>
5:13 pm - Tuesday April 18, 4637

በመካሄድ ላይ ያለውን የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ አስመልክቶ አጭር አስተያየት (አበጋዝ ወንድሙ)

አባይ ጸሀዬና ፣ስዩም መስፍን የዛሬ ሰባት ዓመት፣ አዲሱ ለገሰ፣ ግርማ ብሩና ኩማ ደመቅሳ የዛሬ አራት ዓመት
ከ ኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተሰናብተው የነበረ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ልክ በህወሃት መሃከላዊ
ኮሚቴ ስብሰባ ላይ አባል ያልሆኑ 18 አባላት እንደተሳተፉ ሁሉ አሁንም እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት (ሌሎችም
ሊኖሩ ቢችሉም ምስላቸው ከኢህአዴግ መግለጫ ጋር የታዩት እነዚህ ነበሩ) በመካሄድ ላይ ባለው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ተሳታፊዎች መሆናቸውን ተመልክተናል።

የሰፈር እድር ወይንም የማፊያ ስብሰባ ካልሆነ በስተቀር ራሱን የፖለቲካ ድርጅት አድርጎ የሚቆጥር ቡድን
በሚያካሂደው ድርጅታዊ ስብሰባ ፣ ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባል ያልሆነ
ግለሰብ/ግለሰቦች (ያውም ከአራትና ሰባት ዓመት በላይ አባል ያልነበሩ) በቋሚነት ሊሳተፉበት የሚችል አንዳችም አሳማኝ ምክንያት ሊኖር አይችልም።

ለዚህም ይመስለኛል ስብሰባው እንደተጀመረ የነዚህን ግለሰቦች ተሳትፎ አስመልክቶ አለመጋብባት ተፈጥሮ
እንደነበር የሰማነው። በምን አይነት ሁኔታ አለመግባባቱ እንደተፈታና ስብሰባው እንደቀጠለ ለወደፊት የሚታይ
ቢሆንም ፣ የቆየ የበላይነቱን አስመልክቶ፣ ጸሃይ እየጠለቀችበት እንደሆነና፣ የኦህዴድ አዲሱ አመራርና የነገዱ
ትብብር ያሳሰበው ህውሃት የሸረበው ሴራ አንደሆነ ግልጽ ነው።

ህወሃት ሊገባው ያልቻለው ወይንም መቀበል የከበደው ነገር ቢኖር የነለማም ሆነ የነገዱ እንደከዚህ ቀደሙ
ያለመሆን በራሳቸው ብቻ የመጣ ሳይሆን፣ ባለፉት ጥቂት አመታት የተካሄዱት ሕዝባዊ ትግሎች ያመጡት ጫና
መሆኑን ነው። ይሄም በመሆኑ ህወሃት እንደፈለገው ቢፍጨረጨር ፣ የተለመደውን የመከፋፈል ሴራ
ቢያውጠነጥን ( የዛሬ ወር ወርቅነህ ገበየሁን ተጠቅሞ ቱስ ብሏት የነበረውን የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም በአዲስ
አበባ እንደመከፋፈያ አጀንዳ አሁን በጭንቅ ጊዜ ብቅ አድርጓታል) ከእንግዲህ ወዲህ የበላይነቱን የሚያስቀጥልበት እድል ሊኖር አይችልም።

ትንሽም ቢሆን መንግስታዊና ህዝባዊ ኃላፊነት የሚሰማው ድርጅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በግፍ
እየተገደሉ ባሉበት፣ ከ 600,000 በላይ ዜጎች ዝንትአለም ከኖሩበት በግፍ ተፈናቅለው የተሰደዱበትና፣
ለህይወታቸው አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ መኖራቸው አየታወቀ፣ የአንድ ጠባብ ቡድንን የበላይነት ለማስጠበቅ ሲባል
ብቻ ሴራ ውስጥ ተዘፍቆ መገኘትና ለህዝቡ ችግር መፍትሄ ለማምጣት አለመረባረብ ትልቅ ኢ- ሰብአዊነትን
ያመላክታል።

ይሄም በመሆኑ ይሄን ትርጉም የለሽ ስብስባችሁን በቶሎ ቋጭታችሁ ፣ አፋጣኝ መልስ የሚያስፈልጋቸው
በየስፍራው የሚካሄዱ የዜጎች ግድያ የሚቆምበትንና ፣ የተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በሰላም ተመልሰው
ስለሚቋቋሙበት ጉዳይ ከህዝብ ጋር መምከሩ የተሻለ ነው።

 

Filed in: Amharic