>
8:26 am - Saturday February 4, 2023

”ኢትዮጵያዊነት  በህገ መንግሥቱ ድጋፍ የለውም” (በአርቲስት አያልነህ ሙላት)

በጦማሩ ላይ ጋሽ አያልነህ ይኽን ሁሉ ጣጣ ያመጣብንን አካል በስሙ [ ህወሓት] ብለው መጥራት ብቻ ነው የቀራቸው ። እንዲህ ባለማለታቸው ደግሞ ልንወቅሳቸው አይገባም ። ወዳጄ የቀረው ስም መጥቀስ እንጂ ነገርየውን እንደሁ ዘንቁለውታል ። ደግሞም እንደ እኔ እና እኔን መሰሎች #ከወንዝ_ማዶ ያለመሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል ።

 አቶ አያልነህ ድሮም ቢሆን ደፋር ፣ ቆፍጠን ያሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው ። ድርሰቶቻቸውን በፑሽኪን አዳራሽ ወደ ቲያትር ቀይረው ያቀርቡ የነበረውን ደፋር ቲያትሮቻቸውንም ብዙ ጊዜ አይቼላቸዋለሁ ። እኔ ወደ ራየን ወንዝ ከመምጣቴ በፊት የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅቶ ባደረገልን ግብዣ መሠረት ለጥቂት ቀናት አብሬያቸው የመቆየት ዕድል ገጥሞኝ አይቻቸዋለሁ ። አክሱም ፣ አድዋ ጨርቃጨርቅ ፣ የሃ ፣ አዲግራት መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግን አብረን እስከ አፍንጫው ጎብኝተናል ። ሰውየው ጠያቂ ናቸው ። ተሟጋችም ። እናም ዛሬም ያ ደፋሩ ሰው ስለ ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ሲሉ ባገኛቸው ጊዜ እዚህ ፔጄ ላይ አምጥቼ ለጠፍኩላችሁ ። መልካም ንባብ ።  ዘመድኩን በቀለ

~ ብሔርተኝነት በአንዱ ገፅታ ሲታይ ሀገር ማለት ነው። ሀገርን መውደድ በሀገር ስሜት መስጠም ማለት ነው፡፡ እነዚህን ጥሩ ገፅታዎች ስንመለከት፣ብሔርተኝነት መጥፎ ነው ለማለት አያስችለንም፡፡ ሰዎች ስለ አካባቢያቸው መቆርቆራቸውና አካባቢያቸውን መውደዳቸው መጥፎ አይደለም፡፡ ትልቁ ጥያቄ፣ የኔ ብሔር ከሌላው ይበልጣል። የኔ ብሔር ባህል፣ አኗኗር ከሌላው ይበልጣል ወይም ይሄ ብሔር በዚህ ብሔር ላይ አመራሩ በደል አድርሷል የሚሉና የመሳሰሉ ከፋፋይ ሃሳቦች ሲገቡበት ነው፡፡ ያኔ ብሔርተኝነት ገፅታው ይለወጣል፡፡ እንዲህ አይነቱ ነገር ነው ሃገር የሚያጠፋው፡፡

ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ቋንቋዎች ያሉባትና በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት እየተባለ ነው የሚነገረው፡፡ እኔ ደግሞ ኢትዮጵያ በአንድ መደብ ላይ የተለያዩ አበቦች የበቀሉባት ነች ነው የምለው፡፡ አበቦቹ የየራሳቸው ውበት አላቸው። አንድ ላይ ሆነው የለመለሙበትን መደብ ይዘው ሲገኙ ያምራሉ፡፡ ይሄ ነው የኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና መሆን ያለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁን ያለው ኢትዮጵያዊነት እንደዚህ ነውን? ይሄ ለሁሉም መቅረብ ያለበት ጥያቄ ነው። አሁን መልኩ ጠፍቷል፣ እያንዳንዱ በራሱ ዛቢያ ብቻ የሚሽከረከር ሆኗል፤ ስለ ጠቅላላዋ አንዲቷ ብሔር – ኢትዮጵያ ማሰብ ቀርቷል፡፡ ይሄም የሆነበት ምክንያት ደግሞ ከራሱ ከመንግሥቱ አወቃቀር እንዲሁም ከህገ መንግሥቱ አቀራረፅ የተነሳ ነው። #ኢትዮጵያዊነት በህገ መንግሥቱ ድጋፍ የለውም። በህገ መንግሥቱ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ነው ድጋፍ ያለው፡፡ እያንዳንዱ ብሔር የራሱን ዕድል በራሱ ወስኖ የመገንጠል መብት ሁሉ አለው ይላል ህገ መንግሥቱ፡፡ ይሄ የፈጠረው ጠባብነት ቀላል አይደለም፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮች ምንጭ፣ ህገ መንግሥቱ የፈጠረው ነው፡፡

ሌላው የዚህ ሀገራዊ ቀውስ ችግር መንስኤ፣ የትምህርት ሥርዓታችን አቀራረፅ ነው፡፡ ነባሩን ሀገራዊ እውቀት፣ ባህል፣ አስተሳሰብ ወደ ኋላ ገፍተን ባዶ ሜዳ ላይ ነው ሥርዓተ ትምህርቱን የቀረፅነው፡፡ በሃይማኖትና ባህል አስታከን ነው፣ በውስጡ ጥልቅ ሳይንሳዊ ፍልስፍና (ስነ ከዋክብት ብንል፣ ስነ ፍጥረት ብንል፣ የቀን አቆጣጠር ብንል፣ ህክምና ብንል) የያዘውን ሀገር በቀል እውቀት አሽቀንጥረን ጥለን የውጭውን የተከተልነው። ሀገር በቀል እውቀቶቻችንን፡- ስነ ጥበብን፣ ስነ ስዕልን፣ ስነ ሙዚቃን (ያሬድ) ጥለን ነው የማናውቀውን የተቀበልነው፡፡ ምክንያቱም የፈረንጅ በመሆኑ ብቻ ተቀበልነው፡፡ ይሄ ደግሞ በቀጥታ የተማረውን ማንነቱን አስተፍቶ ነው የሌላውን የያዘው፡፡

እኛን ሀገር በቀል እውቀታችንን ካስተፉን በኋላ እነሱ ተመልሰው ወስደው በዩኒቨርሲቲዎቻቸው ያስተምሩታል፡፡ ግዕዝን ማንሳት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ ለሀገራችን የነበረንን ፍቅር፣ ክብርና አንድነት ካላሉት መካከል አንዱ፣ ከውጭ ዝም ብለን የተቀበልነው ዘመናዊ ትምህርት ነው፡፡

ሌላው ብሔርተኝነትን የሚፈጥረው ድህነት ነው፡፡ ድህነትን መሻገር ያልቻልነው ደግሞ ችግር ፈቺ ሥርዓተ ትምህርት ባለመቅረጻችን ነው፡፡ አሁን የፈረንጅ ቧንቧ ነው የሆነው፡፡
እኔ አሁንም በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን ትልቅ እምነት አለኝ፡፡ በደምና በአጥንት የተገነባ የአንድነት ግንብ እንዲህ በቀላሉ መፍረስ አይችልም፡፡ ህዝብ ለህዝብ እየተገናኘ አሁንም አንድነቱን ለማጠናከር እየታተረ ነው፡፡ አሁንም ይሄን አንድነት ማምጣት የሚቻለው መሪዎች ህዝቡን መስለው ስለ ሀገር አንድነት መስበክ ሲችሉ ነው፡፡ መንግሥት የህዝቡን ምክር መስማት አለበት፡፡ ህዝብ አንድነቱን ዛሬም እንደሚፈልገው እያሳየ ነው፡፡ መንግሥት ከዚህ የህዝብ ቋንቋ ከተለየ ራሱን ማረም አለበት፡፡ በህዝቡ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ አለበት። እውቀቶች በሙሉ በህዝቡ ባህል ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው። ኢትዮጵያዊነት ስንል ይሄን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ዘመናዊነትን በራሳችን ባህል ላይ መገንባት አለብን።

 

Filed in: Amharic