>

“እናት ድርጅት ፥ ግንባር ቀደም በሉኝ ስገዱልኝ” ባይዋ ህወሓት ••• (ያሬድ ጥበቡ)

ህዳር 20 ቀን 2010 ዓም የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ያወጣውን የአቋም መግለጫ ጊዜ ወስጄ አነበብኩት ። በአንድ በኩል እጠብቀው የነበረው “ጠባብነትንና ትምክህተኝነትን እንደመስሳለን” የሚል የተለመደ ፉከራ ባለመሆኑ መደሰቴን መደበቅ አልችልም ። በተጨማሪም “ሃገራችን ኢትዮጵያ” ብሎ በተደጋጋሚም ለመግለፅ መድፈሩ “የመለስ አምልኮ” መሸርሸር መጀመሩን የሚያበስር መስሎ ተሰምቶኝ ነበር ። አሁን ከኦሮም ሕዝብና ከኦህዴድ የተሰነዘረበት ተቃውሞ ሥር የሰደደና በባዶ ፉከራ የሚመለስ አለመሆኑን መረዳቱ በራሱ ቢያንስ ብልጥነቱን ይጠቁመን ይመስለኛል ። ሆኖም አሁን የብልጥነት ሰአት አይደለም ። መግለጫው የስርአቱና የድርጅቱ መሰረታዊ ችግሮች የሚላቸውን ያነሳል ። በጣም በደምሳሳው ። ሆኖም ዝርዝር ላይ ወገቤን ይላል ።

የህወሓቱ መግለጫ “አመራሩ•••ህዝብንና ዓላማን ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ክብርና ጥቅም የሚያስቀድም መሆኑ ታይቷል” ብሎ ሲያበቃ ፥ እዚያው በዚያው፥ “የሂስና ግለሂስ መድረኩ ዓላማ በግለሰብ አመራር አባላት ላይ ያተኮረ ሳይሆን •••” ብሎ መሰስ ይላል ። ህዝቡ ከሚጠይቃቸው አያሌ የሙስናና የህዝብ ንብረት ውድመት ውስጥ አንዱን እንኳ ባነሳ በአቶ አባይ ፀሃዬና በሜቴክ ጄኔራሎች ሽርክና ቀልጦ ለቀረው የስኳር ፋብሪካዎች ማቋቋሚያ 77 ቢሊዮን ብር (77 000 000 000) ፥ አንዲትም ቃል እንኳ የማይተነፍስበት ዓይኑን ያፈጠጠው ትልቁ ችግር ሙስና ወይም ንቅዘት ነው ። በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር በሚሰረቅባት ሃገር ውስጥ፥ የገዢው ፓርቲ አባል የሆነ ድርጅት ለዚያውም እናት ድርጅት በሉኝ ፥ ስገዱልኝ ፥ ግንባር ቀደም በሉኝ ብሎ እህት ድርጅቶቹን የሚያጠራቅቅ ሃይል ዓይኑ ውስጥ የተጋደመውን ፍልጥ ማየት የተሳነው ፍልጡ ስላወረው ይሆን? ወይስ በኢትዮጵያችን ስለተንሰራፋው የሙስና ችግር ሃላፊነት ቢወስድ ተጠያቂነትን ስለሚያስከትልበት ሰግቶ ይሆን?

መግለጫው “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሲደረጉ ከነበሩት የይስሙላ ግምገማዎች በዓይነቱና መልኩ የተለየ ችግሮቹን በሚገባ ለመለየት ያስቻሉት መተጋገል አካሂዷል” ብሎን ተስፋ ከሰጠን በሁዋላ በመግለጫው ውስጥ የተነሱትን ችግሮች ከዓመታት በፊት አንስተው በመሞገታቸው ለተሰደዱ ሃገራቸው መመለስን ፥ ለታሰሩ ነፃነትን ፥ ለተገደሉ የንብረት ካሳንና ከልብ የመነጨ ይቅርታን ስንጠብቅ ፥ “የፌዴራል ስርዓት ጠላቶች ያጠመዱልን ወጥመድ ውስጥ ገብተን የሃገራችንን ኢትዮጵያ ህልውና ፈተና ላይ እንዲወድቅ” አደረግን ብሎ አረፈው ። ከዚህ የባሰ የይስሙላ ግምገማ ከየት ይመጣ ይሆን? እጅግ አሳፋሪ መግለጫ ነው ። ህወሓት ከይስሙላ መግለጫ መራቅ ከፈለገ በጣም በደምሳሳው ያነሳቸውን ሃገራዊ ዙሪያ መለስ ችግሮች ሲያነሱ የነበሩትን ጋዜጠኞች፥ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች፥ አርቲስቶች ወዘተ ከወህኒ መልቀቅ፥ ለደረሰባቸው እንግልት ይቅርታ መጠየቅና ተገቢ ካሳ መክፈል ይገባዋል ። ይህን ሳያደርግና ከልብ መፀፀቱን ሳያሳይ የበላይ አመራሩን በአንድ ቤተሰብ ወጣቶች ተክቻለሁና ተቀበሉኝ ቢል “ቱሪስት ብላ፥ ያውም ከነካሜራው” መባሉ አይቀርም

በወያኔ ኢትዮጵያ በግልም ሆነ በቡድን ተጠያቂ የሚሆን ማንም “የቤተሰቡ አባል” የለም ። የወያኔ አመራር አባል ሲያጠፋ ለጊዜው ይወርዳል እንጂ ለሰረቀው ገንዘብም ሆነ ላጠፋው ህይወት አይጠየቅም ። እንዲያውም የባንክ ብድር ይመቻችለታል ። አመራሩ አድዋዊ ነው ቢባልም ፥ ጠጋ ብሎ ለመረመረው ግን ቤተሰባዊና በጥቅምና ጋብቻ የተሳሰረ ማፊያዊ ሃይል ሆኖ ገጦ ይወጣል ። አበስኩ! እጅግ አሳፋሪ መግለጫ ነው ። ኦህዴድና ብአዴን ይህን በቂ መግለጫ ነው ብለው ከሚቀበሉ ፥ መቀሌ ተመለሱና በጥልቅ ተሃድሶ አድርጋችሁ የቤተሰብ አመራራችሁን አፍርሳችሁ ፥ ታላቁን የትግራይ ህዝብ የሚወክል አመራር ይዛችሁ ተመልሳችሁ ኑ ፥ እናንተ እስክትመጡ ግን እንዳለፈው ጊዜ ቁጭ ብለን አንጠብቃችሁም፥ ሃገሪቷ መስቀለኛ መንገድ ላይ ስላለች እየሰራን እንጠብቃኋለን ሊሏቸው ይገባ ይመስለኛል ።

Filed in: Amharic