>
4:35 pm - Wednesday October 19, 7031

የፕሮ. ሕዝቅኤል ገቢሳና የስሉጥ አቻምየለህ ታምሩ ክርክር ሲዳሰስ ሲፈተሽ! (አምሳሉ ገብረኪዳን)

በኅብር ራዲዮ (ነጋሪተ ወግ) አማካኝነት ፕሮ. (ሊ.ጠ.) ሕዝቅኤል ገቢሳና አክቲቪስት (ስሉጥ) አቻምየለህ ታምሩ ያደረጉትን ክርክር አዳመጥኩት፡፡ አስቀድሜ ኅብር ራዲዮን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ያወያዩን ማለቴ የጋዜጠኛ (ዘጋቢ) ሀብታሙ አሰፋን ብቃትም ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ አቻምየለህንም ጎሽ ተባረክ! ብያለሁ፡፡

እንዳዳመጣቹህት የክርክሩ መንስኤ የነበረው ፕሮ. ሕዝቅኤል በቅርቡ ለነጮች “የአማራ ልኂቃን የቀድሞውን ሥርዓት ለመመለስ ይፈልጋሉ…!” የሚለው ግልብ ክስ ነው፡፡ ሊጠ. ሕዝቅኤል ገቢሳ “የቀድሞ ሥርዓት!” የሚለው የዐፄ ምኒልክንና የዐፄ ኃይለሥላሴን አሥተዳደር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አቻምየለህ መረጃዎቹን ሁሉ በዚህ የአሥተዳደር ዘመን ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ለማድረግ ተገዷል፡፡

ግራ ዘመምና ጽንፈኛ የኦሮሞ ልኂቃን በርካታ ለነሱ የማይመቹና እነሱን የሚያሳፍሩ የሚያሸማቅቁ ችግሮች ስላለባቸው ከዘመነ ዐፄ ምኒልክ ወደ ኋላ ሻገር ብለው ማሰብም ሆነ መነጋገር ፈጽሞ አይፈልጉም፡፡ ተራራ ተራራ የሚያካክለውን ኩነኔ ተሸክመው በጥቃቅኑ ሁሉ ሌላው ላይ ጣት ሲቀስሩ ጉድፍ እንኳ ያለባቸው አያስመስሉም፡፡

ከክርክሩ እንደታዘባቹህት የተማረ የተባለው ሊ.ጠ. ሕዝቅኤልም እንደሌሎቹ ጓዶቹ ሁሉ የራሳቸውን ግመል ግመል የሚያካክል ኃጢአት ሰውሮ ሌላው ላይ ያለችን ትንኝ ትንኝ የምታካክል ኃጢአት እያካበደ በማውራት እውነታን ለማዛባትና ለፖለቲካዊ ጥቅሙ ለመጠቀም ሲንደፋደፍ በመስተዋሉ በእርግጥም “እውነት ይሄ ሰው የተማረና ከአንድ የተማረ ሰው የሚጠበቀው የኃላፊነት ስሜት የሚሰማው፣ ለአመክንዮና ለእውነታ የመገዛት የሞራል (የቅስም) ግዴታና ብስለት ያለው ሰው ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ ማስነሣቱ የሚገርም አይመስለኝም፡፡

የኦሮሞ ልኂቃን ከአማራ ልኂቃን ምን እንደሚፈልጉ ታውቃላቹህ? በአማራ ላይ የሚያቀርቧቸውን ሐሰተኛና የፈጠራ ክሶችን፣ ስም ማጥፋቶችን ሐሰተኛነት የሚያረጋግጡትንና የሚያጋልጡትን ከቋጥኝ የገዛዘፉ መረጃዎችንና እውነታወችን ዋጥ አድርገን እነሱን ሳናነሣ የሚያቀርቧቸውን የፈጠራ ክሶችንና ስም ማጥፋቶችን እውነት ነው ብለን አምነን ተቀብለን በእነኝህ ሐሰተኛ ክሶችና ስም ማጥፋቶች ላይ የሚመሠረት ስምምነት ላይ እንድንደርስ ነው የሚፈልጉት፡፡ አይገርሟቹህም??? በየትኛውም ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ ያለ ግራ ዘመምና ጽንፈኛ የኦሮሞ ልኂቅ ከዚህ አለፍ ብሎ ምሁርነት በሚያላብሰው ሰብእና ላይ በመመሥረትና በመቃኘት ማሰብና መሥራት አይፈልግም፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ተብሎ ከነሱ ጋር መግባባት እንደሚቻል አይገባኝም፡፡

“ለምን አትወያዩም? ፣ ለምን አትመክሩም? ፣ ለምን አትደራደሩም?” ለሚለው ከየአቅጣጫው ለሚመጣ ጥያቄ በጎ ምላሽ የሰጡ፣ ቀና አመለካከት ያላቸው ለመምሰልና ፍትሐዊ የሆነ ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) መፍትሔ የሚሹ መስለው ለመታየት በየውይይት መድረኩ ይገኛሉ እንጅ እነኝህ ዓይነቶቹ የኦሮሞ ልኂቃን ለመግባባትና ፍትሐዊ የሆነ ፖለቲካዊ ስምምነት ለመፍጠር፣ መፍትሔ ለመሻት በማሰብ በአንድም መድረክ ላይ ተገኝተው አያውቁም፡፡ ቀጣሪዎቻቸው ወይም ጌቶቻቸው ባዕዳን የዚህች ሀገር ጠላቶችም ይሄንን እንዲያደርጉ አይፈቅዱላቸውም፡፡

በግሌ ወደፊትም ቢሆን ከእነኝህ ጋር መግባባትና ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል ብየ አልጠብቅም፡፡ ይሁን እንጅ ከነሱ ጋር የሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች በከንቱ ጊዜ የማባከኛ ተግባሮች ተደርገው መቆጠር አይገባቸውም፡፡ ምክንያቱም ከተከታዮቻቸው መሀል ማገናዘብ የሚችሉትን፣ ኃላፊነት የሚሰማውን፣ በተሳሳተ መረጃ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ ያደረጓቸውን ወገኖች ከስሕተት ለመመለስና ትክክለኛ መረዳት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ በኛም በኩል ያሉ ከነኝህ የኦሮሞ ልኂቃን ጋር መሥራት ይቻላል የሚል ከንቱ እምነት ያላቸው ወገኖችንም ለማንቃት ይጠቅማሉና ነው፡፡

ወደ ክርክሩ እንመለስና ፕሮ. ሕዝቅኤል “የቀድሞው ሥርዓት ኦሮሞን ከፖለቲካው ያገለለ ነበረ፣ ኦሮሞ በኢኮኖሚውም ምንም ሚና አልነበረውም!” ለሚለው ግልብና ሲበዛ እንጭጭ ለሆነው ክሱ አቻምየለህ በቀድሞው መንግሥት አብዛኛውን ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣንና ኢኮኖሚውንም (ምጣኔ ሀብቱንም) የተቆጣጠሩት ኦሮሞዎች እንደነበሩ የስም ዝርዝሮችንና ሥልጣናቸውን እየዘረዘረ ሲያረጋግጥለት ሰውየው “አይ እነሱማ አማርኛ መናገር ስለሚችሉ ነው ለሥልጣን የበቁት….ሕዝቡ ግን ስሙን ወደ አማርኛ እንዲለውጥ ይገደድ ነበረ!” በማለት ምላሽ መስማቱ የሰውየውን የብስለት ደረጃ አጋልጦ የሚያሳይ ነው ሆኖ ያገኘሁት፡፡

ምክንያቱም አንደኛ ጀኔራል ጃጌማ ኬሎን ጨምሮ የተዘረዘሩት ስሞች አብዛኞቹ የኦሮሞ ስሞች ናቸውና፡፡ የተቀሩትም ቢሆኑ ቢቀር የራሳቸው ወይም የአባት ስም የኦሮሞ ነውና ነው፡፡ ሕዝቡ ስም እንዲቀይር ቢገደድ ኖሮ እነኝህ የኦሮሞ ስሞች ያሏቸው ዜጎች አብሶ በዚህ የሥልጣን ደረጃ ላይ ሊገኙ አይችሉም ነበርና ነው፡፡  ፕሮ. ሕዝቅኤል ሆይ! ዛሬ ወጣቶቻችን ለየራሳቸው፣ ወላጆች ለልጆቻቸው የፈረንጅ ስም እያወጡ ያሉትና የፈረንጅ ባሕልንና ማንነትን እየተከተሉ ያሉት ፈረንጆች ስላስገደዷቸው ነው ወይ???

ፕሮ. ሕዝቅኤል ስለ የበታችነት የሥነ ልቡና ችግር (inferiority complex) እና ስለ ውጤቱ የማንነት ቀውስ (identity crisis) ምንም የሚያውቁት ነገር የለም እንዴ? ኅብረተሰባችን የፈረንጅ ስም በመጠቀሙና የፈረንጅን ባሕል በመከተሉ ፈረንጆች ለዚህ ተጠያቂ ናቸው ወይ? አንዱ ጠንካራና ስኬታማ በመሆኑ ወይም በመምሰሉ ሌላው እንደ አርአያ ወስዶት ቢከተለው አርአያ ተደርጎ የተወሰደው አካል ወንጀለኛ የሚሆነው በምን መመዘኛና አመክንዮ ነው? ፕሮ. ሕዝቅኤል የምለው ይገባዎታል? ይሄንን ተፈጥሯዊና ሰብአዊ ችግር ነው ወንጀል አድርገው እያቀረቡት ያሉት፡፡

የልቅስ ወንጀል ልንገርዎት፦ ለመሆኑ ዛሬ ወያኔና እናንተ ኦሮሚያ በምትሉት የሀገራችን ክፍል ባሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አንድ አማርኛ ተናጋሪ በቋንቋው መስተናገድ እንደማይችል ያውቃሉ? ወደ 10 ሚሊዮን (አእላፋት) የሚጠጉ አማሮች ተገደው ኦሮሞ እንዲሆኑ እንደተደረጉስ ያውቃሉ? ጠባብ ዘውገኛ ካልሆኑና ሰብአዊ መብት የሚያሳስብዎት፣ ለሰብአዊ መብት የቆሙ ሥልጡን የተማረ ዜጋ ከሆኑ ለምንድነው ስለዚህና ተዘርዝሮ ስለማያልቀው ኦሕዴድ/ኦነግ/ወያኔ በአማራ ላይ እያደረሱት ስላለው ኢሰብአዊ ግፎች የማያወሩት?

ቋንቋን በተመለከተ ወዳነሡት ክስ ልመለስና እንደ አንድ ሀገር ዜጋነታችን መንግሥት የሚሠራበትን ብሔራዊ ቋንቋ አውቆ በመገኘት ተግባብቶ መሥራት በጃንሆይ ዘመነ መንግሥት ብቻ ሳይሆን አሁን በዚህ ዘመንም እርስዎ የሚገኙባት አሜሪካን ጨምሮ የሁሉም ሀገሮች ብሔራዊ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ እንዴት ተሳነዎት ፕሮፌሰር? አሁን በዚህ ዘመን የኦሕዴድ ባለሥልጣናት ከወያኔ ባለሥልጣናት ጋራ የሚግባቡት በኦሮምኛ ይመስልዎታል ወይ? የማዕከላዊ መንግሥት የሥራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑን አያውቁም እንዴ? የትኛው ኦሮሞ ነው አማርኛ ሳይችል ኦሕዴድ ውስጥ በወያኔ ተሹሞ እንዲያገለግል ሥልጣን የተሰጠው? እባክዎን ደረስኩበት የሚሉትን የትምህርት ደረጃዎን በሚመጥን ደረጃ አስፍተውና ጠልቀው ለማሰብ ይሞክሩ ፕሮፌሰር?

የክርክር ነጥቦችዎ በፍጹም በፍጹም ከርስዎ የሚጠበቁና የበሰሉ ሆነው አላገኘኋቸሁም፡፡ በወቅቱ የነበረው ችግር የመንግሥት አካላት አደረጃጀት አቅም ማነስ የፈጠረው ችግር መሆኑን እያወቁ ኦሮሞ በቋንቋው የመዳኘት መብት እንደተነፈገው አድርገው ሲናገሩ፣ እስላሞች መስጊድ ገንብተው በሚኖሩባት ሀገር እርስዎ የእስላም ቆብ ማድረግ አይቻል እንደነበር ሲናገሩ አቻምየለህ ኦሮሞ በኦሮምኛ የተዳኘበትን ችሎት የሚያሳይ ቪዲዮ (ትዕይንተ ኩነት) መረጃ እንዳለው፣ እስላም የሕዝብ ተወካይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ሆኖ የሚያሳይ መረጃ እንዳለ ሲነግርዎት “አያቋርጠኝ!” ከማለት ውጭ መረጃዎቹ ሐሰት መሆናቸውን በማረጋገጥ መከራከር አልቻሉም፡፡ እርስዎን የሚያክል ሰው እንዴት ተራ ሐሰተኛ የጠላት ወሬ ይዞ ያውም በአደባባይ እንዲህ ዓይነት ክስ ያስተጋባል?

በጣም የገረመኝ ነገር ምን መሰላቹህ አቻምየለህ የማያወላዱ መረጃዎችን ለፕሮፌሰሩ ባቀረበ ቁጥር ሰውየው የሚለውን ሲያጣ ይመልሰው የነበረው መልስ ነው “እነኝህ መረጃዎች ለአካደሚክ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ለፖለቲካ አይጠቅሙም!” ማለቱ ነው፡፡ ይህ አባባሉም የእነሱ ፖለቲካ ምን ያህል በሐሰት ላይ የተመሠረተና መረጃ አልባ መሆኑን ያሳያል፡፡ ብቻም ሳይሆን ከዚህ ከንቱ አስተሳሰብ ንቅንቅ ለማለት አለመፈለጋቸውንም ያሳያል፡፡ ሰውየው ግን በዚህ ደረጃ እራሱን እንዳጋለጠ እንኳ የገባው አልመሰለኝም፡፡ ለነ ፕሮ. ሕዝቅኤል ፖለቲካ ማለት ለእውነት ለአመክንዮና ለመረጃ ፊትን አዙሮ፣ ጆሮን ግጥም አድርጎ ደፍኖ ዋሽቶ፣ አወናብዶ፣ አምታትቶ ጥቅምን ማስከበር ማለት ነው፡፡ ሰብእናቸው በዚህ ደረጃ የዘቀጠ ሆነው እያሉ ደግሞ እንደ የተማሩና ኃላፊነት መሸከም እንደሚችሉ ዜጎች እንድንቆጥራቸው መፈለጋቸው ነው አስደናቂው ነገር፡፡

ፕሮ. ሕዝቅኤል! ለመሆኑ ለምንድነው እሱ እውነተኛ መረጃዎች ለአካደሚክ (ለትምህርታዊ) ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ለፖለቲካ (ለእምነተ አሥተዳደር) ሊጠቅሙ የማይችሉበት ምክንያት? ፖለቲካችን እውነታ ላይ ሳይመሠረት እንዴት ሆኖ ነው ፍትሕ ሊሰፍንና ሊመሠረት የሚችለው? ፖለቲካችን እውነታን በሚያረጋግጥ መረጃ ላይ ሊመሠረት ባለመቻሉ አይደለም ወይ ተወሳስቦ መፍትሔ ሊያጣ የቻለው? ለምንስ ነው ፖለቲካችን እውነታ ወይም መረጃ ላይ እንዲመሠረት ያልተፈለገው? ፖለቲካችን እውነታ ላይ ሳይመሠረት እንዴት ነው አለት ላይ የተመሠረተ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ሊመጣ የሚችለው?

ፕሮፌሰር ወገንዎ የተሳሳተ መረጃ ተሰጥቶት የተሳሳተ አመለካከት እንዲጨብጥ ተደርጎ ከሆነ (ሆኗልም) ትክክለኛ መረጃዎችን በማቅረብ የያዘው አመለካከት የተሳሳተ መሆኑን በማረጋገጥ የተሳሳተ አመለካከቱን ማስጣልና ለእውነታው እንዲገዛ ማድረጉ ነው እንጅ አዋጭው፣ በሳሉና ብልሁ እርምጃ ሁለነገራችንን በሐሰትና ፈጠራ ላይ መመሥረቱ ቤትን በአሸዋ ላይ እንደመገንባት ያለ የጅል ሥራ አይደለም ወይ???

እጅግ የገረመኝ ነገር ደግሞ ፕሮ. ሕዝቅኤል “የቀድሞው ሥርዓት ኦሮሞን ከፖለቲካው ያገለለ ነበረ፣ ኦሮሞዎች በኢኮኖሚውም ምንም ሚና አልነበራቸውም!” በማለት ይሄንን የሚያክልን እጅግ ከባድ ክስ አቅርቦ እያለ አቻምየለህ ስም እየዘረዘረ ያቀረባቸውን ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ሰውየው አላውቃቸውም ማለቱ ነው፡፡ አቶ ሕዝቅኤል ሆይ! የእነኝህን ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ማንነት ሳያውቁ ታዲያ እንዴት ሆነው ነው ከዚህ ከባድ የሀገርን፣ የሕዝብንና የመንግሥትን ስም ከሚያጠፋ ጠንካራ ፖለቲካዊ ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ የቻሉት??? እንዲህ ዓይነት ግልብ ሰው ሆነው እያለ እንዴት ታዲያ እንደተማረና ኃላፊነት እንደሚሰማው ሰው እንቁጠርዎት ፕሮ. ሕዝቅኤል?

ፕሮ. ሕዝቅኤል እባክዎን ኃላፊነት ይሰማዎ? በእንዲህ ዓይነት ጉዳይ ላይ የሚያፍሩበትን ክስ ከማቅረብዎ በፊት የጠላት ተራ የስም ማጥፋት ወሬዎችን ከማስተጋባት ባለፈ መሬት ላይ የነበረውን ሀቅ በንስር ዓይን ዓይተው ለመመርመር ይሞክሩ? ይሄኔ ከአንድ የተማረ ዜጋ የሚጠበቀውን የሞራል (የቅስም) ግዴታ በሚገባ ተወጡ፣ ኃላፊነትም የሚሰማዎ ብቁ ዜጋ ሆኑ ማለት ነው፡፡ መሬት ላይ የነበረውን ሀቅ በንስር ዓይን ዓይተው መመርመር ሲሞክሩ ምን እንደሚያገኙ ልንገርዎት? ጨቋኝ የሚሉት አማራ ከሁሉም በከፋ መልኩ ተጨቋኝ የነበረ መሆኑን፣ ግፍ አድርሷል የሚሉት አማራ ማንም ሊደርስበት በማይችልና ከማንም በከፋ መልኩ ግፍ የተጋተ ሕዝብ መሆኑን ይደርሱበትና ጭጭ ይላሉ በሐሰተኛ ውንጀላዎም ይጸጸታሉ፡፡

ፕሮ. ሕዝቅኤል በሽዎች የሚቆጠር ሕዝቡ በየቤቱ እየታጎረ እንዲቃጠል የተደረገ ብሔረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአማራ በስተቀር ሌላ ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ??? የአማራ ገበሬ በብአዴን የወያኔ ካድሬዎች (ወስዋሾች) አንደበት ሲዘለፍ እንደሰሙት ለእግሩ ጫማ የማያውቅና ድሪቷም ለመሆን የበቃው ለምን ይመስልዎታል? ድህነት ላይ በተደረገ ጥናት ስር ለሰደደ ድህነት በመዳረግ ኢትዮጵያ ውስጥ አማራን የሚደርስበት እንደሌለ ያውቃሉ? ለምን ይመስልዎታል አማራ በዚህ የድህነት ደረጃ ላይ ሊገኝ የቻለው? መልሱ እርስዎ አማራ ተጠቀመበት በሚሉት ዘመነ መንግሥታት በእሬና ወይም በተሠሪ ሥርዓት የዚህችን ሀገር ነጻነት፣ ህልውናና ደህንነት ለማስጠበቅ ሳይወድ በግዱ ሁለነገሩን የመገበር ግዴታ ስለነበረበትና ይህ ጉዳይ ባዶ እጁን አራቁቶ ስላስቀረው ነው እሽ?

ፕሮ. ሕዝቅኤል “ለነፍጠኛ….!” ሲሉ በተደጋጋሚ ሰማሁዎት ልበል? ለምሳሌ አቻምየለህ እርስዎ የአማራ ባሉት የመንግሥት ሥርዓት አማራ አለመጠቀሙን እናንተ የበለጠ መጠቀማቹህን የመሠረተ ልማት ግንባታን ትምህርት ቤቶችን ወዘተረፈ. ሲጠቃቅስ “ለነፍጠኞች ታስቦ ነው የተደረገው!” ብለው መልሰው ነበረ፡፡ ነገሥታቱ ሕዝባችን ይሉታል ለሚሉት የአማራ ሕዝብ ሳያደርጉ “ለታጣቂ ወይም ነፍጠኛ አስበው አደረጉ!” ነው እያሉን ያለው? እውነት ይመስልልኛል ብለው ይሄንን ላሉት ለርስው አፈርኩልዎት፡፡ ታሪካችንን በአግባቡ ለማወቅ ያደረጉት ጥረት አለመኖሩ እጅግ ለተዛባና በሚያሳዝን ሁኔታ ለተሳሳተ ድምዳሜ ዳርጎዎታል፡፡ አቶ አሰፋ ጫቦ ነፍሳቸውን ይማርና ባደጉበት በሀገራቸውና በሌላውም አካባቢ ነፍጠኞች ለሚባሉት በነበራቸው የቅርበት አጋጣሚ የዓይን ምስክር በመሆን ከሚያውቁት በመነሣት ባደረጉት ጥናት ከ90 በመቶው በላይ የዐፄ ምኒልክ ነፍጠኛ ሠራዊት የሚባለውና በነፍጠኛነቱ መሬት የወሰደው ኦሮሞ መሆኑን በሚገባ ማረጋገጣቸውን ጨርሶ የሰሙ አልመሰለኝም ፕሮ. ሕዝቅኤል? እናም እርስዎና ጓዶችዎ እባካቹህ! እባካቹህ! እባካቹህ! ኃላፊነት ይሰማቹህ? ለእውነት፣ ለአመክንዮ፣ ለሞራል (ለቅስም) ድንጋጌዎች ተገዙ? ግፍንም ፍሩ???

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

Filed in: Amharic