>
4:31 am - Tuesday January 31, 2023

ኢትዮጵያ ወዴት እየተጓዘች ነዉ? (ነጋሽ መሐመድ ና ሸዋዬ ለገሰ)

የአሜሪካኖች መግለጫ ያሰለቻል። የአዉሮጶች ርዳታ ያደናግራል። የተቃዋሚዎች ጥሪ ያደነቁራል። የመንግሥት መሪዎች ተስፋ፤ ቃል፤ ስብሰባ «ያቅለሸልሻል»። የየዋሕ ኢትዮጵያዉያን መገደል፤ መሰደድ፤ መፈናቀል፤ ከትምሕርት እና ሥራ መስተጓጎል አጣዳፊ መፍትሔ ይሻል። ማነዉ መፍትሔ ሰጪዉ?

ኢትዮጵያ – ሠላም የናፈቃት ሐገር

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ትናንት ድንገት በቴሌቭዥን እንደነገሩን የኢትዮጵያ ሠላም እና መረጋጋት ታዉኳል። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ እንደሚሉት ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ናት። የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ደግሞ «ኢትዮጵያ እሳት ላይ ናት» ይላሉ። ከብጥብጥ፤ አደጋ እሳቱ የሚያድናት አለ ይሆን? አብረን እንጠይቅ።

ተስፋ በርግጥ ጥሩ ነዉ። በየዘመኑ የተፈራረቁት የኢትዮጵያ መሪዎችም ለሕዝባቸዉ ተስፋ ነፍገዉት አያዉቁም። የኦሮሚያ ሕዝብ ሕዳር 2008 ለተቃዉሞ አደባባይ ሲወጣም ጠቅላይ ሚንስትር ሚንስትር ኃይለማርያምም ደሳለኝ እና መንግሥታቸዉም ጥያቄዉ መልስ እንደሚያገኝ እንደብዙ ቀዳሚዎቻቸዉ ሁሉ ተስፋ ሰጥተዉት ነበር። በሶስተኛ ዓመቱ ትናንትም «የተከበራችሁ ያገራችን ሕዝቦች» ላሉት ሕዝባቸዉ ተስፋ ሰጡት። የቀጠለ ቀዉስ፤ ሌላ ተስፋ።

Vertriebene somalische Frau im Rollstuhl (DW/J. Jeffrey)

ኢትዮጵያ ዉስጥ የአደባባይ ተቃዉሞ፤ አመፅ እና ግጭት ከተጀመረበት ከሕዳር 2008 እስከ ሚያዚያ 2009 በነበረዉ ጊዜ ሥለደረሰዉ ጉዳት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሁለት ዘገቦች አዉጥቷል።የኢትዮጵያ ምክር ቤት (ፓርላማ) የሚቆጣጠረዉ ኮሚሽን በኦሮሚያ፤ በአማራ እና በደቡብ መስተዳድር ባደረገዉ ጥናት በመጀመሪያዉ ዘገባዉ 268፤ በሁለተኛዉ 669 ሰዎች መገደላቸዉን፤ በርካታ መቁሰላቸዉን፤ በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመት ሐብት ንብረት መዉደሙን አስታዉቋል። ለሟች ቁስለኞች፤ ለወላጅ፤ ዘመድ ወዳጆቻቸዉ፤ ወይም ሐብት ንብረት ለጠፋባቸዉ የተሰጠ ካሳ ሥለመኖሩ ግን የሰማነዉ ነገር የለም።በአጥፊዎች ላይ የተወሰደ ቅጣትም የለም።

ግድያ፤ ግጭት ሁከቱ አሁንም ከአዲግራት እስከ ወልዲያ፤ ከጨለንቆ እስከ ጋድሌ (ዳሮለቡ) እንደቀጠለ ነዉ። የኢትዮጵያ መንግስት ተስፋም ይንቆረቆራል። ቃል ገቢር ካልሆነ ግን በርግጥ አስጊ ነዉ።የኢትዮጵያ ጉዞም፤ አንጋፋዉ ፖለቲከኛ ሌንጮ ለታ እንደሚሉት ወደ መፍረስ እንዳይሆን ያስፈራል። ለኦሮሞ ነፃነት በነፍጥ የሚዋጋዉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የቀድሞ መሪ ዛሬ ለኢትዮጵያ አንድነት በግልፅ መሟጋታቸዉ ለብዙዎች ግር ያሰኝ ይሆናል እሳቸዉ ግን መልስ አላቸዉ። አቶ ሌንጮ «መፍረስ» ያሉትን ፍርሐት የመኢአዱ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙሉጌታ አበበ የመኖር አለመኖር ጉዳይ ይሉታል። የሕግ ባለሙያ አቶ ተማም አባ ቡልጎ ግን የፖለቲከኞቹን ሥጋት አይጋሩም።ተቃዉሞ፤ ግጭት፤ ግድያዉ አቶ ተማም እንደሚሉት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአዲስ ተስፋ ብሥራት፤ለገዢዎቹ የዉድቀት መርዶ ነዉ።

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ዋሽግተን ይሁኑ ብራስልስ፤ ኦስሎ ይሁኑ አስመራ፤ ለንደን ይኑሩ አዲስ አበባ መንግስትን ለማዉገዝ አንድ ናቸዉ። ግን አይግባቡም። ኢትዮጵያን ካለችበት ችግር ለማዉጣትም የጋራ የሚሉት መፍትሔ የላቸዉም።የመኢአዱ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ግን ፓርቲያቸዉ ለሐገሪቱ ችግር የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ በተለይም ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ያልሞከረበት ጊዜ የለም ባይ ናቸዉ። አቶ ሌንጮ ለታም የሚመሩት ፓርቲ ብሔራዊ እርቅ እንዲወርድ ብዙ መጣሩን ይናገራሉ።  አለ ይሆን? ሐገር ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ከገዢዉ ፓርቲ ጋር መደራደር ሲጀምሩ በአንዳዶች ዘንድ ድርድሩ ለብሔራዊ መግባባት ጥሩ መደላድል ይፈጥራል የሚል ተስፋ አሳድሮ ነበር።ድርድሩ ከተጀመረ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ቀረዉ።እስካሁን ተጨባጭ ዉጤት የለም።

ተደራዳሪዎች ኢትዮጵያን አሁን ሥለሚያብጠዉ ቀዉስ እና መፍትሔዉ ሥራዬ ብለዉ በግልፅ አልተወያዩም።አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት በተቃዋሚዎች ጥያቄ ጉዳዩ ቢነሳም የሰማቸዉ እንጂ ያደመጣቸዉ የለም።

ተቃዉሞ፤ ግጭት፤ ግድያ፤ የትምሕርት አድማና ሥጋቱ ኢትዮጵያን በሚነዉጥበት መሐል አዲስ አበባን የጎበኙት የዩናይትድ ስቴትሱ ተጠባባቂ ረዳት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዶናልድ ያማማቶ መንግሥታቸዉ ለሚደግፋቸዉ ለኢትዮጵያ መሪዎች በሚስጢር ያሉት በርግጥ የነሱ ሚስጢር ነዉ። በይፋ የተናገሩት ግን አፍሪቃ ቀንድ ሠላም ያሳሰባቸዉ መሆኑን ነዉ። በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ግን ያማማቶ አዲስ አበባ ከመግባታቸዉ በፊት እና በኋላም የኢትዮጵያ ሁኔታ «በጣም አሳስቦናል» የሚል አሰልቺ መግለጫዉን አላቋረጠም።

Äthiopien US Botschaft in Addis Abeba (U.S. Embassy/S. Dumelie)

አሜሪካኖች ሥንት ዓመት እንደሚያስቡ አናዉቅም።የዓለም ገንዘብ ድርጅት (IMF) የበላይ ወይዘሮ ክርስቲነ ላጋርድን ብዙ ያሳሰበ፤ አዲስ አበባ ድረስ የወሰደዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ ሊሆን ይችላል።ባደባባይ የተናገሩት ግን ሥለሐገሪቱ ምጣኔ ሐብት ነዉ። የአዉሮጳ ሕብረት ስደተኞችን ለመርዳት 38 ሚሊዮን ዩሮ፤ የኤሊክትሪክ ኃይል ለማስገንባት ከአስር ሚሊዮን ዩሮ በላይ ለኢትዮጵያ መስጠቱን ሰሞኑን ሰምተናል።የኢትዮጵያዉያን እንግልት፤ እልቂት እና ሥጋት ለዋሽግተን ብራስልሶች ከቁብ የሚገባ እንዳልሆነ በግልፅ እየታየ ነዉ።

ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔዉ፤ አቶ ሌንጮ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ እና ከኢትዮጵያዉያን መምጣት ነዉ ያለበት። ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ ተቀናቃኝ ፖለቲከኛ ገና እየተደራደሩ ነዉ።የኢሕአዴግ አባል ፓርቲ መሪዎች ባሕርዳር ላይ ለ37ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል፤ ሐዋሳ ላይ ለ25ኛ ዓመት በዓል፤ መቀሌ ላይ ለአንድ ወር  ግምገማ ተስብስበዉ ነበር። ተሰበሰቡ። ደግሞ እንደ ኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ እንደገና ተሰበሰቡ።

የአሜሪካኖች መግለጫ ያሰለቻል። የአዉሮጶች ርዳታ ያደናግራል። የተቃዋሚዎች ጥሪ ያደነቁራል። የመንግሥት መሪዎች ተስፋ፤ ቃል፤ ስብሰባ «ያቅለሸልሻል»። የየዋሕ ኢትዮጵያዉያን መገደል፤ መሰደድ፤ መፈናቀል፤ ከትምሕርት እና ሥራ መስተጓጎል አጣዳፊ መፍትሔ ይሻል። ማነዉ መፍትሔ ሰጪዉ? ነጋሽ መሐመድ ነኝ። ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

Filed in: Amharic