>
5:16 pm - Wednesday May 23, 6390

የህወሓት ፈርቶ-ማስፈራራት ራሱን ለውድቀት፣ ሕዝብን ለዕልቂት ይዳርጋል! (ስዩም ተሾመ)

አንዳንድ የህወሓት/ኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ከሰሞኑ ሹም-ሽር በኋላ ፌስቡክ ላይ “ምነው ፍርሃት…ፍርሃት አላችሁ?” እያሉ መሳለቅ ጀምረዋል። እንዲህ ያለ የፖለቲካ ዝቅጠት ማየትና መስማት ስለሰለቸኝ አብዛኞቹን ከፌስቡክ ጓደኝነት አግጄያቸዋለሁ። ሆኖም ግን፣ ከእኔ እይታ ውጪ የሚናገሩትና የሚፅፉት ነገር የጋራ በሆኑ ጓደኞች አማካኝነት ወደ እኔ ይመጣል።

በእርግጥ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መሳለቅና መበሻሸቅ የተለመደ ስለሆነ ብዙዎቻችሁ “አሁን ይሄ ምን የተለየ ነገር አለው?” የሚል ጥያቄ እንደምታነሱ እገምታለሁ። ነገር ግን፣ ከህወሓቶች ማስፈራሪያ በስተጀርባ ያለውን እውነታ ለሚያውቅ ድርጊቱ የመጨረሻ የፖለቲካ ድንቁርና መገለጫ እንደሆነ ይገነዘባል። ምክንያቱም፣ የሰሞኑ ማስፈራሪያ፤ አንደኛ፡- የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ፍርሃት ያጋልጣል፣ ሁለተኛ፡- የራሱን የበላይነት ለማስቀጠል ቆርጦ መነሳቱን ያረጋግጣል፣ ሦስተኛ፡- ፈርቶ-ማስፈራራት ራሱን ለውድቀት፣ ሕዝብን ለዕልቂት ይዳርጋል። “ለምንና እንዴት?” ለሚለው የተለያዩ ፅሁፎችን ዋቢ በማድረግ ጉዳዩን በዝርዝር እንመለከታለን።

በመጀመሪያ ደረጃ የአንድን ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ፖለቲካዊ ንቅናቄ በዘውግ ብሔርተኝነት (ethnic-nationalism) በመቆስቆስ እና በራስ የመወሰን መብት (the right of self-determination) ዓላማ በማድረግ፣ በትጥቅ ትግል አማካኝነት ወደ ስልጣን የመጣ የፖለቲካ ቡድን ሌሎች አብላጫ ድምፅ ያላቸውን ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ተመሳሳይ የፖለቲካ ንቅናቄ እንዳይጀምሩ ማድረግ አለበት። ምክንያቱም፣ አብላጫ ድምፅ ያላቸው ማህብረሰቦች በተመሳሳይ የፖለቲካ ንቅናቄ ማድረግ ከቻሉ የአነስተኛ ብሔር የስልጣን የበላይነትንና ተጠቃሚነትን በቀላሉ ማስወገድ ይችላሉ።

ስለዚህ፣ አብላጭ ድምፅ ያላቸውን ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በጎሳ፥ ብሔርና ቋንቋ በመከፋፈል የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ እና የተቀናጀ ንቅናቄ እንዳይኖራቸው ማድረግ የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ በሚወክለው ማህብረሰብ ዘንድ የፖለቲካ ንቅናቄ ለመፍጠር የተጠቀመበትን የዘውግ ብሔርተኝነት ስልት አብላጫ ድምፅ ባላቸው ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ተመሳሳይ የፖለቲካ ንቅናቄ እንዳይፈጠር ለማድረግ ይጠቀምበታል።

እንዲህ ያለ የፖለቲካ ቡድን የቆመለትን የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ሊያሳጣው የሚችል ለውጥና መሻሻል ወይም ሃሳብና አስተያየት ተቀብሎ ለማስተነገድ ዝግጁ አይደለም። በተለይ ደግሞ በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ምንም ዓይነት የማሻሻያ ሃሳብና ድርድር ለማድረግ ፍቃደኛ አይደለም። በመሆኑም፣ ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የሚነሳ የመብትና ነፃነት በኃይልና በጉልበት ለማዳፈን ጥረት ያደርጋል።

በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥና መሻሻል ለማድረግ ዝግጁ ባለመሆኑ ምክንያት እያንዳንዱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፍርሃትና ጥርጣሬ ይመለከታል። ይህንንም በኃይልና በጉልበት በማዳፈን ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል እና የፖለቲካ ልሂቃን መንግስትን እንዲፈሩ፣ በዚህም የስርዓቱን ሕልውና ለማስቀጠል ጥረት ያደርጋል።

የብዙሃኑን እኩልነት የሚገድብ እንደመሆኑ ጨቋኝ ነው። የመብትና ነፃነት ጥያቄ በሚያነሱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ በሚፈፀመው አሰቃቂ ግፍና በደል ደግሞ ጨካኝ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። በዚህ መሰረት፣ የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ጨቋኝና ጨካኝ ነው። እንደ ፈረንሳዊው ምሁር “Montesquieu” አገላለፅ “ፍርሃት” (fear) ጨቋኝና ጨካኝ መንግስት (tyranny) መርህና መመሪያ ነው፡-

 “[E]ach government has a particular “principle” which sets it in motion. In a republic the principle of action is equality and in a tyranny, the principle of action is fear. These moving and guiding principles rule both the actions of the government and the actions of the governed.” An Essay (pdf) in Understanding the Nature of Totalitarianism.

በዚህ መሰረት፣ ፍርሃት (fear) የጨቋኝና ጨካኝ መንግስት መርህና መመሪያ ነው። በተቃራኒው፣ በየትኛውም ግዜ፥ ቦታና ፖለቲካዊ ስርዓት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ፖለቲካዊ ጥያቄ እኩልነት ነው። ምክንያቱም፣ እንደ “Montesquieu” አገላለፅ፣ “እኩልነት” (equality) የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው፡-

“[The] natural love of equality includes love of others as well as love of self, and egoism, loving one’s self at the expense of others, is an unnatural and perverted condition…..” An Essay (pdf) in Understanding the Nature of Totalitarianism.

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ “ፍርሃት” የጨቋኞች ባህሪ ሲሆን “እኩልነት” ደግሞ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። ስለዚህ ሁሉም ሰዎች መብትና ነፃነታቸው እስካልተከበረ ድርስ ዜጎች የእኩልነት ጥያቄ ከማንሳት ወደኋላ አይሉም። ጨቋኞች ደግሞ የእኩልነት ጥያቄ ባነሳው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ አይታቆጠቡም።

ጨቋኞች ለራሳቸው ፈርተው ሕዝብን ያስፈራራሉ። ሕዝብ ደግሞ ጭቆናን ተቀብሎ መኖር ከማስፈራሪያው በላይ ያስፈራል። በመሆኑም፣ የእኩልነት ጥያቄን በጉልበት ለማዳፈን ጥረት በተደረገ ቁጥር አመፅና ተቃውሞ በስፋትና ዓይነት እየጨመረ ይሄዳል። በአንድ አከባቢ በኃይል ያዳፈኑት የሕዝብ ንቅናቄ በሌላ ግዜ እና/ወይም ቦታ ተመልሶ ብቅ ይላል።

በዚህ መሰረት፣ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ ይሄዳል። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በዚያው ልክ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ከቀድሞ ግዜ በበለጠ ሁኔታ ሕዝብን ለማስፈራራት ጥረት የሚያደርግ ከሆነ የሰዎች ባህሪ ፍፁም ይቀየራል። ሕዝቡ በሚያስፈራሩት አካላት ላይ እጅግ በጣም ጨካኝ ይሆናል። ፈፅሞ ባልተጠበቀ መልኩ የኃይል እርምጃ ይወስዳል። ይሄን “Edmond Leach” የተባለው ምሁር እንደሚከተለው ገልፆታል፡-

በዚህ መልኩ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ድንገት ከቁጥጥር ውጪ ይወጣል። የመንግስት ባለው ነገር ላይ ሁሉ የኃይል እርምጃ ይወስዳል። በመንግስት የፅጥታ ኃይሎችና ደጋፊዎች ላይ ያልታሰብ ግፍና በደል ይፈፀማል። በዚህ መሰረት፣ መንግስት ለራሱ ፈርቶ ሕዝብን ሲያስፈራራ፤ በራሱ ላይ ውድቀት፣ በሕዝብ ላይ ዕልቂት ያስከትላል። በመጨረሻም ፈርተው ለሚያስፈራሩ የውድቀትና ዕልቂት መልዕክተኞች በ”Malfunction Records” ተዘጋጅቶ የቀረበውን “Climate of Fear” የተሰኘውን የ”Bitter End” ሙዚቃን በመጋበዝ እሰናበታለሁ፡፡

Filed in: Amharic