱ የጀኔራሉን መገደል ሲሰሙ አጀንዳውን በቁጥጥር ስር ወዳሉት የንጉሰ ነገሥቱ ባለስልጣናት ጉዳይ አዞሩት፡፡ (እርሳቸው ግን በደርግ አባላት ተገድጄ ነው አጀንዳውን ያነሳሁት ብለዋል)

‹‹አማን አንድ ወታደር ነው፤ የእርሱ ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ አይደለም፤ ይልቅ የነዚያን ደም መጣጮች ጉዳይ ዳር ሳናደርስ ከዚህ አዳራሽ አንወጣም›› ያሉት ንዑስ የደርግ አባላት ደርግ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለስልጣናት ስማቸው እየተጠራ ‹‹በለው … ይገደል … ይሙት …›› በሚል የወታደሮች ፍርድ የስብሰባው አዳራሽ ድብልቅልቁ ወጣ፡፡

የሚያስገርመውና የሚሳዝነው ነገር ‹‹በለው … ይገደል … ይሙት …›› ሲሉ የነበሩት ንዑስ የደርግ አባላት ብዙዎቹን ታሳሪዎች በስምም በመልክም የማያውቋቸው መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ብዙዎቹ ታሳሪዎች በሙስና የነቀዙ ግለሰቦች እንደነበሩ የታሪክ ፀሐፍት ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በታሪኳ ዐይታቸው የማታውቃቸውና ለሀገራቸው የደከሙ እንደነአክሊሉ ሀብተወልድ ያሉ ብርቅዬ ሰዎችም ከታሪዎቹ መካከል ነበሩ፡፡ በሙስና የነቀዙት ግለሰቦች ክስም ቢሆን ጉዳያቸውን ለመመርመር በተቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን በኩል መጣራት ይገባው ነበር፡፡

እንግዲህ በዚህ ዓይነቱ አሳዛኝና አስደንጋጭ ውሳኔ 52 የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለስልጣናትና 8 የደርግ አባላት/ባለስልጣናት ሞት ተፈረደባቸውና ተገደሉ፡፡

ሀ). ‹‹ኃይላቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ተጠቅመዋል›› በሚል ውንጀላ የተገደሉ ባለስልጣኖች ባለስልጣኖች (‹‹Gross Abuse of Power››)

1. ፀሃፌትዕዛዝ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ
2. ልዑል አስራተ ካሳ
3. እንዳልካቸው መኮንን
4. ራስ መስፍን ስለሺ
5. አቶ አበበ ረታ
6. ሌተናል ኮሎኔል ታምራት ይገዙ
7. አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ
8. ዶ/ር ተስፋዬ ገብረእግዚዕ
9. አቶ ሙላቱ ደበበ
10. ደጃዝማች ሰለሞን አብርሃ
11. ደጃዝማች ለገሰ በዙ
12. ደጃዝማች ሳህሉ ድፋዬ
13. ደጃዝማች ወርቅነህ ወልደአማኑኤል
14. ደጃዝማች ክፍሌ እርገቱ
15. ደጃዝማች ወርቁ እንቁሥላሴ
16. ደጃዝማች አዕምሮሥላሴ አበበ
17. ደጃዝማች ከበደ ዓሊ ወሌ

ለ). ‹‹ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ተጠቅመዋል›› በሚል ውንጀላ የተገደሉ ባለስልጣኖች (‹‹Gross Abuse of Authority››)

1). አቶ ነብየልዑል ክፍሌ
2). ኮሎኔል ሰለሞን ከድር
3). አፈንጉስ አበጀ ደባልቅ
4). አቶ ይልማ አቦዬ
5) አቶ ተገኝ የተሻወርቅ
6) አቶ ሰለሞን ገብረማርያም
7) አቶ ኃይሉ ተክሉ
8) ብላታ አድማሱ ረታ
9) ልጅ ኃይሉ ደስታ
10) ፊታውራሪ አመዴ አበራ
11) ፊታውራሪ ደምስ አላምረው
12) ፊታውራሪ ታደሰ እንቁሥላሴ
13) ሌተናል ጄኔራል አብይ አበበ
14) ሌተናል ጄኔራል ከበደ ገብሬ
15) ሌተናል ጄኔራል ድረሴ ዱባለ
16) ሌተናል ጄኔራል አበበ ገመዳ
17) ሌተናል ጄኔራል ይልማ ሽበሽ
18) ሌተናል ጄኔራል ኃይሌ ባይከዳኝ
19) ሌተናል ጄኔራል አሰፋ አየን
20) ሌተናል ጄኔራል በለጠ አበበ
21) ሌተናል ጄኔራል ኢሳያስ ገብረሥላሴ
22) ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ደምሴ
23) ሌተናል ጄኔራል አበበ ኃይለማርያም
24) ሜጀር ጄኔራል ስዩም ገድለጊዮርጊስ
25) ሜጀር ጄኔራል ጋሻው ከበደ
26ኛ) ሜጀር ጄኔራል ታፈሰ ለማ
27) ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ
28) ብርጋዴር ጄኔራል ሙሉጌታ ወልደዮሐንስ
29) ብርጋዴር ጄኔራል ግርማ ዮሐንስ
30) ኮሎኔል ያለምዘውድ ተሰማ
31) ኮሎኔል ጣሰው ሞጆ
32) ኮሎኔል ይገዙ ይመኔ
33) ሻለቃ ብርሃኑ ሜጫ
34) ካፒቴን ሞላ ዋቅኬኔ

ሐ). ‹‹የእርስ በእርስ ጦርነት ለመቀስቀስ በተሸረበ ደባ እና ታላቁን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመግታት በተደረገ አሻጥር›› በሚል ክስ ተወንጅው የተገደሉ

1. ካፒቴን ደምሴ ሽፈራው
2. ካፒቴን በላይ ጸጋዬ
3. ካፒቴን ወልደዮሐንስ ዘርጋው
4. ላንስ ኮርፖራል ተክሉ ኃይሉ
5. ወታደር በቀለ ወልደጊዮርጊስ

መ). ‹‹ለመስሪያ ቤት የተገባን ቃል ኪዳን ባለመጠበቅ እና በጦር ኃይሉ ውስጥ ክፍፍል ለመፍጠር ሙከራ ማድረግ›› በሚል ክስ ተወንጅለው የተገደሉ

1). ሌተናል ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም
2). ሌቴናል ጄኔራል ተስፋዬ ተክሌ
3). ጁኒየር ኤርክራፍትማን ዮሐንስ ፍትዊ

እነዚህ ግለሰቦች ከታሰሩበት ተጠርተው እየወጡ በወታደራዊ መኮኒች ተጭነው ተወሰዱና ከ330 በላይ ጥይቶች ተርከፈከፉባቸው፡፡ ይህ ቁጥር በደርግ አባላቱ ብቻ የተተኮሰውን የሚያካትት እንጂ በሌሎች ወታደሮች የተተኮሰውን አይጨምርም፡፡

የመረጃው ምንጮች፡

፩. የኢትዮጵያ የአምስት ሺ ዓመታት ታሪክ ፡ መጽሐፍ ፪ (ካልተረመረለት ልጅ ኢያሱ እስከተዘመረለት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) (ፍስሃ ያዜ ካሣ)
፪. ስለ 60 ዎቹ ባለስልጣናት ግድያ ያልተነገሩ እውነታዎች
፫. የ“60ዎቹ” ግድያ እና ታሪካዊው ደብዳቤ
፬. Nov 23. 1974 – The Day The Derg Massacred 60 Ethiopian Officials
፭. ኖቬምበር 23/1974ን እናስታውስ
፮. ልዩ ልዩ ድረ-ገፆች

ባንታደል ነው እንጂ እነ አክሊሉ ሀብተወልድ በእንደዚያ ዓይነት ሁኔታ መሞት አልነበረባቸውም! ያውም በተራ ወታደር ውሳኔና ተኩስ … Unfair! … ‹‹ውሳኔው የሚያስቅ፣ ፍርዱ የሚያሳቅቅ!››

‹‹እኛን በመግደል ኢትዮጵያን ከድህነቷ የምታወጧት ከሆነ፣ ድርጊታችሁን እንደ ታላቅ በረከት በፀጋ እንቀበላለን››

ፀሐፌ ትዕዛዝ ጠቅላይ ሚንስትር አክሊሉ ኃብተወልድ በደርግ ታጣቂዎች ከመገደላቸው ቀደም ብለው የተናገሩት (ኅዳር 14/1967 ዓ.ም) …

[ማሳሰቢያ ፡ ከላይ የቀረበው ታሪክ ስለሁኔታው በአጭሩ ተቀንጭቦ በመሆኑ እንዲሁም አንዳንድ የስም ስህተቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማወቅ በምንጭነት የተጠቀሱትን መፃሕፍትና ድረ-ገፆችን መመልከት ጠቃሚ ነው]

Filed in: Amharic