>
4:34 pm - Sunday October 16, 1301

ሕወሐት የነደፈው ፍኖተ ካርታ (road map) ኢትዮጵያን ወዴት ይወስዳታል? (ኢ/ር ይልቃል ጌትነት)

ሕወሐት ከመቀሌው ስብሰባ አንድ የተግባር ማስፈፀሚያ ማለትም “በታላቁ መሪያችን መለስ ዜናዊ ባለቤት ታጋይ አዜብ መስፍን ላይ የጨከነ ድርጅት ለጠባብና ትምክሕት ኃይሎች አይንበረከክም” የሚል መፈክር ይዞ የመጣ ይመስላል፡፡
የሕወሐትን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አጠቃላይ ይዘት ስንገመግመው እኩል ለጋራ ዓላማ የታገሉ ሰዎች ጊዜ በሄደ ቁጥር አሁን ባላቸው አኗኗር፣የስልጣን ቦታ፣ተሰሚነት፣የጥቅም ትስስር፣የወንዝ ልጅነትና አምቻ ጋብቻ እና አጠቃላይ ከባቢያዊነትን መሰረት አድርጎ በመቧደን ለድርጅት የበላይነት የሚደረግ ሽኩቻ ጎልቶ የታየበት እንደነበረና ይህም የሚጠበቅ እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ነገር ግን በዚህ ሽኩቻ ውስጥ የትኛውም ቡድን ቢያሸንፍ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ በሚረዱበትና መፍትሔ በሚሉት የአስተሳሰብ መስመር ላይ ምንም ልዩነት የላቸውም፡፡
የመቀሌውን የሕወሐትን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ጨምሮ የብሐራዊ ደህንነት ምክር ቤት ዕቅድ ተብሎ በአዲስ መልክ መምጣት፣የመከላከያ ሚኒስትሩ የአቶ ሲራጅ ፈጌሳ ከስብሰባ በኋላ የሰጡት መግለጫ፣በትግራይና አማራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወቅት አቶ በረከት ያደረጉት ንግግር፣ በሕወሐት የተወሰደው እርምጃ እና የሕወሐት/ኢሕአዴግ ደጋፊ በሆነው አይጋ ፎረም ጥቅምት 21 ቀን 2010 ዓ.ም “የኢሕአዴግ የመፍረስ አደጋና የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ” በሚል ርዕስ የወጣውን ባለ 25 ገፅ ትንታኔ አያይዘን ስንመለከተው የወቅቱን የሀገራችንን ፖለቲካ በተመለከተ በሕወሐት በኩል አንድ የተደረሰ ድምዳሜ እንዳለ ያሳያል፡፡ ይሕውም
1.የቀድሞው ጥልቅ ተሃድሶ ውጤታማ እንዳልነበረ
2.የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በከፊል መቆየት እንደነበረበት
3.በኢሕአዴግ በኩል ከባድ የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠና ይህም ሀገራችንን ለእርስ በእርስ ጦርነት እና የብተና አደጋ ሊዳርግ ይችላል የሚል ሲሆን በምክንያትነት የሚያቀርቡትም የኢሕአዴግ አሴቶች የነበሩት ሕዝባዊነትና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በአባል ድርጅቶቹ እየተሸረሸሩ ነው የሚል ነው፡፡
በአጠቃላይ በአይጋ ፎረሙ ፅሁፍ መሰረት ትግራይ በመቶ ሺዎች የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ በፀረ ዲሞክራቶችና በፀረ ኢሕአዴጎች እየተደቆሰ ነው፣አማራ በትምክህተኞችና በኪራይ ሰብሳቢዎች እየተደቆሰ ነው፣የኦሮሞ ህዝብ በትግሉ የጠፋው የኦነግ አስተሳሰብና ተግባር ሊውጠው ተነስቷል ስለሆነም በእነዚህ ተፃራሪ ሃይሎች ኢሕአዴግ ሊቀጥል አይችልም፤ኢሕአዴግ አንድነቱን ይዞ መቀጠል ካልቻለ ደግሞ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ እንደ ቀድሞው ይጎዝላቪያ መበታተን ይሆናል የሚል ነው፡፡
በሕወሐት ግምገማ ይህንን የድርጅትና የሀገር መፍረስ አደጋ ለመታደግ በሕወሐት የተጀመረውን ግምገማ በሞዴልነት በመውሰድ በሌሎች አጋር ድርጅቶች ስር ነቀል ግምገማ በማድረግ በሚደረስበት ውጤት በትምክህትና ጠባብ ሃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ የሚል ነው፡፡ ሕወሐት ስርዓት አልበኝነት ከመንገሱ በፊትና ሀገር በወሮበሎች ከመተራመሷ በፊት የቱርክ ፕሬዝደንት ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር እንደወሰዱት ዓይነት እርምጃና የእስፔን መንግስት ህገ መንግስቱን ለማስከበር በካታሎን ተገንጣዮች ላይ የወሰደውን ዓይነት ቆራጥ እርምጃ መውሰድ አለብን በማለት በባለ 25 ገፅ ፅሁፍ ይገልፃል፡፡
የአሁኑ የሕወሐት አጠቃላይ የችግር ግምገማና የመፍትሔ አቅጣጫ ምንም ዓይነት የአስተሳሰብ ለውጥ ያልታየበት ያለውን ሀገራዊ ችግር የፖሊሲና የአስተሳሰብ ሳይሆን የድርጅት የማስፈፀም አቅም ችግር አድርጎ በማየት አሁንም በተለመደው መንገድ በመቀጠል ከቀድሞው በባሰ ከችግሩ መግዘፍና አስቸኳይነት በመነጨ ድንጋጤ ጠንከር ያለ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ ያቀደ ከተፈጥሯዊ የችግር እድገት ጋር ተያይዞ የተሰጠ ምላሽ (chain reaction) ነው፡፡ በመሆኑም የሀገራችን ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ በመምጣቱ የሚወስዱትም እርምጃ ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን ከማሳየት ባለፈ ሕወሐት ሀገራችን ላለችበት ሁኔታ የሚመጥን መፍትሔ ለማምጣት ፍላጎትም ሆነ አቅም እንደሌለው በግልፅ ያሳያል፡፡ በ1993 ዓ.ም ያደረገውን የድርጅት ተሃድሶ አሁን ላለው ችግር መፍትሔ ለመስጠት በምሳሌነት በመውሰድ አሁንም በድርጅታዊ የፖለቲካ ሽኩቻ ቅርቃር ውስጥ ሆኖ አሁን ላለው የኢትዮጵያ ችግር ተመሳሳይ መፍትሔ ለመስጠት እየጣረ ነው፡፡
ሕወሐት መገንዘብ ያልፈለገውና ያልቻው ነገር ቢኖር ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ አሁን እስካለንበት 2010 ዓ.ም ድረስ ያለውን የፖለቲካ እድገት ነው፡፡ በአለፉት 17 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ከገጠር ወደ ከተማ ፍለሰት ተፈጥሯል፣ከፍተኛ የወጣት ቁጥር ወደ ስራ ኃይልነት (work force) በመግባቱ ከፍተኛ የሆነ የስራ አጥ ቁጥር ተጥሯል፣በአረብ አቢዮት ምክንያት በተቀሰቀሰው የለውጥ ፍላጎት አዲስ የፖለቲካ አመለካከት ተፈጥሯል፣የመረጃ ልውውጥና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚነት ጨምሯል፣የኑሮ ውድነት፣ሙስና፣የገቢ መራራቅና የአስተዳደር ብልሹነት ተስፋፍቷል፣በሕወሐትና በሌሎች የግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል የነበረው የጌታና የሎሌ ግንኙነት ተሸርሽሯል፣ህዝቡም በደረሰበት ጭቆና ግፍ ምክንያት ያለማንም ቀስቃሽ በራሱ ጊዜ የመብት ጥያቄዎችን አንግቦ መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ሕወሐት አሁን ይዞት የመጣው የመፍትሔ አቅጣጫ ከላይ የጠቀስኳቸውን ነባራዊ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ያላስገባ ስለሆነና እነዚህን ግምት ውስጥ አስገብቶ ሀገራችን ያለችበትን ችግር የሚመጥን መፍትሔ ለመስጠት የተፈጥሮ ባህሪው የሆነው የአናሳ አገዛዝ (minority rule) ስለማይፈቅድለት የነበረውን የችግር አፈታት ዘዴ ለማጠናከር ከመሞከር ባለፈ ምንም አዲስ ነገር የለበትም፡፡ ስለዚህ የሕወሐት ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ መሆኑን በመገንዘብ የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ በለውጥ ሃይሎች እጅ ብቻ የወደቀ በመሆኑ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በኃላፊነትና በአጣዳፊነት ከባድ ስራ መስራት ይጠበቃል፡፡

Filed in: Amharic