>
5:33 pm - Monday December 5, 2692

ከህዝብ አዉራዎች ላይ እጃችሁንና አይናችሁን አንሱ!! (ሃራ አብዲ)

ሁለት የኦሮምያ ባለ ስልጣናት ላይ ጥቃት ለማድረስ ዉብሸት ላዉጋዉ ወልደሰማያትና ባዩ ትህትና ዘሩ የሚባሉ ግለሰቦች ፣ ከደህንነት መስሪያ ቤት ተልእኮ መቀበላቸዉ ተሰማ!!

እንግዲህ ምን እንላለን?

የሀገራችን ሰዉ እንዲሆንበት የማይፈልገዉን ነገር፤ ህልም እልም፤ ህልም እልም፤ እንዲል፤ እኔም ህልም እልም ፣ ስል አመሻሽቼ ሃሳቤን ሳላጋራ አይኖቼን ለእንቅልፍ መክደን አልሆን ቢለኝ ነዉ በዉድቅት ለሊት ይህችን መጫጫሬ።
ህወሃትን የያዘዉ ሌሎችን የአለም አምባገነኖችን የሚይዘዉ አባዜ በመሆኑ የማይቀርለትን ዉድቀት
ከማፋጠን ለመታቀብ የፈለገ አይመስልም። ቢያንስ ባሁኑ ጊዜ። ሀገሩንና ወገኑን ከመዉደድ አልፎ መጪዉ ጊዜ የሚያሳስበዉ ኢትዮጵያዊ ፣ በሚችለዉ፣ ህወሃትን አደራ ብሎአል። አስጠንቅቆአል። የመጀመሪያዋን ጥይት ብትተኩስ የመጨረሻዎቹ ጥይቶች ባንተ እና በደጋፊዎችህ ላይ ይዘንባሉ በሚል ቅላጼ፣ በቀደመዉ እብሪቱ እንዳይቀጥል መክሮአል። ከእንግዲህ ጨዉ ለራስህ ስትል ጣፍጥ ካለበለዚያ ድንጋይ ነዉ ብለዉ ይጥሉሃል ፣ ነዉ።
ከላይ በስም የተጠቀሱት ግለሰቦች የኢ, ፌ, ድ, ሪ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መታወቂያ አላቸዉ። ይጉዋዙበት የነበረዉ ኮሮላ መኪና ታርጋ ቁጥር 279887 አ አ መሆኑንና ተልእኮዉን የሰጣቸዉ የደህንነቱ ሃላፊ ጌታቸዉ አሰፋ መሆኑን የህብር ራዲዮ ዘግቦታል እና ነገሩ በህልም እልም የሚበተን አልሆነም። ግን በእጅጉ የሚያሳዝነዉ፣ ህወሃት በማንአለብኝነትና በድንቁርና ሊወስደዉ ያቀደዉ እርምጃ በሙሉ በመጨረሻ እራሱን መቀመቅ የሚከተዉ መሆኑ ነዉ።
በፓርቲዬ እና በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት ታዉጆብኛል እያለ የሚያላዝነዉ ህወሃት የህዝባቸዉን የልብ
ትርታ አዳምጠዉ ምላሽ ሊሰጡ በተዘጋጁት የኦፒዲኦ ባለስልጣናት ላይ ጥቃት በማሰብ ለመጨረሻዉ
የጣእር ሞቱ እራሱን እያዘጋጀ መሆኑ ለሰሚዉ ግራ ነዉ። መቼ ነዉ ፈሪዎች፣ አምባገነኖች ጠብመንጃ አንቀዉ መሞት የሚተዉት? መቼ ነዉ ጠብመንጃዉን አሰቀምጠዉ እንደ ጀግና ስልጣን ለህዝብ የሚያስረክቡት? መቼ ነዉ እንደገደሉ መኖር ማብቂያ እንዳለዉ የሚረዱት? ዳሩ ምን ይደረግ? ጨቁዋኞች በጉልበት ከላይ ሆነዉ ረግጠዉ መግዛት ስለለመዱ ከስር የሚሆኑ አይመስላቸዉም። (big time!!) ያቺ የመጨረሻዋ ጠብታ ስትሞላ ከስር መሆን ብቻ አይደለም፣ አጥንታቸዉ እንዳይገኝ ሆነዉ ነዉ መቀመቅ የሚወርዱት። ይህንን በነ ሳዳም ሁሴን፣ በነ ሙአመር ጋዳፊ አይተነዋል። የህወሃት ወያኔዎች ግን ይህን ለማየት ጊዜ አልነበራቸዉም። ኢትዮጵያን በዉስጥ ቅኝ አገዛዝ በመሸንሸንና በሀገራችን ከጫፍ እስከ ጫፍ በመራወጥ ዝርፊያ ላይ ተጠምደዉ ነበር።
ዉብሸት ላዉጋዉ ወልሰደማያትና ባዩ ትህትና ዘሩ፣ የአማራ ማህበረሰብ ስም በመታወቂያቸዉ ላይ ቢጻፍም እውነተኛ ማንነታቸዉ በኦሮምያ ፖሊስ ተጣቶ እስከሚቀርብ ድረስ ዝርዝሩ ይቆየን። ዋናዉ ጉዳይ እዚህ ጋ ምንድነዉ ?

ህወሃት የሚገድለዉን ገድሎ ፣ የሚያጫርሰዉን አጫርሶና ለሃያ ሰባትአመታት ገደማ የዘረፈዉን የሀገር ሃብት ይዞ በመጨረሻዉ ትግራይን ገንጥሎ የሁለት ሀገር መንግስት መሆን ሲመኝ አዙሮ የሚያመዛዝንበት አስተሳሰብ የሌለዉ መሆኑ ደግሞ ያበሳጫል። የኢትዮጵያ ህዝብ በዘመናዊ መሳሪያ አይደለም ፋሽስት ኢጣልያን ያርበደበደዉ!! አሁንም ወያኔን እገባበት ገብቶ የበላዉን ከማስተፋት የሚያግደዉ ነገር አይኖርም። በሰሜን ኤርትራ በደቡብ ኢትዮጵያ ሆነዉ እንዲህ ሽር ጉድ የተባለላትን ትግራይ ሳንድዊች ያደርጉዋታል። የማታ ማታ ትግራይን መገንጠልንም ትቶ (አያደርግም አይባልም) ዘራፊዎቹ በዉጭ ሀገር ያከማቹትን ሃብት እየበላን ተንደላቀን እንኖራለን እንዳይሉ፣ ውጭ በሰላም የሚያኖራቸዉ የለም። በደም የቦካ ታሪካቸዉ ለአለም ፍርድ ቤት ቀርቦ ቀሪ ዘመናቸዉን ፣ በቀረብኝ ጮማዉ፤ ድቁሴን በበላሁ፣ እያሉ በእስር ቤት እሳት እንደገባ ስጋ ተኮማትረዉ ወደማይቀረዉ ሞታቸዉ በዉርደት ያዘግማሉ።
ላሁኑ የጥቃቱ ኢላማ የሆኑት እነ እከሌ ናቸዉ ለማለት አልፈልግም። ጠላት ደስ አይበለዉ!!! እንዳሉት ተሳክቶላቸዉ ጉዳት እንኩዋን ቢያደርሱባቸዉ፣ ወያኔዎች እንደሚያስቡት የህዝቡ ትግል አይቆምም። እነሱም ጠዋት ታይቶ ማታ እንደሚጠፋ ጤዛ የሚጠፉና የሚረሱ አይሆኑም። ከአርባ አመታት በላይ በዙፋን ላይ ተኮፍሰዉ በመጨረሻ ሌባ ሌባ እየተባሉ ከስልጣን የወረዱት አፄ ሃይለስላሴ የህዝቡን አመፅ ማስቆም ስላልቻሉ ነዉ። ከአስራሰባት አመት የደም ስልጣን በሁዋላ መንግስቱ ሀይለማርያም እንደ ሎጥ ሚስት ወደ ሁዋላህ እንዳያይ በርሮ ወደ ሙጋቤ እግሬ አዉጭኝ ያለዉ የኢትዮጵያን ህዝብም፣ ሌሎቹንም የለዉጥ ሀይሎች ትግል በግድያ ብዛት ማስቆም ስላልቻለ ነዉ።
ወያኔዎችም አፈር ድሜ በልተዉ፣ በቅጫም ተወረዉ አራት ኪሎ ቤተመንግስት የገቡት ጀግናዉ የኢትዮጵያ ሰራዊት የደርግን አገዛዝ በመጠየፉና ጠብመንጃዉን ዘቅዝቆ መንገድ ስለለቀቀላቸዉ ነዉ። በዚያ ቅጥፈታቸዉ ለዉጥ እናመጣለን በማለታቸዉ ሰራዊቱ ወር ተራዉን ለእነሱ አሳለፈ። ለደርግ ዉድቀት ሌሎች ብዙ ፋክተሮች ቢኖሩም፣ ላሳስባቸዉ የምፈልገዉ ይሀንኑ ብቻ ነዉ። ጊዜዉ ሲደርስ ለዉጥ አይቀሬ ነዉ። ጊዜዉ አሁን ደርሶአል። እነዚህ ክፋት የደገሱላቸዉ የኦሮሞ ጀግኖችና የኢትዮጵያ ተስፋዎች፣ ቢኖሩም ባይኖሩም ታሪካቸዉን ትዉልድ ከትዉልድ ሲቀባበለዉ ይኖራል። መንግስቱ ንዋይ፣ ገርማሜ ንዋይ፣ በላይ ዘለቀ፣ አፄ ቴዎድሮስ፤ አጼ ምኒሊክ እና እልፍ ጀግኖች ተረስተዉ እንደሆን፣ ያሁኖቹም ጀግኖቻችን ይረሳሉ ብለዉ ይጠብቁ። እነርሱ እንደሚፎክሩት በእነሱ አይበገሬነት አይደለም ወደስልጣን የመጡት። ታግለን ደርግን አሸንፈናልና ለመቶ አመት ኢትዮጵያን እየጠላን ፣ እየዘረፍን፣ እያብጠለጠልን እንገዛታለን ብለዉ የሚደነፉት፣ ለማያዉቃቸዉ ይታጠኑ። በቅድምያ ደርግ እራሱን በራሱ ነዉ የጣለዉ። በእብሪት። እነርሱም የደርግን ፈለግ በመከተል አጥፍተዉ ሊጠፉ
ጠብመንጃ በመወልወል፤ ሰራዊት ወደከተማ በማስገባትና በኦሮምያ ባለስልጣናት ላይ ጥቃት  ማቀድ የመጨረሻዉን ትንቅንቅ ለማድረግ የተዘጋጁ ይመስላሉ። ወዲሁም፤ ሁለቱ የጥፋት መልእክተኞች
በሚሰጡት ምስክርነት እዉነቱ ጸሃይ ከሞቀዉ በሁዋላ ተልእኮዉን የሰጡት እነ ጌታቸዉ አስፋ በሰፈሩት ቁና ይሰፈራሉ። ፓርቲዬንና ህዝቤን ያለዉ ዘረኛ ከመቅጽበት እጁን ከጠብመንጃ፤ ልቡን ከሰራዊቱ ላይ ያንሳ። ሰራዊቱ የሀገርና የህዝብ መከታ ነዉ። አሁንም ጀምበር ፈፅማ አልጠለቀችም። ከህዝብ አዉራዎች ላይ እጃችሁንና አይናችሁን አንሱ!! እንኩዋን በእናንተ ጥቃት ደርሶባቸዉ ይቅርና ከእንግዲህ እንቅፋት እንኩዋን ቢመታቸዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆ ብሎ ተነስቶ እንደሱናሚ እንደሚያጥለቀልቃችሁ እወቁት!!

Filed in: Amharic