>

የወያኔ አገዛዝ ካጠመደልን የርስ በርስ እልቂት ህዝባችንንና አገራችንን እንታደግ! 

 [የአርበኞች ግንቦት 7 ርዕስ አንቀፅ]

የህወሃት አገዛዝ ለሥልጣን ዕድሜው መራዘም ሲል በአገራችን ያሰፈነው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ የጋራ ታሪክ ባለቤት የሆነውን ህዝባችንን በባህልና በቋንቋ ሸንሽኖ አንደኛው ከሌላኛው ጋር ምንም የሚያቆራኘው ታሪካዊም ሆነ ወገናዊ ትሥሥር በመካከሉ እንደሌለ በመስበክ እያንዳንዱ በጥላቻና በጥርጣሬ እንዲተያይ የማድረግ ስልታዊ እርምጃ ነው።
ተደጋግሞ እንደተገለጸው ህወሃት የተጠቀመበት ይህ የአንድ አገር ዜጎችን በቋንቋና በባህል ከፋፍሎ የመግዛት ፖሊሲ አውሮፓዊያን አፍሪካን በቅኝ ግዛትነት በተቀራመቱበት ዘመን ከተጠቀሙበት ስልት የተቀዳ መሆኑ ግልጽ ነው። በዚያን ዘመን ቅኝ ግዛት ሥር የወደቁ የአፍሪካ አገሮች የቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸው ተጠቃለው ከወጡላቸውና በራሳቸው ዜጎች መመራት ከጀመሩ ወዲህ እንኳ ትተውባቸው ከሄዱት የርስ በርስ ክፍፍል መውጣት አቅቶአቸው ላለፉት 50 እና 60 አመታት በመገዳደልና አንዱ ሌላውን እንደጠላት በመቁጠር ሲናቆሩ ከባርነት ቀንበር ነጻ ወጥቻለሁ ላለው ህዝባቸው ኑሮ መሻሻል አንዳችም ፋይዳ ሳያስገኙ በተቃራኒው የመከራ፤ የስቃይና አለመረጋጋት ምንጭ ሆነው ዘልቀዋል ።
በትግራይ ህዝብ ሥም የሚነግደው ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይን የሚመራው የአድዋ መንደርተኞች ስብስብ ይህንን ለጥቁር ህዝቦች ስቃይና መከራ ምንጭ የሆነውን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በአገራችን ሲያስተዋውቁ አላማቸው ግልጽ ነበር። “የመንግሥትን ሥልጣን ያለምንም ተቀናቃኝ እስከወዲያኛው በመቆጣጠር የአገር ሃብት እና ገንዘብ መዝረፍ ያስችለናል ፤ በወጣትነት ዕድሜያችን የታገልንለትን የታላቋን ትግራይ ግንባታ ለማሳካት ይረዳናል ፤ ካልሆነም ደግሞ ልጆቻችን በዕውቀትና በኢኮኖሚ የበላይነት ይዘው አገሪቷን ለዘለዓለሙ ለመግዛት የሚችሉበትን እድል ይሰጠናል” በሚሉ ስሌቶች ነው። በእርግጥም ይህ ስሌታቸው ተሳክቶላቸው ባዶ እግራቸውን ሚኒልክ ቤተመንግሥት ድረስ የዘለቁ የቀድሞ ተጋዳላዮች የአገሪቱን ሃብት እንዳሻቸው በቤተሰብ እና በቡድን ተቧድነው ለመበዝበር ችለዋል። ልጆቻቸውን ዋጋቸው እጅግ ውድ ወደ ተባሉ የአውሮፓ፤ የአሜሪካና የኤሲያ ትምህርት ቤቶች በመላክ ከፍተኛ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲቀስሙና በተተኪነት ሥልጣን ለመረከብ እንዲችሉ አዘጋጅተዋቸዋል። ጥጋብ በፈጠረው እብሪት ተወጥረው ለድል ካበቃቸው የቀድሞ ወዳጃቸው እና የአሁኑ ጠላታቸው ሻቢያ ጋር በመላተም የታላቋ ትግራይ ግንባታ ህልማቸው ህልም ሆኖ የቀረ ከመሆኑ በቀር ምንም ያላሳኩት ነገር የለም ።
ያ ሁሉ ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመላው አገራችን እየተስተዋለ የመጣው ታጋሽና አስተዋይ የሆነው ህዝባችን ለህወሃት ሥልጣን ዕድሜ መራዘም አይነተኛ መሠረት ሆኖ በማገልገል ላይ ያለውን የልዩነትና የጥላቻ ግድግዳ በርግዶ በመውጣት “እኛ አንድ ነን ! አንከፋፈልም ! ” በማለት በዘረኝነትና በአምባገነናዊነት ላይ የተቃውሞ ድምጹን በጋራ ማሰማት ጀምሮአል። በተለይ በመካከላቸው በተዘራው ያልተቋረጠ የጥላቻ ቅሰቀሳና ፕሮፖጋንዳ እስከ ወዲያኛው በጠላትነት እንዲተያዩ የተፈረደባቸው አማራ እና ኦሮሞ ይህንን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በመናድ በጋራ ጠላታቸው ህወሃት ላይ በአንድ ድምጽ ተቃውሞ ማሰማት መጀመራቸው የአድዋ ማፊያዎች የቆሙበትን መሬት ያራደባቸው ብቻ ሳይሆን ዙሪያ ጥምጥማቸውን ሊወጡት የማይችሉት ገደል አድርጎባቸዋል። በዚህም የተነሳ ህወሃት በተስፋ መቁረጥ ስሜት የመጨረሻውን የአጥፍቶ መጥፋት እርምጃ ለመውሰድ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው።
ሰሞኑን በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ወጣት ተማሪዎች ትግሪኛ ተናጋሪ በሆኑ የዕድሜ እኩዮቻቸው ላይ እጅግ አደገኛ የሆነ እርምጃ መውሰድ የጀመሩት ህወሃት ከበስተጀርባ ሆኖ በሚሰራው አንዱን ከሌላው የማጋጨት እኩይ ተግባር እንደሆነ ሁሉም ተገንዝቦታል። አዲግራት ውስጥ ለትምህርት በሄደ የ19 አመት የአማራ ተወላጅ ላይ የተፈጸመው ግድያ የብሄር ግጭት ለመፍጠር ሆን ተብሎ በህወሃት የተሸረበ ሴራ መሆኑ አያጠያይቅም። በዚህ ሴራ ምክንያት በአብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች የተቀሰቀሰው የበቀል እርምጃ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለሁለት የትግራይ ተወላጆች ህይወት ህልፈት እና ለበርካቶች ከያሉበት ዩኒቨርሲቲዎች ግቢ መሸሽ ምክንያት ሆኖአል። በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል የተቀሰቀሰው የብሄር ግጭት ሳያባራ አገዛዙ ጨለንቆ ላይ የአጋዚ ጦር በማዝመት እጅግ የሚሰቀጥጥ ጭፍጨፋ ፈጽሞአል። በጭፍጨፋውም ቁጥራቸው 20 የሚደርስ የኦሮሞ ተወላጆች ህይወት ሲቀጠፍ በርካቶች ለመቁሰል አደጋ መጋለጣቸው ተረጋግጦአል። የኢትዮጵያ ህዝብ “የ27 አመት የህወሃት አፈናና ጭቆና ያብቃ! “ ብሎ በመጠየቁ ጥያቄውን አቅጣጫ ለማስቀየር ህወሃት በየቦታው የለኮሰው የብሄር ግጭት ለማንም የማይበጅ ፤ አገሪቷንና ህዝቧን ብቻ ሳይሆን ህወሃትን ጭምር መልሶ የሚያቃጥል አደጋ ያዘለ መሆኑን ህወሃቶች ልብ ሊሉት የቻሉት አይመስልም።
ከአንድ ወር በላይ በፈጀው የመቀሌው ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባቸው ፍጻሜ ላይ እንደ አዲስ ከሰየሟቸው የአመራር አባላቶች መካከል አብላጫዎቹ ከህወሃት ውልደት ጀምሮ የነበሩና አገራችንና ህዝባችን ላይ እስከ ዛሬ በተፈጸሙ ወንጀሎች ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑ ግለሰቦች መሆናቸውን እንኳን በስሙ የሚነገደው የትግራይ ህዝብ የተቀረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያውቀዋል። ህወሃት እነዚህኑ ወንጀለኞች ቦታ በመቀያየር “ታድሼና ተጠናክሬ” ወጥቻለሁ በማለት ህዝባችን ለነጻነቱ እና ለመብቱ እያካሄ ያለውን ትግል በፈረጠመ ወታደራዊ ጡንቻው ለመጨፍለቅ ወስኖ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ይፋ አድርጎአል። በዚህ የውሳኔ እርምጃው ኦሮሚያ ውስጥ ገብቶ በርካታ ንጹሃንን የመጨፍጨፍ እርምጃ ከመውሰድና በየዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የብሄር ግጭቶችን ከመቀሰቀስ አልፎ ህዝባችን መረጃ የሚያገኝባቸውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ ስርጪቶችን በማወክ ከአየር ላይ እንዲወርዱ አድርጎአል። በዩኒቨርስቲዎች ግቢ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደ ህብረተሰቡ ውስጥ ሊዛመት ይችላል ብሎ በከፍተኛ ሁኔታ በሰጋባቸው ከተሞችና ዞኖች ውስጥም የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲስተጓጎል እያደረገ ነው።
ህወሃት በተስፋ መቁረጥ ስሜት እየወሰደ ባለው እርምጃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ቦታዎች በተነሱት የብሄር ግጭቶች ውድ ህይወታቸው እንዲቀጠፍ እና ለአካል ጉዳተኝነት ለተዳረጉት ዜጎች ሁሉ ብቸኛ ተጠያቂ እንደሆነ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል። በእንዲህ አይነት እብሪትና ጥጋብ የህዝብ ተቃውሞን እስከ መጨረሻው መጨፍለቅ እንደማይቻልም በተግባር ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ ተግቶ ይሰራል።
ህዝባችን ውድ ልጆቹን በየጊዜው በአጋዚ ጨካኝ ጦር ጥይት እየተነጠቀ በመጠየቅ ላይ ያለው የመብት ጥያቄ ፤ ይህ አገዛዝ ከሥር መሠረቱ እንዲቀየር እና በሚመርጠው መንግሥት የሚተዳደርበትን የዲሞክራሲ ሥርዓት ለማምጣት እንጂ ለሩብ ከፍለ ዘመን መከራውና ሰቆቃው ተጠያቂ የሆኑ ጥቂት የአደዋ ልጆች በቤተሰብ እና በመንደር ተሰባስበው በተሃድሶና በግምገማ ስም ተጠናክረው የመከራ ዘመኑን እንዲያራዝሙለት አይደለም።
በመሆኑም በዚህ የህወሃት ሥርዓት ውስጥ ተወልደውና አድገው የሥርዓቱን አስከፊነት በመረዳት ለነጻነታቸው እየታገሉ ያሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እርስ በርስ በጠላትነት ከመተያየት ወጥተው አፍላ ጉልበታቸውንና ለለውጥ ያላቸውን እምቅ ሃይል የጋራ ጠላታቸው በሆነው ወያኔ ላይ ብቻ በማዋል የአገዛዝ ዘመኑን ለማሳጠር እየተካሄደ ያለውን አገራዊ ትግል እንዲያጠናክሩ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪውን ያቀርባል። የትግራይ ህዝብንና በህወሃት ውስጥ የተሰባሰቡትን ጸረ ህዝብ ሃይል ለያይቶ መመልከት እጅግ ጠቃሚ ነው። ስለዚህም ህወሃት በአገራችንና በህዝባችን ላይ ሲፈጽም ለኖረው ወንጀሎች የትግራይ ወገኖቻችንን በሙሉ በጅምላ መፈረጅ ሊያስከትለው የሚችለው አደጋ ለአገራችንም ሆነ ለህዝባችን የሚበጅ አይሆንም። ይልቁንም ህወሃት ባጠመደልን የርስ በርስ ግጭት ውስጥ ገብተን አገራችንና ህዝባችንን ከማይወጣበት መከራ ውስጥ እንዳንከት ሁላችንም ጠንከረን በጋራ መንቀሳቀስ ይኖርብናል። የእያንዳንዳችን ዲሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብት የተከበረባት ፤ የኢኮኖሚ ብልጽግናና ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት ፤ የእያንዳንዳችን ደህንነትና ጥቅም የሚጠበቅባት አንዲት ሉአላዊት አገር ባለቤት መሆን የምንችለው እጅ ለእጅ ተያይዘን ህወሃት ከደገሰልን የርስ በርስ ግጭት ወጥተን በጋራ የአገዛዝ እድሜውን ማሳጠር ስንችል ብቻ እንደሆነ አርበኞች ግንቦት 7 ያረጋግጣል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !

Filed in: Amharic