>

የአሁኗ ኢትዮጲያ ለሰላማዊ ለውጥ ቀርቶ ለመፈንቅለ መንግስት እንኳን ያልታደለች ሀገር ናት (ስዩም ተሾመ)

አቶ ጌታቸው አሰፋ የሀገሪቱ የደህንነት ኃላፊ እንደመሆናቸው መጠን በተለያዩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ሊገቡ እንደሚችሉ ይገመታል። ይህን የማድረግ ስልጣን የተሰጣቸው የሀገርና ሕዝብን ደህንነት ለማስከበር እንጂ የህወሓትን የፖለቲካ አጀንዳ እንዲያስፈፅሙ አልነበረም። የዊኪሊክስ መረጃ ማንበብ ስለ አቶ ጌታቸው የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ጥሩ ምልከታ ይሰጣል። እንዲህ ያለ የሃሳብና አመለካከት ነፃነትን እንደ ወንጀል የሚቆጥር ግለሰብ የአንድ ሀገር የመረጃና ደህንነት ኃላፊ መሆኑ በራሱ ያሳቅቃል። በዚህ ላይ አንድን ብሔር የሚወክል የፖለቲካ ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ አባል መሆናቸው ደግሞ እጅግ በጣም ያስገርማል። አንዳንድ የህወሓት/ኢህአዴግ ደጋፊዎች የአቶ ጌታቸው አሰፋ የፎቶ ምስል “የላቸውም” ብለው ሲለጥፉ ማየት ደግሞ የባሰ ያስቃል።

አቶ ጌታቸው የህወሓት ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል ነው። ስለዚህ ህወሓቶች የሚያውቁት እኛ የማናውቀው ሰው በሁላችንም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ይወስናል። እንበልና በህወሓትና ኦህዴድ ወይም ብአዴን መካከል አለመግበባትና ልዩነት ቢፈጠር፣ እንደ ድርጅቱ አባል የህወሓትን አጀንዳ ለማስፈፀም ይስራል። ልክ ጉዳዩ እየከረረ ሄዶ የህወሓትን የስልጣን የበላይነትና ተጠቃሚነት የሚነካ ሆኖ ሲገኝ የሀገርና ህዝብን ደህንነት እንዲያስከበር የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት የድርጅቱን ጥቅምና የበላይነት ለማስከበር ይጠቀምበታል። ከመረጃና ደህንነቱ ኃላፊ ጎን ደግሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ዋና አዛዥ ይከተላል። በዚህ መልኩ የሀገሪቱ የደህንነትና መከላከያ መዋቅርና የሰው ኃይል የህወሓትን የስልጣን የበላይነት ለማረጋገጥ ይውላል። መቼም ከሀገሪቱ የመከላከያና ደህንነት መዋቅር ውጪ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ አይታሰብም። እነዚህ ሁለት መስሪያ ቤቶች አደረጃጀት ደግሞ የህወሓትን የበላይነት በማስቀጠል ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ስለዚህ መፈንቅለ መንግስት እንኳን ቢደረግ በእነዚህ ሁለት አካላት ፍቃድና ድጋፍ እንደመሆኑ ዓላማው የህወሓት የበላይነት ማስቀጠል ይሆናል። በአጠቃላይ፣ የአሁኗ ኢትዮጲያ ለሰላማዊ ለውጥ ቀርቶ ለመፈንቅለ መንግስት እንኳን ያልታደለች ሀገር ናት።

Filed in: Amharic