>

ዉሳኔ አልባዉና አይቋጬው የኢሓአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቲ ስብሰባ (ግርማ ካሳ)

ስለ ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ የጠየቃችሁኝ አላችሁ። ስብሰባውን ገና አልጨረሱም።እንደ ዜና ሊቀርብ የሚችል የወሰኑት ዉሳኔ የለም። የአባዱላን ከአፈጉባዬነት ለመልቀቅ ያስገባዉን መለቀቂያ ከመቀበል ውጭ። እርሱም ቢሆን እንደትልቅ ነገር የሚቆጠር አይደለም። አባዱላ ለቀቀ ቆየ ያው ነውና።

በስራ አስፈፃሚው ህወሃቶች ከአጋሮቻቸው ጋር ጊዜ በመግዛት እነ ለማንና ገዱን ለማዳከም እየሞከሩ ነው።እነ ለማና ገዱን በስብሰባ ጠምደው፣ “እንደዚህ ቅር ያላችሁ አይመስለንም ነበር፤ እናሻሽላለን፣ እናስተካክላለን፣ አንዳንድ ነገሮች እንለቃለን፣ አንድ ሆነን መቀጠል አለብን ፣  ወደ ዉሽ ሳንወጣ ተመካክረን እንፈታዋለን….” በማለት እያዘናጉና እያማለሉ ፣ ውስጥ ውስጡን ግን ህወሃቶች ስራቸውን እየሰሩ ነው። ስብሰባው በተራዘመ ቁጥር ሕወሃት አፈር ልሳ መነሳቷ፣ የበለጠም ፈርጥማ መዉጣቷ አይቀሬ ነው። ኦህዴዶችና ብአዴኖች ካልነቁ።

ትልቁ ስትራቴጂያቸውም እነለማ የጠየቁትን እሺ ብለው ገዱን መምታት፣ ኦሮሞውን ከሌላው መለየት  ነው። እነ ለማን ለማስደስት በሚል አንደኛ  አዲስ አበባን ህዋሃት የመስዋት በግ ለማድረግ ተዘጋጅቱዋል። ሁለተኛ አፋን ኣሮሞም በላቲን የፋዴራል ቋንቋ ሊሆን ይችላል። ሶስተኛ ህወሃት አብዲ ኡመር እንዱሰበሰብ ያደርጋሉ። አራተኛ የመከላከያና ደህንነቱ ሳይነኩ  ከኣህዴድ  ጠ/ሚ እንዱሆን ሃሳብ አለቸው።

ሆኖም እነ ለማ መገርሳ ከነገዱ ጋር ያላቸውን መቀራረብ ለማበላሸት ፍላጎት ያለቸው አይመሳልም።  ከዚህም የተነሳ ምንም ስምምነት እስከአሁን የለም።

ከብአዴን 3 አመራሮች ( አለምነህ መኮንን፣ አህመድ አብተው፣ ጫኔ ከበደ) የህወሃትን አቋም ይዘዋል። ሶስት መሃል ሰፋሪ ናቸው። ሶስት ገዱን ጨምሮ ወጥረው ይዘዋል። አብዛኛው የብአዴን አመራር ህወሃትን የሚደግፍ ወይም አደርባይ ፈሪ ስለሆነ ብአዴን ደካማ ሆኖ ነው የቀረበው። ከዚህም የተነሳ የአማራ ክልል ህዝብ ጥያቄ ምላሽ የማግኘቱ እድል ዜሮ ነው።

አህዴድ ጋር ከአንዱ በስተቀር (ወርቅነህ ገበየሁ) ስምንቱ የኣባላት ተመሳሳይ አቋም ነው ያሳዩት። ከዚህም የተነሳ ኣህዶድ በስብሰባው ፈርጠም ብሎ ነው የወጣው።

ስብሰባው ምንም ነገር ሳይቋጭ ከሳምንታት አልፎ ከወራት ሊቀጥል ይችላል።  ሕወሃቶች ምንም መሰረታዊ ዉሳኔ ሳይወሰን  በሰብሰባ ላይ ስብሰባ፣ በግምገማ ላይ ግምገማ እያሉ ፣ እያጭበረበሩ፣ እየደለሉ፣ እየከፋፈሉ፣ የሕዝብ ጥያቂ ሳይመለስ ቢቀጥሉ ደስታቸው ነው። ትልቁ ጥያቄ ግን ያ እንዲሆን ኦህዴዶችና ብአዴኖች ይፈቅዳል ወይ የሚለው ነው።

Filed in: Amharic