>

የኢሕአፓው አምበል የክፍሉ ታደሰ ነገር ... (አቻምየለህ ታምሩ)

ጅብ በማያውቁት ሃገር ሄዶ ቁርበት አንጥፍሉኝ እንዳለው …

የቀድሞው የደርግ አባልና የጎጃም ክፍለ ሃገር የደርግ ተጠሪ የነበረው መቶ አለቃ እሸቱ ዓለሙ ያለ ፍርድ በፈጸመው ዘግናኝ ጭካኔ ዘ-ሄግ ኔዘርላንድስ ውስጥ ክሱ በአንድ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል። የመቶ አለቃ እሸቱ ዓለሙ ጭካኔ አንድና ሁለት የማይባል ነው። የመቶ አለቃ እሸቱ ዓለሙን ጉዳይ አስመልክቶ ከሚወጡ መረጃዎች መካከል አንድ ያስገረመኝ ነገር ቢኖር የኢሕአፓው ክፍሉ ታደሰ ምስክር ሆኖ መቅረብ ነው።

ኢሕአፓ እንደ ድርጅት ምህርት የሌላቸው የጨካኝ ነፍሰ በላዎች ስብስብ ነው። የኢሕአፓ መሪዎች አይደለም ከነሱ አስተሳሰብ የተለየውን ሌላውን ሰው ለራሳቸው ድርጅት አባላት እንኳ ርህራሔ የሌላቸው በዱልዱም የሚያርዱ ነፍሰ በላዎች ናቸው። የኢሕአፓ መሪዎች በግፈኛነታቸው ከደርግ ቢበልጡ እንጂ አያንሱም። ክፍሉ ታደሰም እንደ ኢሕአፓ ማዕከላዊ አባልነቱና ስራ አስፈጻሚነቱ በንጹሀን ላይ እየፈረደ ሲያስረሽን የነበረ የኢሕአፓው እሸቱ ዓለሙ ነው። በንጹሃን ሕይወት ላይ እየፈረደ ሲያስረሽን የነበረው ክፍሉ ታደሰ መልኩን በመስታዎች እያየ በእሸቱ ዓለሙ ላይ ምስክር ሆኖ መቅረቡ ጅብ በማያውቁት ሃገር ሄዶ ቁርበት አንጥፍሉኝ አለ የሚለውን እንዳስታውስ አድርጎኛል። ንጹሀን እንዲገደሉ እየፈረደ ሲያስረሽን የኖረው ክፍሉ ታደሰ ምን ንጽህና ኖሮት ነው በእሸቱ ዓለሙ ላይ ምስክር ሆኖ የቀረበው?

በእሸቱ ዓለሙ ላይ ግፉዓን ለምስርክት ቢቀርቡ የተገባ ነው፤ ያስረሸነው ሰው የአስከሬን ቁራጭ እንኳ እንዳይገኝ አድርጎ ክቡሩን የሰው ልጅ ሙት ገላ በአሲድ ድምጥማጡን እያጠፋ ሲረሽንና ሲያስረሽን የኖረው ክፍሉ ታደሰ እሸቱ ዓለሙን ወንጀለኛ ነው ብሎ የመመስከር የሞራል ልዕልና የለውም። አገርና ሕግ ቢኖረን ኖሮ እሸቱ አለሙም ሆነ ክፍሉ ታደሰ ባንድ ላይ እጃቸው የፍጥኝ በመጫኛ ታስሮ በረሸኑት ሕዝብ ፊት ለፍርድ ይቀርቡ ነበር።

Filed in: Amharic