>
8:10 am - Sunday January 29, 2023

ተቃዋሚ ኃይሎችና ኢህአዴግ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች! (ዮናሰ ሀጎስ)

ይህ ፅሁፍ ሁሉንም ተቃዋሚዎች እንደማይወክል ይሰመርበት!
ለምንድን ኢህአዴግን እንቃወማለን? 
ስለ ግድያው ነው? ስለ እስራቱ ነው? ስለ ጭቆናው ነው? ወይንስ ስለ አፈናና ብዝበዛው ነው?
•°•
አይደለም! በኔ እምነት እነዚህ ነገሮች የችግሩ ውጤት እንጂ ራሱ ችግሩ አይደሉም።
•°•
ኢህአዴግን የምንቃወምበት ዋንኛው ምክንያት «ከኔ የተለየ እንዳታስቡ» በማለቱ ብቻ ነው። ሌላ ምንም ምክንያት የለም።
•°•
ኢህአዴግ ከኔ የተለየ እንዳታስቡ በማለቱ ምክንያት ከሱ የተለየ አቋም ያላቸውን ሰዎች ሲያሳድድና ሲገርፍ ሲያስርና ሲገድል 26 ዓመት ቆይቷል። የኢህአዴግ መስራች የሆነው ሕወሐት ገና ከበረኃ ሳለ ጀምሮ ከማዕከላዊው እምነት የተለየ አቋም ያራመዱ ሰዎችን እየረሸነና እየገደለ ነው ወደ ስልጣን ላይ የመጣው። በዚህ ምክንያት ብዙ ከተራ አባላት እስከ ድርጅቱ አመራሮች ድረስ የግድያና ስደት ሰለባ መሆናቸውን ዛሬ በሕይወት ተርፈው ታሪኩን ለመናገር በበቁት የቀድሞ የድርጅቱ አመራሮች በእነ ዶክተር አረጋዊ በርሄና ሌሎችም የተመሰከረለት ሐቅ ለመሆን ችሏል። ሕወሐት/ኢህአዴግ ከራሱ የተለየ አቋም የሚያራምዱ አካላትን ለማጥቃት ሲፈልግ መጀመርያ የሆነ ታርጋ ይለጥፍላቸዋል። «ቅጥረኞች፣ ባንዳ፣ የሻዕቢያ ተላላኪዎች፣ የግንቦት 7 ቅጥረኞች፣ የግብፅ ቅጥረኞች፣ የሳውዲ ቅጥረኞች (ድምፃችን ይሰማ ላሉ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት የተሰጠ ታርጋ)፣ ኦነግ፣ ትምህከተኞች፣ ጠባቦች፣ ሐገር አፍራሾች …» እነዚህ ባለፉት ዓመታት በገዢው አካል የፕሮፖጋንዳ ማዕከላት ስንሰማቸው የኖሩ ታርጋዎች ናቸው። አንድ ጊዜ ታርጋው ከተለጠፈ በኋላ ዒላማ የተደረጉ ሰዎችን በገፍ ለማሰር፣ ለመግደልና ከሐገር ለማባረር ምቹ ይሆንለታል። ይህ አሰራር ከበረኃው ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የዘለቀ አሰራር ነው። ብዙዎቹም የዚህ ሰለባ ሆነው የደረሱበት ሳይታወቅ የቀሩ፣ ለስደት የተዳረጉ፣ የተገደሉና የተደበደቡ አሉ።
•°•
እነዚህ ችግሮች ተደራርበው ነው ዛሬ ላለንበት ሐገራዊ ተቃውሞ ደረጃ የደረሱት። ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ይህ ችግር እዚያው በረኃ ላይ እያለ መፍትሔ አግኝቶ ኢህአዴግ ገና ከምስረታው የተለዩ ሐሳቦችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚያወያይና የሚያራምድ አሊያም ሐሳብን በሐሳብ ድባቅ እየመታ የሚሄድ ድርጅት ሆኖ ቢሆን ኖሮ ላለፉት 26 ዓመታት ያየናቸው ችግሮች አይከሰቱም ነበረ። ኢህአዴግም አሁን የምናየው አጣብቂኝ ችግር ውስጥ አይገባም ነበረ።
•°•
የሚያስገርመው ታድያ ይህን ባሕርይ የኢህአዴግ አብዛኞቹ ተቃዋሚዎችም መያዛቸውና ይህን ባህርይ ይዘው ኢህአዴግን ለመተካት ማቀዳቸው ነው። አብዛኞቹ የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ልክ እንደ ኢህአዴግ አንድ መስመር ብቻ ተከትለው መጓዝ የሚፈልጉና ከዛ መስመር የተለየ ሐሳብ ለሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ሆነ አካል «ወያኔ!» አሊያም ሰውዬው ትግሬ ካልሆነ «የወያኔ ተላላኪ» የምትል ታርጋ ለመለጠፍ ወደኋላ የማይሉ መሆናቸው እነዚህ ተቃዋሚዎች በኢህአዴግ ከተተኩ ሐገሪቷ የአምባገነን መለዋወጥ እንጂ ሌላ ጠብ የሚል ለውጥ እንደማታይ አመላካች የሆነ ነገር ነው። እነዚህ ተቃዋሚዎች ልክ ሕወሐት ከበረኃ ወደ ስልጣን እየመጣ በነበረበት ጊዜ ያደርገው እንደነበረ ሁሉ በመፈክር የሚያምኑ እነርሱ «ፍለጠው!» ሲሉ ሰዉም ከኋላቸው ግርር ብሎ አብሯቸው «ፍለጠው!» ብሎ እንዲጮህ የሚፈልጉ ዓይነት መሆናቸው በሂደት ስልጣን ላይ ከተደላደሉ በኋላ እነዚህ ዛሬ የምናያቸው እስራቶችና ግርፋቶች የማይቀሩ መሆናቸውን በግልፅ የሚያሳይ ነገር ሆኖ አግኝቼዋለሁኝ።
•°•
ሌላው ኢህአዴግንና ተቃዋሚዎችን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች የሚያደርጋቸው ነገር አደረጃጀታቸው ነው። 
•°•
ለዘመናት አህዳዊ አስተዳደር ስትከተል የነበረችው ኢትዮጵያ በ1983 ይህ ዓይነቱ አስተዳደር የብዙ ብሔሮችን ማንነት እና መገለጫ የሚረግጥ ጭቆና የሚፈጥር ስለሆነ ወደ ፌደራላዊ ስርዓት መቀየር አለበት በማለት ስልጣን ላይ የወጣው ኢህአዴግ የሐገሪቱን አስተዳደር ወደ ፌደራላዊ ስርዓት ቀየረው። ይህ መሆኑ ብዙም የሚያስከፋ አልነበረም። ብዙ ብሔሮች በቋንቋችን የመፃፍና ስራ የመቀጠር እድል አገኘን ብለው ተደስተውበት ነበረ። ሆኖም ይህ ፌደራላዊ ስርዓት በብሔሮች ላይ የተመሰረተ ሆነና በተለይ በሁለት ብሄር አዋሳኝ ቦታዎች ላይ በሚኖሩ ማሕበረሰቦች ላይ የማንነት ጥያቄዎችን መፍጠር ጀመረ። ይሄ የማንነት ጥያቄ እየተብላላ ሲሄድ የድንበር ግጭት ቆሰቆሰ። በቋንቋቸው በመማራቸው የተደሰቱ ብሔር ብሔረሰቦች የፌደራሉ የስራ ቋንቋ አማርኛ በመሆኑ በፌደራሉ ውስጥ ተቀጥረው ለመስራት የነበራቸው እድል በጣም ቀነሰ። ከዛም አልፎ ተወልደው ካደጉበትና ከተማሩበት ክልል ውጭ ሌላ ክልል ሄደው ስራ ለመቀጠር አዳጋች ሆነባቸውና ራሱኑ አጨብጭበው የተቀበሉትን የፌደራላዊ ስርዓት ማማረር ጀመሩ። (97 ላይ አዲስ አበባ ውስት ሐገር ያንቀጠቀጠ ተቃውሞ በነበረበት ጊዜ ከከተሞች ውጭ ባሉ ሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ ይህንን ፌደራላዊ ስርዓት ይደግፉ የነበሩት ይበላቸው! በስንት መከራ ያገኘነውን በቋንቋችን የመተዳደር መብት ሊያስነጥቁን ነው… እያሉ በዝምታ አልፈውታል) ዛሬ በየቦታው የብሔር ተኮር ስርዓቱ የፈለፈላቸው ችግሮች እንደ ቦንብ መፈነዳዳት ሲጀምሩ ሁሉም ክልል ግራ ቀኝ ሳይል የዚህ ስርዓት አማራሪ ሆኖ ተገኘና አረፈው።
የኢህአዴግ አደረጃጀት በብሔር የታጠረ መሆኑ ብቻ አይደለም የችግሩ መንስዔ። በሐገሪቷ ውስጥ ያሉት 83 ብሔረሰቦች በአራት ብሔር ተኮር ድርጅት ተጨፍልቀው መግባታቸው ራሱ ያመጣው ከፍተኛ ችግር አለ። በኢህአዴግ ድርጅት ስራ አስፈፃሚ ውስጥ 9 የትግራይ ተወላጆች፣ 9 የአማራ ተወላጆች፣ 9 የኦሮሞ ተወላጆችና 9 ከደቡብ ክልል የተገኙ ተወላጆች በሐገሪቱ እጣ ፈንታ ላይ የመወሰን መብት ሲያገኙ አብዛኞቹ ብሔረሰቦች አጋር በሚባሉት ድርጅቶች ከመወከላቸው ውጭ በዋናው የኢህአዴግ ድርጅት ፈላጭ ቆራጭ ማዕከል ውስጥ ግን አንዲትም ጠብታ ድምፅ የሌላቸው መሆኑ በራሱ ትልቅ ክፍተት ፈጥሯል። ባጠቃላይ ኢህአዴግ በድርጅቱም ሆነ በሐገሪቷ የተከተለው አደረጃጀት ለዛን ጊዜ ሁሉንም ያስደሰተ ይምሰል እንጂ እየቆየ እየቆየ እንደሚፈነዳ የምድር ውስጥ ቦንብ አሁን በየቦታው ለራሱም ለሐገሪቷም ከፍተኛ ችግር እያመጣ ነው።
•°•
ወደ ተቃዋሚዎች ስንመለስ በአሁኑ ጊዜ ተደራጅተናል ከሚሉ ተቃዋሚዎች ውስጥ ምናልባት አግ7 ካልሆነ በቀር ሁሉም ለማለት በሚቻል ሁኔታ በብሔር የተደራጁ ናቸው። በተለይ በቅርቡ የተጀመረው የኦሮማራ እንቅስቃሴ ኢህአዴግ ሐገሪቷ ውስጥ ያሉትን ብሔር ብሔረሰቦች በአራት ግንባር ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች ጨፍልቆ እንደ ሰርዲን ለመክተት ያሰበውን አካሄድ ይበልጥ ባጠበበ ሁኔታ የሐገሪቷን መፃዒ እድል በአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ስም ብቻ በተደራጀ ኃይል ለመወሰን የሚደረግ ርብርቦሽ ተቃዋሚውና ኢህአዴግ እውነትም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን የሚያሳይ አድርጎታል። ሐገሪቷ በኢህአዴግ የመጣባትን የብሔር ተኮር አደረጃጀት በአንድ ድምፅ እየተቃወመች ባለችበት በዚህ ሰዓት ላይ ሌላ ከኢህአዴግ በባሰ ሁኔታ የጠበበ አደረጃጀት በራሷ ላይ ለመጫን ትፈልጋለች ብሎ የሚያስብ አካል መፈጠሩ በጣም አስገራሚ ሁኔታ ላይ መድረሳችንን አመላካች ሆኗል። የፌደራል ሲስተማችንን ባንቀይረው እንኳን በመልካዓ ምድራዊ አቀማመጥ ላይ መስርተነው ከጎሳና ብሔር ተኮር አጀንዳዎች ወጥተን ለሁሉም በምትበቃዋ ምድሪታችን ላይ በሰላም መኖር የምንችልበትን ሁኔታ ተቃዋሚዎች በመንደፍ ሁሉም ዜጋ ከኢህአዴግ ውድቀት በኋላ ደህንነት ተሰምቶት ሊኖርባት የሚችልባትን ሐገር የመገንባት ስራ መስራት እየተቻለ ራሱ ኢህአዴግ ከ26 ዓመታት በኋላ በወደቀበት መስመር ተከትለው በመንጎድ ለውጥ ለማምጣት መሞከር በጣም የሚያስገርም ሆኖ ይታየኛል።
•°•
እንደማጠቃለያ…
•°•
ተቃዋሚ ለመባል አንድ አካል መጀመርያ ከሚቃወመው አካል በሁሉም ነገር ተሽሎ መገኘት አለበት። የምንቃወመው አካል በሚረግጥበት ኮቴ ተከትለን እየረገጥን መስመርህ ተሳስቷልና ስልጣንህን ለኛ ለቅቀህ እኛም ባንተ መስመር ተጉዘን የተለየ ውጤት እናመጣለን ማለት የዋሆችን ያታልል ይሆናል እንጂ ብልጣብልጦችን አያታልልም።

Filed in: Amharic