>
4:34 pm - Sunday October 16, 8304

የታማኝ በየነ ታማኝ ትንቢት (ሃብታሙ አያሌው)

ትንቢት.1

አርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የመናገር ብቻ ሳይሆን የመተንበይ ክህሎቱም ከፍ ያለ እንደሆነ በልበ ሙሉነት መናገር ይቻላል!
“ዛሬም ፈፅሞ ነፃ አይደለንም !
ዛሬም በመሳሪያ አገዛዝ ስር ነን”
ታማኝ በየነ 1983 ዓ.ም

ገና በጠዋት ነፍጥ ያነገቱት የህወሓት በርኽኞች የአዲስ አበባን አስፓልት በኮንጎ ጫማና በታንክ ጎማ ሲረመርሙ የነፃ አውጭነት ካባቸውን በልብ አድርስ ንግግሩ ከትከሻቸው ሞሽልቆ “we are not free at all, we are still under the gun !” (ዛሬም ፈፅሞ ነፃ አይደለንም፤ ዛሬም በመሳሪያ አገዛዝ ስር ነን ያለው ጉጅሌዎቹ ሚኒሊክ ቤተመንግስት ደርሰናል ብለው እንዳወጁ ነበር።1983 ዓ.ም

‘ዛሬም’ በማለት የዕለትን ተሻግሮ መፃዒውን ማመላከት ከስነ – ቋንቋ ወይም ከስነ – ፅሑፍ በላይ ትንቢታዊነቱ ጉልህ ስለመሆኑ መፅሐፍ ቅዱስ አስረጂ ነው። ዘመኑ ገና አመተ ፍዳ ሆኖ ሳለ ወደፊት ከሺህ ዓመት በኋላ የሚሆነውን አሻግሮ በትንቢት መነፀር በማየት “ፅዮን ሆይ ሙሽራሽ መጥቷል” ይላል። ወደፊት  የሚሆነውን ዛሬ አምጥቶ ተወልዷል ይላል።
==
የታማኝን ቃል 1983 ዓ.ም የሰማው ሰው ከሃያ ስድስት አመታት በኋላ ዛሬም ሲሰማው ያው አንድ ነው፤ ያው እውነት ትላንትም ዛሬም ህያው ነው። BBC ፕሮግራሙን ቢደግመው (የዛሬ ብሎ ቢያስተላልፈው) በይዘትም በቃላትም ሳይታረም የዛሬ ዜና መሆን ይችላል። ከጋዜጠኛውና ከታማኝ እድሜና ተክለ ሰውነት በቀር የተለወጠ አንዳች ነገር የለም። ስለዚህም ነገር ታማኝ መፃዒውን ተንብዮ ነበር እንላለን።

ትንቢት. 2

“እንዳንጠያየቅ ፓስፖርትና ቪዛ”

ህወሓት ይዞብን የመጣውን የጎሳ ፖለቲካ መርገም ያለተርጓሚ ተረድቶ የመጨረሻውን አስከፊነት ትላንት ላይ ሆኖ ዛሬን የተነበየበት የታማኝ በየነ የትንቢት ቃል ነው።
==
ዛሬ የትንቢቱ ቃል ደርሶ አንዱ ክልል ከሌላኛው ክልል የመጣውን ወደ ክልልህ ሂድ ሲል እያፈናቀለ በኩራት መግለጫ የሚሰጥበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ተማሪዎች የመማሪያ ጓዛቸውን እየሸከፉ ዩኒቨርሲቲያቸውን ለቅቀዋል። እንደ ታማኝ ትንቢት ቪዛ ጥየቃው ዛሬ ሃላል ሆኖአል።

ትንቢት. 3

“የአንድ ብሔረሰብ አባላት በበላይነት በሚረግጧት ሀገር እንዴት ስለ እኩልነት ማውራት ይቻላል ! ይሄን ግፍ ከዚህ በላይ መሸከም አይቻልም” ታማኝ የእኩልነት ዘመን በሚል በኢሳት ባቀረበው ልዩ ዝግጅት የተናገረው።

የታማኝ የትላንቱ ትንቢታዊ የማስጠንቀቂያ ቃል። ዛሬ እውን ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ዳር እስከዳር “Down Down Weyane” ወያኔ ይውደም እያለ ነው። ታማኝ “በእኩልነት ዘመን” ፕሮግራሙ በተለይ ህወሓት ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው የመከላከያ ተቋም ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ በማስረጃ እየዘረዘረ አስረድቶ ነበር። ዛሬ ያ’ የመከላከያ ሽፍታ ቡድን በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል በጭካኔ የዜጎችን ነፍስ ይቀጥፋል፤ የሀገርን እምብርት ገልብጦ ይዘርፋል። ከስር ማስረጃው እንደሚያመለክተው በባሌ ቦረና ዞን ዲሽቃ ይዞ ከሰባ አመት በላይ የሆኑ አዛውንትና ከአስር አመት በታች የሆኑ ህፃናትን በግፍ የጨፈጨፈው ሀገር እየመዘበረ ንብረት እያሸሸ ያለው የመከላከያ ቡድን ስለመሆኑ በደብዳቤ ያረጋገጡት የወረዳው አስተዳዳሪ ናቸው። የታማኝ የትላንት እንባና ምሬት ዛሬ የኦሮሚያ አስተዳደርም ምሬትና እንባ ሆኖአል። ታማኝ “ይሄን መሸከም አይቻልም” ሲል የተነበየው ስለመድረሱ እልፍ እውነቶች ትንቢቱን ስሙር በማድረግ እያረጋገጡ ነው።
==
በቅርቡ የአማራ አስተዳደር እና የትግራይ አስተዳደር ብአዴንና ህወሓት በጎንደር ከተማ ባደረጉት ስብሰባ
ህወሓት ለገባበት አጣብቂኝ፤ ለደረሰበት ውድቀት ዋነኛ ተጠያቂ ኢሳትና ታማኝ በየነ ናቸው ሲል በይፋ የከሰሰበት ምክንያት በእርግጥም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ ይሰማኛል። አዲስ አበባ እግራቸው ሲረግጥ ከፍ ባለ ተቃውሞ በጎ እድል ሳይሆኑ መርገም መሆናቸውን አጋልጦ መፃኢ ጉዞአቸውን እየተነበየ 26 ዓመታት (በግዛት ዘመናቸው ልክ የተቃወመቻውን) ዋነኛ ጠላት ማለታቸው ባይገርምም አይጠቅምም እያለ ያወገዘውን እነሱን አምርሮ የተቃወመበትን ዘረኝነት ገልብጠው ለሱ በመስጠት “ለነ ታማኝ በየነ ብለን አማራ ትግሬ አንባባልም ኢትዮጵያዊነን” ያሏት ቧልት መታለፍ የለባትም። በርግጥ ዘረኝነቱ የነሱ ወይስ የታማኝ በየነ ? እቺ የቦታ እንቀያየር ነገር ወዴት ወዴት እያመራች ነው ? ታማኝ ዛሬስ ምን ይተነብያል ?
ይቆየን …

Filed in: Amharic