በህወሃት ወያኔ እስር ቤት የሚገኙ ወገኖቻችን በስምና በአካል የሚታወቁ ቢኖሩም ስም ዝርዝር ጠቅሶ መጨረስ ፈጽሞ አይቻልም አላማቸውና ትግላቸው ግን አንድ ነው !! ለራሳቸው ሳይሆን ለእኔም፣ለአንተም፣ ለአንችም ብለው ስለሃገራቸው ነጻነት የሚታገሉ በዘረኛው ህወሃት ወያኔ እጅ ወድቀው በወህኒ ቤት የመከራን ጽዋ እየቀመሱ የሚገኙ በብዙ ሽ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ስቃይና መከራ ያበቃ ዘንድየጀመሩትን የነጻነት ትግል ከዳር ለማድረስ ከጎናቸው እንቁም ። ፍትህ በወያኔ እጅ ወድቀው በእስር ለሚሰቃዩት ኢትዮጵያውያን በሙሉ ይሁን !!
ማዕከላዊ እሥር ቤት ውስጥ፣ አንድ መርማሪ ቃሌን ይቀበላል። ይጠይቀኛል እመልሳለሁ ። በክፍሉ ውስጥ መርማሪ ፖሊሱና እኔ ብቻ ነበርን ።…በመሃል አንድ ሲቪል የለበሰ ሠው በሩን ከፍቶ ገባ።….ክፍሉ ውስጥ( ቃል የምሰጥበት) ትንሽ ጎርደድ ፣ ጎርደድ ካለ በኅላ ፣ ሳላስበው በጥፊ መታኝ ።…ይቺ ጥፊ አደገችና በንጋታው ወደ ቦክስ ተቀየረች።
በዚያው ቀን ለሊት ላይ የታሰርኩበት ክፍል ተከፈተ። በክፍሉ ምንም ዓይነት ብርሃን ሥላልነበረ፣ በሩን የከፈተውን ሰው መለየት አልቻልኩም ።….ወዲያው፣ ረጅም የባትሪ ብርሃን ዓይኔ ላይበራብኝ ። ማንነታቸውን ያለየኋቸው ሰዎች ክፍሌ ውስጥ ዘለቁ ። ….” ተነስ” ተባልኩ ።…ተነሳሁ ።…ዓይኔን በጨርቅ ግጥም አድርገው አሰሩት ።……..በእነሱ መሪነት፣ ( ክንዴን ይዘው)ክፍሌን ለቅቄ ወጣሁ ። ወዴት እንደሚወስዱኝ አላውቅም ።…ግን፣ ኮረኮንች ላይ እንዳለሁ ይታወቀኛል ።…ጫማ ስላላደረኩ፣ እግሬን ጠጠር ይወጋኝ ነበር ።…ከዚያም ደረጃ መውጣቴንአስታውሳለሁ ። ደረጃውን እንደጨረስኩ አንድ ቤት ውስጥ አስገቡኝ ።….(ቤት ውስጥ መግባቴን ያወኩት፣በሩን ሲከፍቱ ስለሰማሁ ነው) ወዲያው በጠረባ መትተው ጣሉኝ ከዚያም..የሚችሉትን አደረጉ ።…እስኪደክማቸው።
………በዚያም አላቆሙም አንስተው ገለበጡኝ ። ……( ቶርች)….ሲጨርሱ ተሸክመው ክፍሌ ውስጥ ጥለውኝ ሄዱ ።
ይህ ከላይ የተፃፈው ታላቁ እና ጀግናው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ የደረሰው በደል ነው ። እስክንድር ነጋ ይህን ሁሉ መከራ የተቀበለው እና እየተቀበለ ያለው በኢትዮጵያዊነቱ የኢትዮጵያ ጉዳይያገባኛል ፤ ፍትህ ፣ ነፃነት እና እኩልነት ይገባኛል ብሎ ነፍጥ አንስቶ ሳይሆን ብዕር ጨብጦ ሃሳቡን በወረቀት ስለገለፀ ነው ።
እስኪ እናንተ እውነት ለሰው ልጅ ክብር ካላችሁ ፤ ስለ ኢትዮጵያ ያገባናል ካላችሁ እና እንደ እስክንድር ነጋ ፍትህ ፣ ነፃነት እና እኩልነት ይገባናል ምትሉ ከሆነ ይህ ዓይነት ግፍ በኢትዮጵያ ውስጥሲፈፀም እንዴት ዝም ትላላችሁ ? እኛስ እንደዜጋ መች ነው ይሄን መንግስት ልክ የምናስገባው ?
ጋዜጠኛ እስክንድር እንደብዙሐኑ እነሱ የሚፈልጉትን ፈጽሞ ከባለቤቱ ከስርካለም ፋሲል ጋር ልጃቸው ናፍቆት እስክንድርን ት/ት እያመላለሰ ( በነገራችን ላይ እስክንድር ነጋ በመጨረሻ እስርቤት ሲገባ ልጁን ናፍቆትን ከት/ቤት በሚያመጣበት ሰዓት ነበር እና ደህንነቶች ሲጎትቱት እና ሲያዋክቡት ይህ ህፃን ልጅ ተመልካች ሆንዋል ። እስኪ አስቡት ይህ የሆነው እናንተ ላይ ቢሆን እናልጃችሁ ተመልካች ቢሆን ? ትዳሩን እያሞቀ እና ስራውን በስደትም ይሁን በአገር ውስጥ መኖር ይችል ነበር ። እስክንድር ግን ከልጁ ከናፍቆት እና ከባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል ይልቅ በፍትህ ፤በነፃነት እና በእኩልነት የተገነባችን ኢትዮጵያ ለልጁም ሆነ ለወገኖቹ ተፈጥራ ማየትን መረጠ ። ነፃነት ፣ ፍትህ እና እኩልነት እያለ እነሆ በቃልቲ ከታሰረ አራት አመት በላይ ሆነው ።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ይህን ግፍ ለባለቤቱ ለሰርካለም ፋሲል ሲነግራት ምን እንደተስማት ለማወቅ በሷ ጫማ ውስጥ መቆም አይጠበቅም ። እንዲህ ዓይነት ግፍ እና መከራ በወገኖቻችን ላይሲፈጸም እነሆ 25 ዓመት አለፈ ። ግን እስከመቼ ??
***
በግፍ የ25 ዓመታት ጽኑ እስራት ተፈርዶበት
( በይግባኝ ወደ 16 ዓመት “ተሻሽሏል“)
አበበ ቀስቶ
.
<<አበበ ቀስቶ ገራሚ ሰው ነው፡፡በካድሬነት ዘመኔ ኢህአዴግን የሚንቅ እንደሱ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ብዙሃኑ በፍራቻ አቁማዳ ውስጥ ተደብቆ በነበረበት ሰዓት ኢህአዴግን በአደባባይበመቃወም ፣ሌቦችን በማጋለጥ ፋና ወጊ ነበር፡፡ ስለብዙዎቹ ባለስልጣናት የማያውቀው ሚስጥር የለም፡፡በምርጫ 92 በተቃራኒ መስመር ብንሰለፍም መቀራረብ ፈጥረን ነበር፡፡ ብዙ ነገሮችንአጫውቶኛል፡፡ በሂደት ሳጣራው የተጋነኑ ነገሮች ቢኖሩም አብዛኞቹ ትክክል ነበሩ፡፡
በተለይ የህዝቡን ስሜት ከማንበብ አንጻር ከፍተኛ ብቃት ነበረው፡፡ ቀበሌዎችን በቁጥር እየጠራ ፣‹‹በዚህ ታሸንፉኛላችሁ፣ በእነዚህ ደግሞ በዝረራ አሸንፋለሁ›› ይለን ነበር፡፡ እያደር የአበበአሸናፊነት ፍንትው ብሎ ወጣ፡፡ ከምርጫው ፉክክር ገለል የሚልበት አማራጮች ታሰቡ፡፡ እሱን ማስፈራራት የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ምድር ቢንቀጠቀጥ የሚፈራ ሰው አይደለም፡፡ በቁጥጥር ስርለማዋል ደግሞ ወንጀል ሲሰራ እጅ ከፍንጅ መያዝ አለበት፡፡ ስለዚህ የቀረው የመጨረሻ አማራጭ በገንዘብ መደለል ሆነ፡፡ ለመደለያ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ እናምከዶክተር ቶፊቅ አምሳ ሺህ ብር ተመደበለት፡፡ አግባብተው እንዲሰጡት ደግሞ ዳኛ ልኡልና ኪሮስ ተመራጭ ሆኑ፡፡ሁለቱ ሰዎች ገንዘቡን ይዘው አበበን ማግባባት ቀጠሉ፡፡ እያደር ለኢህአዴግየምርጫ ኮሚቴ ተስፋ ሰጪ መልእክቶች መደመጥ ጀመሩ፡፡
ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀረው አበበ ውሳኔውን አሳወቀ ‹‹የተጋበዝኩትና ብራችሁን የተጠቀምኩት እናንተ ጋር የማይነጥፍ የብር ማምረቻ ስላለ ነው፡፡ምርጫ የምወዳደረው ግን ለገንዘብሳይሆን ይህን አስከፊ ስርዓት ለመጣልና ለነጻነቴ ነው፡፡ በዚህ ላይ ለመደራደር ህሊናዬ አይፈቅድም››፡፡
አበበ ተወዳደረ፥ ግን አሸንፎ ተሸነፈ፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ አበበ የህዝብ ብሶት የሚያመው ትንታግ ታጋይ ነበር፡፡ ከጅማ ሰፈር እስከ ሜክሲኮና ስድስት ኪሎ በእግሩ እየሄደ የሚያስተጋባ፡፡ አበበ የህዝብ አይንና ጆሮ ነበረ፡፡ የነዋሪውንምሬትና እንግልት በአደባባይ የሚያጋልጥ፡፡ አበበ የኢህአዴግ ካድሬዎችን ንቅዘት እየተከታተለ የሚያጋልጥ አሸባሪ ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበረው አሊ አብዶ ከሚፈራቸው ሰዎች አንዱ አበበ ቀስቶ ነበር፡፡
***
(አንዷለም አራጌ ፣ ከቃሊቲ)
.ሕዝብ የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት በሆነበት ሃገር ፍትህ ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ትቀመጣለች፡፡ እውነትም ምሰሶና ወጋግራ ሆና ፍትህን ዘወትር የመደገፍ እድሏን ትጎናጸፋለች፡፡ በኢትዮጵያ የፍትህና የእውነትንየክብር ቦታና ሚና አፈ-ሙዝ ወስዶታል፡፡ ፍትህና እውነት ደግሞ ትቢያ ላይ ተጥለዋል – ምንም እንኳ እንደወደቁ ባይኖሩም፡፡ በኢትዮጵያ ፍትህና እውነት ትቢያ ላይ ባይጣሉ ኖሮ ለዓመታት ይቅርናለሰዓታት እንኳን በእስር ቤት ግርጌ መጣል ባላስፈለገንም ነበር፡፡
ፍትህና እውነት በኢትዮጵያ አድራሻ ቢኖራቸው ኖሮ ለዚህ ዓለም እንግዳ የሆኑት ልጆቼ ለዓመታት ሳይሆን ለሰዓታት እንኳን የአባታቸውን ፍቅር በግፍ ባልተነጠቁ ነበር፡፡ ፍትህና እውነት የሰፈኑባትኢትዮጵያ እውን ብትሆን ኖሮ ለዓመታት ሳይሆን ለሰዓታት እንኳን ባለቤቴ ከእኔ ጋር የመኖር ሰብዓዊ መብቷን ተገፋ በወጣትነት እድሜዋ የመበለትነት ህይወት የመግፋት እዳ ባልወደቀባት ነበር፡፡ ፍትህናእውነት በኢትዮጵያ
ሰማይ ላይ እንኳን መንሳፈፍ ቢችሉ ኖሮ በሃሰት ዶሴ ከታሰርኩ በኋላም ለዓመታት በእስር ቤትውስጥ ተጨማሪ የግፍ ፅዋ እንድንጎነጭ ግድ ባልሆነብኝም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ እውነትና ፍትህ ከትቢያ የተሻለ ቦታ ቢኖራቸው ኖሮ ረጅም ርቀት አቆራርጠው ሊተይቁኝ የሚመጡ ጠያቂዎቼ የመጠየቅ መብታቸውን ለዓመታት ሳይሆን ለሰዓታት እንኳንባልተነፈጉም ነበር፡፡
በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊቷ ኢትዮጵያ እኔና ቤተሰቤ ፍፁም ኢሰብዓዊ ከሆኑ ነገሮች ጋር ተላምደን፤ በሞትና በህይወት መካከል ያለው ልዩነት እስኪጠፋን ድረስ በአባቶቻችን፣ በራሳችንና በልጆቻችን ሃገር፤ በህዝባችን ፊት በማናለብኝነት ጥቂት አፄዎች ጢባጢቢእንዲጫወቱብን ተበይኖብናል፡፡ በውል የማውቀውን የራሴን ጉዳይ በዋናነት ባነሳም የእኔና የቤተሰቦቼ ህይወት የእነ እስክንድር ነጋንና ሌሎች አንባቢ ፈፅሞ የማይዘነጋቸው ኢትዮጵያውያንና ቤተሰቦቻቸውም ፅዋ መሆኑን ፈፅሞ ዘንግቼው አይደለም፡፡ በየትምቢሆን አንድ
ዜጋ የግፍ ፅዋ እንዲጎነጭ ሲገደድ የሚጠጣው የኢ-ፍትሃዊነት ስቃይ ጥልቅ ነው፡፡ በተለይ ግን በሚወደው ህዝቡ ፊትና የእኔ ብሎ በሚኮራበት ሃገሩ እንደርሱ ደምና ስጋ የለበሱ ጥቂቶች ያሻቸውን ሲፈፅሙበት የግፉ ስቃይ ከመቼውም በላይ ይከፋል፡፡ ይህንንከመሰለው የኢፍትሃዊነት ስቃይ ለአፍታም ቢሆን የሚያሳርፋቸው ግን አንድ ነገር አለ፡፡ አንባቢ የማይዘነጋቸው ወይዘሮ ሮዛ ፓርክስ
መቀመጫቸውን ለቀው የኋላ ወንበር ላይ እንዲቀመጡ አሊያም ከአውቶብስ እንዲወርዱ ሲጠየቁ በእግራቸው መሄድን መምረጣቸው ብቻ ሳይሆን ለምርጫቸው የሰጡት አመክንዮ ጥልቅ ትርጉም አለው፡፡ ‹‹በእግርሽ ይሄንን ያህል ማይል መጓዝ ይሻላልን?››ለሚለው ጥያቄ ‹‹እግሮቼ ይደክማሉ ነፍሴ ግን ታርፋለች›!›› ብለው ነበር፡፡
እኔም በምወዳት ሃገሬ በህዝቤ ፊት ከእነቤተሰቤ የግፍ ሰለባ ብሆንም ህሊናዬን የሚጎረብጠኝ ነገር ባለመኖሩ የእኔም ነፍስ እረፍት አላጣችም፡፡ የሌሎች በግፍ የታሰሩ ጓደኞቼም ህሊናቸውው ፍፁም እረፍት የተጎናፀፈ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ትልቁ የህሊና እዳ በሃሰትካሰሩኝ በኋላም በግፍ ተግባራቸው የሚመፃደቁት አሳሪዎቼ እንጂ የእኔ አይደለም፡፡ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል የተገደደ እኔን የሚመስል
ዜጋ ሞትንም እንኳን ቢሆን በክብርና በደስታ ለመጋፈት ይዘጋጃል እንጂ ህሊናውን ሰላም በሚያሳጣ ድር ተጠልፎ አይወድቅም፡፡
ውድ አንባቢ በእኔ ጫማ ውስጥ ቢቆሙ ከዚህ የተለየ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? በሃገርዎ፣ በህዝብዎ ከምንም በላይ በህልውናዎና በእጣዎ ላይ የግል አቋምዎን እንዳያራምዱ በሃሰት ዶሴ ተጠርቀው መቀመቅ ቢወርዱ ከዚህ የተለየ አቋም ሊኖርዎት ይችል ይሆን?
በሚያምኑበት ጉዳይ ተሸብበው የሚነገርዎትን ብቻ እንዲፈፅሙ ቢነገርዎት ይስማማሉን? የመብቶቹ ባለቤት ላልሆነ ዜጋ ሰው መሆን ማለት ምን ትርጉም ይሰጣል? ይኸ ሁሉ አንሶ በእሾህ በታጠረ የፖለቲካ ሰርጥ ውስጥ በተቦዳደሰ እግርዎ እያነከሱእንዳይንከላወሱ እንኳን ‹‹እግር በመቁረጥ›› ፈሊጥ የተካኑ ገዥዎች እግርዎን ቢቆርጡት ምን አይነት ስሜት ይፈጥርብዎታል? ጥቂት ዙፋን ላይ የተቀመጡ ባለጊዜዎች ምን ማሰብ እንዳለብዎ እንኳን ሳይቀር ሲወስኑልዎ እና ባጠቃላይ የርስዎ ህልውናና ተፈጥሮአዊ መብትዎችዎ በነሱ መዳፍ ስር ያሉ፤ ከፈለጉ ብቻ ቆንጥረው የሚሰትዎ ካላሻቸው የሚነፍጉት ሲሆን ምን አይነት ትርጉም ይሰጥዎት ይሆን?
አዎ ሀገር በጭቆና ቀንበር ስር ስትወድቅ ድጋፍ ብቻ እንጅ የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት ስርየት የሌለው ሃጢያት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ለገዥዎች በታጠረው አጥር ውስጥ በድፍረት ለማቋረጥ ሲሞክሩ ‹‹ቀዩን መስመር አልፈዋል›› በሚል አይቀጡ ቅጣት ይቀጣሉ፡፡በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ግፎች እንደነውር ወይም ግፍ ሳይሆን አገዛዙን ለማስቀጠል የሚያስፈልጉ፤ ከትልቅ አዕምሮ የተቀዱ ልዩ የፖለቲካ ቀመሮች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ በአገዛዙና የግፍ ሰለባ በሆነ እኔን በመሰለ ዜጋ መካከል የሚደረገው ትግል ከወትሮው የተለየ ነው….፡፡
***
…