አብዮታዊ ዴሞክራሲ ይሉታል። ልማታዊ ዴሞክራሲም ይሉታል። ምንም ብያኔ የለውም። ‘ሴንትራላይዝድ’ ወይም ‘የተማከለ ዴሞክራሲ’ ነው። የአራቱ ፓርቲዎች ሥራ አስፈፃሚዎች (ፍትሓዊ ባልሆነ) “በዕኩልነት መርሕ” ይሰባሰባሉ። እነሱ በዝግ የሚወስኑት በፓርላማ ሕግ ሆኖ ይወጣል፣ ተቋማት ወለም ዘለም ሳይሉ ያስፈፅሙታል። ሕገ መንግሥት የለም፣ ነጻ ተቋም የለም። ያለው *የተማከለ ዴሞክራሲ* ነው። የ36 ሰዎች አምባገነናዊ አስተዳደር ነው። ዴሞክራሲ ሕዝባዊ አስተዳደር ነው። እዚህ ሕዝብ የለም።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት 36 የኢሕአዴግ ሰዎች ምን እየመከሩ[ብን] ነው?
ባለፉት ወራት ኦሕዴድ በኢሕአዴግ አለቃ ላይ ማፈንገጡን የሚያሳዩ ክሰተቶች ነበሩ። ብአዴንም መለስ ቀለስ እያለ ነበር። አሁን በዝግ ስብሰባቸው ምን እንደተከሰተ የሚነግረን የለም። ሁሉም በታማኝነት የጋራ ነገር ይዘው ለመውጣት እየተጉ ይሆን? እንደዚያ ከሆነ በጋራ ጭቆናውን ሊቀጥሉ ተስማምተዋል ማለት ነው። ምክንያቱም፣ የአገሪቱ ችግሮች ሁሉ መነሻ ይህ የተማከለ ዴሞክራሲ የሚሉት በዴሞክራሲ ሥም የጥቂት ሰዎች አምባገነንነት የሚሰፍንበት ስርዓት ነው። እሱ ካልተቀረፈ ችግሮቻችን ሁሉ ይቀጥላሉ።
የተማከለ ዴሞክራሲ ያልተማከለ ስርዓት ቁንጮ ከሆነው ፌዴራሊዝም ጋር ይጋጫል፤ ምክንያቱም ለክልሎች አስተዳደራዊ ነጻነት አይሰጥም። የተማከለ ዴሞክራሲ የመንግሥት (ሕዝባዊ) ተቋማት ነጻነት ጋር ይጋጫል፤ ምክንያቱም የተቋማቱ አሠራር እና አቋም በማዕከላዊው ኮሚቴ ነው የሚወሰነው። የተማከለ ዴሞክራሲ ዴሞክራሲያዊ አይደለም። የብዙ ሰዎች የትብብር አምባገነንነት ነው።
የግንባሩ አባል ፓርቲዎች ሕዝባዊ ጥያቄዎችን ለማዳፈን ሳይሆን ለመመለስ ከፈለጉ፣ ‘የተማከለ ዴሞክራሲ’ የሚሉትን አሠራር ማስቆም አለባቸው። ከዚያ ውጪ፣ ወደ ውጪ!